አዲስ አበባ፡- ህገወጥ የገንዘብና የመሳሪያ ዝውውርን እንዲሁም የተደራጁ ወንጀሎችን በማስቆም ረገድ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ ሥራ መስራቱ ተገለፀ፡፡
አገልግሎቱ በትናንትናው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሲያከናውናቸው የቆዩ የሪፎርም ሥራዎችን አስመልክቶ በፅህፈት ቤቱ ገለፃ አካሂዷል፡፡
የአገልግሎቱ የውስጥ መረጃና ደህንነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ለጋዜጠኞች እንደገለፁት፣ተቋሙ በየጊዜው ከህብረተሰቡ በሚደርሱት የተለያዩ መረጃዎች መሰረት ተልእኮዎችን በማዘጋጀት በአከናወናቸው ተግባራት የተለያዩ መጠን ያላቸው የውጭ አገር ገንዘቦች ከአገር እንዳይሸሹ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ህገወጥ ምንዛሪ የሚካሄድባቸውን ልዩ ልዩ ቦታዎችን በመለየትና ተደጋጋሚ ተልእኮዎችን በመፈፀም የማዳከም ሥራ በስፋት ተሰርተዋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቷ ጠረፎች በኩል ሊሸሹ የተዘጋጁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ባልተለመደ ሁኔታ የተደራጁና በጦር መሳሪያ የተደገፉ የወንጀል ተግባሮች እየተካሄዱ የነበሩ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፤ በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ተቋሙ ሰፊ የመረጃ ሥራዎችን በመስራት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የወንጀሉ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይም በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በህገወጥ መንገድ ሊገቡ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰው፣ አብዛኞቹ የጦር መሳሪያዎች ከሱዳንና ከቱርክ የሚገቡ መሆናቸውም በመታወቁ ከአገራቱ ጋር ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባመ፣የህዝብ ተሳትፎን ከማረጋገጥ አኳያ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ለተቋሙ መረጃ የሚሰጥበት ሥርዓት መዘርጋቱን የገለፁ ሲሆን፤ የተለያዩ የህገወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውሮች እንዲሁም የተደራጁ ወንጀሎችን በማጋለጥ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
በአስናቀ ፀጋዬ