ኢትዮጵያ ባህል የበረከተባት የተዋበ ማንንት የነፃት ውድ ምድር ናት። ኢትዮጵያዊነት የባህል ድርብርብነት የመከባበር ተምሳሌት፤ የአብሮ መኖር ውህድ ውጤት ነው። ማንነታችንን የሰሩት ሁሉም እሴቶቻችን ማህበረሰባዊ እሴቶቻችንን የእርስ በእርስ መከባበራችንን የሚያጎሉ፤ የአብሮ መኖር ትስስራችንን የሚያደምቁ ሀብቶቻችንም ናቸው።
አንድ ህብረተሰብ እራሱን የሚያስተዳድርበት ባህላዊ ስርዓቶችና ደንቦች ቀርጾ በእነዚህ በቀረጻቸው መተዳደሪያ ደንቦች መመራት እና መገልገል ሲጀመር ባህሉንና ቋንቋውን ጠንቅቆ መረዳቱን ያመለክታል። ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ እየተጠቀመባቸው ያሉት ባህሉንና ቋንቋውን የመጠበቅ ማህበራዊ ግዴታውን መወጣቱን የሚያሳይ ነው። ታዲያ እንዲህ ያሉ ባህል ባለቤቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ጊዜውን ባገናዘበ መልኩ እንዴት ወርቃማ እሴቶቻቸውን ይጠብቃሉ? እንዲሁም ይከውናሉ ብለን ስናስብ ብዙ የምናገኛቸው መልሶች አሉ። ምላሹም ማስተዋልና ጥበብ መሆኑን እንረዳለን። ማስተዋል ማለት ትክክለኛን ጊዜ ያወቀ፤ ወቅቱ የሚጠይቀውን ባህሪ አሟልተው የሚገኝ እንደሆነም እንገነዘባለን።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዲያ ጥብቅ በሆነ መተሳሰርና ባህላዊ እሴት በመቀራረብ ውስጥ የሚኖር ማህበረሰብ እንደቀድሞ እንዳይሆን፤ ማህበራዊ ትስስሰሩን አጠናክሮ እንዳይቀጥል የሚያስገድድ ችግር ገጥሞታል። ኮሮና ! ይህ ወረርሽኝ አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚያስገድድ በመሆኑ በማህበር የሚከወኑ ተግባራትን መፈጸም እንዳይቻል አድርጎታል።
በጎ የሆኑ ባህሎችን በተመሳሳይ እና በለመድነው መንገድ የምንተገብርበት ጊዜ ላይ አይደለንም። ይህ ከሆነና ጊዜውን ያላገናዘቡ ድርጊት ውስጥ ከገባን ግን ራስን፣ ቤተሰብንና አገርን ለኪሳራ እና ለሞት የሚዳርግ ነው፤ ስለዚህ ትክክለኛ ጊዜን በማወቅ ተገቢውን ተግባር መፈጸም ራስን፣ ቤተሰብንና አገርን ማትረፍ ይቻላል።
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማህበራዊ ትስስሩ በጠነከረበት አገር አካላዊ ርቀትን ጠብቆ መኖር ከባድ ነው። እስቲ ይሄን ጉዳይ በይበልጥ ወደሚያስረዳን አንድ ጉዳይ እናምራና ርእሰ ጉዳያችንን በርሱ ላይ እናተኩር። በአገሪቱ በማህበር ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ለቅሶ ወይም ሀዘን አንዱ ነው።
ህይወት ያለው ነገር በመጀመሪያ ይወለዳል፣ ያድጋል ከዛም ይሞታል። ሞት እና ልደት በተቃራኒ ጽንፍ የቆሙ ክስተቶች ናቸው። ይህ ጉዳይ ደግሞ ህይወት ላላቸው ነገሮች ሁሉ የሚሰራ ነው። በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ የሞት እሳቤ በሚከተለው መልኩ ተገልጿል። “ሞት የነፍስና የስጋ መለየት ወይም ህይወት ማጣት፤ ይህም በስጋዊ ወይም በመንፈሳዊ ሊሆን ይችላል” ይላል።
‹‹ስጋዊ ሞት›› የስጋን ፍላጎት በመጉዳት፣ ራስን ዝቅ በማድረግ እምነቱ በሚፈቅደው መልኩ ራስን ለእምነቱ ማስገዛት ሲሆን፤ ‹‹የነፍስ ሞት›› የምንለው ደግሞ ሀይማኖቱ ወይም መንፈሳዊ ማንነቱ የሚገዛበትን ህግ ጥሶ መገኘት ነው። ሞት በህይወት ውስጥ ያለና አብሮን የኖረ ነገር ቢሆንም በተከሰተ ጊዜ በሰው ልጅ ላይ የሚያሳድረው ከፍተኛ ስሜት አለ። ይህ ስሜት ደግሞ ሀዘን ነው። ይህ ሃዘን ደግሞ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ለቅሶ ነው። ይህ ክንዋኔ ደግሞ እንደየ አገሩና ባህሉ የተለያየ መልክ አለው።
አንድ ሰው በጠና ሲታመም የቤተሰብ አባላቶች እና ወዳጅ ዘመድ ከአጠገቡ አይለዩም። ታዲያ ታማሚው ከቤተሰብ እና ከወዳጅ ዘመድ እንዲሁም የሃይማኖት አባት በተሰበሰቡበት ሟች ንብረት ያለውን ከሆነ ለልጆቹን ብሎም እርሱ ይሰጥልኝ ላለው ሰው እንዲደርስ ይናዘዛል። ዕዳም ካለበት እንዲሁ እንዲከፈልለት እንዲሁ ይናገራል። ታዲያ ይህ በጠና የታመመው ሰው ነፍሱ ከስጋው መለየቷ እንደታወቀ፣ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት አሊያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሆኑ ከእነርሱም የተመረጡ እና የተወሰኑ ሰዎች በመሆን ወዲያው ሟችን ይዞ በመሄድ ለመገነዝ በሚመች ቦታ ወይም ክፍል ውስጥ ያደርጉታል። የሟች በድንን በተዘጋጀው ቦታ እነዚሁ ሰዎች አጥበው ይገንዙታል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም ከገናዞች ውጭ እዚያ ቦታ ማንም ድርሽ እንዲል አይፈቀድም።
ከሚገነዝበት ክፍል ውጭ ያለው ለቀስተኛ ለሟች እንደቅርበቱ መጠን ሀዘኑን ይገልጻል። ጸጉሩን የሚነጭ፣ ፊቱን የሚቧጥጥ ተነስቶ ከመሬት የሚፈርጥ እና በልዩ ልዩ መንገድ ሀዘኔን ይገልጽልኛል ባለው መልኩ የለቅሶ ተግባሩን ይከውናል። ሌሎች ደግሞ በለቅሶ ዜማቸው የሟችን ደግነት፣ ለጋስነት፣ ጀግንነት የመሳሰሉ ምግባሩንና ተግባሩን የሚገልጹ ግጥሞች ይደረድራሉ።
አስክሬኑ ከሰፈሩ ሲነሳ፣ የሃይማኖት አባቶች ፊት ቀድመው ይመራሉ። ከሃይማኖት አባቶች ራቅ ብሎ አስክሬኑን የተሸከሙ ሰዎች ይከተላሉ። አስክሬን የተሸከሙትን በመከተል ለቀስተኞች ይከተላሉ። የቀብር ቦታ እንደደረሱ የሃይማኖት አባቶች የመጨረሻውን የቀብር ጸሎት ስርዓት ይጀምራሉ። መቃብር ቆፋሪዎችም ስራቸውን ያከናውናሉ። አስክሬኑም በመጨረሻ ወደ ማረፊያው ይገባል። ከዚያ መቃብሩ አፈር ይለብሳል። የሐዘኑ ጊዜ እንደየ ሀዘንተኛው ባህል እና ሃይማኖት ቢለያይም አብዛኛው ከሶስት እስከ ሰባት ቀን ለቅሶ ይቀመጣል።
በዚህ ወቅት ወዳጅ ዘመድ የሆነ ለቅሶ ይደርሳል። ያስተዛዝናል። ለማስተዛዘኛ የሚሆን “የእዝንም” ይዞ ይመጣል። በዚህ ወቅት ሐዘንተኞች አንድም ቀን ብቻቸውን አይሆኑም። ይህ የለቅሶ ስርዓት ፍጹም የሆነ ለማህበራዊ እና ለአካላዊ ንክኪ የሚያጋልጥ ነው በወቅቱ ልክ እና አስፈላጊም ባህላዊ ማህበራዊ ክዋኔ ነው።
የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ግን እንደቀድሞ ከኑዛዜ እስከ ማስተዛዘን ያለውን ባህላዊ ማህበራዊ ክዋኔን ማድረግ ለበሽታው ተጋላጭነት ይጨምራል። በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት እንዲህ ያለው መልካም የሆነው ንክኪ፤ የለቅሶ ስርዓት በከተማም ሆነ በገጠር በመንግስት፣ በሃይማኖት አባቶች በአዋጅ ተከልክሏል።
የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ ባሳለፍነው ሳምንት በወይራ የጋራ መኖሪያ አንድ ሀዘን የደርሰባቸው ቤተሰብ ለቅሶ ስርዓት ለመመልከት ታድሜ ነበር፤ ለቅሶ ሊደርስ የመጣው ሰው በሙሉ ዳር ዳር ይዞ ቆሟል፤ የቅርብ ቤተሰብ ደግሞ ሀዘኑን ለመግለጽ እንደቀድሞ መከወን አለመቻሉ ሀዘናቸውን እንደልባቸው አለመግለጻቸው ይልቅ መብሰልሰል እንደጨመረባቸው ለመታዘብ ችያለው።
ለቅሶውን ሊደርሱ ከመጡት መካከል የሟች የቅርብ ዘመድ ነኝ ያሉት አቶ ሙስጠፋ ሙዘይን በዚህ ወቅት መሞት ዕድለ ቢሰነት ነው ያሉ ሲሆን ለሟችም ለሀዘንተኛ እጅግ ልብን የሚያደማ ነው ብለዋል፤ ሀዘንተኛን እንደ ቀድሞ አቅፎ ደግፎ ማጽናናት ባለመቻላችንም ሀዘናችንን ጥልቅ አድርጎታል፤ ፈጣሪ ይህንን ክፉ እንዲያነሳልን ከልጅ እስከ አዋቂ የሚገባውን ጥንቃቄ በማድረግ በያለንበት መጸለይ አለብን ብለዋል።
አቶ ሙዘይን አክለው እንዳሉት በሙስሊም ዘንድ አንድ ሰው ሲሞት ለሟች የሚሆን ጸሎት ይደረጋል፤ ይህ ደግሞ የሚከናወነው በህብረት በመሆን ነው፤ አሁን ግን በዚሁ ወረርኝ ምክንያት ይህንን እንኳ ማከናወን አልተቻለም ብለዋል።አቶ ሙዘይን ይናገራሉ ይህ ጸሎት እንዳይቀር ብቻ በህግ በተፈቀደው መሰረት ከአራት ያልበለጡ አባቶች አድርገውታል።
ሌላኛው ለቅሶ ደራሽ ሙርሺዳ አብራር እንደምትለው የዘመዷን ለቅሶ ላይ እንደፈለገችው ሀዘኗን መግለጽ አለመቻሏን ገልጻለች። ይህ ብቻ አይደለም ትላለች ሙርሺዳ ዘመዶቼን ሀዘናቸውን እንዲረሱ ቀርቤ አብሬያቸው በመሆን አቅፌ ደግፌ ብሎም ቤታቸው አድሬ ማስተዛዘን ባለመቻሌ ሀዘኔን ከፍ አድርጎታል ብላለች። አሁን ሙርሺዳ ትናገራለች ሀዘንተኛውንም ቢያንስ ለሶስት ቀን ከተቻለ ደግሞ ለሰባት ቀን አጠገቡ በመሆንና አጅቦ በማጫወት ስራ በማገዝ ማጽናናት የተለመደ ነው። አሁን ላይ ይህንን ድርጊት በወረርሽኑ ምክንያት ማድረግ አለመቻሉንም ተናገራለች።
ለተጎጂው ቤተሰብ ለወዳጅ ዘመድም ሀዘኑን ጥልቅ እንደሚያደርገው ጠቅሳም የተሻለ ቀን ሲመጣ እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ክዋኔዎችን እንደቀድሞው ማድረግ እንደሚቻል ተስፋዋን ትናገራለች። ለጊዜው ግን ከመጣው ችግር አይብስምና እንደ ለቅሶ ያሉ ማህበራዊ ክዋኔዎችን ለጊዜው ገታ ማድረግ እንደሚገባ ገልጻለች። በአገሪቱ ላይ የመጣውን ክፉ ወረርሽኝ መንግስና የጤና ባለሙያዎች የሚሉትን በመስማት ነገን ለመየት መተባበር መታገስ እና በስርዓት ልንወጣ እና ልንገባ ይገባናልም በማለት መልክቷን አስተላልፋለች።
የአዋጁን ድንጋጌ የመፈፀም ብልህነት
እንደሚታወቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ስርጭትን ለመከላከለል ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።ታዲያ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ደንቦችን አውጥቷል። ከማስፈጸሚያ ደንቦች የተከለከሉ ተግባራት ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል ደግሞ ለሃይማኖታዊም ወይም ማህበራዊ አላማ፣ ለመንግስታዊ ስራ እና ወይም መሰል አላማ አምልኮ በሚደረግባቸው ቦታዎች በመንግስት ተቋማት በሆቴሎች በማናቸውም የመሰብሰቢያ አዳራሾችና በማናቸውም ቦታ አራትና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ ላይ መገኘት የተከለከለ መሆኑን ይገልፃል።
በዚህ ደንብ መሰረት ደግሞ “ለማህበራዊ ዓላማ” ተብሎ የተገለጸው የሚያካትተው ሰርግ፣ ለቅሶ፣ ልደት፣ እድር፣ እና ለመሳሰሉትን ነው።
በአስቸኳይ ጊዜው እንደተገለጸው ለቅሶን በቀድሞው ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስነስርዓት መፈፀም እንደማይቻል ግልጽ ነው። ስለሆነም እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ክዋኔዎችን ይህ ወረርሽኝ እስኪያልፍ ድረስ ገታ ማድረግ ቢቻል ለራስም፣ ለቤተሰብም ሆነ ለአገርም ጠቃሚ መሆኑ እሙን ነው። ህግም ማክበር ተገቢ ነው።
ነገ በሰላም ለመገናኘት እና የምንፈልገውንም ማህበራዊ ህይወት እንደወደድን ለመከወን መንግስትም፣ የህክምና ባለሙያዎች እና የሃይማኖት አባቶች የሚሉትን መተግበር ዛሬን ከዚህ ክፉ ወረርሽኝ አልፎ ነገን ለማየት እንዲረዳን ያደርጋል።
እንደሚታወቀው ራስን ከማንኛውም ሰው ቢያንስ ሁለት የአዋቂ ርምጃ በመራቅ፤ የመተንፈሻ አካላት ህመም ምልክቶች ወይም ማስነጠስ እና ማሳል የታዩባቸው ሰዎች አካባቢ ስንሆን ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እጅ መጨባበጥን፣ መተቃቀፍንና መሳሳምን ማስወገድ መልካም ነው። በተጨማሪም ራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ የተጠቀምንባቸው ቁሳቁሶችን ማለትም ጓንቶች፣ የፊት ጭንብሎች፣ የመከላከያ ሽርጦች፣ ቱታዎች/በመላ አካላችን የሚጠለቁ ልብሶች ተጠቅመን የምንጥላቸው የጫማ መሸፈኛዎች) በጥንቃቄ ማጥለቀና ማውለቅ በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህን ቁሳቁሶች በአግበቡ ለመጠቀም ደግሞ መልካም የጥንቃቄ ተሞክሮዎችና የአጠቃቀም መመሪያዎችን በትክክል መከተልን ይጠይቃል።
እንደመውጫ
የሰው መሞት ቁጥር ሆኗል፤ ሬሳ መዝገን የአለማችን የእለት ተዕለት ተግባሯ ከሆነ ሰነባበቷል። ለወትሮ በኢኮኖሚ በፖለቲካ በማህበራዊ ጉዳዮቻቸው ፈርጣማ ጡንቻ ያላቸው ሀያላን አገራት አሁን ግን በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ክንዳቸው ታጠፏል። አንገታቸውን ተደፍቶ የመፍትኤ ያለ እያሉ ነው፤ ሃያላኑ ዝለዋል ደክመዋል። ዙሪያ ገባው ጨልሞባቸዋል፤ የሚይዙት የሚጨብቱትን አጥተዋል፤ ሆስፒታሎች ሞልተዋል…ብቻ ነገር ግራ ሆኗል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአፍሪካ በተዳከመ ኢኮኖሚና የማህበራዊ ንክኪ በእጅጉ በሚበዛበት ኑሮ ይህ በሽታ ተጨምሮ የችግሩን አሳሳቢነቱን ከፍ ያደርገዋል። ለዚህም ከሞት ጋር ለሚደረገው ግብግብ ያሉንን ሁሉ እድሎች፣ አቅሞች መጠቀም የግድ ይላል። ወረርሽኙን በተሻሉ ሆስፒታሎች፣ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም በዘመናዊ መሳሪያዎች መቆም እንደማይቻል ሃያላኑን ሲፈትን አይተናል።
‹‹ጠቢብ ሰው ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል›› እንዲል መጽሐፉ ይህንን ቸነፈር ማምለጥ የሚቻለው ምክርን በአግባቡ በመስማት እና በተግባርም በማዋል ነው። ለምሳሌ በአዋጅ የተነገረው በባለሙያዎች የተነገረን ሰዎች በብዛት በሚገኙበት እንደ የጤና አጠባበቅ ተቋም፣ አረጋውያንን የመንከባከቢያ ማዕከል፣ የጤና እክል ያለበት ወይም ነፍሰ ጡር ቤት፣ የታመሙና በበሽታው የተጠረጠሩ የሚቆዩባቸው፣ ማግለያ ቦታዎች ወይም አንቅሰቃሴ የታገደባቸው ከልሎች፣ ያስክሬን ማቋያ፣ ያስክሬን መገነዣ ወይም ሰርዓት ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎች፣ እንደ ሰርግም ያሉ የደስታ ቦታዎችና ህዝብ በብዛት የሚኖርባቸው የከተማ ስፍራዎች (ማለትም የተፋፈጉና ንጽህና የጎደላቸው)፣ የስደተኞች ማቆያ ጣቢያ ያሉ ቦታዎች ከመሄደ በመታቀበ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት መተባበር ያስፈልጋል። በወረርሽኙ ምክንያት ደግሞ የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን ለማይችሉ ወገኞች ድጋፍ በማድረግ እና በተገቢው መንገድ በመድረስ በተጨማሪም አገሪቱ ያላትን የመቻቻል፣ የሰላም እና የፍቅር እሴቶች በመጠቀም የመጣብንንና የሚመጣብንን ሰይጣናዊ የጥፋት ውሃ ለመከላከል ለመግታት መረባረብ ይገባናል። ኢትዮጵያ የፍቅር የመቻቻል አገርና ምድርነቷ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
አብርሃም ተወልደ