የበጎ አድራጎት ስራዎችን መከወን የህሊና እርካታ እንደሚሰጠው ይናገራል። ወጣቱን በተለይ በባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ከኮሮና በሽታ ጋር ተያይዞ በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች እና የህክምና ባለሙያዎች አልባሳትን በማቅረብ ተግባር በርካቶች ያውቁታል። በወጣትነት እድሜው ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠር የቻሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ በመሰማራት ጠንካራ ሰራተኝነቱን አስመስክሯል። ተግባቢ እና ለስንፍና ቦታ የሌለው ስለመሆኑ ደግሞ የሚያውቁት ሁሉ ይናገራሉ።
አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ ይባላል። የተወለደው በጎንደር ከተማ መግቢያ ላይ በምትገኘው አዲስ ዘመን ከተማ ነው። ከቤተሰቡ አምስት ልጆች መካከል የበኩር ልጅ ሆኖ ተገኝቷል እና እንደታላቅ ወንድምነቱ ተጨማሪም ሃላፊነት አለበት። በልጅነቱ ጊዜያት ከትምህርቱ ይልቅ ወደ ቴክኒክ ስራዎች ያደላ እንደነበር አይዘነጋም። በተለይ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን መፈታታትና እና መገጣጠምን ይወድ እንደነበር ያስታውሳል። ይህን ሁሉ ሲያደርግ ግን የቤተሰቦቹን ንብረት በማይጎዳ መልኩ መሆኑን በልጅ አዕምሮውም ለመለየት አይከብደውም ነበር። በሀገሩ ወግና ስርዓት መሰረት ያሳደጉት ወላጆቹ በመምህርነት ሙያ የተሰማሩ በመሆኑ፤ የቴክኒክ ስራውን ይበልጥ አሳድጎ እንደሚያዩት ተስፋ ነበራቸው።
ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ ዘመን ከተማ ከተከታተለ በኋላ፤ ለተጨማሪ ትምህርት ያመራው በጣና ሐይቅ ዙሪያ ወደተቆረቆረችው ባህር ዳር ከተማ ነበር። ወደ ባህርዳር እንዲያቀና ያደረገው ደግሞ የአውቶ መካኒክ ትምህርት ለመከታተል ወደግል ኮሌጅ መግባቱ ነው። በከተማዋ ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር ቤት ተከራይቶ ትምህርቱን መከታተል ቀጠለ። በወቅቱ የሚያስፈልጉትን ወጪዎች የሚሸፍኑለት ቤተሰቦቹ ናቸው። ብዙ ፈተናዎችን አልፎም የሶስት ዓመት ትምህርቱን አጠናቀቀ።
ከትምህርቱ ማጠናቀቅ በኋላ አንድ ዓመት የመንግስት ቴክኒክና ሙያ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ ሰርቷል። እንዲህ ከሆነ በኋላ ሰፊ ዕውቀትን እንዳገኘ ከሚናገርበት የግል ተቋም በአውቶ መካኒክ ሙያ በመምህርነት መስራት ጀመረ። በመምህርነቱ ስራ ላይ እያለ የግል ስራ ለመጀመር የሚያስችል ሀሳብ ወደአዕምሮው ይመላለስ እንደነበር ያስታውሳል። ይህንን ሃሳቡን የተረዳው እና በእንጨት ስራ ላይ የተሰማራው ጓደኛው ደግሞ በረጅም ጊዜ ክፍያ የሚፈጸምባቸውን 25 የተማሪ ወንበሮች አዘጋጅቶ አቀረበለት። ጎንደር የሚገኙ ዘመዱ ደግሞ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ሁለት ሺህ ብር ከፍለው ቴዎድሮስን የአውቶ መካኒክ ትምህርት ቤት እንዲከፍት ድጋፍ አደረጉለት።
ቴዎድሮስም ካጠገቡ ባሉት ወዳጆቹ ተበረታቶ ለሶስት ዓመታት ካስተማረበት የግል ተቋም በመልቀቅ የአሽከርካሪነት ሙያ ማሰልጠኛ ከፍቶ በግሉ መስራት ጀመረ። በወቅቱ በሳምንት ከ20 እስከ 25 የሚደርሱ ተማሪዎችን ይቀበል ነበር። ድርጅቱን በስራአስኪያጅነት እየመራና እያስተማረም በጥንካሬ መንቀሳቀሱን ቀጠለ። ይሁንና የግል ስራው ከአምስት ወራት በላይ ሊዘልቅ አልቻለም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መንግስት የአሽከርካሪነት ሙያ ማሰልጠኛዎች መኪናዎች ሳይኖራቸው ማሰልጠን አይችሉም የሚል ህግ በማውጣቱ ነበር።
ቴዎድሮስ ቀደም ብሎ ተማሪዎችን በንድፈ ሃሳብ የተደገፈ ትምህርት ከሰጣቸው በኋላ ወደ አሽከርካሪ ፈታኞች ዘንድ በመሄድ የተግባር ስልጠና የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻች ነበር። አሰራሩ ሲቀየር ግን የቴዎድሮስ ማሰልጠኛ ምንም አይነት ተሽከርካሪ የሌለው በመሆኑ ተዘጋ።
ቴዎድሮስ ግን ከአውቶ መካኒክነት ሙያው ባለፈ ባህርዳር ላይ የላብራቶሪ ቴክኒሻንነት ትምህርት ወስዶ ነበርና የግል ድርጅቱ ሲዘጋ በተለያዩ ተቋማት በላብራቶሪ ቴክኒሻንነት እየሰራ አንድ ዓመት ያክል አሳልፏል። በመቀጠልም የግል አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ድርጅት ውስጥ ዳግም በመምህርነት ለመስራት ስምምነት አደረገ። በመምህርነቱ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ተቀጥሮ ከሰራ በኋላ ወደተቋረጠው የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ የግል ስራው ለመመለስ የሚያስችለውን ዝግጅት ማድረጉን ቀጠለ።
ከሌሎች ሰዎች ተሽከርካሪ በመከራየት መስራት እንደሚቻል በማወቁ የቅጥር ስራውን አቋርጦ ዳግመኛ የግል ማሰልጠኛውን ከፈተ። አንድ ባለሶስት እግር እና
ተጨማሪ ባለአራት ጎማ ተሽከርካሪ በአስራአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር የወርኪራይ በመክፈል ለማሰልጠኛው የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን አገኘ። በመቀጠልም አስፈላጊውን የንግድ ፈቃድ መስፈርት በማሟላትም በ2001 ዓ.ም ላይ የግል ስራውን እንደአዲስ ጀመረ።
ማሰልጠኛውን ሲከፍት ግን ቀድሞ በሌሎች ተቋማት ሲሰራ በሙያው ብቃት የሚያውቁት ወጣቶች በብዛት ወደእርሱ መጉረፋቸውን ተያያዙት። ቴዎድሮስም በይፋ ስራውን በጀመረ በመጀመሪያዋ ቀን ብቻ ተማሪዎችን ለስልጠና በመመዝገብ 55 ሺህ ብር ሰበሰበ። የመዘገባቸውንም የተግባር ስልጠና ጭምር በመስጠት በአንድ ወር ውስጥ ጥሩ ገቢ በመሰብሰብ እራሱን በሚገባ አደራጀ። በጥቂት ወራት ውስጥም በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንጃ ፈቃድ ሰልጣኞችን በማስተማር ዕውቅናውን በባህር ዳር ከተማ ከፍ አደረገ።
ከኪራይ ተሽከርካሪዎችም በመውጣት ለማሰልጠኛው የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን መግዛት ጀመረ። አንድ ብሎ
የጀመረው የተሽከርካሪ ቁጥርም በጥቂት ዓመታት እያደገ ከአስር በላይ አደረሰው። እንዲህ እንዲህ እያለ ለበርካቶች የአሽከርካሪነት ስልጠና የሰጠው ቴዎድሮስ ከአመት ዓመት የንብረት እድገት ብቻ ሳይሆን የሰራተኞችን ቁጥርም እየጨመረ ከ50 እና 60 በላይ ሰራተኞችን የሚቀጥር ድርጅት ባለቤት ሆነ። በዚህ ስራ በባህር ዳር ከተማ ታዋቂነትን ሲያተርፍ እና አቅሙም ሲጠናከር በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ ተጨማሪ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ወደመክፈቱም ተሸጋገረ።
አሁን ላይ የቴዎድሮስ ማሰልጠኛ ተቋሞች ላይ የአሽከርካሪነት ስልጠና ብቻ ሳይሆን የቴክኒክ ስራዎችም ይከናወናሉ። በተለይ ባህር ዳር ከተማ ዘመናዊ ማሽን በመግጠም የተሽከርካሪ ምርመራ ወይም ቦሎ ምርመራ ስራውን በስፋት እያከናወነ ይገኛል። አሁን በድርጅቶቹ ስር በአጠቃላይ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 25 ደርሷል። ቴዎድሮስ በባህር ዳር እና በአዲስ አበባም በማሰልጠኞቹ ስር ለ110 ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር ችሏል።
ወጣቱ ባለሃብት በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርቶ እራሱን ብቻ ሳይሆን አገሩንም የመጥቀም ፍላጎት እንዳለው ይናገራል። በዚህም ምክንያት ወደጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው በመሳቡ የጋርመንት ፋብሪካን ገንብቷል። ከመንግስት የማሽን ሊዝ ኪራይ በመውሰድ ከውጭ ሀገራት የተለያዩ የጨርቃጨርቅ ማሽኖችን ካስገባ በኋላ የጋርመንት ኢንዱስትሪውን ከሁለት ዓመታት በፊት ተቀላቅሏል። ባህር ዳር ከተማ ላይ ሊቦ ጋርመንት ብሎ የሰየመው ድርጅቱንም በ11 ሚሊዮን ብር ካፒታል መነሾነት መጀመሩ ለእርሱ ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ስራ ነበር።
የተለያዩ የጅንስ አልባሳትን፣ የጸጥታ አካላት እና የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን አልባሳት ለማምረት ሰፊ ውጥን ይዞ ቢነሳም ገበያው ግን የሚስብ እንዳልሆነ ነው የሚናገረው። በተለይ ለዘርፉ የተሰጠው አነስተኛ ትኩረት እና የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ከሀገር ውስጥ ይልቅ ለውጭ አምራቾች ጨረታዎችን አሳልፈው የሚሰጡበት
መንገድ ስራውን ጎድተውታል። በይበልጥ ግን የመብራት መቆራረጥ ችግር አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰት በመሆኑ ለጄኔሬተርና ነዳጅ ወጪ እንደዳደረገው ነው የሚናገረው። ይህንን እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በዘርፉ ቢኖሩም ቴዎድሮስ ግን እጅ አልሰጥም ብሎ መስራቱን እንደቀጠለ ነው።
የተለያዩ የጅንስ አልባሳትን እና ቲሸርቶችን እንዲሁም የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች አልባሳትን በማምረት ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል። አሁን ላይ ደግሞ የኮሮና በሽታ ከተከሰተ በኋላ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በሺዎች የሚቆጠሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን በማምረት ላይ ይገኛል ።
ለዚህ ተግባር ያነሳሳው ደግሞ የአንድ ጓደኛው ጥያቄ መሆኑን ይናገራል። ጓደኛው የጭምብል እጥረት በማጋጠሙ እንዲገዛለት ይጠይቀዋል። ቴዎድሮስም ወደፋርማሲ ጎራ ብሎ ጭምብሉን ቢጠይቅ ከ25 ብር በአንድ ጊዜ 250 ብር መግባቱ ይነገረዋል። ይህ የዋጋ ውድነት ከተፈጠረ ደሃው ህብረተሰብ በምን አቅሙ ይገዛዋል በሚል እሳቤም እራሱ ዲዛይን ያደረገውን ሙከራ ስፌት በመያዝ በፋብሪካው ውስጥ በሚገኙና ከጥጥ በተሰሩ ጨርቃጨርቆች በብዛት እንዲመረት ማድረግ ጀመረ።
ያመረታቸውን ጭምብሎችም በነጻ እንደሚያቀርብ በማህበራዊ ድረገጾች በመልቀቁ በርካቶች እንደሚፈልጉ በስልክ እየደወሉ አሳወቁት። ለአቅመደካሞች እና ለተለያዩ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ድርጅቶች ጭምብሎቹን በስፋት በማምረትና በማቅረብ ማህበራዊ ሃላፊነቱንም መወጣቱን ቀጠለ። በዚህ መልኩ የተሰሩ 20 ሺህ ጭምብሎችን በነጻ ማከፋፈሉን አቶ ቴዌድሮስ ይናገራል።
‹‹በነጻ አቅርብልን›› ጥያቄው ግን የመግዛት አቅም ካላቸው ተቋማት ጭምር መቅረብ ሲጨምር ቢያንስ የመስሪያ ዋጋውን ሸፍኖ ጭምብሎቹ በአነስተኛ ዋጋ እንዲቀርቡ ለማድረግ ወሰነ። በዚህ መንገድ በጋርመንቱ የሚገኙ የጥጥ ጨርቆችን በመጠቀም የሚዘጋጀውን ጭምብል በቀን እስከ 15 ሺህ ብዛት ሲያመርት ቆይቷል። ከአንድ ሳምንት በፊት ግን በተለያዩ የጤና ማዕከላት ያለውን የህክምና ባለሙያዎች አልባሳት ችግር በመመልከት ከውጪ ሀገራት የሚመጡ የሕክምና አልባሳትን ወደመስራቱ ተሸጋግሯል።
በተለይ በኮሮና ለይቶ ማከሚያ ማዕከላት ለሚሰሩ ባለሙያዎች የሚገዛው እና ምንም አይነት እርጥበት የማያስገባው የሕክምና ልብስ ከቻይና በአንድ ሺህ አምስት መቶ ብር እንደሚገዛ እና በርካታ የጤና ማዕከላት ደግሞ ይህን የማሟላት አቅም እንደሌላቸው ካወቀ በኋላ ይህንኑ እያመረተ በነጻ በማቅረብ ላይ ይገኛል። በተለይ በአማራ ክልል ለሚገኙ ዞኖች በእራሱ ዲዛይን የተሰሩ የህክምና አልባሳት ተወዳጅ በመሆናቸው ለጤና ቢሮዎች በነጻ አስረክቧል። ይህን ስራ የተመለከቱ አንድ ሺህ የለይቶ ማከሚያ የህክምና አልባሳትን እንዲያቀርብ አዘውታል፤ እሱም አንዱን በአንድ ሺህ ብር ዋጋ እያመረተ ለማቅረብ ተነጋግሯል።
ከዚህ ባለፈ ግን በኮሮና የተዘናጋውን ህብረተሰብ ለማስተማር አዲስ ፈጠራ ይዞ ብቅ ማለቱን ቴዎድሮስ ይናገራል። በኮሮና አምሳል የተዘጋጀና በድምጽ ሰዎች እንዲራራቁ የሚያስተምር ተንቀሳቃሽ ፈጠራ በማዘጋጀት ለችግሩ መፍትሄ ለመሆን ተነስቷል። ተንቀሳቃሽ የኮሮና አምሳሉን ለማዘጋጀት አንድ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ የተጠቀመ ሲሆን ለአጠቃላይ ወጪውም 350 ሺህ ብር ወጪ እንዳደረገ ይናገራል። በአሁኑ ወቅት 253 ሰራተኞች እና 520 የስፌት ማሽኖች ያሉት የጋርመንት ስራው ፊቱን ወደጤና ግብዓቶች ምርት አዙሯል። በሌላ በኩል ደግሞ በመጋዘን ከነበሩት የአልባሳት ምርቶች መካከል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያላቸውን ለጎዳና ተዳዳሪዎች በማበርከት ለወገን ደራሽ ወገን ነው የሚለውን በተግባር አሳይቷል።
ቴዎድሮስ የጨርቃጨርቅ ስራውም ሆነ የሌሎች ድርጅቶቹ ህልውና የሚረጋገጠው ዜጎች በጤና ሲቆዩ መሆኑን መረዳቱ ለዚህ ሁሉ የበጎ አድራጎት ስራ መነሻነት እንደሆነው አልሸሸገም። ይህ ይበል የሚያሰኝ ተግባሩ እና የስራ ውጤቱ ግን የመጡት በጠንካራ ትግል መሆኑን ነው የሚናገረው። ማንኛውም ወጣት አትርፎ እና የተሻለ ህይወት መምራት የሚችለው እራስን በጤና ከመጠበቅ ባለፈ ስንፍናን ተጠይፎ በስራ ማሳለፍ ከቻለ ነው የሚለው ደግሞ ደጋግሞ በሚያስተላልፈው ምክሩ ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
ጌትነት ተስፋማርያም