አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በ2010 በጀት ዓመት ከቀረቡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የክስ መዝገቦች 92 ከመቶ የሚሆኑት ውሳኔ ማግኘታቸውን የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡ የፍርድ ቤት ጉዳዮችንም በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ አጭር የፅሁፍ መልዕክት ለመከታተል የሚያስችል አሠራርም ተዘርግቷል፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የችሎት ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ ኦልያድ ያዴሳ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ በ2010 ዓ.ም 617ሺ460 የክስ መዝገቦች ቀርበው 567ሺ738 የሚሆኑት መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል። አፈፃፀሙ 91 ነጥብ 9 ከመቶ ሲሆን ይህም በክልሉ በሁሉም ደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች ፍትህን በወቅቱና በቅልጥፍና ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ማሳያ ነው፡፡
የፍርድ ቤት አሰራር ቀልጣፋ እንዲሆን በሰው ኃይል ማሟላት ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው ለአብነትም በ2005 ዓ.ም በወረዳ ፍርድ ቤቶች የነበሩት 963 ዳኞች በ2009 ዓ.ም 1ሺ336 ደርሰዋል፡፡ በተመሳሳይ ዓመት በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች 102 ዳኞች የነበሩ ሲሆን በ2009 ዓ.ም 288 ደርሰዋል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ በ2005 ዓ.ም 35 ዳኖች የነበሩ ሲሆን፤ በ2009 ዓ.ም ወደ 78 ከፍ ብሏል፡፡ ይህም ሆኖ አሁንም ብዙ ዳኞች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ኦሊያድ ገለፃ፤ በፍርድ ቤት አሰራር ግልጽ፣ ተጠያቂነት ለማስፈን በ258 የወረዳ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም፣ በ39 በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ካሜራዎች ተተክለዋል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይህን የመተግበር ምዕራፍ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ይህም የፍርድ ቤት አሰራር ግልጽ፣ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እና ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ መርሆችና አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ የታሠበ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ባለጉዳዩ ባለበት ሆኖ በተለይም ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደ ሰበር በኤሌክትሮኒክስ ጉዳዩን እንዲከታተል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሞባይል አጭር መልዕክት ጉዳይን ለመከታተል የሚያስችል አሠራር የተጀመረ ሲሆን፣ ይህን በቀጣይ በሰፊው ተግባራዊ ለማድረግ ታስቧል፡፡ በተለይም በሰበር ጉዳዮች እና ሌሎች ፍርድ ቤቶች ላይ በስፋት እየተሠራ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት የፍርድ ቤቶችን አሰራር ቀልጣፋና ዘመናዊ እንዲሆን፣ ጠንካራ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ሥራውን በአግባቡ የሚያከናውን ፍርድ ቤት እንዲኖር ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አስገንዝበዋል፡፡
ከኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተገኘው መረጃ በኦሮሚያ ክልል 304 የወረዳ፣ 21 ከፍተኛ እና አንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፤ በወረዳ ደረጃ 62 ቋሚ ምድብ ችሎት፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ስድስት እንዲሁም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሦስት ቋሚ ችሎቶች አሉ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር