በአዲስ አበባ የተቋቋመውን የጥርስ ህክምናቸውን መርጠው የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ደንበኞች በርካታ ናቸው። በበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸውም የሚታወቁት እንስት በተለይ ለአረጋውያን እና ለዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ላላቸው ሰዎች ነፃ የጥርስ ህክምና በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውንም ይወጣሉ። እረፍት ብዙም እንደማያውቁ እና ለስንፍና ቦታ እንደሌላቸው ደግሞ አብረዋቸው የሠሩ ይመሰክሩላቸዋል። በሥራቸው ጠባይ ምክንያት ደግሞ ዓለምን ዞረዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። አሁን ላይ ግን በሚወዷት ሀገራቸው መቀመጫቸውን አድርገው በሕክምናው ዘርፍ ጉልህ አሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛሉ፡፡
ዶክተር እመቤት ገዛኸኝ ይባላሉ። የሚናሮል ህንፃ ባለድርሻ እና የዶክተር እምቤት የጥርስ ህክምና ተቋም ባለቤት ናቸው። ሐረር ከተማ ውስጥ የተወለዱት ዶክተር እመቤት ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው። ሐረር ከተማ ይወለዱ እንጂ ድሬዳዋ የሚገኙ አያቶቻቸው ጋር በየጊዜው ስለሚሄዱ ድሬዳዋንም ልክ እንደ አደጉባት ከተማ ይቆጥሯታል። የሦስተኛ ክፍለ ጦር ሠራዊት አዛዥ የነበሩት አባታቸው ደግሞ በሥራ ምክንያት ወደ ጅግጅጋ እና ቀብሪደሐር ከተሞች ሲሄዱ ቤተሰባቸውም አብሮ ይጓዘ ነበርና ዶክተር እምቤት በልጅነታቸው ለጥቂት ጊዜያት ሶማሌ ክልል ውስጥ የመኖር እድሉን አግኘተዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ ሐረር ከተማ ጠቅልል እና ማልቴዝ የተባሉ ትምህርት ቤቶች ነው። በልጅነታቸው ለነርሶች ልዩ ፍቅር ነበራቸው። ሲያድጉ ሰዎችን ለመርዳት እና ለመንከባከብ ፍላጎት ስላላቸውም ነርስ እሆናሁ ብለው ያስቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። አምስተኛ ክፍል ሲደርሱ ግን የውጭ አገር የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደኩባ የሚያመሩበት ዕድል ተፈጠረ። በጊዜው ገና የ11 ዓመት ልጅ ከነበሩት ዶክተር እመቤት በተጨማሪ ደግሞ ሁለቱ ታናናሽ ወንድም እና እህታቸው አብረዋቸው ወደኩባ ለትምህርት ይጓዙ ነበር። በወቅቱ ግን በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የተሳተፉት አባታቸው ህይወታቸው አለፈ። በመሆኑም የዶክተር እመቤት እናት ሦስት ልጆቻቸውን ወደኩባ ሸኝተው በከፍተኛ የሐዘን ድባብ ወደቤታቸው ተመለሱ።
በኩባ ሳንዲያጎ ከተማ ትምህርታቸውን የቀጠሉት ዶክተር እምቤት ከትምህርቱ በተጨማሪ ስምንት እና የዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንድምና እህታቸውን እንደታላቅ ብቻ ሳይሆን እንደ እናትም ሆነው የመንለከባከብ ሃላፊነት እንደነበራቸው አይዘነጉትም። በወቅቱ የነፃ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚዎች ግማሽ ቀን ተምረው ግማሽ ቀን ደግሞ በግብርና ሥራ እና በተለያዩ ሥራዎች ላይ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረግ ነበርና ዶክተር እመቤት አጨደውም ሆነ ኮትኩተው ካበቁ በኋላ የሚያገኟትን ትርፍ ጊዜ አያባክኗትም። ይልቁንም በሚኖራቸው ጊዜ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ትምህርት ቤት የሚማሩትን ታናናሾቻቸውን በየጊዜው በመጠየቅ ይነከባከቧቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ከትምህርት ቤት የሚሰጣቸውን ጥቂት የኪስ ገንዘብ እንኳን ይዘው ከእራሳቸው ይልቅ ለታናናሾቻቸው አንድ ነገር ለማድረግ ቅድሚያ ይሰጡ ነበር። በወቅቱ ግን በየዓመቱ የሚያገኙትን ሰርተፊኬት እንኳን የሚያሳዩት ወላጅ አጠገባቸው አለመኖሩ ብዙ ቢያስከፋቸውም፤ ከጊዜ ብዛት ግን ከእራሳቸው አልፎ ለታናናሾቻቸው መከታ መሆን ቻሉ። አብረዋቸው ወደኩባ ካመሩ ኢትዮጵያውያን ልጆች ጋር ልክ እንደእህት እና ወንድም ቅርርብ መፍጠራቸውም ስለቤተሰብ እያሰቡ መጨነቁን አስረሳቸው።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም አጠናቀው ሳንቲያጎ ደኩባ ወደተሰኘው እውቅ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በዩኒቨርሲቲውም የመረጡትን የጥርስ ህክምና ትምህርት መከታተል ጀመሩ። በዚህን ሰዓት የኪስ ገቢያቸውም ከፍ በማለቱ እና የአገልግሎት ሥራውም ስለቀረ የተሻለ የጥናት ጊዜ አግኝተዋል። እርሳቸው ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ደግሞ ታናሽ እህታቸውም በትራንስፖርት ዘርፍ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደኢትዮጵያ ተመለሱ። ዶክተር እምቤት ረጅም ጊዜ የሚፈጀውን የሕክምና ትምህርት በጥሩ ውጤት አጠናቀው ከሰባት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ በኋላ በተራቸው ወደሀገራቸው መመለሳቸው አልቀረም። ወደሀገራቸው ሲገቡ ደግሞ የ24 ዓመት ወጣት ነበሩ።
የኩባው የትምህርት ጊዜ ሰፊ የአስኳላ፣ የሕይወት ልምድ እና ጽናትን አጎናጽፏቸው በድል አጠናቀውታል። ወደኢትዮጵያ መጥተው ከቤተሰብ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ ግን ወዲያውኑ ለተጨማሪ የሕክምና ስልጠና ወደ አሜሪካ አቅንተው ከሰባት ወራት በኋላ ተመለሱ።
ከዚህ በኋላ ታዲያ ትዳርም መጣና የመጀመሪያ ልጃቸውን ወለዱ። በሕክምና ሙያቸው ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ የሁለት ዓመት የአገልግሎት ግዴታ ነበርና ወደአሰላ ከተማ ሆስፒታል ተመድበው የመጀመሪያውን የቅጥር ሥራ ጀመሩ። በአሰላም ጥሩ ቆይታ ሲያሳልፉ፣ ከተማዋንም ወደው ከህዝቡም ጋር በጥሩ ተግባቦት ሕክምናቸውን ያከናወኑበት ወቅት ምንጊዜውም ከአዕምሯችው እንደማይጠፋ ይናገራሉ።
ከአሰላ ሆስፒታል በኋላ አዲስ አበባ በመምጣት በፖሊስ ሆስፒታል የኮንትራት ቅጥር የጥርስ ሐኪም ሆነው አገልግለዋል። በፖሊስ ሆስፒታልም በርካታ ታካሚዎችን ሲያስተናግዱ ከሙያቸው በተጨማሪ ጥሩ ተግባቦት ነበራቸውና እርሳቸውን ፈልገው የሚመጡ ደንበኞች በርካታ እንደነበሩ አይዘነጉትም። በኮንትራት ቅጥር ላይ እያሉም ተጨማሪ ሥራዎችን በግል የሕክምና ተቋማት እየተዘዋወሩ መሥራትም ጀምረው ነበር። ለሁለት ዓመታት ፖሊስ ሆስፒታል ከሠሩ በኋላ ግን ሴት ልጅ ብቻዋን ብትንቀሳቀስ ምን ይከብዳታል? እኔስ ብቻዬን ብሠራ ይህን ፈተና አልፈዋለው ወይ? የሚለውን ለመፈተሽ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸውና በተግባር ለማየት በግላቸው ለመሥራት ይወስናሉ።
ወስነውም አልቀሩ የዛሬ 16 ዓመት ገደማ ዶክተር እመቤት የግል የጥርስ ሕክምና ክሊኒካቸውን ከፈቱ። በአዲስ አበባ ጌታሁን በሻህ ህንፃ ላይ በ20 ሺህ ብር የወር ኪራይ ክሊኒካቸውን ሲመሰርቱ የመጀመሪያ የቤት ኪራይ የቅርብ ጓደኛቸው ሲሸፍኑ አንድ ማሽን ደግሞ አሜሪካ በሚገኙ የቤተሰብ አባላት አማካኝነት ተገኘ። የጽዳት ሠራተኞችን በመቅጠር እና ስለ ሥራቸው የሚገልፁ ማስታወቂያዎችን በመልቀቅ የህክምናውን ተግባር ለመከወን ዝግጅት አጠናቀቁ። ዶክተር እመቤትም በወቅቱ በክሊኒካቸው ውስጥ አንድ ማሽን እና ጥቂት የጥርስ ህክምና ቁሳቁሶችን በመያዝ የሕክምናውን ተግባር የሚከውኑ ብቸኛዋ ባለሙያ ነበሩ።
ሥራ በጀመሩ በመጀመሪያዋ ቀን ጥቂት ደንበኞችን አስተናግደው እንደነበር ያስታውሳሉ። በጥቂት ቀናት ውስጥም በርካታ ታካሚዎችን በማስተናገድ ለስድስት ወራት ትከስሪያለሽ የሚለውን የአንዳንድ ሰዎችን ሃሳብ ፉርሽ አደረጉ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዶክተር እመቤት ፖሊስ ሆስፒታል እያሉ ከሚያገኟቸው ታካሚዎች ጋር ጥሩ ተግባቦት በመፍጠራቸው እና ቀረቤታቸውንም በማጠናከራቸው የተገኘ ገበያ መሆኑን ያስረዳሉ። እንዲህ እያሉ በጥቂት ወራት ውስጥ ክሊኒካቸው ታዋቂ የጥርስ ህክምና ማዕከል በመሆኑ በርካታ ሰዎች የሚጎበኙት ተመራጭ ቦታ ሆነ።
ሥራው እየተደራጀ ሲመጣም ተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎች በመቅጠር የማሸኖቻቸውንም ቁጥር ጨመሩ። ዶክተር እመቤት በክሊኒካቸው የሚቀጥሯቸው የጽዳት እና ሌሎች ሠራተኞች አብዛኛዎቹ ወጣት ሴቶች ናቸው። እነርሱንም በማስተማር ለህክምናው ዘርፍ ግብዓት እንዲሆኑ ማብቃቱን ያውቁበታል። በተለይ በ200 እና 220 ብር በጽዳትነት ከቀጠሯቸው እንስቶች መካከል አሁን ላይ ዶክተር እና የጤና መኮንን ደረጃ የደረሱ አሉ።
በሥራቸው ከሠሩ የጽዳት ሠራተኞች መካከልም ትምህርታቸውን በማሻሻልም በዴንታር ቴራፒስትነት እና በከፍተኛ የሕክምና ሙያ የደረሱ እና አሁንም አብረዋቸው የሚሠሩ ባለሙያዎችም መኖራቸውን ይናገራሉ። ይህ መተጋገዝም ለተሻለ ለውጥ መርቷቸዋል። የዶክተር እመቤት ጥሩ ግንኙነት ከሠራተኞቻቸው ባለፈ ከህንፃው አከራዮቻቸውም ጋር የተቆራኘ ነው። በርካታ ጊዜያት የጌታሁን በሻህ ህንፃ ባለቤቶች በሃሳብም ሆነ ሰፋ ያለ ቦታ በሚፈልጉበት ጊዜ ተጨማሪ የኪራይ ቦታዎችን እየለቀቁላቸው ለሥራቸው እገዛ እንዳደረጉ አይዘነጉትም።
ዶክተር እመቤት የጌታሁን በሻህ ህንፃ ባለቤቶች አከራዮቻቸው ጥሩ ቢሆኑላቸውም የእራሳቸውን ህንፃ ገንብተው መሥራት ደግሞ ፈልገዋል። እናም አሜሪካ የሚገኝ የቤተሰባቸው አባል ወደ ሀገርቤት ሲመለስ የትኛው ዘርፍ ላይ አብረው መሥራት እንደሚችሉ ያማክራቸዋል። እርሳቸውም ህንፃ ገንብተው የሕክምና ተቋሙም የእራሱ ቢሮ እንዲኖረው የሚያስችል እና ተጨማሪ የሚከራዩ ሱቆችም ያሉት ግንባታ ላይ ቢሰማሩ መልካም እንደሚሆን ሃሳብ ያቀርባሉ። በመሆኑም ሾላ አካባቢ የሚገኝ የቤተዘመድ መሬት ላይ ባለድርሻ ሆነው የሚያሰሩት እና ከመሬት በላይ 10 ወለሎች ያሉት ህንፃ ግንባታ ተጀመረ።
በወቅቱ አሜሪካ ያለው ቤተሰባቸው ለግንባታው የሚሆን ገንዘብ በየጊዜው ቢልክም የእራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት ደግሞ ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠል የግድ ነበር። የህንፃው ግንባታ ከፍተኛ ገንዘብ የጠየቀ በመሆኑ ግን ዶክተር እመቤት ተሽከርካሪያቸውን እና የተለያዩ ንብረቶቻቸውን እስከመሸጥ የደረሰ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ያስታውሳሉ። ለህንፃው የሚሆን ብድር ከባንክ እስኪፈቀድላቸውም የግንባታውን ማጠናቀቂያ በተለይም የአሉሙኒየም ሥራውን ትራኮን ትሬዲንግ በዱቤ አገልግሎት በማከናወኑም ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል ይላሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ በብዙ ጥረት በመሃል አዲስ አበባ ያማረ ህንፃ ገንብተው አጠናቀቁ። ከተከራዩበት ህንፃ ለቀውም ባለድርሻ በሆኑበት ወደሚናሮል ህንፃ ሙሉ ዕቃቸውን አዘዋወሩ።
በህንፃው ውስጥም ዘመናዊነቱን የጠበቀ የጥርስ ሕክምና ሥራቸውን በማስፋፋት አገልገሎቱን በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መስጠቱን ቀጠሉ። በህንፃው ሌላኛው ክፍል ደግሞ በልጃቸው ሮሚ ስም የተሰየመው እና ሮሚ ቢውቲ እና ስፓ የተሰኘው የውበትና ንጽህና መጠበቂያ ተቋም ተከፍቶ አገልገሎት እየሰጠ ይገኛል። ልጃቸው ስም በሰየሙት በሮሚ የውበትና የንጽህና መስጫው ክፍል ብቻ 120 ሠራተኞች ቀጥረው እያሠሩ ይገኛል። በሚናሮል እና ዶክተር እመቤት የሕክምና ተቋም ሥር ደግሞ 350 ቋሚ እና ከሰላሳ በላይ የኮንትራት ሠራተኞች አሉ።
የቤተሰብ ያክል ቅርርብ ያለበት የዶክተር እመቤት የሕክምና ተቋም አሁን ላይ በተደራጁ መሣሪያዎች እና በበርካታ ባለሙያዎች ተጠናክሮ ሰፊ ሕክምና እየሰጠ ይገኛል። በዶክተር እመቤት ሥር ተቀጥረው ከህንድ፤ ፊሊፒንስ፣ ኩባ እና ኮርያ የመጡ ሰባት የውጭ አገራት ከፍተኛ ባለሙያዎችም የጥርስ ህክምና ይሰጣሉ። በአንድ የጥርስ ማሽን የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ 18 ማሽኖች ደርሷል። ከአሜሪካ እና አውሮፓ የእርሳቸውን ሕክምና ተቋም አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ በርካታ ደንበኞች አሏቸው፤ በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡት ህክምና ከውሮፓውያን ጋር ቢነፃፀር የተሻለ እንጂ የማያንስ መሆኑን እርግጠኛ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ዶክተር እመቤት አሁን ላይ በዓለም በጥርስ ሕክምና የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የያዘውን ማሽን በ300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር አስገብተው ተጨማሪ ማዕከል ለመክፈት ዝግጅት ላይ ናቸው። ማሽኑ ሲገባም እራሱን የቻለ የጥርስ ሕክምና ላብራቶሪው አቋቁመው ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ የጥርስ ህክምናን እንደሚከናወንበት ይናገራሉ። ውጥናቸው በቅርብ ጊዜያት እውን ሲሆን በጥርስ ሕክምና ቱሪዝም ኢትዮጵያ ተመራጭ እንድትሆን የሚያደርግ ዕድል እንደሚፈጠር ያስረዳሉ። ሐሳባቸው እንዲሳካ እኛም መኞታችን ነው።
አራት ልጆች ያሏቸው ዶክተር እመቤት ከሙያቸው በተጨማሪ ልጆቻቸውን አሳድገው ለቁም ነገር ማብቃት ችለዋል። ለእርሳቸው ሥራ ማለት ፍሬ ያለው በጥራት የሚከናወን ሙያ ማለት ነው። ማንኛውም ሰው በሙያው ትጋት ካለው ማደግ የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። በተለይ ወጣቱ ትውልድ ጊዜውን በአልባሌ ነገሮች ከሚያሳልፍ የተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርቶ ነገውን የተሻለ ለማድረግ ቢነሳ ውጤቱ ያማረ ይሆናል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2012
ጌትነት ተስፋማርያም