የሰው ልጅ የአኗኗር ስልት አንዱ ከአንዱ መለየቱ የታመነ ነው። ይህም በባህል በትውፊት፣ በእምነት አስተምህሮ፣ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በሙያ ባህሪና በሌሎች ተጨማሪ ነገሮች እየተደገፈ የሚናከወን ስልት ነው። ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ የአኗኗር ስልት የማን ነው ብለን ስንል ከእነዚህ በአንዳቸው ወይ ከአንድ በላይ በሆነ ምክንያት ሰው የኑሮ ስልቱ አንዱ ከአንዱ የተለየ ሆኖ ይገኛል።
ቁምነገሩ የኑሮ ከፍታው፣ እና ዝቅታው ሳይሆን እንዴት ነው መስተጋብሩ ነው፤ ዋናው ጥያቄ። በቅድሚያ ራሱ ከራሱ ጋር ያለውን ቅርበትና ውህደት ይጠብቀዋል። ራሱን በሚገባስ ያውቃል? ወይስ በደመነፍስ ነው፤ የሚኖረው? ለአንዳንዶቻችን በደመ ነፍስ የሚኖረው የሌላው ኑሮ፣ ያልሰለጠነ የሚመስለን የሌላው ዘይቤ በአካባቢው ቅቡልነት ያገኘ ድንቅ የአኗኗር ስልት መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን ?!
በደቡባዊና በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙት አርብቶ አደር ወገኖቻችን የሚኖሩበት የኑሮ ስልት ከተሜና ትምህርት ቀመስ የሆንነውን እኛን የከተማ ነዋሪዎች የሚያስገርም እና እነርሱን የምናይበት መንገድ ያንሸዋረረ ነው። ምክንያቱም የኑሮ ስልታቸው እኛ ከምንኖርበት፣ የእምነት ወጋቸው እኛ ከምናውቀው፣ የአለባበስና የጋብቻ ባህላቸው እኛ ከምንገምተው ውጭ መሆኑን ስናስብ እንደመዘግነን ያደርገናል፤ ይንና በእነርሱ ዘንድ ቅቡልነት ያገኘ የኑሮ ዘይቤ ከሆነ እንዳለ መቀበልና የራሳችንን ማሳየት ነው፤ የሚበጀው። እነርሱን ሄደን እንዳየን እነርሱም መጥተው እኛን እንዲያዩ ማድረግ ነው፤ መድኃኒቱ።
አንድ ወዳጄ እንዳጫወተኝ፤ ከዛሬ 25 ዓመት ገደማ በፊት የኢትጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ጫወታ በቤተ መንግሥት ለማቅረብ ትልቅ ዝግጅት ተደርጎ ነበረ። (በነገራችን ላይ ይሄ ባህላዊ ጫወታ ከዚያም በፊት ይደረግ ነበረና ለመጀመሪያ ጊዜ የሚባል ነገር የለም፤ ብሎኛል ወዳጄ) ለመቀበል ምክንያት የሆነኝ አንድም፣ እነዚህ ባለባህል ህዝቦች ከዚያን ጊዜ በፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩና በቀደመው ዘመን የብሔረሰቦች ኢንስትቲዩት ተቋቁሞ ለእነዚህ ወገኖቻችን የጥናት ማዕከል መከፈቱን አንብቢያለሁና።
ወደአጫወተኝ ጫወታ ልመልሳችሁና፤ እነዚህ ወገኖቻችን አዲስ አበባ እንደደረሱ ወቅቱ የበልግ ዝናብ የሚጥልበት ጊዜ ነበር። አዲስ አበባ እኝኝ በሚያሰኘው ዝናብና ብርዷ ሁላችንንም የተቀበለችበት ወቅት ነበር። ታዲያ ብርዱ በነማን ቢብስ ጥሩ ነው? ያለጥርጥር በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ ነበር። ጥርሶቻችው ጭምር ነበር የሚንቀጫቀጨው። ስለዚህ ቀላል ብርድ ልብሶች ተሸምተው እንዲገለድሙ ነው የተደረጉት ሌሎች ልብሶችም ተገዝተውላቸዋል። እናም አንዱ አርብቶ አደር ያለኝ ነገር እጅግ አስገርሞኛል፤ የከተማ ሰው ከላይ እስከታች ልብስ የሚለብሰው ሰውነቱ ስለሚቆስል ነው ብለን እናስብ ነበር፤ ለካ እንደኛ ስለማይኖር መሆኑ አሁን ገባኝ ብሎኛል።
የራሳችን ልጆች ለትምህርት ሄደው ሲመለሱ እነርሱ እኛን ከማቀፋቸው በፊት እንደባህላችን እንዲለብሱ ነው የምናደርጋቸው ብሎኛል ሲል ነው፤ ያጫወተኝ። እውነት ነው፤ የራስን ልክ ለማወቅ ሌላውንም ማየት ጥሩ ነው።
እነርሱም እርቃን የሚለብሱት፣ የበረሃው ረሞጫ ግለት ከልብሳቸው ሌላ ቆዳቸውን እንዲገፉት የሚገፋፋ ዓይነት መሆኑ ነው። ይህንን ከተገነዘብንላቸው የማይለብሱት የሚኖሩበት መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ስለማይፈቅድላቸው መሆኑን ማጤን አይገደንም ።
ውጫዊ ሁኔታዎች በውስጣዊ አስተሳሰባችንም ላይ የራሳቸው ተጽዕኖ እንዳላቸው ማሰብም መልካም ነው። እነዚህ ወገኖቻችን ለጋብቻ የሚሄዱበት ብቃትን የመለኪያ መንገድ ከተሜ ለሆንነው ለእኛ ላይዋጥልን ይችል ይሆናል፤ በዚህ አካባቢና ሁኔታ ውስጥ ለሚያልፍ ሐመር ወይም ዳሰነች ወይም ቤንች፣ ወይም ዲዚ ግን ከዚ ያለፈ መስፈርት የለም። ይህ የግርፍና ከብት የመዝለል ባህል የወንድነትም የውገናም ባህል መለኪያ ብቻ ሳይሆን ለሚወዳት ልጅ የከፈለው የሰንበር ዋጋ ጭምር ሆኖ ይኖራል።
እነርሱ የእኛን ልጆች ታቱ ( ንቅሳት ) በማየት ሊገረሙ እና አሁን ይሄ ፍቅር ነው ሊሉ ሁሉ ይችላሉ። በነገራችን ላይ መነቀስ የፍቅር ብቻ ማሳያ ስልት ነው እያልኩ አይደለም። አንዳንዴ ሴቶቹ ልጆች የሚወዱትን ሰው የመጀመሪያ ፊደል በመነቀስ፣ ሲያሳዩ ወንዶቹ ልጆች ደግሞ የልጅቱን ምስል በሆነ የአካላቸው ክፍል በመነቀስ ፍቅራቸውን ለማሳየት ሲሞክሩ ይታያሉ።
በእውነት ግን ለምንወደው ሰው እምነታችንን የምናሳየው በንቅሳት ነው? የምንወደውን ሰው ፍቅራችንን ለመግለጽ የሚረዳን ፎቷቸውን ማንጠልጠል ነው? ይህ ሁሉ እውነት እንዳልሆነና ልብ ለውጥ የሚሻ ናፋቂ እና አማታሪ ዓይን የተገጠመለት ፍጥረት መሆኑን መሳት የለብንም፤ በተለይ በወጣነት ዘመን።
የዚህ ጽሁፌ አላማም ራሳችንን ስንፈትሽ ምን እንመስላለን ማለት ፈልጌ ነው። ለምንወዳቸው ሰዎች በአካልም፣ በመንፈስም በልቦናም የተገለጠ ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነን፣ ወይስ በአንደበታችንና በንቅሳታችን መግፁ በቂ ነው ብለን እናስባለን።
ይህንን ከምንወዳቸው ሰዎች ጋራ ባለው ግንኙነት ዙሪያ አነሳሁት እንጂ፤ ልባችንን ለእውቀትና እጆቻችንን ለሥራ በመግለጽ ውስጥ ያለን ሚና ምን ያህል ባለን አቅም የታገዘ ነው? መቼም ራሳችንን በንባብ፣ መልካምና የበቁ ሌሎችን በማዳመጥና የሚተገበሩ ሰዎችን በማየት ማዳበር ካልቻልን ራሳችንን የማበልፀጊያ መንገድ የለንም። ለዚህስ ስንቶቻችን ራሳችንን ለመግለጽ ዝግጁ ነን? ምን እናነባለን? የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ በቀን ምን ያህል እናነባለን? 20 ገጽ 40 ፣ 50፣ ወይስ መጽሐፍ ሙሉ እንጨርሳለን? ይህ እንደተሰጠን የልብ ትጋት የሚለካ ቢሆንም እናነባለንን ወይ የሚለው ዋናው ጥያቄ ነው።
አብርሐም ሊንከን (ስመጥሩው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ) የሚነበብ ነገር ፍለጋ፣ እስከ 15 ኪሎ ሜትር በእግሩ ተጉዞ መጽሐፍ ተውሶ ያነብብ እንደነበረ ይናገራል። ስለመጻህፍት ጠቃሚነትም ሲያወራ አይጥምም፤ በተባለ መጽሐፍ ውስጥ እንኳን የሚጠቅም አንድገጽ አታጡም፤ ይላል። የዚያ አንድ ገጽ እውቀት ታዲያ ወደውስጣችሁ የሚጨመር ነው ይልና አለመጣሙንም ማወቅ የሚጥሙ መጻህፍትን ለማድነቅ በር ይከፍትላችኋል፤ ማለቱ ይነገራል።
መጽሐፍ ለመዋስ የሚጓዘውን ጉዞ ያህል ለመመለስ የማይጓዝ መሆኑን ስታስቡ ደግሞ በዚህ ትጋቱ ላይ፤ ፍፁምና እንደሌለው ታስባላችሁ። እውነት ነው፤ ታዲያ ለሌሎች አውሶ ለመጠየቅም እንዲሁ ነው። ከዚህ የምንማረው ለመዋስ የተጋኸውን ያህል ለማዋስ መትጋትም የተገባ በመሆኑ ስለእርሱ የሚሰማንን ቅሬታችንን ያጠፋዋል።
ማንም ሰው ስሕተት የማይገኝበት ፍፁም አይደለም። ዋናው ቁም ነገር ሊሳሳት መቻሉን መቀበል ላይ ነው፤ እንዴት ተሳሳተ ይሉኛል የሚል ሰው እየሰራ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ሙት ነው። ከውጭ ላለው ሰው ጥያቄ መልስ የማይሰጡ ራሳቸውን ብቻ የሚዳምጡና መልስ ሲሰጡ የፈለጉትን የሚናገሩ ናቸው። በሥነ-ፍጥረት እንደዚህ ያሉ ሰዎች አይሰሩም፤ ሰዎች ግን በጊዜ ሂደት እነዚህን ጠባያት ያዳብራሉ።
አንድ ጊዜ በደርግ አገዛዝ ዘመን ሚኒስትር የነበሩትና፣ በአንደበተ ርቱእነታቸው የሚታወቁት፤ በአምባሳደርነት ማዕረግ የሚጠሩት፣ አምባሳደር ካሳ ከበደ (ዶ/ር)፤ ቪኦኤ (የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ አማረኛው ዝግጅት ክፍል) ስለቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጎሹ ወልዴ፣ አሜሪካ ሄዶ መቅረትና ስለሚፈጠረው ክፍተት፣ ሲጠይቃቸው ጎሹ ወዳጄ ነው፤ ብርቱ ሰው መሆኑን አውቃለሁ፤ አሁን ያለበትን ሁኔታ አላውቅም…ወዘተ… አሉ መልስ ሲሰጡ ጋዜጠኛው በስጨት ብሎ ስለሰውየው እና እርሶ የግል ግንኙነት ወደኋላ እመልስበታለሁ፤ አሁን ግን በሥራው ላይ ምን ክፍተት ይፈጠራል? ብሎ ሲሞግታቸው ጓድ መንግሥቱም፣ ጎሹ ወልዴን በጣም ይተማመኑበት ነበረ፤ በተረፈ በአንዳንድ ነገር ይጠራጠረኝ እንደነበረ ሰዎች ነግረውኛል፤ በማለት ከጥያቄው ጋር ያልተያያዘ መልስ የተሰጠው ጋዜጠኛ፣ የምንፈልገውን ሳይሆን የሚፈልጉትን ነው፤ እኮ የሚናገሩት ሲላቸው፤ በግሌ እየፈተሸከኝ ነው? (Are you Interogetting me?) የምርመራ ጋዜጠኝነት የሚባልም ነገር አለ፤ ሲል ቁጣቸውን እንዳለዘበው ተደምጧል። በዲፕሎማሲ ቋንቋ ጠያቂዎችህ፣ የሚፈልጉትን ሳይሆን የምትፈልገውን ንገራቸው፤ የሚል አባባል አለና ያንን የተከተሉ ነበረ፤ የሚመስለው። ይሁንናም ብዙ ሰዎች ስትጠይቋቸው የፈለጉትን እንጂ የምትፈልጉትን አይነግሯችሁም።
አንዲት ዘመዳችን መምህርትም፤ ዘመድ ሞቶባት ርዕሰ መምህሩን ዘመድ ስለሞተብኝ ልሄድ መሆኑን ልነግርህ ነው፤ የመጣሁት ስትለው። “ለምን ቅዳሜና እሁድ አትሄጂም ፤” የሚል መልስ ሲሰጣት ፤ “ በቀጠሮ የሚሞት ዘመድ ይስጥህ!” ብላው እንደወጣች ለሰዎች ተናግራለች። አንዳንድ ሰዎች ምንን መቼ መናገር እንዳለባቸው አያውቁም።
ስንቶቻችን በአንደበትና በድርጊት ራሳችንን እንመስላለን። ሽሮ በልተን ወጥተን፣ የበላችሁትን ምግብ ምንነት የሚመረምራችሁ ያለ ሰው ይመስል፤ “ስቴኪኒ” ይዘን መታየት የሚቀናን፣ ስንቶች አለን? ከውስጣችን እውነተኛ ማንነት ይልቅ ማንነታችንን ለሌሎች አሳልፈን የሰጠንና በማይገባ ምንይሉኝ ሰንሰለት ራሳችንን ጠፍረን ያሰርን ስንት ሰዎች አለን። ውጫችን ውስጣችንን የበለጠብን፣ ለሌሎች ሰዎች አስተያየት ራሳችንን ስንገዛ ስንቶች እንኖር ይሆን?
ለሌሎች ሰዎች አስተያየትና ትችት ራስህን ካስገዛህ ራስን ፈልገህ መቼም አታገኝም። ብዙ ሰዎች አንተ ራስህን ፈትሸህ እንድታገኝ እና መንገድህን እንድትቀጥል አቅጣጫ ጠቋሚ (ኮምፓስ) ይሆኑኛል ብለህ ካሰብክ ያሰብክበት አትደርስም። ምክንያቱም ያንተ ዕጣ ፈንታ ወይም ግብህ የወደቀው ባንተ እጅ እንጂ በአስተያየት ሰጭዎችህ ፈቃድ ሥር አይደለም ።
እየሞከርክ እያለህ ብትወድቅ ይሻላል እንጂ በአድራሾች ግፊት ከግቡ የደረሰ ማንም የለም። እየሞከርክ ስትወድቅ እንደገና መሞከርን ትለማመድበታለህ እንጂ አታፍርም፤ መውደቅ ተንከባልሎ መቅረት ነው ዳግመኛ መሞከር ግን ነፍስ መዝራት ነው፤ ህዳሴ ማግኘት ነው። ስትሞክር ክፉና ተሰበርክ ? እንኳን ተሰበርክ መጠገኛው ያለው በአንተ እጅ ነው ወጌሻ ፍለጋ መንደር ለመንደር አትዙር፤ የመንደር ወጌሾችማ፣ አጥንትህ ተሰብሮ እንደሆነ ሥርህን ጨምረው አዙረው ሽባ ያደርጉሃል። (ስለልምድ ወጌሾቻችን ተራዳኢነት እያንኳሰስኩ አለመሆኑን አጢኑልኝ) ይልቅ ልምዱም እውቀቱም የሌላቸውን ልብ አዝል፣ አዕምሮ ሰንክል ሰዎች እተናገርኩ ነው።
ስለዚህ ራስህን ፈትሽ! ስትፈትሽ የወደቅክባቸውን ነገሮች መርምር፤ የመረመርካቸውን እርምጃዎችህን አጢን፤ ቅደም ተከተሉ ነበር ስህተቱ? ጉልበት አለመጨመርህ ነው? የገንዘብ አቅም ነው? የመፈተሻው መድረክ ነው? ጊዜው ነው? ወይስ ምን? ብለህ ጠይቅና ልቦናህ አውጥቶና አውርዶ የሚነግርህን ተቀበል። ከዚያ እርምጃ ውሰድ።
አንድ ነገር ላክልልህ እወዳለሁ፤ ወደምትፈልገው መንገድ ለመድረስ አቋራጭ መንገዶችን አትጠቀም፤ በምንም ምክንያት ግብህ ምንም ያህል የተቀደሰ ቢሆንም የምትከተለው ያካሄድ ስልት ስህተተኛ ከሆነ ውጤትህ ያመረ ቢመስልም የክፋትና ስህተት አሻራው እድሜ ዘመንህን ይከተልሃልና ድልህ ዘለቄታዊ አይሆንምና፤ ወደኣላማህ ለመሄድ የምትራመድበትን መንገድ አጥራው።
በጥቅምቱ አብዮት (የሩሲያ አብዮት )የመጨረሻዎቹ ወራት፣ የንጉሡ አገዛዝ በሥራ ማቆም አድማ፣ በሠራተኞች አመጽ በአርሷደሮች ቁጣ ተመልቶ ነበረ። ያኔ ታዲያ ሌኒን፤ ቤተ-መንግሥቱን ለመያዝ የሚደረገውን ጥረት እየመራ በዚህ ቦታ ጓዶቻችን ተጎዱ፣ በዚያ ቦታ የአርሷደሮች ማሳ ተቃጠለ እያሉ ሲነግሩት፣ ሰማ ሰማና “በሲኦልም በኩል ቢሆን ተጉዘን ክሬምሊንን መቆጣጠር አለብን” ሲል መናገሩ ተደምጧል። እውነት ነው፤ ለብዙ ሚሊየን ሰዎች እልቂትና ሞት ምክንያት የሆነውን “አብዮት” የተባለውን ማህበረሰባዊ ጉድ ወደዚህ ምድር በሰው ልጆች ደም ማምጣ ችለዋል። ነገር ግን፣ የሌሎቹ የአገዛዝ ስልቶች ከ200 ዓመታት በላይ ሲዘልቁ የነሌኒን አገዛዝ፣ ( ላባደሩ ባይኖርበትም “የላባደሩ አምባገነንነት” ይሉታል፤ እነርሱ) ከ70 ዓመት ከፍ ማለት አልቻለም። ምክንያቱም ወደሚፈልጉት ግብ ለማድረስ ብዙ የማይፈለግ የደም አበሳ ፈስሶበታል፤ በስህተት የተሞሉ የእልቂት መንገዶች ተሂደውበታልና ነው።
አንዳንዴ ማህበራዊ የሚመስሉን የታላላቅ ግብ ሃሳቦች በአንድና ሁለት ሰው ጭንቅላት ውስጥ ተጸንሰው ነው፤ ወደማህበረሰባዊ ስርፀት የሚሄዱት። እነሌኒን ሲጀምሩ ወደቁ፤ እነ ስታሊን ተከተሉትና ሰውን በመደብ፣ በአሰላለፍ መተሩትና በተገኘበት እንዲገደል የሚያዝዝ ቀላጤ እያወጡ ሰየፉት። ይህ የቀይ ሽብር ጦስ መልክና ቅርፁን ሳይለውጥ ህጋዊ ከለላና አደረጃጀት ከሰይፍ ተሰጥቶት በኢትዮጵያ ምድርም (ከ1969-72 ዓ.ም.) ለአራት ዓመታት ያህል ጋልቧል። ታዲያ በአጥፊ ጀግንነት የተሳተፉትን ሰዎች ሳያጃግን ለትውልድ ወቀሳ ዳርጎ በ10ኛው ዓመት ላይ ጉዞ ፍታቱ ተፈጽሟል።
ይህ የታሪካችን አካል የሆነውን ክፋት ማስቀረት ይቻል ነበር። ይሁንናም አብዮታውያን ከተባሉት አካላት ወይም አገሮች ስንገለብጥ ክፋቱን ያለሰብዓዊነት፣ ቁጥጥርን ከምህረት ጋር ሳንደባልቅ ሆነና ትውልድ ጥርሱን የነከሰበት እልቂት ተፈጥሮ በዘመኑ የተሰራውንም ደግ ይዞት ገደል ገባ።
በግል ራሳችንን ስንፈትሽ የምናየውን ግድፈት አርመን ለመጓዝ የምንችለውን ያህል እንደማህበረሰብም አረሙን ነቅሰን በማውጣት ስህተታችንን በማይደግም መልኩ ተያይዘን ለመሄድ ከልባችን፣ ልባችንን መፈተሽ ይገባናል። ከጥፋታችን ተምረንና አጥፊውን እንዲታረም አስተምረን፣ መጓዝ ቀሪ የቤት ሥራችን ነው።
ያልተፈተሸ ማንነት፣ ያልተሰራ ሰብእና ውጤት ይሆንና በውጤቱም ሐዘናችን እየከበደ፣ ቁዘማችን እየቀጠለ ይሄዳል። በተፈተሸ ማንንት ግን ሐዘን፤ ንዴት ና ብስጭት ስፍራ የላቸውም። ሰው ድክመቱን አውቋልና አረሙን ጎልጉሎ በማውጣት የህይወት አዝመራውን ያበለጽጋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ