የእረፍት ቀኑን በቤቱ ያሳለፈው ወጣት ከሰአት በኋላ ከመኝታው አረፍ ብሎ ቀጣዩን ዕቅድ ያብሰለስላል። ድንገት ግን ቀሪውን ጊዜ ፊልም ማየት እንዳለበት ውስጠቱ ሹክ አለው። በድንገቴው ሃሳብ አላንገራገረም። በቅርቡ ካሉት በርካታ ሲዲዎች አንዱን መርጦ ከቴሌቪዥኑ ከተዛመደው የዲቪዲ ማጨወቻ ሆድ ሰደደው። ጥቂት ቆይቶ ዲቪዲው ከሚፈልገው ምስል ጋር አገናኘው።
ወጣቱ ሳምንቱን ሙሉ በኮሌጅ ትምህርቱ ላይ አተኩሯል። የዛሬውን የዕረፍት ቀን በዚህ መልኩ ማሳለፉም ደስብሎታል። አንዳንዴ ከቅርብ ጓደኞቹ ጋር ወጣ እያለ መዝናናት ምርጫው ነው። ከባልንጀሮቹ በሚኖር መዝናናት አይረሴ አጋጣሚዎችን ያስታውሳል። ብዘዎቹ የሚያዝናኑ ቢሆኑም ጥቂቶቹ ደግሞ በወጣትነት ስሜት የተዋዙና አላስፈላጊ ዋጋ የተከፈለባቸው ናቸው።
ወጣቱ ሲያየው በቆየው ፊልም ዘና ሲል ቆይቷል። ከዚህ በኋላም ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር ወጣ ብሎ ሻይ ቡና ቢል አይጠላም። ይህን እያሰበ አእምሮውን አርቆ አሻገረው። ከሄደበት ጥልቅ ሃሳብ ከመመለሱ በፊት ግን የእጅ ስልኩ እየጠራ መሆኑን አወቀ። በስልኩ ግንባር ላይ ያለውን ስም እንዳየ ተጣድፎ አነሳው። የቅርብ ጓደኛው ደጀኔ ነው። ፊቱ በፈገግታ እንደበራ ሀሎ ሀሎ ሲል ምላሽ ሰጠ።
መጀመሪያ…
ደጀኔ ዕለቱን በመዝናናት ማሳለፍ ፈልጓል። ለዚህ የሚሆን ገንዘብም በኪሱ መኖሩን ያውቃል። ከትምህርት መልስ መደሰት የሚወደው ወጣት ባልንጀሮቹ ብዙ ናቸው። አብዛኞቹ የመጠጥ ሞቅታን ይወዳሉ። ሲዝናኑ ተሰባስበው በመሆኑ ለጠብ ያሰቧቸውን ከመግጠም አይመለሱም። ወጣትነታቸው በተመሳሳይ ስሜት አውሎ ያሳድራቸዋል። በተገናኙ ጊዜ ቋንቋና ድርጊታቸው አንድ ነው።
ደጀኔ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ቀበና ከሚባል አካባቢ ነው። ቤተሰቦቹ እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ትምህርት ቤት የላኩት ገና በጠዋቱ ነበር ። ሁሌም ቢሆን መልካሙን የሚመኙት ወላጆች በልጃቸው ተስፋን ይዘው ኖረዋል። በትምህርቱ ጠንክሮ እንዲማር ይፈልጋሉ። በዕውቀቱም ከሌሎች እንዲያንስ አይሹም። ሲያሳድጉት የሚፈልገውን እየጠየቁ፣ የጠየቀውን እያሟሉ ነው።
ደጀኔ እንደወላጆቹ ፍላጎት ሆኖ በትምህርቱ በረታ። በአንደኛ ደረጃ ትምህርቱ መልካም ውጤት ሲታይበት ቤተሰቦቹ ደስ አላቸው። እሱም ቢሆን የነገውን ትልቅ መሆን አስቦ የያዘውን አጠበቀ። ተምሮና ተመራምሮ በተሻለ መንገድ ለመቆምም የአቅሙን ሁሉ ታገለ።
ትምህርትና ደጀኔ መታገላቸውን ቀጥለዋል። አሁን በዕድሜው ጭምር የበሰለው ታዳጊ የማትሪክ ፈተናን ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው። አስረኛ ክፍል ሲደርስ ወላጆቹ የተለየ ግምት ሰጥተው ተንከባከቡት።
እንደታሰበው ሆኖ ደጀኔ የአስረኛ ክፍል ፈተናን ወሰደ። ቀጣይ የሚኖረው ጊዜ ለእሱ ወሳኝና አስፈላጊ የሚባል ነው። አሁን ከልጅነቱ ብዙ ሲያስብበትና ወላጆቹም ስለእሱ መልካሙን ሲያቅዱለት የኖሩት እውነት መሰረት ይጣልበታል። እናም ከፈተናው በኋላ ውጤቱን ተስፋ አድርጎ ጠበቀ።
የፈተናውን ውጤት የመስሚያ ጊዜው ደረሰ። ደጀኔና ባልንጀሮቹ ወደ ትምህርት ቤታቸው ሄደው ውጤቱን ለመቀበል ጓጉ። አብዛኞቹ እንደታሰበው ሆኖ የተፈለገውን አገኙ። ጥቂቶቹም የሰሩትን ያህል አላጡም። ደጀኔና አንዳንዶች ግን በቂ የሚባል ውጤት አልያዙም።
ከማትሪክ ውጤቱ በኋላ የደጀኔ ወላጆች ቅር ተሰኙ። አሁንም ግን ተስፋ አልቆረጠም። በልጃቸው ዕጣ ፈንታ ላይ መክረው አማራጮችን ፈለጉ። ደጀኔ የታሰበውን ያህል ውጤት ባያመጣም በግል ኮሌጅ እየከፈሉ ሊያስተምሩት ወሰኑ። የወላጆቹን ፍላጎትና የማስተማር ጉጉት ያስተዋለው ወጣት በሃሳባቸው ተስማማ። በአንዱ የግል ኮሌጅ ተመዝግቦም ትምህርቱን ቀጠለ።
ወላጆቹ ተስፋቸው ዳግም ሲቀጠል ቢያስተውሉ ውስጣቸውን ተስፋ መላው። አሁንም ልክ እንደትናንቱ ያሻውን እያሟሉ የጠየቀውን እየሰጡ ማስተማራቸውን ቀጠሉ። የልጃቸው ፍላጎት ከትናንት ይልቅ ዛሬ ላይ ይለያል። ዛሬ ያላቸውን ቀንሰው ከማስተማር ባለፈ ለትራንስፖርትና ለሌሎች ወጪዎቹ ተጨማሪ አቅምን ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ አሁን ባለበት የዕድሜ አፍላነት ከእኩዮቹ በታች እንዲሰማው አይሹም። የኪስ ገንዘቡን ሲሰጡ መዝናናት እንዳለበት ያስባሉ።
ደጀኔ የእራሱን ሃሳብ ከወላጆቹ ጉጉት አዳምሮ በትምህርቱ በረታ። ቤተሰቦቹን አስደስቶ ያሰበው ጥግ ለመድረስም በየቀኑ ብርቱ ተማሪ ሆኖ ትጋቱን አሳየ። ብዙ ጊዜ በርከት ብለው ከሚገናኙ ባልንጀሮቹ ጋር ይዝናናል። አንዳንዴ መዝናናታቸው ከሻይ ቡና አለፍ ብሎ አስከመጠጥ መጎንጨት ይደርሳል። ጨዋታ ደምቆ ሞቅታው ሲከተል ግን ውሎና ምሽታቸው በሰላም ላይቋጭ ይችላል።
የአፍላነት ፈተና
በመዝናኛ ስፍራዎች ከሌሎች ጋር በሚኖር አለመግባባት ከጭቅጭቅ አልፎ ድብድብ ጭምር ይኖራል። እንዲህ በሆነ ጊዜም ከማስማማትና ከመገላገል ይልቅ ተደርቦ በመጣላት ጠቡን ማባባስ የተለመደ ነው። ይህ አይነቱን አጋጣሚም ደጀኔና ባልንጀሮቹ ሲያልፉበት ኖረዋል።
እነ ደጀኔ የአፍላነት ስሜት እየፈተናቸው ብዙ አልፈዋል። በትምህርት ከማተኮር ባለፈ በሚዝናኑበት ቦታ ጠበኞቻቸውን ሲያገኙም በርቀት እየተያዩ መዛዛቱን ለምደውታል። አንዳንዴም የቆየ ቂምና ጥላቻ ካለ መልሶ ለጠብ መፈላለጉ ይኖራል ።
ብዙ ጊዜ ደጀኔ በኪሱ ገንዘብ ባለው ጊዜ ከመጠጥ ያለፈ ግብዣ ላይ ማሳለፍ ይወዳል። የቅርብ ጓደኞቹን ጠርቶም ምሳ አልያም ራት መጋበዝ ደስ ይለዋል። እንዲህ የሚያደርገው ከውስን ጓደኞቹ ጋር ነው። ይህን የሚያውቁ የቅርብ ባልንጀሮቹም ከግብዣው በኋላ አይቀሬውን መጠጥ ፉት እያሉ አብረውት ይቆያሉ።
ደጀኔ በወላጆቹ እገዛ መማር የጀመረውን የኮሌጅ ትምህርት አጠናቆ የሚመረቅበት ጊዜ ደርሷል። ይህን የሚያውቀው ልቦናውም ወደመዝናናቱ ማጋደል ጀምሯል። በዘንድሮው ዓመት ትምህርቱን አጠናቆ ለመመረቅ ሲበቃ ከራሱ አልፎ ለወላጆቹ እፎይታ እንደሚሆን ያውቃል።
ቤተሰቦቹ ከልጅነቱ ጀምሮ ዋጋ የከፈሉበት ልጃቸው እንደሆነ የሚረዳው ወጣት ከምንም በላይ እነሱን አስደስቶ የወላጅነት ምርቃታቸውን ማግኘት ይሻል። ከትምህርቱ መጠናቀቅ በኋላም በፈለገው ሙያ ተሰማርቶ የልቡን ፍላጎትና የልጅነት ህልሙን መፈጸም ይፈልጋል። ይህን ሲያስብም ፊቱ በፈገግታ ይበራል።
የልጅነት ጓደኞቹ ባገኙት ውጤት ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን እያሰበ ቅር ሲሰኝ ኖሯል። በወላጆቹ በጎነት የመማር ዕድሉን አግኝቶ ከመንገድ ያለመቅረቱ ደግሞ ያለመዘግየቱን አረጋግጦለታል። እናም ዘንድሮ እሱም እንደባልንጀሮቹ ወግ ደርሶት ከኮሌጁ ይመረቃል።
ደጀኔ ይህን ተስፋ እያሰበ ፊቱ በፈገግታ በራ። የትናንቱን መዘናጋት ረስቶም ነገን መልካም ለማድረግ በሃሳብ ተጓዘ። ከአሁን በኋላ በዕድሜና በጊዜ መቀለድ የለም። ከመማር በኋላ ስራ፣ ከስራ በኋላም የሚፈልገው ሁሉ ይሳካል። ድንገት የእጅ ስልኩን አንስቶ ቁጥሮቹን ነካካ። ከተደጋጋሚ ጥሪዎች በኋላ ሞባይሉ ‹‹ሀሎ!››… የሚል ጎርናና ድምጽ አሰማው።
ደጀኔ የቅርብ ጓደኛውን ምላሽ እንዳገኘ ምን እየሰራ እንደሆነ ጠየቀው። ከቤት መዋሉንና ፊልም አይቶ መጨረሱን ነገረው። ጥቂት ካወጉ በኋላ አሹ ስጋ ቤት አካባቢ እንዳለና እንደሚጠብቀው ነግሮት ራት ሊጋብዘው እንደሚፈልግ ፈቃዱን ጠየቀ። ባልንጀራው አላቅማማም። በተባለው ሰአት በቦታው እንደሚገኝ ነግሮት ስልኩን ዘጋው።
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም ማምሻ
የሰኔ ወር ተጋምሷል። ቅዝቃዜ እየጀመረ በመሆኑ አብዛኞቹ አለባበሳቸውን ቀይረዋል። ዕለቱን ዳምኖ የዋለው ሰማይ ማምሻውንም እንደከበደው ቀጥሏል። ደጀኔ ቤት በመዋሉ የውጭ ቅዝቃዜውን ለመላመድ እየሞከረ ነው። የቀጠረው ጓደኛው እስኪመጣ ከአንድ ሆቴል በራፍ አረፍ ብሎ ባሻገር ማንጋጠጡን ይዟል። ጥቂት ቆይቶ የቀጠረው ሰው ብቅ አለ። ሰላምታ ተለዋወጡና ተያይዘው ወደ ሆቴሉ ሳሎን አመሩ።
በደጀኔ ጋባዥነት የተጀመረው ራት እንደተጋመሰ በጨዋታ መሃል ያዘዙትን መጠጥ መጎንጨት ጀመሩ። ሰአቱ እየገፋ ምሽቱ ሲቃረብ ወደ ሆቴሉ አንዳንድ እንግዶች ብቅ ማለት ጀመሩ። አብዛኞቹ የሚጠጣ አዘው የሚዝናኑ ናቸው። በርከት ያሉትም ጠረጴዛ ከበው የጓደኝነት ጨዋታውን አድምቀዋል። ሌሎች ብቸኞች ደግሞ ከአንድ ጥግ መሽገው በያዙት መጠጥ እየቆዘሙ ነው።
በጊዜ የተጀመረው የደጀኔና የጓደኛው ቆይታ ጊዜውን ገፍቶ ምሽት ሶስት ሰአት ላይ ደርሷል። ሁለቱ ጓደኛሞች ማግስቱን ትምህርት ቤት እንደሚገቡ ያውቃሉ። ዕለቱን መዝናናት መፈለጋቸው ግን ሁሉን ያስረሳቸው ይመስላል። ከተቀዳው እየተጎነጩ ፣በጎደለው እየተኩ ጨዋታቸውን ቀጠሉ።
ሶስት ሰአት ከሰላሳ ሲሆን በእነሱ ዕድሜ ያሉና በርከት ያሉ ጓደኞች ግር ብለው ወደ ሆቴሉ ገቡ። ደጀኔና ባልንጀራው ወጣቶቹን እንዳዩ አርስ በርስ ተያዩ። ወደ ውስጥ ከገቡት መሀል ደጀኔ አንደኛውን ወጣት ቀድሞ ለይቶታል። ከዚህ በፊት በነበራቸው ግጭት ተጣልተው እስከመሰዳደብ ደርሰዋል።
ደጀኔ ጠበኛውን ወጣት እንዳየው አንድ ጉዳይ ትውስ አለው። ከግጭታቸው በኋላ ይህ ልጅ የጓደኞቹን ቡድን አደራጅቶ ሊደበድበው ሞክሯል። በወቅቱ ሙከራው ባይሳካም በየአጋጣሚው ባገኘው ቁጥር ሲዝትበትና ሲያስፈራራው ቆይቷል። ዛሬ ደግሞ እሱ ካለበት ተገኝቶ በርቀት እየገላመጠው ነው።
ደጀኔና ባልንጀራው የጠበኛውን ሁኔታ አስቀድመው ጠርጥረዋል። ምንአልባትም ጓደኞቹን ሰብስቦ የመጣው በስፍራው መኖራቸውን በማወቁና ጠብን ለመጫር በማሰቡ ሊሆን ይችላል። ሁለቱም ነገር ተነስቶ ችግር ከመምጣቱ በፊት ከሆቴሉ መውጣት እንዳለባቸው ተስማሙ። ይህን አስበው ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ግን ጠበኛው ወጣት ደጀኔ ፊት ለፊት ቀርቦ ትንኮሳ ጀመረው።
ደጀኔ የወጣቱ አመጣጥ ለነገር መሆኑን በማወቁ ቀረብ ብሎ ‹‹አትልከፈኝ›› ሲል አሳሰበው። ለጠቅ አድርጎም ነገር የሚፈልገው ከሆነ ሊያስቀይመው እንደሚችል አስጠነቀቀው። ወጣቱ የደጀኔን ንግግር ከንቀት ቆጥሮ ግንፍል ማለት ጀመረ። ከደጀኔ የሰማው ቃል አብሽቆትም ፊት ለፊቱ ተጋፈጠው። ግንባር ለግንባር መፋጠጣቸውን ያየው የደጀኔ ባልንጀራ ከመሀል ገብቶ ሊገላግል ሞከረ። የሁለቱም ሃይል በማየሉ ግልግሉ በእሱ አቅም ብቻ የሚፈታ አልሆነም። አሁንም ደጀኔ ቀድሞ የተናገረውን እየደጋገመ ‹‹አትልከፈኝ አስቀይምሃለሁ›› ማለቱን ቀጠለ። ወጣቱ መስማት አልፈለገም።
ደጀኔና ጓደኛው ቤት ቀይረው ለመዝናናት ወሰኑና ሂሳብ ከፍለው ወጡ። በስፍራው ደርሰው ጥቂት እንደቆዩ ግን ወጣቱ ከነጓደኞቹ ተከትሏቸው ከሆቴሉ መድረሱን አስተዋሉ። ሁለቱ ዳግም ሲተያዩ ለድብድብ ተጋበዙ። በዚህ መሃል የተከሰተው የወጣቱ ጓደኛ ከደጀኔ ጋር ተያያዘ። ደጀኔ እሱን በቴስታ ከመምታቱ ጠበኛው ወጣት የደጀኔን ሁለት እጆች የኋሊት ይዞ ሊያስመታው ሞከረ። ደጀኔ አልተሸነፈም።
ጠቡ ተጋግሎ መተናነቁ ሲያይል ጓደኞቹን ጨምሮ ሌሎች ገላጋዮች ከመሀል ገቡ። ለአፍታ ያህልም ሰላም የወረደ መስሎ ግርግሩ ተቀዛቀዘ። ጥቂት ቆይቶ ግን ጠበኛው ወጣት ከሆቴሉ ፈጥኖ ወደበር ወጣ። ደጅ ደርሶም አንድ ትልቅ ድንጋይ አነሳ። ወዲያውም ደጀኔ አልፎት እየሄደ መሆኑን አስተዋለ። ተከተለው። የያዘውን ትልቅ ድንጋይ አነጣጥሮም በጀርባው ላይ ጣለው።
ደጀኔ በላዩ የወረደበትን ትልቅ ድንጋይ ማምለጥ አልቻለም። እንደምንም ህመሙን ተቋቁሞ ትከሻው ላይ ነጥሮ የወደቀውን ድንጋይ ከመሬት አነሳ። ድንጋዩ ከእጁ እንደገባም አቅሙን አጠንክሮ ወደወጣቱ መልሶ ወረወረው። ትልቁ ድንጋይ ዒላማውን አልሳተም። በፍጥነት ከታሰበው ደርሶ ጠበኛውን ወጣት ከመሬት ዘርሮ ጣለው። ደጀኔ ወጣቱና ድንጋዩ እኩል መውደቃቸውን እንዳየ ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ሲል ተፈተለከ።
የተጎጂው ወጣት ጓደኞች ደጀኔን ለመያዝ ከኋላው ሮጡ። ዙሪያውን ከበውም እያዋከቡ ሊይዙት ሞከሩ። አልቻሉም። ደጀኔ በፍጥነት እየሮጠ አመለጣቸው። አባራሪዎቹ በጨለማው እያሳበረ በመንደሩ መሀል የገባውን ሯጭ ሊደርሱበት አልቻሉም።
የፖሊስ ምርመራ
በማግስቱ ፖሊስ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ስፍራ ደርሶ ጉዳዩን አጣራ። በዕለቱ በሁለቱ ወጣቶች መሀል በተፈጸመው አለመግባት የጠበኛው ወጣት ህይወት ማለፉን ሲያውቅም በስፍራው የነበሩትን ሁሉ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን አጣራ። ተጠርጣሪውን ለመያዝ ባደረገው ጥረት ካለበት አግኝቶ ለጥያቄ አቀረበው። ደጀኔ የፈጸመውን ድርጊት አልደበቀም። ሟች እሱን ወርውሮ በመታበት ድንጋይ መልሶ እንደመታውና በዚሁ ምክንያት ህይወቱ ማለፉን እንደተረዳ ተናገረ። ጉዳዩን በምርመራ የያዙት ዋና ሳጂን ምስጋናው ደረጀና ደጉ ዓለም አቦዬ የተጠርጣሪውን የዕምነት ክህደት ቃል በመዝገብ ቁጥር 586/ 10 ላይ አንድ በአንድ አሰፈሩ።
ውሳኔ
ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓም ለመጨረሻ ውሳኔ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርደቤት 20ኛው የወንጀል ችሎት በተከሳሽ ደጀኔ አበበ ላይ የቀረበውን የተራ ሰው መግደል የወንጀል ድርጊት በአግባቡ መርምሮ አጠናቋል። ፍርድ ቤቱ በፖሊስና በዓቃቤ ህግ የቀረቡለትን መረጃና ማስረጃዎች ከህጉ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔም ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሰምንት ዓመት ከስምንት ወራት አስራት ይቀጣ ሲል በይኗል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2012
መልካምስራ አፈወርቅ