አቶ በዛብህ ታምሩ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም “ፍረዱኝ” በሚል አምድ ሥር የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና አመራሮች ላይ ባነሱት ቅሬታ ዙሪያ የራሴ አስተያየትና መልስ ለመሰጠት ነው በሚል የኮሚሽኑ ሠራተኛና የማኔጅመንቱ አባል የሆኑት አቶ ሐረጎት አብረሃ የሚከተለውን በጽሁፍ አድርሰውናል።
በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም ግለሰብ የተሰማውን እና የሚያምነውን ሐሳብ በነፃናት ያለምንም ፍርሃት መግለፅ በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብኣዊ እና ዲሞክራሲያዊ ቃልኪዳኖች (Conventions) የተደነገገ እና አገራት ለሚያወጧቸው ሕጎች ተገቢውን ጥበቃ እና ድጋፍ የሚሰጠው መብት ነው። ሀገራችንም እነዚህን ቃልኪዳኖችና ሕጎች በተሟላ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግበራዊ አድርጋለች ባይባልም እንደ አንድ በዴሞክራሲ እያደገች እንዳለች አገር በተለይም ከለውጥ ወዲህ ምህዳሩን ለማስፋት በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች መሠረት ዜጎች የፈለጉትን የማሰብ፤ ያሰቡትን በፈለጉት መንገድ የመግለጽ መብት ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ።
ግለሰቡም እንደ ዜጋ ይህን መብት ተጠቅመው ስለ ኮሚሽኑ፣ ስለ አመራሩና ሠራተኞቹ በአጠቃላይ ስለ ፀረ ሙስና ትግሉ የሚመስላቸውን ሐሳብ ማንፀበራቃቸው በግሌ ተቃውሞ የለኝም።
እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ግን የምናነሳቸው ነፃ ሃሳቦች የሌሎችን መብት የማይጋፋ፤ ከጥላቻና ከግል ፍላጎት የፀዱ፤ ተቋማዊና የመንግሥት አሠራር የማያደፈርሱ፤ ሐሳብን በነፃነት ለመግለፅ የወጡ ሕጎችን ያከበረ መሆን ይገባዋል። ከጅምላ ፍረጃ ወጥቶ በማስረጃ መደገፍም አለበት። በተለይም ስለ አንድ ተቋም ወይም አመራር በሙስና መዘፈቅ ለመግለጽ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል፤ ይህ ካልሆነ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ነው።
አቶ በዛብህ ታምሩ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም በፍረዱኝ አምድ ያነሷቸው ጉዳዮችም ለረዥም ጊዜ በግል ሲያነሱዋቸው የቆዩ፤ በቡድን መሪ፣ በኮሚሽኑ የበላይ አመራር እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ በቂ መልስ ሲሳጣቸው የቆየ ቢሆንም ጉዳዩ ንቆ እንዳላየ ማለፍ ውድ አንባብያንና የኮሚሸኑ ሠራተኞች የሚያሳስት በመሆኑ ለተነሱት ጉዳዮች ኮሚሽኑ መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም በወጣው እትም አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል፤ ሆኖም አንባብያን ተጨማሪ መረጃ እንዲኖራቸው፤ ጎልተው መወጣት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲወጡ እንዲሁም እኔን ጨምሮ ጠቅላላ የኮሚሽኑ የማኔጀመንት አባላት በጅምላ መከሰሳችን ተገቢ ባለመሆኑ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ የራሴን አስተያየት ለመስጠት ፈልጌያለሁ።
በተቋሙ ውስጣዊና ውጫዊ ቅሬታ፣ ጥቆማ የሚቀርብበት የራሱ ሥርዓት ያለውና አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ነው። ለኮሚሸኑ የሚቀርቡ ቅሬታዎችና ጥቆማዎች ሦስት አይነት መፍቻ መንገዶች ያሉ ሲሆኑ፤ ከአገልገሎት አሰጣጥና ከሥነ ምግባር ጥሰት ጋር የተያያዘው በኮሚሽኑ ሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል፤ ከቅጥር፣ ዕድገት ወይም ዝውውር ጋር የሚነሱት ለቅሬታና አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ እንዲሁም የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን በነበረበት ጊዜ በምርመራና ዓቃቤ ሕግ በኩል ሲሆን ደግሞ ጉዳዩ ከሙያዊ ነፃነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በሙያው ልምድ ያላቸው ገለልተኛ የሆኑ መርማሪዎችና ዓቃብያነ ሕግ ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ቅሬታዎች ተጣርተው መፍትሔ የሚሰጥበት አሠራር እንዳለ ይታወቃል።
ሌላውን ትተን እንኳን ከ2004 እስከ 2008 ዓ.ም ከሥነ ምግባር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ 108 ጥቆማዎች ቀርበው፤ ተጣርተው መፍትሔ የተሰጠበት አግባብ እንዳለ ማንሳት ይቻላል፤ እኔም መረጃው አለኝ። ይህ የሚያሳየው ኮሚሽኑ ለሚቀርበው እያንዳንዱ ቅሬታና ጥቆማ መፍትሔ ለመስጠት ያለውን ቁጥጠኝነት ነው። ኮሚሽኑ መተቸት የነበረበት ይህንን ሳያደርግ ቢቀር ነው እንጂ የአቶ በዛብህ ፍላጎትና ቅሬታ እሳቸው በፈለጉት መንገድ ስላልተፈታ የኮሚሽኑን ስም ማጥፋት አያስፈልግም፤ ማንንስ ይጠቅማል? በዚህ መልኩ የግል ፍላጎትንስ ማሳካት ይቻላል ወይ ? ፍርዱን ለአንባብያን ሰጥቻለሁ።
ግለሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርቤ ኮሚሽኑ መፍትሔ አልሰጠኝም፤ ሠራተኞችን ለማድመጥ ፍቃደኛ አይደለም የሚል ሐሳብ አንስተዋል ። እንደ ምሳሌ ያነሱትም ኮሚሽኑ የሚከተለው የፀረ ሙስና ፖሊሲ እና ስትራተጂ ትክክል አይደለም፤ የሚዘጋጁ ሞጁሎች ችግር አላባቸው፤ ኮሚሸኑ ውስጥ ሙስና አለ፤ አመራሩ አልተለወጠም የሚሉና ሌሎቸም ናቸው ።
እውነት ነው ግለሰቡ እነዚህ ጉዳዮች በተደጋጋሚ በኮሚሽኑ ስብሰባዎች አንስተዋል። ሆኖም ግን መፍትሔ አላገኘሁም የሚለው ሐሳብ ውሸት ነው። ውሸት ሲደጋገም እውነት ሊመስል ይችላል እንደሚባለው ጉዳዩ በተደጋጋሚ እየተነሳ የኮሚሽኑ ስብሰባ እየረበሸ ስለሄደ፤ በቅርብ አለቆቻቸው እንዲሁም በኮሚሽኑ አመራር የተሰጣቸው ትክክለኛ መልስ ለመስማት ፍቃደኛ ባይሆኑም ኮሚሽኑ ሊከተለው ከሚገባ ራዕይ እና ስትራተጂ ጀምሮ ቅሬታዎች እስከሚፈቱበት ድረስ አሉ የሚሉዋቸውን ህፀፆች እና መፍትሔዎች በጥናት አስደገፈው እንዲያመጡ፤ በጥናቱ ላይ የማኔጅመንት አባላት እንዲወያዩበት እንደሚደረግ እንዲሁም አሳማኝ ሆኖ ከተገኘ የግለሰቡ ሐሳብ የኮሚሸኑ ማሻሻያ አካል ሆኖ የማይወስድበት አግባብ እንደሌለ በግልፅ መልስ ተሰቷቸዋል።
ከዚህ ውጭ ሠራተኛ በተሰበሰበ ቁጥር አጀንዳ ለማስቀየር የሚደረግ ጥረት ተገቢ ስላልሆነ ለመጨረሻ ጊዜ ጉዳዩ እንዲቋጭ አለኝ የሚሉት አመራጭ ሐሳብ ለማኔጅመንት እንዲያቀርቡ መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ፍሬንዲ ሺፕ ሆቴል በተደረገው የኮሚሸኑ የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀምና አጠቃላይ የሠራተኛ ግምገማ ላይ ግልፅ አቅጣጫና ምክር በኮሚሽኑ የበላይ አመራር ቢሰጣቸውም ለመተግበር ፍቃደኛ አልነበሩም፤ የጥናት ሰነድ ማቅረብም አልቻሉም።
ታዲያ አማራጭ ሐሳብ አለኝ ብሎ በየስብሰባው የሚያውክ ሰው ሃሳቡን እንዲያቀርብ ዕድል ሲሰጠው ለምን አያቀርብም? ይህንን ማድረግ ሳይቻልስ እንዴት ነው የኮሚሽኑ አመራርና ሠራተኞች ማሳመን የሚቻለው? ግለሰቡ እንደማንኛውም ተገልጋይ ቅሬታቸውን ውስጣዊ አሠራርን ተከትለው ተቋሙን ሊያንፅ፣ ሊያሻሽል በሚችል መልኩ ከግል ፍላጎትና ጥላቻ ተላቅቀው ሐሳባቸው በጥናት አስግደፈው ማቅረብ እንዲችሉ ዕድል ተሰቷቸው ነበር። ይሄን ዕድል መጠቀም ሲገባቸው ከ10 ዓመታት በላይ የሠሩበትን ተቋምና የሥራ ባልደረቦቻቸውን ከምንም ተነስተው ማብጠልጠል ለምን አስፈለገ? ፍርዱ ለአንባብያን እና ለኮሚሽኑ ሠራተኞች ትዝብት ትቸዋለሁኝ።
ሌላ ግለሰቡ ያነሱት ጉዳይ የኮሚሽኑ አመራሮች ሙሰኞችና ለለውጥ ዝግጁ ያልሆኑ፤ ብቃት የሌላቸው ናቸው ብለዋል፣ ይህ ፍፁም ነጭ ውሸት፤ በተለይም ሙሰኛ ናቸው ማለታቸው በቀላሉ የሚታይ ስላልሆነ በማስረጃ አስደግፈው ማቅረብ ካልቻሉ በሐግ የሚያስጠይቃቸው ጉዳይ ነው ።
ተቋሙ ከለውጥ ጋር የሚሄድ አመራር የለውም የሚለው ሐሳብ ስህተት መሆኑን በተወሰነ መልኩ ማስገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው ኮሚሸኑን የሚመሩት አንድ ኮሚሽነርና ሁለት ምክትል ኮሚሽነሮች ናቸው። ከአንድ ምክትል ኮሚሽነር ውጭ የተቀሩት ከለውጥ በኋላ የተሾሙ ናቸው። አንድ ምክትል ኮሚሽነር ግን ቀደም ብለው የተሾሙና የመጀመሪያ ስድስት ዓመት የሥልጣን ጊዜያቸውን ባለፈው ዓመት ያጠናቀቁ በመሆኑ ካላቸው እውቀት፤ ብቃትና ሥነ ምግባር አንፃር ለተጨማሪ ስድስት ዓመት እንዲመሩ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርጠው የተሾሙ ናቸው። ታዲያ በብቃታቸው፤ በሥነ ምግባራቸው ለውጡን ይመራሉ ተብለው በከፍተኛ የሀገሪቱ መሪ ታምኖባቸው የተሾሙትን አመራሮች ሙሰኛ ናቸው፤ ለውጥ አይቀበሉም፤ የባለፈው ሥርዓት ተከታይ ናቸው ብሎ መፈረጅ ከየት የመጣ ድፍረት ነው ?
እውን አቶ በዛብህ በጠቅላይ ሚኒስትር ለሚሾም ሰው ብቃት አለው የለውም፤ ተለውጧል አልተለወጠም፤ ለአመራር ይመጥናል አይመጥንም ብለው የመፈረጅ ሃላፊነት ማን ሰጣቸው? ይሄን ለማለት የሚያስችል የተሟላ መረጃ አላቸው? ይሄ ጉዳይ ተራ ክርክር ቢሆንም ግለሰቡ ካላቸው የጥላቻ መንፈስ የተነሳ መሆኑን አንባብያን ሊረዱት ይገባል ።
ታዲያ ግለሰቡ በማስረጃ ያልተደገፈ፤ በተደጋጋሚ በተቋም ደረጃ መልስ የተሰጠው ጉዳይ በሚዲያ ወጥቶ ኮሚሽኑና የኮሚሽኑ አመራር እንዲሁም የማኔጅመንቱን ወደ ማብጠልጠል ወይም ማጠልሸት የገቡበት ምክንያት ምንድን ነው ? በዚህ ጉዳይ በሚዲያ መነታረክ ለህዝብ ይመጥናል ብየ ባላስብም ግለሰቡ የሄዱበት ርቀት የተቋሙን ገፅታ የሚያበላሽ አደገኛ ተግባር ነው። በመሆኑም ለግለሰቡ የተሰጠውን ሐሳብ የመግለፅ ዕድል ለእኔም የሚገባ በመሆኑ የጉዳዩ ፍሬ ነገር በቅጡ ለመረዳትና ከተራ ውንጃላ በስተጀርባ ያለውን ጉዳይ ማንሳት የግድ ይላል።
ግለሰቡ ኮሚሽኑን በሀሰት ለማጠልሸት መነሻ ያደረጉት ጉዳይ አንድ የሥራ ክፍል ለመምራት አቅም ይኑራቸው እና አይኑራቸው ሌላ ጉዳይ ሆኖ ዳይሬክተር ለመሆን ከፍተኛ የሆነ የሥልጣን ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው። ግለሰቡ ምን ያህል የሥልጣን ጥማት እንዳላቸው ያሳያሉ ያልኩዋቸውን መነሻ ምክንያት ላንሳ። የዳይሬክተር ቦታ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለማግኘት ካላቸው ፍላጎት በመነጨ ዳይሬክተር ሆነው እየሠሩ ያሉ አመራርን ብሔራቸውን መነሻ በማድረግ፤ ከአሁን በፊት እርስ በእርስ በፈጠሩት ፀብ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች ከተቀበሉት ተገቢ ያልሆነ 17 ሺህ ብር አበል ጋር በተያያዘ በተጣራው ጉዳይ ለምን አጣሩብኝ፤ አጋለጡኝ የሚል ቂም በመያዛቸው ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁን በዳይሬክተርነት ያሉ ባለሙያ ከምርመራ እና ዓቃቤ ሕግ ጋር በተያያዘ ከላይ በተገለፀው መሠረት ተጣርቶ የማያስጠይቅ እና በምስክሮች ያልተደገፈ መሆኑን ግልፅ ሆኖ እያለ ለእሳቸው ጥቅም ሲባል ለምን አሁን ካሉበት ሃላፊነት ተነስተው አልተጠየቁም፤ ለምንስ እስከ አሁን በሃላፊነታቸው ቀጠሉ ብለው ቅሬታ ማንሳታቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው የሚፈልጉትን የዳይሬክተርነት ደረጃ ለማግኘት የወሰዱት እሳቤ ነው።
አሁን በመደቡ ላይ ያሉት አመራር የዳይሬክተርነቱን ቦታ እንዴት እንዳገኙትና ግለሰቡ በምን መልኩ ከቦታው እንደተነሱ ኮሚሽኑ በስፋት መልስ የሰጠበት ስለሆነ ማንሳት አልፈልግም። እንዲያውም በአንድ ወቅት በህጋዊ መንገድ ጠይቀው አይገባህም የሚል መልስ ሲሰጣቸው ያጡትን ሥልጣን በድርጅት አባልነት ይገኝ ይሆናል በማለት ለአንድ ዓመት የድርጅት አባል ከሆኑና ብዙ ጥረት ካደረጉ በኋላ በዚህ መልኩም ሳይሳካ ሲቀር ራሳቸውን ከአባልነት ያገለሉ ባለሙያ ናቸው።
በሦስተኛ ደረጃ በሥነ ምግባር ትምህርትና ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች የስልጠና ቡድን አባል ሆነው በሠሩበት ወቅት ከቡዱን መሪና ከሁሉም አባላት ጋር የከረረ ፀብ ገብተው በማኔጅመንት አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ አንዱ ችግር ፈጣሪ ግለሰቡ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ምክንያቱም ደግሞ የሥልጣንና የጥቅም ፍለጋ መሆኑን አሁን በሥራ ላይ ያሉና የለቀቁ የቡድኑ አባላት የሚያውቁት ሀቅ ነው።
በአራተኛ ደረጃ ግለሰቡ በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም አዲስ ኮሚሽነር መሾማቸውን ስላወቁ ይሄን አስታከው የሚፈልጉትን የዳይሬክተርነት ሥልጣን ማግኛ የተሳሳተ ስሌት ወሰደው ሊሆን ይችላል ብዬም እገምታለሁ።
በተጨማሪ ግለሰቡ ኮሚሸኑ የሰጣቸው ሃላፊነትና ተግባር በአግባቡ የመወጣት ችግር ያለባቸው ባለሙያ ናቸው ። በዚህ ጉዳይ ላይ ማንኛውም የኮሚሽኑ አመራር እና ሠራተኛ ቢጠየቅ የሚያረጋግጠው ሀቅ ነው። ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው አዳዲስ አሠራሮች በቅንነት ተቀብለው ከመተግበር ይልቅ መጨቃ ጨቅ የሚያበዙ፤ የቅርብ አለቃ ትእዛዝ የማይቀበሉ፤ ከቡድን አባላት ጋር የማይግባቡ፤ ግለሰብና ቡድን መለየት አቅቷቸው በጅምላ የሚፈረጁ ናቸው። ከብዙ በጥቂቱ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ሁለት ምሳሌዎች ማንሳት አንባብያን ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያገዛል።
ኮሚሽኑ በተለያየ ጊዜ ወቅታዊ የማስተማሪያ ሞጁሎችን በጥራት ያዘጋጃል በማሰልጠኛ ማኑዋል መሰረትም ለሁሉም ባለሙያዎች አቅጣጫ በመስጠት እንዲያሰለጥኑ ያደርጋል ግለሰቡ ግን ከሌሎች ባለሙያዎች በተለየ መልኩ ለማስተማሪያ የሚጠቀሙት ፓወር ፓይንት የቆየ፤ በማኑዋሉ መሰረት ያልተዘጋጀ፤ አዳዲስና ወቅታዊ መረጃ የማያካትት መሆኑን ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከሰልጣኞች ተደጋጋሚ ቅሬታ ስለቀረበባቸው ጉዳዩ በማኔጅመንት ታይቶ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተጣርቶ እንዲቀርብ በተወሰነው መሰረት ትክክል መሆኑን በመረጋገጡ አሰለጣጠናቸውን እንዲያሻሽሉ ሂስ ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም ለመማር ዝግጁነት የሌላቸው በመሆኑ እስከ አሁን ለመለወጥ አልደፈሩም።
እንዲያውም በዚህ ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋማት ጋር ሄደው የፊት ለፊት ትምህርት እንዳይሰጡ በቢሮ ሆነው ድጋፍ እንዲያደርጉ የተደረገበት አግባብ እንዳለም አንባብያን ሊያውቁት ይገባል፣ ይህ በኮሚሽኑ ማኔጅመንትና ሠራተኞች በግልፅ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። የፈለገ ሰውም በወቅቱ በኮሚቴ የተጣራውን ሪፖርት በአካል መጥቶ ማየት ይቻላል። ታዲያ ፓወር ፖይንትን ለማሻሻል አቅም ያጠረው ግለሰብ እንዴት ሰፊ ማንበብ፤ ጥናትና ምርምር የሚጠይቀውን የአንድ ተቋም ፖሊስና ስትራተጂ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ ይችላል? ተቀባይነት አጣሁ ያሉት ከእውነት የመነጨ ሳይሆን የተለመደው ተራ ቅጥፈት ነው።
ሌላው ማሳያ አድርጌ የማነሳው ጉዳይ ኮሚሽኑ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የፀረ ሙስና ሰርቬይ በሚያስጠናበት ጊዜ ኮሚሽኑን ወክለው የቴክኒካል ኮሚቴ አባል ሆነው እንዲሠሩ የተመደቡ ቢሆንም ሥራው ከባድ በመሆኑ በወቅቱ የነበራቸው አስተዋጽኦ ሲታይም አነስተኛ በመሆኑ በሌላ ባለሙያ እንዲተኩ ተደርጓል። አቶ በዛብህ በውስጣቸው ቢደብቁትም ወደ ተራ ዘለፋና ስድብ ያስገባቸው ወደ ተቋማት ሄደው እንዳያስተምሩ መደረጋቸው የፈጠረባቸው ፀፀት እና ቁጭት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም። ታዲያ አቶ በዛብህ የራሳቸው አቅም ውስንነት አይተው አቅማቸውን ለማሻሻል ሌት ተቀን ከመጣር ይልቅ ሌላ ሰው አቅም የለውም ብለው ለመተቸት መሞከር ከሞራላቸው እና ከህሊናቸው ጋር እንደሚያጋጫቸው ምንም ጥርጥር የለኝም።
በመሆኑም አንባብያን ሊረዱት የሚገባው ጉዳይ አቶ በዛብህ ያነሷቸው ቅሬታዎች፣ ውንጀላዎች ከግል ፍላጎት፤ ቂምና ጥላቻ ተነስተው እንጂ፤ አሳማኝ የሆነ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድ ተቋሙ የሚገነባ ሐሳብ አይደለም። ይህንን ጉዳይ ሳነሳ ግን እንደማንኛውም ተቋም ኮሚሽኑም ከሥነ ምግባርና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ሙሉ በሙሉ የፀዳ ነው ለማለት ፈልጌ ሳይሆን ተቋሙ አለኝ የሚላቸው ድክመቶች እና ችግሮች ሲኖሩ የአቶ በዛብህ አቤቱታ ሳይጠበቅ በየጊዜው ሲፈታቸው የነበረ ይህንን ለማድረግም ሥርዓት ያበጀና ቁርጠኝነት ያለው በመሆኑ ነው። አሁንም ይሁን ወደፊት በማስረጃ የተደገፉ ቅሬታዎች፣ አቤቱታዎች ከቀረቡ ተቋሙ የማይፈታበት አግባብ አይኖርም ።
ከዚህ ውጭ ‹‹ውሃ ደጋግመው ቢወቅጡት ያው እምቦጭ›› እንደተባለው በሀገርና በተቋም ደረጃ ስንት ሪፎርም እና ለውጥ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ከዛሬ አራት እና አምስት ዓመት በፊት የተነሱትንና እልባት የተሰጣቸው ጉዳዮች እንደ አዲስ ትልቅ አጀንዳ አድርጎ ለማንሳት መሞከር ህብረተሰብን ለማሳሳት ካልሆነ በስተቀር አንዳችም ፋይዳ የለውም። ምናልባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ የኮሚሽኑ አመራሮች ሙስና ላይ ተዘፍቀዋል ብለው በድፍረት ያነሱት ጉዳይ በቀላሉ መታየት ስለሌለበት በማስረጃ ተደግፎ ካልቀረበ የስም ማጥፋት ወንጀል ስለሆነ የኮሚሽኑ የሕግ አገልግሎት አግባብ ባለው አካሄድ ይጠይቃቸዋል ብዬ አስባለሁ።
በመጨረሻም አቶ በዛብህ የፈፀሙት ተራ ውንጀላና ዘለፋ በመልከም ሥነ ምግባር ህዝቤንና አገሬን አገለግላለሁ፤ መንግሥት የሰጠኝን ሃላፊነት በአግባቡ እወጣለሁ ብሎ ቃለ መሃላ ከፈፀመ አንድ ሥነ ምግባር አለኝ ብሎ ከሚያስብ የኮሚሽኑ ሠራተኛ የሚጠበቅ አይደለም። ስለሆነም ስህተታቸውን አምነው፤ ተቋሙን ይቅርታ ጠይቀው በሂደት እንዲማሩበት፤ ከተቸከሉበት የተሳሳተ የድሮ አስተሳሰብ፤ ከዘረኝነት አውድ እንዲሁም ተራ የስም ማጥፋት ወጥተው ጡረታ ለመውጣት በቀሯቸው አጭር ጊዜያት ተቋሙ የጀመራቸውን የለውጥና የሪፎርም ሥራዎች በማስቀጠል ኮሚሽኑንና ህዝባቸውን ቢክሱ መልካም ነው የሚል ሀሳቤን ማቅረብ እወዳለሁ።
ቸር ወሬ ያሰማን !
የኮሚሽኑ የማነጅመንት አባል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012