በአገራችን አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድመና ድህረ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ በፍትሐዊነት እንደማያገለግልና ከአሿሿም ጋር ተያይዞም ወቀሳና ቅሬታ ሲቀርብበት ከርሟል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሆነው ተሹመዋል። ከእሳቸው ሹመት ጋር ተያይዞ አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን አነጋግረናል፡፡
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አዲስ የተሸሙት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን በ1997ዓ.ም ከተካሄደው ምርጫ ጀምሮ እንደሚያውቋቸው በማስታወስ፣ተመራጭ ባይሆኑም በፖለቲካው ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ በምርጫ ሂደት የነበሩትን ክፍተቶች ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የህግ እውቀት ያላቸው በመሆናቸው ለተሰጣቸው የኃላፊነት ቦታ እንደሚመጥኑ ይገልጻሉ፡፡
ከእስር ዘመናቸው ጀምሮ በፖለቲካው ውስጥ አለመሆናቸውን እንደሚያውቁ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በመሆኑም ወይዘሪት ብርቱካን አድሎ ያደርጋሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ እርሳቸውም ለህግ የበላይነት ከፍተኛ ስሜት እንዳላቸው ያውቋቸዋል፡፡ በመሆኑም የህግ እውቀታቸውን ተጠቅመውና በምርጫ ቦርዱ ላይ ይስተዋል የነበረውንም ክፍተት በማገናዘብ ሁሉንም አቻችለው መጪው ምርጫ ፍጹም ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ቀናና የህዝብ መገለጫ እንዲሆን እንደሚሰሩ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡
ወይዘሪት ብርቱካን ለቦታው የሚመጥኑ ቢሆኑም የምርጫ ስራን ማስፈጸም ቀላል ባለመሆኑ በሀገሪቷ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ዴሞክራሲ የሰፈነበት ምርጫ እንዲካሄድ የሚፈልግ አካል ከጎናቸው ሊሆኑ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ የቦርድ አባላት አመላመል ላይም በተመሳሳይ ጥንቃቄ ባለው መልኩ ከተከናወነ፣ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞችም ባለሙያዎችና ጠንካሮች ከሆኑና በገለልተኛ የፍትህ ሥርዓት ከተደገፈ ተቋሙ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ይገልፃሉ፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ‹‹ሊኖሩ ከሚችሉ ሰዎች አንዷ ናት፡፡ እንደግለሰብም በምርጫው ላይ ችግር የለብኝም፡፡ ጥሩ አሸጋጋሪ ልትሆን ትችላለች፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከማይታመኑ ተቋማት አንዱና ከላይ እስከታች ችግር ያለበት በመሆኑ ከዜሮ ጀምሮ ማዋቀር ስለሚያስፈልግ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፈተና ማለፍ ይጠበቅባታል›› በማለት የሚታመን ተቋም ለማድረግና እስከ ቀበሌ የሚዘልቅ አሰራር ለመዘርጋት ከባድ ስራ እንደሚጠብቃቸው ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ግን መንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ያላደረጉበት ሹመት ትክክል ነው ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል፡፡
ለለውጡ የመንግስት ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር መረራ፣ የግለሰቧ ችሎታና ፍላጎት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ኃላፊነቱ የወይዘሪት ብርቱካን ብቻ ሳይሆን «የኔ ነው» የሚል አካል መኖር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ የኔነት ስሜት እስኪፈጠር ስራው ሊያደክማቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኳሱ ያለው በገዥው ፓርቲ ሜዳ ላይ ነው›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የለውጥ እንቅስቃሴው ተጀመረ እንጂ ገና ነው›› የሚሉት ዶክተር መረራ ጉዳዩ የመቶ ሚሊዮን ህዝብ እንደሆነና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን እንደገና የማዋቀሩ ስራ በጋራ መከናወን እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ‹‹ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርጦ በፓርላማ ያፀድቃል የሚል በህገመንግስቱ ላይ ተቀምጧል፡፡ የወይዘሪት ብርቱካንም ሹመት ከዚህ የተለየ አይደለም›› ይላሉ፡፡ በወይዘሪት ብርቱካን የህግ አዋቂነትና የተሰጣቸው ኃላፊነት አይወጡም ብለው ግን አያምኑም፡፡ ነገር ግን ወይዘሪት ብርቱካን ብዙ ጥያቄ የማያስነሳ ስራ መስራታቸው የሚረጋገጠው በስራ ከታዩ በኋላ እንደሆነና በሂደት የሚታይ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ ለስራቸው መሳካት የፖሊሲ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደጎን የተወ የአንድ ፓርቲ ውሳኔ ብቻ ነው የሚያንፀባርቀው፣ የሚጠበቅበትን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አልተወጣም፡፡ በሚል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመቃወም መሻሻል እንዳለበት በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ስናቀርብ የነበረ በመሆኑ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የትግላችን ውጤት ነው›› ያሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በወይዘሪት ብርቱካን ሹመት ፓርቲያቸው ደስተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ጫኔ ማብራሪ የወይዘሪት ብርቱካን ሹመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የገቡት ቃል አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ወይዘሪት ብርቱካን ህዝባዊ ተቋም እንዲሆን የማስቻል አቅም አላት የሚል እምነት አላቸው፡፡
ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የስራ ውጤት ወደፊት የሚታይ ቢሆንም በሹመታቸው ላይ ተመሳሳይ የድጋፍ አቋም አላቸው፡፡ ጠንካራ አቅምና ለስራውም ቅርበት ያላቸው መሆናቸውንም መስክረውላቸዋል፡፡
ለምለም ምንግሥቱ