ወጣት ነው፤ ሊያውም በሀያዎቹ ዕድሜ ክልል መጨረሻ ላይ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ነው። አንዳንዶች በዚህ የወጣትነት እድሜያቸው በስንፍና ተይዘው እና ለቤተሰሰብ ሸክም ሆነው መላው ጠፍቷቸው ሲንቀሳቀሱ ቢታይም እርሱ ግን ቤተሰብ ከመምራት ባለፈ በጥረቱ ባገኘው ገንዘብ ደግሞ ንግዱን እየከወነ ይገኛል።
አቶ ዳንኤል ፈየራ ይባላል ባለታሪኩ። በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ አመያ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው አጆበሃ አካባቢ በ1983 ዓ.ም የተወለደው። ለእናትና አባቱ የመጀመሪያ ልጅ ቢሆንም ያደገው አስር ልጆች ባሉበት ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ቤተሰቡ በእርሻ ስራ የሚተዳደር በመሆኑ አቶ ዳንኤልም ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የግብርና ስራ ላይ በመሰማራት ወላጆቹን ያግዝ እንደነበር ያስታውሳል። በእረኝነቱም ቢሆን ከብቶችን በማገድ እና በመላላክ ጭምር ወላጆቹን ይረዳ ነበር።
ከስራው በተጨማሪ ደግሞ ለትምህርቱም ጽኑ ፍላጎት ነበረው። እናም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ዳሊዳክ የተሰኘው ትምህርት ቤት ጀመረ። ይሁንና ከቤቱ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የሶስት ሰዓት የእግር ጉዞ ማድረግ ነበረበት። ጉዞው ግን አድካሚ ስለነበር እና አሰልቺም ስለሆነበት ከወላጆቹ ተለይቶ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ወደሚኖሩት የአጎቱ ቤት ሆኖ አስኳላውን መከታተል ቀጠለ።
በትምህርቱ ደግሞ ጎበዝ ነበረና ጥሩ ውጤት እያመጣ ከክፍል ክፍል መሸጋገሩን ተያያዘው። የአጎቱ ሁለት ሴት ልጆችም ታዲያ አብረውት አንድ ክፍል ይማሩ ነበር። ወደስድስተኛ ክፍል ሲዘዋወሩ ግን አንድ ቀን አጎታቸው ሁለቱን ሴት ልጆቻቸውን እና አቶ ዳንኤልን አስቀምጠው ትምህርታዊ ጥያቄ አነሱላቸው። በወቅቱ መልሱን የሚመልሱት ግን ሴት ልጆቻቸው ሳይሆኑ አቶ ዳንኤል ብቻ በመሆኑ አጎታቸው በእጅጉ ተበሳጭተው ልጆቻቸውን መቆጣት ጀመሩ።
ይህ ሁኔታ ግን ቤተሰቡ ውስጥ ስሜታዊነት በመፍጠሩ አቶ ዳንኤል ወደሌላ ዘመድ ቤት ሄዶ መማር እንዳለለበት በልጅነት አዕምሮው ተሰማው። እናም ለትምህርት ሲል አሁንም ሌላኛው አጎቱ ቤት በመዘዋወር አጆ ጊዶ የተባለ አካባቢ መማሩን ቀጠለ። ከስድስተኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል በአጆ ጊዶ ሆኖ ተከታተለ።
ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲሸጋገር ግን በአቅራቢያው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወደ አመያ ከተማ ተጉዞ መማር ግድ ሆነበት። አመያ ከተማ ላይም ከጓደኞቹ ጋር አነስተኛ ቤት ተከራይተው መማር ጀመሩ። በወቅቱ ለምግብ እና ለተለያዩ ወጪዎች የሚሆን በቂ ገንዘብ ባይኖረውም በሳምንት አንድ ጊዜ ከቤተሰብ በሚላክለት ስንቅ አማካኝነት ምግቡን ያገኝ እንደነበር ያስታውሳል።
ከአመያ ከተማ አንስቶ እስከ ወላጆቹ ቤት ድረስ የሶስት ሰዓት የእግር መንገድ የሚያስኬድ በመሆኑ በሳምንት አንድ ቀን ዳቦ እና ቆጮ እንዲሁም የተለያዩ ቶሎ የማይበላሹ ምግቦች በመንገደኛ አማካኝነት ይላክለታል። እንዲህ እንዲህ እያለ በወቅቱ የመሰናዶ ትምህርት መግቢያ የሆነውን ውጤት 10ኛ ክፍል ላይ በማምጣቱ ወደ 11ኛ ክፍል ተሸጋገረ። በጊዜው ምቹ ሁኔታ ተሟልቶላቸው 10ኛ ክፍልን ያላለፉ ተማሪዎች ወደተለያየ የስራ መስክ መሰማራታቸውን ቢያውቅም እርሱ ግን ከኑሮ ውጣ ውረድ ጋር እየታገለ መማሩን አላስተጓጎለም።
አመያ ከተማ ላይ 11ኛ ክፍልን እየተማረ ሳለ ግን በከተማዋ የፌዴራል ፖሊስ አዲስ የምልመላ ቅጥር እያከናወነ መሆኑን ይሰማል። እናም በአጠቃላይ የኑሮ ጫናው መክበድ እና ከቤተሰብ ቀለብ እያስላከ መማሩ ስላሳሰበው የፌዴራል ፖሊስ የመሆን እድሉን ተጠቅሞ ስራ መያዝ እንዳለበት በአጋጣሚ ውሳኔ ላይ ደረሰ።
የፌዴራል ፖሊስነት ምዝገባውን አከናውኖ መስፈርቱን በማሟላቱም በ2001 ዓ.ም ውርሶ ወደሚገኘው የፖሊስ ማሰልጠኛ ተላከ። አድካሚውን እና እልህ አስጨራሹን የ11 ወራት ስልጠና በብቃት ማጠናቀቅ በመቻሉ ለስራ ዝግጅት እንዲያደርግ ተነገረው። በመቀጠልም አዲስ አበባ ተመድቦ እንደሚሰራ ስለተነገረው ወደመዲናዋ መዳረሻውን አደረገ። በወቅቱ የመጀመሪያ ደመወዙ 658 ብር ሲሆን ግብር እና የምግብ ሲቆራረጥ እጁ ላይ የሚደረሰው ገንዘብ 270 ብር ብቻ እንደነበር አይዘነጋውም።
አዳሩ የፖሊስ ካምፕ ውስጥ በመሆኑ ለመኝታ እና ለምግብ ተጨማሪ ወጪ እንደማያወጣ በማሰብ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር በወር የሁለት መቶ ብር እቁብ ገባ። ከወጪ ቀሪ የምትተርፈውን 70 ብርም ለዩኒፎርም ማጠቢያ ሳሙና መግዣ እና ለተለያዩ ጥቃቅን ወጪዎች በማዋል አብቃቅቶ መኖሩንም ችሎበት እንደነበር አይዘነጋውም። ወዲያውም በዕቁብ ብሩ አማካኝነት ለትምህርት የሚከፍለው ገንዘብ በማግኘቱ ከአንድ የግል ኮሌጅ የአካውንቲንግ የርቀት ትምህርቱን ጀመረ።
ቀን ላይ ስራውን በሚገባ አከናውኖ ምሽት ላይ ወደ ማረፊያው ሲያቀና የአካውንቲንግ ትምህርቱን ጥናት በማከናወን አንድ አመታትን አሳለፈ። ከአመት በኋላ ግን መኝታው ስር የደበቀው መጽሃፎቹ በመገኘታቸው ትምህርት መጀመሩ ታወቀ። በወቅቱ የቅርብ አለቃቸው ደግሞ ለፌዴራል ፖሊስ ትምህርት አያስፈልግም ብለው የሚያስቡ በመሆናቸው አቶ ዳንኤል ላይ በግምገማ ሰበብ ውርጅብኝ አዘነቡበት።
ከስራው ይልቅ የግል ፍላጎቱን ያስቀድማል በሚል ትምህርት መማሩን እንደጥፋት ቆጥረው የቅርብ አለቆች ለበላዮቻቸው ተናገሩ። አቶ ዳንኤል ግን በጉዳዩ ተስፋ ቆርጦ ዝም አላለም። ይልቁንም የበላይ አለቆቹ ፊት ትምህርት መማሩ ጥቅሙ ለእራሱ ብቻ ሳይሆን ስራውንም ለማሻሻል የሚበጅ መሆኑን በመንገር በነፃነት የኮሌጅ ትምህርቱ እንዲፈቀድለት ታገለ። ጥረቱ በመሳካቱ ትምህርቱን በነጻነት ተከታትሎ ከአራት ዓመታት በኋላ በዲፕሎማ ተመረቀ።
የፖሊስነት ደመወዙም 1 ሺህ 163 ብር ደረሰ። ይሁንና የተሻለ ስራ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ስር በማግኘቱ ከፌዴራል ፖሊስ መልቀቂያ አስገባ። በወቅቱ የሰባት ዓመት የአገልግሎት ጊዜያውን ሳይጨርስ መልቀቅ በመፈለጉ የሚጠበቅበትን የገንዘብ ክፍያ አከናውኖ በኦሮሚያ ባንክ በጥበቃ ስራ ተቀጠረ። በባንኩ ጥበቃ እየሰራ በትርፍ ጊዜው ደግሞ የማታ የአካውንቲንግ የዲግሪ ትምህርቱን መከታተሉን ቀጠለ። በጎንም የመንጃ ፈቃድ አውጥቶ የተሻለ ህይወት ለመኖር የሚያደርገውን ጥረት ከፍ አደረገ። በትንሹ የጀመራትን ቁጠባም አጠናክሮ ቀጥሏል።
በእረፍት ጊዜው ግን አብነት አካባቢ የሚገኝ የአጎቱ የመለዋወጫ ሱቅ ዘንድ ማዘውተር መጀመሩን ያስታውሳል። ወደሱቁ እየሄደ ስራውን መመልከት እና አጎቱን መርዳት ልምዱ አደረገ። በሱቁ ስላለው የገበያው ሁኔታ፣ ስለእቃዎቹ ምንነት እና ዋጋ ማጥናቱንም ተያያዘው። በዚህ ወቅት ግን ወደወላጆቹ መንደር ድረስ በማቅናት የአባቱን መሬት ማሳረስ እና ስለከብት እርባታ ሁኔታው ቁጥጥር ማድረጉን አላስተጓጎለም ነበር።
በመሃል ግን ለአራት ዓመታት የተከታተለው ትምህርቱን በ2010 ዓ.ም ላይ በዲግሪ አጠናቆ ተመረቀ። ትዳርም መጣና ወደሁለት ጉልቻ ተሸጋግሮ ኑሮውን በአዲስ አበባ ስር አደረገ። ከትዳር በኋላ መመካከሩም ሲመጣ ደግሞ ከባለቤቱ ጋር የግል ስራ እየሰሩ ኑሯቸውን ማደራጀት እንዳለባቸው ሃሳብ መለዋወጥ ጀመሩ።
ትዳር ከያዙ ከሶስት ወራት በኋላ ግን የግል ስራ ለመስራት ሲወስኑ በጥቂቱም ቢሆን የለመደው የተሸከርካሪዎች መለዋወጫ ንግድን ምርጫው መሆን እንዳለበት ወሰነ። እናም ወደገጠር በመሄድ አንዳንድ ከብቶችን በመሸጥ እና ለረጅም ዓመታት ከቆጠባት ገንዘብ ላይ በመጨመር 60 ሺህ ብር አካባቢ አገኘ።
ከባለቤቱም ዘንድ የነበረ ተጨማሪ ገንዘብ በማግኘቱ የንግድ ሱቅ ለመጀመር ተነሳ። የጥበቃ ስራውን ሳይለቅም አማኑኤል አካባቢ የሚገኝ አነስተኛ ሱቅ በአራት ሺህ ብር ተከራይቶ የተለያዩ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን መነገዱን በ2011 ዓ.ም <<ሀ>> ብሎ ጀመረ። አንድ ሰራተኛ ቀጥሮም ከባለቤቱ ጋር ሱቁን እየተቆጣጠሩ መነገዱን ተያያዙትት። ይሁንና ለስድስት ወራት ያክል ቢነግድም ገበያ በመጥፋቱ ኪሳራ መምጣቱ አልቀረም። በዚህ ወቅት ታዲያ የተሻለ ገበያ እንዲገኝ ሱቁን በርካታ ጋራዥ ወደሚገኝበት የአማኑኤል አካባቢ አዘዋውረው። በተጨማሪም የጥበቃ ስራውን ትቶ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ወደመለዋወጫ መሸጫ ንግዱ አተኮረ።
የሱቁን አድራሻ ወደ መካኒኮቹ የስራ ቦታ ካስጠጋ በኋላ ግን ጥሩ ገበያም ማግኘት ቻለ። አቶ ዳንኤልም በየእለቱ ከደንበኞች የሚጠየቁ አዳዲስ እቃዎችን በማስገባት ንግዱን አጠናከረ። ከሱቁ ገቢም ለትዳሩ እና ለኑሮው የሚሆን የተሻለ ገቢ ከማግኘቱም ባለፈ መጠነኛ ጥሪትም መቋጠር ጀምሯል። መለዋወጫ ሱቋንም ለማስፋፋት በሚል 800ሺህ ብር ከአነስተኛ እና ጥቃቅን ቢሮ ጠይቆም እስኪሰጠው ድረስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
መንግስት ለወጣቱ ብሎ የሚመድበው ገንዘብ በትክክለኛው መንገድ መስጠት ከተቻለ ሀገር የማትለወጥበት ምክንያት እንደሌለ የሚናገረው ዳንኤል እርሱ የጠየቀው ብድር በመጓተቱ ግን ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የሚችልበት ስራ መዘግየቱን ይናገራል። ይሁንና ስራውን ሳያቋርጥ በየጊዜው አቤቱታውን እያቀረበም በወጣትነቱ ጠንካራ ነጋዴ መሆኑን እያሳየ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በመለዋወጫ ሱቁ ውስጥ አጠቃላይ ያሉት ንብረቶቹ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር እንደሚገመት የሚናገረው አቶ ዳንኤል፤ ዛሬም ነገም የሚያገኛትን ትርፍ በአግባቡ በመጠቀም ለተጨማሪ እቃዎች ግዥ እንደሚያውላት ይገልጻል። በህይወት ዘመኑ በርካታ ጊዜ እንደወርቅ ተፈትኖ ማለፉ እንዳጠነከረውም ይናገራል።
በኑሮው ማደግ የተነሳ የከተማ ሰው ሆኛለሁ ብሎ የገጠር እርሻውን ከመቆጣጠር አልቦዘነም። ይልቁንም መጠነኛ እረፍት ሲያገኝ ለቤተሰቡ የሚሆን እህል እያስመረተ ይገኛል። ይህ ጥረቱ ነገ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት ይዞለት እንደሚመጣ ደግሞ ተስፋ ሰንቋል። ስራ ማለት ለአቶ ዳንኤል ከበጎ አስተሳሰብ ጋር እያደገ የሚሄድ የጥረት ውጤት ነው። ማንኛውም ወጣት ነገውን እያሰበ ከአልባሌ ሱስ ርቆ ቀንም ማታም መስራት ከቻለ ከእራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን ብሎም ሀገሩን የማይጠቅምበት ምክንያት የለውም የሚለው ደግሞ ምከሩ ነው።’ ቸር እንሰንብት !!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
ጌትነት ተስፋማርያም