ደግነት በማይከለከል ፈቃድ ለሌሎች ራስን የማካፈል በጎ ስራ ነው። ደግነት፣ ለተራበ ምግብ ለታረዘ ልብስ፣ ለታመመ ጠያቂነትና መጽናኛ የመሆን ልባዊ ፈቃድ ነው።
ይህ ዘመን አንዳችን ራሳችንን ለሌሎች በመክፈል፣ ካለን ነገር ላይ ለማካፈል ልንነሳበት የሚገባ ዘመን ነው። ማንም ለራሱ ብቻ ሊኖር የማይችልበት እና ለሌሎች መቆም የሚገባን ዘመን ላይ ደርሰናል። ለነገሩ ቤተሰቦች ያለን ቤተሰቦቻችን በትምህርት ቤቶች ደግሞ መምህሮቻችን ስለደግነት ዋጋ በብዙ አስተምረውናል። ዛሬ ግን ደግነታችንን የግድ ልናሳይ የሚገባን ጊዜ ላይ ዓለማችን ደርሳ አድርሳናለች። ስለዚህ ከጉድለታችን ለማካፈል በደግነትም ለመሳተፍ እንዘጋጅ።
አውቃለሁ ደግነትን ግዴታ ማድረግ ያስቸግራል፤ የውዴታ ግዴታ ግን ሊሆን ግን ጊዜው ብሎናል። ያለንን ለመብላት ለመጠጣትና፣ ለመልበስ ለመኖርና ለመስራት ጊዜ ሁኔታዎችና ሰላም እንዲሁም ጤና ያስፈልገናል። ከእነዚህ አንዱ ወይም ሁለቱ ሲጎድሉ መኖር ትርጉም ያጣብናል።
ይህንን በጥቂቱ ለማብራራት ሁሉ ነገር ኖሯቸው በጤና ማጣት የሚሰቃዩ ሰዎች የበይ ተመልካች ሲሆኑ ብዙ ጊዜ አይተናል። ቤታቸው ውስጥ በሚኖር ድግስ ቢፌ አዘጋጅተው ከ20 በላይ ልዩ ልዩ ምግብ ጠረጴዛ ላይ አሰናድተው ሌላውን ብሉልኝ እያሉ እነርሱ ያዘጋጁትን የማይበሉ ሰዎች ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳጋጠሟችሁ አምናለሁ። በሌላ በኩል እጅግ ሃብታም የሆኑና ለዓለም የሚተርፍ ባለጸጋ ምድር ይዘው ሰላም በማጣት ማእድናቸውን አውጥተው የሀብታቸውን ትሩፋት መጠቀም ያልቻሉ ብዙ ሐገራት አሉ። ወደግለሰብ ደረጃም ብታወርዱት እጅግ የሞላቸው ባለጸጎች ሆነው በቤታቸው ውስጥ ባጡት ሰላም የጎሪጥ እየተያዩ ያላቸውን ሀብት በቅጡ ሳይደሰቱበት የሚያልፉ ሀብታሞችን ቤቱ ይቁጠራቸው። እንኳን ለመስጠት ሊኖሩበት የማይችሉትን ሀብት ታቅፈው እስከዘላለሙ ያሸልባሉ።
አሁንም ሌላ ገጽ እንግለጽ ካልን አለመተማመንና ጥርጣሬ በነገሰበት ግንኙነት ውስጥ ሁሌ መገፋፋትና መቀናቀን ስለሚኖር፣ ይህ ያለባቸውና ኑሮ የእውር ድንብር የሆነባቸው ቤቶች የፍቅር ያለህ ኡ… ኡ…! ቢሉ አያስገርመንም።
ሰላም፣ ፍቅር፣ ጤናና ትእግስት ቤት ያልሰሩበት ሐገር ነዋሪዎች፣ ሁሌ ጭቅጭቅና አተካራ ገንዘባቸው ስለሚሆን በሰከነ፣ በተረጋጋና፣ መቻቻል በሰፈነበት መንገድ ችግራቸውን ካልፈቱ ኑሯቸው የእሮሮ ኑሮ ነው፤ የሚሆነው። ከዚህ ቤት አንድ ሰው አግኝታችሁ ብታናግሩ የሚነግሯችሁ አቤቱታ የትየለሌ ነው። ጧት ማታ ንትርክና ይህን አጎደልክ፣ ያን አላሟላህም፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ነው፤ የሚሆነው። በዚህ ቤት ጉድለት እንጂ ሙላት አይነገርም።
ከዚህ ይልቅ አንዳቸው ላንዳቸው ደግነት ቢያሳዩ ነገሮች የቀለለ፣ ሥራው የሰመረ፣ ህብረቱ ሃያል፣ ጸጋውም የበረከተ ይሆንላቸውና የምስጋና ህይወትን መምራት ይሆንላቸዋል።
በደግነት ሌሎችን ለማሰብ ብዙ እስኪኖረን ድረስ መጠበቅ አያስፈልገንም። ካለን ትንሽ ላይ መስጠት የምንችለውን ያህል ከፍሎ መስጠት ነው፤ ደግነት። ለደግነት፣ ብዙ እስኪኖረን ድረስ ከጠበቅን አንድም፣ የጠበቅነው ብዙ ምን ያህል እንደሆነም ስለማናውቀው እያንዳንዱ ክምችት ሌላ ክምችት ይፈልጋልና ፍለጋችንን አናቆምም፤ ሁለትም ባስፈላጊው ጊዜ ለተፈለገው ነገር ላንደርስ እንችላለንና ካለን ማካፈል ይመረጣል።
ሰው ለመስጠት ሲነሳ የበለጠ ማንነት እንዳለው ካልተገነዘበ በስተቀር ስጦታው ንፉግነት ይሆናል። ምክንያቱም የሰጪ እጅም ልብም እኮ ሁልጊዜ ከላይ እንጂ ከታች አይሆንም። ስለዚህ ይህንን ልእልና ማስተዋል ይገባዋል።
ስለዚህ ስንሰጥ ባለን አቅም ይሁን፤ በሚፈለግብን ጊዜም እናድርግ፤ ለሚገባቸውም ወገኖች ማድረጋችንን እንወቅ።
ደግነት በብርድ ላይ ደጅ ለሚያድረው ወገን የሚሞቅ እሳት ነው። ደግነት፣ አድራሻው ለጠፋበት ሰው አፋላጊነት ነው፤ ደግነት ቆፈን ባለበት ስፍራ ለሚያንጠረጥረው ብርድ ልብስ ነው። ደግነት፣ የሐሩር ጥም ላንገላታው ወንድም ውሃ ማድረስ ነው። ደግነት ማደሪያ ስፍራ ላጣችው የጎን ማሳረፊያ ፍራሽ፣ በተሰራ ቤት ውስጥ መጠለያ መሆን ነው። ደግነት በወሊድ ሰኣት ደም ለፈሰሳት እናት የደም ልገሳ ማድረግ ነው። ከዳር ቆሞ ግን “ህዝቡ የታለ፣ ጨካኝ ሆኗል መተዛዘን ጠፋ፤” ብሎ ማማረር ደግነትም ደግ አሳቢነትም አይደለም። በተግባር ከተጠቀሱት አንዱን ለማድረግ መነሳት ነው፤ ደግነት። እርስዎ የቱን ይመርጣሉ? ተቀምጦ ማማረሩን ወይስ ካልዎት ጥቂት ማካፈሉን?
ደግነት፣ ውለታ የማይፈልጉበት የልብ ስጦታ ነው። አምላካችን ለእኛ ክረምትን የሚያህል ስጦታ ለአዝመራ ማምረቻነት አጥለቅልቆ ሰጥቶን፣ ከእኛ ከምስጋና በቀር የውሃ ምላሽ እንደማይጠይቀን ሁሉ ደግነታችን ለወሮታ ምላሽ መሆን የለበትም።
አምላካችን፤ በልግንና ጸደይን ሰጥቶን በወቅት እርሱ እንደማይለዋወጥ፣ ከለጋስነቱም እንደማይቆጥብ፣ በጸጋ ስጦታው አንበሽብሾን በስጦታው እንደማይፀፀትና መልሶ ለመውሰድ እንደማይጠይቀን ሁሉ እንዲሁ በደግነትህ ደስ ሊልህ እንጂ ራስህን ከባለውለታነት በመቁጠር ልትኩራራበት እንዳልተሰጠህ እወቅ።
ያለንን ለሚገባው እንስጥ፣ ያለንን በለጋስነት እናካፍል! ስናካፍል መልካም እኛነታችንን ወደሌላው እያካፈልን ነውና ደስ ይበለን። ስትሰጥ ከተቀባይህ ፈገግታን መቀበልህን አትርሣ። ያንን በደስታ ጸዳል ያበራ ገጽ የትም አታገኘውም። ለዚያ ደስታ ምክንያት በመሆንህም ልብህ በሐሴት የዕረፍት መስክ ውስጥ ትሆናለች።
ደግነት ዋጋው እጅግ የከበረ ነው። ደግነት ገንዘብና ንብረት ሳይሆን ሰውን ያህል የከበረ ነገር ለደግ አድራጊው ያመጣለታል። ደግነት የላቀና ያማረ መልክ ይዞ፣ በምላሹ ሰውን ያህል ነገር ወደራስ ቤት የሚያመጣ፤ የሚያበዛና የሚያትረፈርፍ መሆኑን እናያለን።
ነገሩን ያጎላልን ዘንድ አንድ ምሳሌ እነሆ ማለት እሻለሁ። በአንድ ሐገር ውስጥ እድሜው የገፋ መስፍን ነበረ። ሶስት ልጆች ኖረውት ሶስቱንም ተገቢውን የአስተዳዳር የህግና ሌሎችን ስፖርታዊ እውቀቶች ቢያስተምራቸውም ከእነርሱ መካከል የእርሱን ቦታ ተክቶ ህዝቡን የሚያስተዳድረውን መምረጥ ፈለገና እስከዛሬ በህይወት ካጋጠማችሁና በማድረጌ ደስ ተሰኝቼበታለሁ፤ ብላችሁ ከምታምኑበት ታሪክ አንዱን ተራ በተራ ንገሩኝ ሲል ይጠይቃቸዋል።
የመጀመሪያው ልጅ ተነሳና አባባ ለአደን ወጥቼ በነበረ ጊዜ እናትና ልጅ አጋዘን አንድ ላይ አገኘሁና ግልገሊቱን በጠመንጃዬ ነጥዬ በመምታት፤ እናትየዋ ሌላ አጋዘን እንድትወልድ መተዌን ሳስብ እደሰታለሁ፤ ሲል ተናገረ።
አባትም፣ እናቲቱን አጋዘን አለመግደልህ መልካም ነው፤ ይሁንና ለምን ጥቅም ስትል ግልገሉን አጋዘን ገደልኸው ? ሲል ጠየቀው፤ “እንደዚሁ ለደስታ”ሲል ዘና ብሎ መለሰለት።
ሁለተኛው ልጅም ተነሳና፤ አንድ ደሃሰው በጎዳና ምጽዋት ሲጠይቅ አገኘሁና ለምን እንደሚለምን ስጠይቀው፣ እንዴት ከመሬቱና ከቤቱ በጎረቤቱ ተፈናቅሎ እንደተሰደደና ሜዳ ላይ ለልመና መውጣቱን አብራርቶ፤ የደረሰበትን በደል ዘርዝሮ ነገረኝ፤ በዚህም ሳቢያ ጎረቤቱ ወዳለበት አካባቢ ሄጄ ሰውየውን ወደ ስፍራው መልሼና አስጠንቅቄ መምጣቴን ሳስብ ደስ ይለኛል፤ ሲል ጉዳዩን ተረከ።
ለመሆኑ ችሎት ላይ ስቀመጥ ግራና ቀኙን፣ ከሳሽና ተከሳሽን ሳናግር ሰምተህ ታውቃለህ አይደል፤ እንደዚሁ የተበደልኩ ባዩን አቤቱታ ብቻ ሰምተህ ፈረድክ ወይስ በዳይ የተባለውንም ሰው ቃል ሰምተሃል? ሲል ጠየቀው። ተበዳይ በደል ባይደርስበት ለልመና ይወጣል ብለህ ታስባለህ የኔ አባት ? ሲል መልሶ ጠይቆ በዳይን መጠየቅ አላስፈለገኝም፤ ስፍራውም ላይ ስደርስ የመስፍኑ ልጅ መጣ፤ ሲባል ሰፈር ለቅቆ ሸሸ፤ መባሉን ዘግይቼም ቢሆን ሰምቻለሁ፤ ሲል ለአባቱ መለሰለት።
አባትም የመጀመሪያውን ልጅ፣ ለደስታህ ስትል በሌላው ላይ ሀዘን ለመጨመር ባለማቅማማትህና ባለማሰብህ ቅር ብሎኛል፤ አለና ሁለተኛው ልጄ ፍርድህ ሚዛናዊነት የጎደለውና ርትዓዊ ቢሆንም ፍትሐዊ ያልሆነ እርምጃ ነው፤ የወሰድከው፤ ካለ በኋላ ሶስተኛውን ልጅ አንተስ አለው ?
አባቴ እኔ ብዙም ያደረኩት ነገር የለም፤ ምናልባት አሳዝንህ ይሆናል፤ እኔን ግን አስደስቶኛል። አባባ ነገሩ እንዲህ ነው፤ አለው። ካንተ ጋር ክፉኛ ይጋጭና በሞት ይፈላለግ የነበረው፣ የአቅራቢያችን ግዛት መስፍን ፈረሱ ገደል ገብቶበትና እርሱም ጉድባ ውስጥ ገብቶ የድረሱልኝ ድምጽ ሲያሰማ አግኝቼው፤ ወዲያው ከፈረሴ ወርጄ ወደመልካም መሬት ካመጣሁት በኋላ በአቅራቢያው ወዳለ ህክምና ጣቢያ በፈረሴ ወስጄ አሳክሜ ለህክምናው ከፍዬ ወደ መኖሪያችን መምጣቴን ሳስበው ደስ ይለኛል። በአጠገቡ ሰው ባለመኖሩ ደግሞ ተገርሜ ነበረ።
ስሰናበተውም ያንተ ልጅ መሆኔን ነግሬው ስወጣ በድንጋጤ ከተኛበት አልጋ ላይ ሊወድቅ ነበረና፤ አጽናንቼው ነው የመጣሁት፤ ሲል ተረከለት።
አባትም በመገረም፤ ለዚህ ነው ያ፣ ሞገደኛ ሰው ከቶውንም ጨዋ የሆነውና ጉዳዩ ባልገባኝ ነገር ደብዳቤ የጻፈልኝ፤ አለና ልጄ ራስህን ለአደጋ አጋልጠህ የፈጸምከው ጀብዱ ከአንበሳ መንጋጋ ግዳዩን እንደመንጠቅ ያህል የሚያስፈራ ነው። ይሁንናም ጠላትን በፍቅር እንደ ማሸነፍ ያህል ጀግንነት በዚህ ዘመን አይሞከርም። ይህ ያንተ ደግነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተፈጸመው የሳምራዊው ደግነት ጋር ወደረኛ የሚሆን ነው፤ ካለው በኋላ ለጠላት ልበ-ሰፊ የሆነውን የልጄን ልብ ክፉኛ ወደድኩት።
ስለዚህ ቀጣዩ የግዛቲቱ መስፍን የሚሆነው እርሱ ነው፤ አላቸውና ትልቀኛው ወንድሙ በጦር ታግዘዋለህ፤ ሁለተኛውን ደግሞ ዳግመኛ የፍትህ ስህተት ስለማትፈጽም በፍርድ ትረዳዋለህ፤ እርሱ ግን በቅን መንገድ የሚያስተዳድር መሪያችሁ ነው፤ ሲል መለሰላቸውና የጥያቄዬ ግብ ይኸው ነበረ፤ አላቸው።
ደግነት ጠላትን መውደድም ነው። ደግነት ከሚያስፈራ ወገን ጋርም በእምነት መንገድ መጀመርም ነው። ደግነት፣ ነዳጁ ፍቅርና መስዋእትነት የሆነ፣ በቅንነት የሚሰራ የሩቅ መንገድ መጓጓዣ ሰረገላ ነው። ስለዚህም ነው፤ ደግ መሆን “ የማይተመን ዋጋ ያለው መልስ አለው፤” የምንለው።
“መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና (ሉቃ 6፡35)።”ይላል መጽሐፋችን።
የደግነት ምንጩ ፍቅር ነው፤ ለሰው ልጅ ያለንን ድንቅ ፍቅር ማሳያ ነው። ያ፣ ፍቅር ደግሞ ሰጥቶ የማይጠግብ አድርጎ የማያልቅበትና አድማስ የለሽ ነው። “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤” የኣለማችን ታላላቅ ቴክኖሎጂዎች፣ የህክምና ልህቀትና የሃብት ስፋት ሳይሆን ከልብ የመነጨው የደግነት አባት ፍቅር ግን ያለውን ሁሉ ይሰጣል፤ ለብዙ ነገራችንም መድሃኒት ነው።
ደግነት ከልብ የሆነ ሰብዓዊ ወዳጅነትን መግለጫና ለሌሎች ፍቅራችንን የማሳያ መንገድ ነው። ሌላው ሊሆንለት የሚገባውን ግን የማይችለውን ነገር እኔ እችልልሃለሁ ማለት እኮ ነው፤ ደግነት። ስለዚህ ደግነት ለራስ ሳይሆን ከራስ ያለፈ ለሌሎች የመሰጠት ፀጋ ነው። መታደል አይደል ? !!!
በጨለማ ላይ ብርሃን ብልጭ ሲል ጨለማው ሸሽቶ እንደሚሄድ፣ በተሰጠን የስጦታ ፀጋ እንደተመረጡ እንደተወደዱ የፅድቅ እጆች፣ በእጃችን የጽድቃችን ፍሬ ደግነታችን ይታይ እንጂ ለመጽደቅም ለመመፃደቅም አናደርገውም። ህይወታችንን ከሌሎች ተቀበልን እንጂ እኛ አላመጣነውም፤ ይህን በልባችን ይዘን፣ እኛም ለሌሎች የረሐባቸው ጥጋብ፣ የጥማታቸው ርካታ፣ የእርካታቸው መሸፈኛ ልብስ እንድንሆን ነው የተጠራነው። ይህም በፍፁም ትህትና፣ ጨዋነትና መሰበር እንጂ በመኮፈስና በግብዝነት የሚከናወን ተግባር አይደለም። ስንሰጥ እንዲሁ እንደተቀበልን እንቁጠር ምክንያቱም ቀድሞ ብዙ ተቀብለናልና።
እኛ ጥሩዎችም ደጎችም መሆናችንን ማሳየት ይገባናል፤ ጥሩ ስንሆን ትህትናችን ለራሳችን የሚሰማንና የሚታየን ሲሆን፤ ደግ ስንሆን ደግሞ ለተደረገለት ሰው ጥቅምና ለፈጠረን አምላክ ደስታ ነው። አንደኛው የህይወት ዘይቤያችን ሲሆን ሌላኛው ኑሯችንን ይጨምራል፤ ስለዚህ ጥሩም ደጎችም ሆነን ይህን ክፉና አስፈሪ የጨለማ ጊዜ የደግነት ብርሃን እያበራንበት የበሽታንና የዓለምን ክፉ ጉልበት እንስበር፤ የበሽታን ቅስም ሰባሪነት እንመክት። በአጭሩ ደግነታችን በአስፈላጊው ቦታና ጊዜ ባለን አቅም ይገለጽ።
የእኔ ፣ አንተና አንቺ….. የምን ልርዳህ …ደግነት፣
ወቅታዊው ችግር ለመረረው ነፍስ ጣፋጭ ጠብታ ነው።
…. መድረሻ ላጣ የመጠጊያ አለት ነው።
…. ተስፋ ለቆረጠ የተስፋ ወጋገን ነው።
…. ጨለማው ለበረታበት የብርሃን ብልጭታ ነው።
አነሰ ሳንል እንስጥ….. አይበቃም ሳንል እናበርክት…. ይጎድልብኛል ሳንል እንለግስ፤ በቸርነት የከሰረ ደግ፣ አይቼም ሰምቼም አላውቅምና እንርዳ። እመኑኝ ታላላቆች፣ በማይነጥፍ ሁኔታ ታላቅ የሆኑት በመስጠታቸው ነው።
እጅግ የበዛ ንብረትና ሐብት በግፍ የሰበሰቡ ወገኖች እረፍታቸው የቆቅ፣ መኝታቸው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው፤ ሁሌ ስጋት ነው። ሁለመናቸው በንፍገት የተመላ ስለሆነ ሲጠየቁ የተዘረፉ ስለሚመስላቸው አይሰጡም። ይልቅ ካላቸው ትንሽ ያካፈሉ ብሩካን ናቸው። እውነቱን ለመናገር፣ “…. የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ሆኖ ሳለ….” ለማከማቸት የምንባክንበት ምክንያት መኖር የለበትም። ሳንባክንም ሳናባክንም ያለንን እንስጥ፣ እነዚህ ደጋጎች፣ ሲያንቀላፉ የሞት ያህል ተዘልለው፤ ሲያርፉ እያንኮራፉ የሚነሱ ብፁዓን ናቸው።
ደግነታችን ፈጥኖ ደራሽነት ነው። ፈጥነን ልንደርስላቸው የሚገቡ ብዙ ሰዎች በዙሪያችን አሉና እንቃኛቸው፤ እንድረስላቸው። በፍራሽ ላይ ፍራሽ ከደረበና የላባ ትራስ ከተደገፈ፣ እንቅልፍ አልባ ሌሊት ይልቅ፣ በሰሌን ላይ ካለም ደርበው የተኙት እንቅልፍ ይጥማል። ስናካፍል ጎናችን እርፍ ይላል፤ በንፍገት ስንገለማመጥ ጀርባችን ይላላጣል። ስለዚህ፤ እንስጥና እርፍ እንበል! ሌላውንም ከመቅበዝበዝ እናሳርፍ !!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ