ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከህመም እፈውሳለሁ በሚል የሴቶችን ጉንጭና ጡት እየመጠጠ ገንዘብ የተቀበለ ሰው ፍርድ ቤት መቅረቡን በመግለጽ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
ጉንጭና ጡት በመምጠጥ ህመምተኛን አድናለሁ የሚል የፌዝ ዶክተር ተከሰሰ
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በልዩ ልዩ ቀበሌዎች እየተዘዋወረ የሴቶችን ጉንጭና ጡት እንዲሁም የወንዶችን ሆድ በአፉ እየመጠጠና በምላሱ እየላሰ ከህመም ፈውሳለሁ እያለ አታለለ የተባለው አበራ ደቀሱ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ። በተከሳሹ ላይ የቀረበበት የአቃቢ ሕግ ክስ እንደሚያመለክተው ሰኔ 30 ቀን 1962 ዓ.ም በአርበኞች መንገድ ኗሪ የሆኑትን የአቶ መኮንን ባርሶማን ባለቤት እመት በለጤ ገብረ ጻዲቅን ከፊታቸው ላይ የቆዳ በሽታ አድናለሁ ብሎ በአፉ ሲስማቸውና ሲመጣቸው ውሎ 50 ብር ተቀብሎ ጠፍቷል የሚል ነው።
የግል ክስ አመልካቹ አቶ መኮንን በርሶማ ለፖሊስ ባመለከቱት ቃል ተከሳሹ አበራ የፊት ቆዳ በሽታ አውቃለሁ ብሎ ባለቤታቸውን እንዲያድንላቸው በ150 ብር ተዋውለው ሚስታቸውን ጉንጫቸውን እያገላበጠ ሲስማቸው ውሎ በቀብድ ስም 50 ብር ተቀብሎ መቶ ብሩን እንደገና መጥቶ ከመጠጠ በኋላ አድኖ እንዲወስድ መስማማታቸውን አስረድተዋል።
በአበራ ላይ የቀረበው ሁለተኛና ሶስተኛ የአቃቢ ሕግ ክስ በተጨማሪ እንዳመላከተው፣ በዚሁ በአዲስ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ቀናት ከደጃዝማች ነሲቡ ሰፈር ኗሪ የሆኑትን አቶ ገብረ ሕይወት ዋናኘህን እና እመት ይሁዜ መርስዔን በተመሳሳይ ማጭበርበር ወንዱን ሆዳቸውን ሴቷን ጡታቸውንና ጉንጫቸውን በመምጠጥና በመሳም ከበሽታው አድናለሁ ብሎ ገንዘብ መቀበሉን የሚዘረዝር ነው።
ተከሳሹ ሰዎቹን ጡታቸውን፣ ጉንጫቸውንና ሆዳቸውን እየመጠጠና እየላሰ የሆድ፣ የአንጀትና የጉንጭ በሽታ አድናለሁ እያለ ብር የተቀበለው በመያዣ ስም ሲሆን ቀሪውን ብር ካዳንኩ በኋላ ትሰጡኛላችሁ በማለት ወዲያው እየጠፋ መቅረቱን የአቃቢ ሕግ ማስረጃ ያስረዳል። አበራ ከፖሊስ ጣቢያ በፍቃደኝነት በሰጠው ቃል እንደገለጸው ይህንን መሳይ አድራጎት በከተማው ውስጥ በመዘዋወር መፈጸም ከጀመረ ሁለት አመት እንደሞላው አስረድቷል።
ተከሳሹ ዕድሜው 28 ዓመት ነው። ፈጽሟል ስለተባለው ወንጀል ከፖሊስ ጣቢያ ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት ሶስት ሰዎች እንዳስረዱት የሴቶቹን ጉንጫቸውንና ጡታቸውን፣ የወንዶቹን ሆዳቸውን እየሳመና እየመጠጠ ከበሽታ አድናለሁ ብሎ ገንዘብ እየተቀበለ መሄዱን በጣቢያው የምርመራ መዝገብ ላይ አስፍረዋል።
ተከሳሹ ከአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፖሊስ አማካይነት ተይዞ በቀረበ ጊዜ የእምነት ክህደት ቃሉን ከሰጠ በኋላ በምስክር ተረጋግጦበት ቅጣት እንዲወሰንበት አቃቢ ሕጉ አቶ ታደሰ ሐጎስ አመልክተው ነበር። ለፍርድ ቤቱ ጉዳዩ አዲስና አስደናቂ ነገር በመሆኑ በችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛና ረዳቶቻቸው ዳኞች በነገሩ ተወያይተውበት ከሁሉ አስቀድሞ የግል ተበዳይ ነን ባዮቹ ከችሎቱ ቀርበው ሁኔታውን እንዲያብራሩ ስላዘዙ ተከሳሹ በቀጠሮ ወደ እስር ቤት ተመልሷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012
የትናየት ፈሩ