ትውልዱ አዲስ አበባ አማኑኤል ከሚባለው ሰፈር ነው። ገና በወጉ ጡት ሳይጥል ነበር ወላጅ እናቱን በሞት ያጣው። የልጅነት ዕድሜውን ሳያጣጥም አባቱ ጉራጌ አገር ‹‹ጉንችሬ›› ከሚባል ስፍራ ወሰዱት። አባት የወላጆቻቸውን መሬት እያረሱ በሚያገኙት ገቢ ልጃቸውን ማሳደግ ያዙ።
ህጻኑ ሙሰማ የጎደለበት የለም። ከጓሮው እሸት፣ ከማጀትም ወተት እየተጎነጨ በቡረቃ አደገ። መልካም የሚባለው የልጅነት ጊዜው አልፎ በዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር እንደ እኩዮቹ ለትምህርት ቤት አልተፈቀደለትም። የአባቱን ትከሻ ከድካም ያሳርፍ ዘንድ ቀንበሩን ተቀብሎ ሃላፊነትን ተረከበ። በጉርምስና ጉልበቱ ጥሩ ገበሬ ወጣው። በላቡ ወዝ እያረሰ የሚያገባው እህልም ከጎተራው ሞልቶ በረከትን አስገኘለት።
ሙሰማ በሚያደርገው መልካም ተግባር ከአባቱና ከአያቶቹ ምስጋና ከምርቃት ተቸረው። እንደልጅነቱ ሳይቦርቅ ለቤተሰቦቹ ፍላጎት ማደሩም ለብዘዎች ምሳሌ ሆነ። ውሎ ሲያድር ግን የወጣቱ ልብ መሸፈት ያዘ። የማያውቀውን የትውልድ ስፍራ አዲስ አበባን መናፈቅ ጀመረ። ይህን ሲያስብ የገጠር ህይወቱ አስጠላው። አሁን እሱም እንደታላቅ ወንድሙ ከተሜ መባልን ይፈልጋል። ጥሩ ለብሶና አምሮበት የሚታየው ደግሞ ሁሌም ከሚያልመው ከተማ ሲደርሰ ብቻ ነው። በእሱ ዕምነት እስካሁን ገጠር ያሳለፈው ጊዜ ከበቂ በላይ ነው። ከተማ ተወልዶ የገጠር ልጅ መሆኑም ያበሳጨዋል። ሙሰማ ይህን እያሰበ አዲስ አበባ ለመግባት ቆረጠ።
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ዕትብቱ የተቀበረባት መሆኑን ጠንቅቆ የሚውቀው ወጣት በአካል ሲያገኛት ይበልጥ ወደዳት። በናፍቆት የወደቀላት አገር ተቀብላ ስታስተናግደው ነገሮች ሁሉ ተቃኑለት። ታላቅ ወንድሙን ጨምሮ የቅርብ ዘመዶቹ በወጉ ተቀብለው አስተናገዱት። እንግድነቱ እንዳበቃ ስራ ለመያዝ ማፈላለግ ጀመረ። ሙሰማ ቀለም ባለመቁጠሩ የተገኘለት እንጀራ የጉልበት ስራ ሆነ። ከቀናት በኋላ ከአንድ የዘመድ እንጨት ቤት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። የሚያገኘው ገንዘብም ለዕለት ወጪው አገዘው። ከተማውን ለምዶ ከብዘዎች ሲግባባም የገንዘብ ዋጋና ጥቅም ገባው። በዚህ ጊዜም ጥሪት መቋጥርን አውቀ። ይህ ልምድ ይበልጥ እንደሚበጅ ሲገባው ጅምር ስራውን ትቶ ወንድሙ ቤት ለመኖር ወሰነ።
አዲስ ህይወት
አሁን የከተማ ህይወትና ሙሰማ በአግባቡ ተዋውቀዋል። መግቢያ መውጫውን ጠንቅቆ ለማወቅ ጌዜ ያልፈጀበት ወጣት የተሻለ ለመኖር አማራጮች የበዙ መሆናቸው እየገባው ነው። ለቀናት ውሎ አዳሩን በወንድሙ ቤት ያደረገው ወጣት ለቀጣይ ህይወቱ ማሰብ ጀምሯል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ራስን መለወጥ እንደሚገባ እያቀደ ነው። ለዚህ ሃሳቡ ማረፊያ የሆነውን የታክሲ ረዳትነት ሲያገኝም አይኑን አላሸም።
ውስጡን ደስ እያለው ገንዘብ ተቀባይ ሆነ። ሙሰማ ኑሮውን ከታላቅ ወንድሙ ቤት አድርጎ የታክሲ ላይ ስራውን ቀጠለ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ከተማውን ይበልጥ አሳወቀው። ውሎና ተግባራቸው ከሚለይ እኩዮቹ ጋር ተግባባ። ወጣቶቹ ያሰቡትን አማከሩት። አልተቃወመም። ሃሳባቸውን ተቀብሎ ዓይኖቹን በሚሰረቁ የመኪኖች ሆድ ዕቃ ላይ አተኮረ። ለስራ በሚዞርባቸው አካባቢዎች የሚመለከታቸው መኪኖች ያጓጉት ጀመር። ስራው ጥቅም እንዳለው ሲረዳ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ የመኪኖቹን ፊትና ኋላ መዳበስ ለመደ። በእጁ የሚገቡ ዕቃዎችን እየሸጠም ትርፉን መካፈል ጀመረ። ድርጊቱ እየጣፈጠው ሲመጣ በልማዱ ገፋበት። አሳቻ ጊዜና ቦታን እየመረጠ የመኪኖችን ዕቃዎች ከላያቸው ማራገፍ ያዘ። በአዲሱ የስራ ልማድ የገንዘብ ቦርሳው ሞላ።
ለፍቶ ከማደርና ወር ጠብቆ ከሚከፈል ደሞዝ የስርቆት ተግባሩ እንደሚያዋጣ ገባው። መኪኖች ለጉዳይ በቆሙበትአጋጣሚ የእጅ ሙያውን የሚያሳየው ሙሰማ ድርጊቱ ከሌሎች ልቆ የተሻለን ማግኘት መለያው ሆነ። ለዚህ ድርጊቱ አነጣጣሪ አይኖቹ ከፈጣን አግሮቹ አብረው ያግዙት ያዙ። አንድ ቀን ሙሰማ የተለመደውን ስራ ሊከውን ወደ ቆሙ መኪኖች አነጣጠረ። ከስፍራው ደርሶም መላ አካላቸውን ሊዳብስ ከመረጣቸው መሀል ወደ አንዱ ተጠጋ። ጀርባውን አስደግፎ ፈጣን እጆቹን ልኮ ስራውን ከመጀመሩ በፖሊሶች ዓይን ገባ።
ፖሊሶቹ በእጁ ያለውን የመኪና እቃ አሲይዘው ወደጣቢያ አደረሱት። በበቂ ምስክሮች እማኝነትና በፖሊሶች እጅ ከፍንጅ የተያዘው ሙሰማ ከህግ ቅጣት ማምለጥ አልቻለም። ክስ ተመስርቶበት ወደ ማረሚያ ሊወርድ ግድ አለው። ሙሰማ የስድስት ወራት ቅጣቱን አጠናቆ እንደወጣ ስራ መፈለግ አላሻውም። ወደቀድሞው ተግባሩ ተመልሶ የመኪና ዕቃዎችን መስረቁን ቀጠለ። የነበረውን ልምድ አዳብሮም በድርጊቱ ተመላለሰበት። ከሌሎች አብሮ በጨለማ የሚፈጽመው ዘረፋን ቋሚ መተዳደሪያ አደረገው። መሰል ጓደኞቹ ጨለማን ተተግነው በሚፈጽሙት ዝርፊያ ግንባር ቀደም ሆኖ የሰፈሩ ስጋት ለመሆን በቃ።
ዝርፊያ በቡድን
ሙሰማና ባልንጀሮቹ አሁን የምሽቱ ዝርፊያ መኖሪያቸው ሆኗል። ቀን በጫት ቆይታ ሲመክሩ ይውላሉ። ጀንበር አዘቅዝቃ ስፍራው በጨለማና ጭርታ ሲያዝም ቦታ ለይተው ለዝርፊያ ይሰማራሉ። የበርካታ ጊዜ ልምዳቸው በእግረኞች ላይ ያተኮረ ነው። አካባቢውን በውል የማያውቁና ምሽቱ የቀደማቸው አንዳንዶች በእነሱ ወጥመድ ለመውደቅ አይዘገዩም።
እነ ሙሰማ ሁሌም ቢሆን ጩቤና ድንጋይ ከእጃቸው አይጠፋም። በመዘረፉ አምኖ ያለውን ያላስረከበ መንገደኛ ቢኖር እርምጃ ለመውሰድ ወደ ኋላ አይሉም። ከመቀደማቸው በፊት መቅደምን የሚሹት ባልንጀሮች ድርጊታቸው ፈጣንና ጭካኔ የተሞላ ነው። ሁሌም በምክክር የሚሰማሩት ጓደኛሞች ያገኙትን ተካፍለው ስለነገው ድርጊት ለውይይት ሲቀመጡ አይዘገዩም። ሙሰማና የዝርፊያ ባልንጀሮቹ ዘወትር ተቀምጠው የሚመክሩበት የሎሚ ሜዳ አዲሱ ድልድልይ ለምሽቱ ስራ ያሰማራቸዋል።
ስፍራው በጨለማ ተውጠው ለሚከውኑት ተግባር ሁሌም እንዳገዛቸው ነው። በሙሰማ አዝማችነት የሚፈጽሙት ተግባር በቀናቸው ጊዜም ማግስቱን እየቃሙ ይዝናናሉ። ለእነሱ የአስኮ መድሃኒያለም ዙሪያ ገባ ግዛታቸው ነው። በመንገዱ ከሚያልፉ የምሽት መንገደኞች ኪስና ቦርሳ የሚሹትን አያጡም። ጭርታውን ተጠቅመው፣ ጨለማን ተተግነው የሚዘርፉት ገንዘብና ሞባይል ኪሳቸውን ሲያደልብ ኖሯል።
ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም
ዕለተ ቅዳሜን ከሰአት ሙሰማና ጓደኞቹ ከተለመደው የሎሚ ሜዳ ድልድይ ላይ ተቀምጠው ሲመክሩ ውለዋል። ካሳለፉት ልምድ ቀኑ የመዝናኛና የተለየ ሲሳይ መገኛ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በዚህ ቀን በስካር ሞቅ ብሏቸው መንገዱን የሚያቋርጡ እግረኞች አይጠፉም። ሙሰማ እንደለመደው ከጓደኞቹ መምከር ጀምሯል። የቅዳሜን ምሽት ከሌሎች ቀናት በተለየ መስራት እንዳለባቸው እያሳመነ ነው። አምስት ሆነው የከበቡት ዘራፊዎች የምሽቱን ስምሪት መምረጥ ጀምረዋል። ጨለማው የሚያግዛቸውንና አካባቢው የሚደብቃቸውን ስፍራ ለይተው ለምሽቱ ተግባር ተዘጋጅተዋል። ሁሉም በጎናቸው የሻጡት ስል ቢላዋ አብሯቸው ለመሆኑ እየነኩ አረጋግጠዋል። የሚቀራቸው ቢኖር ለሁለት ተከፍለው የሚዘርፉበትን ቦታ መለየት ብቻ ነው።
ምሽት አንድ ሰአት ከሰላሳ ሲሆን ሁሉም ዘራፊዎች ወደጉዳያቸው ሊበተኑ ግድ አለ። በሁለት የተከፈለው ቡድን ዳግም በሁለትና ሶስት ተዋቅሮ አቅጣጫውን ለየ። አጋጣሚ ሆኖ ሙሰማ የደረሰው ለሁለት ከተከፈለው ቡድን ሆነና ከባልንጀራው ሀይረዲን ጋር ሊሰማራ ተዘጋጀ።
ሰአቱ ሲቃረብ እነ ሙሰማ የመድሃኒያአለምቤተክርስቲያን ጀርባን ይዘው ቁልቁል ወረዱ። ጥግ ይዘው ከመመሸጋቸው በፊት ጓደኝዬው በኪሱ የያዘውን ባለ ቢጫ እጀታ ቢላዋ ለሙሰማ አሳየው። ሙሰማ ትጥቁን ባየ ጊዜ ለምሽት ስራቸው በቂ መሆኑን አረጋገጠ። ካሉበት ሆነው በጨለማ ብቅ የሚል መንገደኛን ጠበቁ። ኮቴ እያዳመጡ ኮሽታን እየለዩ አነጣጠሩ።
ለጊዜው ምንም የለም። ጥቂት ቆይቶ በርቀት ያዩትን ለማረጋገጥ አንጋጠጡ። አልተሳሳቱም። ሁለት ሰዎች የሞቀ ጨዋታ ይዘው ወደ እነሱ እየመጡ ነው። ወንድና ሴት ናቸው። ከመጠጋታች በፊት ራሳቸውን ደብቀው ድምጻቸውን አጠፉ። ሁለቱ መንገደኞች ጨለማው ያስፈራቸው አይመስልም። በፊታቸው አንዳች ስጋት ሳይነበብ ከሎሚ ሜዳ ወደ አስኮ በሚወስደው ጎዳና መጓዝ ጀምረዋል። እነ ሙሰማ ከነበሩበት ፈጥነው ተነሱ። በዚህ መሀል ሀይረዲን ሽንቱን የሚሸና መስሎ ከአንድ ጥግ እንደመቆም አለ።
ይህኔ ሙሰማ ከፊትለፊታቸው ሆኖ መንገዳቸውን በማገድ አስቆማቸው። ድንገቴውን ድርጊት ያስተዋለው መንገደኛ በፊቱ የተለየ ንዴት ተነበበ። ሙሰማ ስሜቱን ሲመለከት ወደ ሴቷ ቀርቦ ሊፈትሻት ሞከረ። መንገደኛዋ በድንጋጤ እንደተዋጠች ምንም ያለመያዟን አረጋገጠችለት። ሙሰማ አላመናትም። ይበልጥ ተጠግቶ ሊፈትሻት ፈለገ። ወዲያው ግን ሃሳቡን ሰረዘ። እሷን ትቶ ወደ ወንዱ ተጠጋ። መንገደኛው ድርጊቱ ስላናደደው ግብግብ ገጠመው። ተያያዙ። ሙሰማ ፍልሚያው የበረታ ቢመስለው ከጓደኛ ቢላዋውን ተቀበለ።
ታፋው ላይ ወግቶም የያዘውን ቁጭ እንዲያደርግ አዘዘው። ግብግቡ ቀጠለ። መንገደኛው እግሩ እየደማ ሙሰማን በ‹‹እምቢኝ›› ባይነት ታገለው። ጓደኛው እየጮኸች ነው። የእሱን መጎዳት አላወቀችም። ደጋግማ የያዘውን እንዲሰጣቸው ትወተውታለች። እሱ አሁንም በአልሞት ባይነት መታገሉን ቀጥሏል። ድንገት በርቀት ብቅ ያለችው ቪትዝ መኪና ጨለማውን በብርሃን ስትሞላው ዘራፊዎቹ ተሯሯጡ።
የመኪናዋን መቃረብ ያየችው መንገደኛም እጇን ዘርግታ የሾፌሩን እርዳታ ጠየቀች። ባለመኪናው አጠገባቸው እንደደረሰ እንደመቆም አለና ፍጥነቱን ጨምሮ ተፈተለከ። የመኪናውን መራቅ ያስተዋሉት እነ ሙሰማ ተመልሰው መንገደኞቹን ተጠጉ። ሙሰማ የጀመረውን ቀጠለ።
የያዘውን እንዲሰጠውም መንገደኛውን ታገለ። አሁንም አሻፈረኝ ብሎ መቁረጡን ሲያውቅ የመለሰውን ቢላዋ አውጥቶ ሁለት እጆቹንና ደረቱን ሶስት ጊዜ ወግቶከኪሱ ገባ። ይህኔ መንገደኛው በኪሱ ያለውን ሁሉ እንዲወስድ ፈቀደለት።
ሙሰማ በኪሱ ያገኛቸውን ሁለት ሞባይሎች አጥብቆ ያዘ። ወዲያው የተጎጂው የጭንቅ ጨኸት አካባቢውን አደረሰው። እነ ሙሰማ ያገኙትን ይዘው ስፍራውን ሲለቁ ድምጽ የሰሙ ሰዎች ከቤተክርስቲያኑ አቅጣጫ ብቅ ማለት ጀመሩ። ሰዎቹ የተጎዳውን መንገደኛ ባዩ ጊዜ ለእርዳታ ፈጠኑ። በአካባቢው የሚያልፉ መኪኖችን እየለመኑም ሀኪም ዘንድ ለማድረስ ተጣጣሩ። በቀላሉ አልተሳካም። የምሽቱ መግፋት ካሰቡት ሳያደርሳቸው ቀርቶ ተጎጂው ብዙ ደም ፈሰሰው። እነ ሙሰማ ያቀዱትን እንደፈጸሙ በጫካው አሳብረው ወደ ብርሃን ዘለቁ። ፈጥነውም የስልክ ደንበኛቸው የያዙትን እንዲገዛቸው ጠየቁ።
ደንበኛው ለዛሬ የሚሆን ገንዘብ እንደሌለው ነገራቸው። ሞባይሎቹን ይዘው ለጓደኛቸው ወንድም በአንድ ሺህ ሶስት መቶ ብር ሸጡና የዝርፊያ በለስ ካልቀናቸው አጋሮች ጋር ሲዝናኑ አመሹ። ምሽቱ እንዳሰቡት በደስታ አልተሞላም። በስካር ስሜት ጠብ ተነስቶ ከሌሎች ጋር ተጋጩ። ከእነሱ መሀል አንደኛው በመፈንከቱም ከለሊቱ ስምንት ሰአት ሊበታተኑ ግድ ሆነ።
የፖሊስ ምርመራ
በዛን ቀን ምሽት ፖሊስ በስፍራው ስለደረሰው አደጋ ሰምቶ ምርመራውን አጣራ። በዕለቱ በነበረው ዝርፊያ የመንገደኛው ህይወት ማለፉን ባወቀ ጊዜም ጥልቅ ምርመራ በማድረግ መረጃዎችን ሰበሰበ። ምክትል ሳጂን ሲሳይ ተሾመና የተዋቀረው ቡድን ደጋጋሚ ወንጀለኞቹን አድኖ ለመያዝ ጊዜ አልፈጀም። በበቂ መረጃና ማስረጃ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ በህግ ቁጥጥር ስር አዋሉ።
ውሳኔ
የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሀምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም በችሎቱ ተሰይሞ የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በህግ ለመዳኘት ተዘጋጅቷል። ፍርድ ቤቱ በፖሊስና በዓቃቤ ህግ ምርመራ በአግባቡ ተጣርቶ የቀረበለትን ክስ መርምሮ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል። በውንብድናና በሰው መግደል ወንጀል ተጠያቂ ያደረጋቸውን ባልንጀሮች እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ እስር የቀጣ ሲሆን ሙሰማ መሀመድን በአስራ ስምንት አመት ጽኑ፣ እንዲሁም ተባባሪውን ሀይረዲን ሁሴንን በአስራ አራት አመት ጽኑ በመቅጣት ፍርድ እንዲያገኙ አድርጓል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2012
መልካምስራ አፈወርቅ
እምቢኝ! ባዩ መንገደኛ