በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ህዳር 1879 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የሚነገርላት የአዲስ አበባ ከተማ የሥልጣኔ አጀማመሯ ከ1886 እስከ 1931 ዓ.ም እንደሆነ የታሪክ ድርሳን ያመለክታል::
የዘመናዊ ከተማነት መልክና ቅርጽ መያዝ እና የትልልቅ ህንጻዎች መገንባት ከተማዋን ወደ ስልጣኔ ማዕከልነት ያሸጋገሯት ክስተቶች መሆናቸውን ታሪክ ያወሳል:: የከተማዋ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና የቆዳ ስፋቷ እያደገ መምጣት እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ባለጉዳዮችን በአግባቡ ማስተናገድ በማስፈለጉ ደግሞ በ1909 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መቋቋሙም ይነገራል:: ማዘጋጃ ቤቱም የከተማው ‹‹የማህበር ቤት›› ተብሎ ይጠራ ነበር::
ይህ ስያሜ የተሰጠውም ማዘጋጃ ቤቱ እንዲመሰረት ግፊት ሲያደርጉ በነበሩት በሶሪያው እድሊቢ እንደሆነ ነው የሚነገረው።ቀድሞ ‹‹የከተማ ማህበር ቤት›› የሚለው ስያሜ አዲስ አበባን አይወክልም በሚልም ማዘጋጃ ቤት የሚል ስያሜ እንደተሰጠው በታሪክ ሰፍሯል::
በወቅቱ ለአዲስ አበባ ከተማ እድገትና ለከተማዋ ህዝብ ደህንነት ሲባል በ1926 ዓ.ም የሚያከናውናቸውን ተግባራት በ16 ዋና ዋና ክፍሎች ከ250 ባልበለጡ ሰራተኞች የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ስራውን ያከናውን ነበር:: የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ሕንፃ በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ በነበሩት አፄ ኃይለሥላሴ ጥቅምት 23 ቀን 1942 ዓ.ም. የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ወደ ግንባታ የገባው ደግሞ ከዛሬ 70 ዓመት በፊት ሲሆን፣ ግንባታውም 15 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ከታሪክ መረዳት ይቻላል::
የሕንፃውን የዲዛይን ስራ የሰሩትም ጣሊያናዊው አርቱሮ ሜዜዲሚ እንደሚባሉ ነው የሚገለፀው:: አዲሱ ህንፃ ለግንባታ ብቻ ስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል:: ለጽህፈት ቤት እቃዎች፣ ለአዳራሽ ማስጌጫዎችና ለሌሎች ቁሳቁስ ግዥ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ በመደረጉም በአጠቃላይ የህንፃው ሙሉ ግንባታ ወጪ ስምንት ሚሊዮን ብር የፈጀ ስለመሆኑ ነው በታሪክ የሚገለፀው::
በወቅቱ ሕንፃው ሲሰራ 200 ልዩ ልዩ ክፍሎች ነበሩት:: የመኪና ማቆሚያና የመናፈሻ ቦታዎችን ጨምሮ 75 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈው ሕንፃ የተመረቀው ግንባታው ከተጀመረ ከ15ዓመታት በኋላ በዕለተ ሐሙስ፣ በወርሃ ጥር፣ በቀን 27/1957 ዓ.ም. ልክ ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ:: የህንፃ ግንባታው ይካሄድ የነበረው ቀንና ሌሊት ነው::
በተለይ ህንፃው ሊጠናቀቅ አካባቢ አንድ ሺህ 900 ሰዎች ተሳትፈዋል፤ አንድ ሺህ 300 ሰዎች ቀን ሲሰሩ ይውሉ እንደነበርም ይነገራል:: 600 ሰዎች ደግሞ ሌሊት በግንባታው ላይ ይሳተፉ እንደነበር ከታሪክ ለማወቅ ተችሏል:: በአሁኑ ወቅት ማዘጋጃ ቤቱ ለተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ በሚል በእድሳት ላይ ይገኛል::
ይህ ፅሁፍ የቀረበው በምንጭነት ‹‹አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሊኒየም›› በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ሚሊኒየም ጽህፈት ቤት በ2000 ዓ.ም ባሳተመው መጽሄት የማዘጋጃ ቤቱን ታሪክ “የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አመሰራረትና አገልግሎት” በሚል ርዕስ ካሰፈረው ፅሁፍ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድረ ገፅ ላይ ስለከተማዋ ማዘጋጃ ቤት አመሰራረት የሰፈረውን ፅሁፍ ለመቃኘት በመሞከር ነው::
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
አስቴር ኤልያስ