“እውነተኛ መሪ ሀገሩ ፈተና በገጠመው ሰዓት ሕዝቡ ከዚያ ፈተና እንዲወጣ ለማገዝ ‘ምን ማድረግ አለብኝ?’ ሲል ራሱን ይጠይቃል።አድርባዩ ደግሞ ‘ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ እንዴት ራሴን ከፍ ለማድረግና የምሻውን ሁሉ ለመጨበጥ እችላለሁ?’ ብሎ ይብሰለሰላል ፡፡” ኃይለጊዮርጊስ ማሞ የተባሉ የፍ – ት – ሕ አምደኛ በቅርቡ” የፖለቲከኛ በየዓይነቱ ! “ በሚል ካደረሱን ዘመኑን የዋጀ መጣጥፋቸው የቃረምሁት ነው።
በዚህ ጥቅስ ማንጠሪያነት የሁለት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እርስ በርሱ የሚጣረስ ወለፈንዲ መግለጫን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሰሞነኛ ተጨባጭና ትክክለኛን ውሳኔ መሳ ለመሳ እንመለከታለን ፡፡ በተያዘው ዓመት ሊካሄዱ ቀን ከተቆረጠላቸው የ70 ሀገራት ምርጫዎች ባለፈው አንድ ወር ብቻ በመላው ዓለም በ40 ሀገራትና ግዛቶች ሊካሄዱ የነበሩ 60 ብሔራዊ ፣ የከተማና አካባቢያዊ ምርጫዎች በኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ስጋት የተነሳ ወደ ሌላ ጊዜ መራዘማቸውን International Institute for Democracy and Electoral Assistance (International IDEA) በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ በድህረ ገጹ ይፋ አድርጓል።ከእነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያ ፣ ናይጄሪያ ፣ ዚምባቡዌ ፣ ኬንያ ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ጋምቢያና ቱኒዚያ ከአህጉራችን ይገኙበታል።
በአሜሪካ 25 ግዛቶች የዴሞክራት እጩዎችንና የማሟያ ምርጫዎችን ፣ በአውሮፓ 16 ሀገር አቀፍ ፣ የፓርላማ ፣ የከተሞችን ምርጫና ሕዝበ ውሳኔዎች ፣ በእስያ 8 የብሔራዊ ፣ የአካባቢና የማሟያ ምርጫዎች ፣ በአውስትራሊያ ፣ በሰለሞን ደሴቶችና ፓፑዋ ኒው ጊኒ እንደዚሁ ተራዝመዋል። በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ተጨማሪ 30 ሀገራትና ክልሎች ምርጫቸውን ያራዝማሉ ተብሎ ይጠበቃል።የየሀገራቱ ውሳኔ ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ህይወት የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ የሚያስረግጥ ነው፡፡
እንዲህ ባለ ፈታኝ ጊዜ የመሪዎች የመወሰን አቅም ፣ አስተባብሮ የመምራት ክህሎትና ጥበብ እንዲሁም የመሪዎች ማንነት የሚፈተነው ከፖለቲካ ጥቅም በላይ ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት ለማዳን በሰጡት ስትራቴጅካዊና ታክቲካዊ አመራር ነው።እዚህ ላይ የአሜሪካንን መሪ ከሲንጋፖርና ከደቡብ ኮርያ ያነጣጥሯል።እንደ ዶናልድ ትራም ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት አሲዞ ፣ ረክዞ ፖለቲካዊ ቁማር የሚቆምር ከሆነ እርሱ መሪ ሳይሆን የፖለቲካ ሱቅ በደረቴ ነው።አቶ ኃይለጊዮርጊስ ፣ “ሀገር የመምራትን ስልጣን የጨበጠ በመንግስትነትም ዙፋን ላይ የተቀመጠ መሪ እውነተኛ ማንነቱ የሚገለጠው ፈተና ወይም ውድቀት ከፊቱ የተደቀነ ጊዜ ነው ።“ፀሐፊው እንዳሉት በዚህ አስተዛዛቢና ፈታኝ ሰዓት የለውጥ ኃይሉም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ የወርቅ ሚዛን እየተመዘኑ ነው።ምንም እንኳ የምዘናውን ውጤት ለማወቅ ጊዜው ገና ቢሆንም ከአሁኑ ከሚዛኑ ለመጉደል ዳር ዳር የሚሉን እየተመለከትን ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ሁለት “እህትማማች” ፓርቲዎች በዚህ የጭንቅ የጥብ ቀን ክቡር ከሆነው የሰው ልጅ ህይወት ይልቅ ፓርቲን፣ ፖለቲካዊ ሒሳብ ማወራረድንና ነጥብ ማስቆጠርን ያስቀደሙ ፤ ጭር ሲል ፖለቲከኛ የሆኑ ፤ መንግስትን የማገት አባዜ የተጠናወታቸው የሚያስመስል መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የፕሬዝዳንታዊ ታሪክ አጥኝዎችና የህይወት ታሪክ ጸሐፍት ዶሪዝ ከርነስ እና ጆን ሜቻም አንድ መሪ ሊያሟላቸው ከሚገቡ ዋና ዋና ባህሪያት አንዱ የሕዝብን ችግር እንደ ራስ ማየት ፣ መረዳት ነው ይላሉ።ሰሞኑን የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦ ፌ ኮ) ያወጡት መግለጫ ፣ ሕዝብ በዚህ ፈታኝ ፣ አስፈሪና አስጨናቂ ሰዓት በሞትና በህይወት መካከል በቀጭን ገመድ እየተራመደ እያለ ፖለቲካና ምርጫ አጀንዳዎቹ ሊሆኑ እንደማይችሉ እያወቁ መግለጫ መስጠት ለምን አስፈለጋቸው ? ይሄን መረዳትስ እንዴት ተሳናቸው!?
ፍርሃቱን ፣ ጭንቀቱንና ችግሩን እንደ ራሳቸው ችግር አይቶ መጋራትና የመፍትሔው አካል መሆን ሲገባቸው ፤ ሕዝብ ያለምንም የጎሳ ፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ልዩነት እጅ ለእጅ ተያይዞ በአንድነት ቆሞ ወረርሽኙን ለመመከት እየተረባረበ ባለበት ፤ የሕክምና ባለሙያዎች ፣ የወገን አለኝታ የሆኑ ዜጎችና የካቢኔ አባላት ለህይወታቸው ሳይሰስቱ 24 ሰዓት ያለ እረፍት እየሰሩ ባሉበት በሀገሪቱ ሰማይ የፍርሀት ዳመና በዳመነበት እንዲህ ያለ ትኩረት አስቀያሽ መግለጫ ማውጣት ምን ይሉታል!? የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጋቢትና በሚያዚያ ማጠናቀቅ ከሚገባው ዋና ዋና ስራዎች መካከል የመራጮች ምዝገባ ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ፣ ሥልጠናና ሥምሪት ፣ የመራጮች ትምህርት ፣ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ሥርጭትና የመሳሰሉት ተግባራት በኮቪድ19 ወረርሽኝ የተነሳ ተስተጓጉለዋል።
በምርጫው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተጣለበት ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት እያደረገ ሳለ ካለፉት ሶስት ወራት በፊት በዓለማችን ከሶስት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ በሀገራችን የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሰውን ልጅ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ፣ የመንግስትንና የግል ተቋማትን አሰራር እንደገና በመበየኑ ሌሎች ተቋማት እንዳደረጉት ምርጫ ቦርድም ስልጣኑን ተጠቅሞ የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ ሰርዟል።የሌሎች ሀገራት ምርጫ ቦርዶች እንዳደረጉት በነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ቀን እንዲሁም የቅድመና ድህረ ምርጫ ጊዜ ሰሌዳዎችን ሰርዟል፡፡
የቀድሞው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ፣ “ ኮቪድ19 እና ምርጫ “ በሚል ርዕስ ፍ-ት-ሕ መፅሔት ላይ ባስነበቡን መጣጥፍ ፣ “ …’ በዝናብ እንዴት አርገን ቀስቅሰን ነው ምርጫ የምንወዳደረው ? ‘ ሲሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች ፤ “ በኮቪድ19 የተነሳ የምርጫ ሰሌዳ ሲሰረዝ ለምን ይብሰከሰካሉ ሲሉ በዘወርዋራ ይሞግታሉ ።“ኦሎምፒክን ያህል ግዙፍና ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ዓለም አቀፍ ሁነት ተራዝሞ እያለ ፤ ምን አልባት ለብጥብጥ ሰበብ ሊሆን የሚችል ምርጫ ቢራዘም ለምን ይገርመናል ? “ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ይሁንና ኦነግና ኦፌኮ ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ምርጫ የመሰረዝ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም ሲሉ በጋራ መግለጫቸው ነቅፈው ፤ መልሰው “ ኮቪድ-19 በምርጫ 2012 እቅድና የጊዜ ሰሌዳ አፈጻጸም ላይ ተግዳሮቶችን ደቅኖ ቦርዱን እየተፈታተነ መሆኑን” እንረዳለን ፣ “ በማለት ይውጋህንና ይማርህን ያዛንቃሉ ። ነገር ግን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ “ የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን።ውሃ ቀጠናቸውም ፣ “ ቦርዱ እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ኦነግና ኦፌኮ የተገኙበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ አዘጋጅቶ ምክክር ተደርጎ እንደነበር ጠቅሶ ፤ በስብሰባው መጨረሻ ላይ ሌላ ዙር ውይይት እንደሚኖር ቢገለጽም ይህ ሳይሆን ውሳኔ ላይ መድረሱ አግባብ አይደለም ።
“ የሚል ነው።በዘወርዋራ ያለ እኛ ቡራኬ ምን ሲደረግ ማለታቸው ነው ።ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተቀበሉትን እነ ኦነግ ምርጫ ቦርድ ወደ ውሳኔ “ የሄደበት መንገድ “ ለምን በአቋራጭ ሆነ አይነት ያዙኝ ልቀቁኝን ምን አመጣው !? መንገድ መሪስ ማን አደረጋቸው ። ላለፉት 25 እና 50 ዓመታት የተጓዙበትን የዝንጀሮ መንገድ መቼ አጣነውና።
ወረርሽኙን ለመከላከል ማህበራዊ ፈቀቅታ social distancing በታወጀበት ፤ ምዕመናን ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በቤት እንዲያካሂዱ ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች በራቸውን በዘጉበት ፣ ዜጎች ከአሁኑ ቁጥር የሚልቅ ቀሳ ወይም ውሽባ (ኳራንቲን) ይገባሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ፣ የመንግስት ሰራተኞች ስራቸውን በቤታቸው እንዲሰሩ ፣ ሀገር አቋራጭና ሌሎች ማህበራዊ ፈቀቅታን የሚጥሱ መጓጓዣዎች በታገዱበት ፣ ሰባት ክልሎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አከልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ፤ ምርጫ ቦርድ ለዛውም ለሁለተኛ ጊዜ ሰብስቦ ፍቃዳችንን ሳያገኝ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን መሰረዙ ትክክል አይደለም ማለት እስከ ግማሽ ክፍለ ዘመን ከዘለቀ የፖለቲካ ፓርቲ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ልሒቅ ለዛውም በዚህ አስጨናቂ ጊዜ የሚጠበቅ አይደለም ።
ሲሆን ሲሆን ምን እናግዝ እንዴት እንቀናጅ ባሉ። ለዛውም የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ሊያስቀይር የማይችል ፤ ሌላ አስማተኛ አማራጭ ያላቸው ይመስል ።ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን የመወሰን ስልጣኑን ተጠቅሞ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረዙ ከጠረጴዛው ያገኘው ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አምኖ መቀበል እንጂ በሰበብ አስባቡ ማንገራገር አይገባም።በዚህ ድባብ የሚካሄድ ምርጫስ እንዴት ግልፅ ፣ ነጻ ፣ ፍትሐዊና አሳታፊ ሊሆን ይችላል ? እንደ አለመታደል ሆኖ እንጂ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ተፎካካሪ ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳደረጉት የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ይራዘም የሚለውን ጥያቄ ቀድመው ማቅረብ የነበረባቸው እነሱ መሆን ሲገባቸው።
በሰሞነኛ መግለጫቸውም ሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባሳዩን ምግባር አያድርገውና አሸንፈው ስልጣን ቢይዙ እንዴት እንደሚገዙን ፣ ከሀገርና ከሕዝብ ይልቅ ማንን እንደሚያስቀድሙ አበክረን የደረሰንበትን መደምደሚያ የሚያጸና ሆኖ አግኝተነዋል።
ለዚህ ነው ከድርጅት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን ፣ ሀገርንና ሕዝብን ከሚያስቀድም መዳረሻ (ፌርማታ) ሳይደርሱ ባቡሩ ሲንገጫገጭ ሀዲዱን የሳተ መስሎአቸው ዘለው ወረዱ የምንለው።የተቃርንዎች ከማንነት ዛጎል (ሼል) ባሻገር ገዝፈው ከፍታው ላይ የሚታዩትን ኢትዮጵያን ፣ ኢትዮጵያዊነትን ፣ ኩሩውን ሕዝባችንና ርዕያችንን አሻግረን እየተመለከትን ጉዞአችንን ቀጥለናል።ሙኀዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረትና የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሸል ኦባማ “አትውረዱ!” እንዳሉት አንወርድም፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከዚህ መቅሰፍት ይጠብቅ ! አሜን ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 29/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com