የኮሪዶር ልማት- ትናንትን በነበር ዛሬን በተግባር

የዛሬን አያድርገውና ከዛሬ ሃምሳ ዓመታት በፊት ሀገራችን በአፍሪካ መዲናነት እንዳትመረጥ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ፣ ይሁንታቸውን የነፈጉ ሀገራት ቁጥር በርካታ ነበር። የዛኔ ለተቃውሟቸው ዋነኛ ሰበብ የነበረው ‹‹ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋና መቀመጫነት የሚያበቃ ንጹህና ምቹ የሚባል ገጽታ የላትም›› የሚል ነበር፡፡

በወቅቱ ሀገራችን ለአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ካበረከተችው አይረሴ ውለታ አንፃር በዚህ ስያሜ መታወቋ ለኢትዮጵያውያን በእጅጉ የሚያስቆጭ ነበር። እንዲያም ሆኖ አጋጣሚው በጥንካሬ ለለውጥ የሚያነሳሳ ብርታት መሆኑ አልቀረም። በየጊዜው ስሟን እያጠለሹ የመቀመጫ መንበሯን ለመንጠቅ የሚጋፉትን ሁሉ በጥበብ ለማሸነፍ ሃይልን ፈጥሯልና፡፡

አዲስ አበባ በብዙ ፈተናዎች መሃል ክፉ ስያሜዋን ፍቃ ለማጥፋት የለውጥ ዕድገቷን ስታሳይ ቆይታለች። በዚህም ታሪክና ማንነቷን ጠብቃ ለመራመድ ተደናቅፋ አታውቅም። ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ እያስመዘገበችው ያለው ዕድገት ግን እጅን በአፍ የሚያስጭን ተአምር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህች የአፍሪካ ቀደምት መዲና ፣ እንደ ስሟ ልኬታ መራመድ ከጀመረች ወዲህ ከሠለጠኑት ሀገራት ጎራ የሚያሰልፋትን ሥልጣኔ እየተላበሰች ለመሆኑ በድፍረት መናገር ይቻላል።

አሁን አዲስ አበባ አሮጌ ልብሷን ቀዳ ጥላለች። የቆሸሸ ማንነቷን አራግፋም በማይታመን ገጽታ ተውባለች። ትናንት ለእይታ የሚከብዱ ሥፍራዎች ዛሬ በ ‹‹ነበር›› እየተወሱ ነው። ቀድሞ ለአፍንጫ የማይመቸው ክፉ ሽታ አሁን በመልካም መዓዛ ተተክቷል። ውብና ጽዱ ሥፍራዎች፣ ለመንገደኞች ማረፊያ ተመችተው ብዙሃንን መማረክ ይዘዋል። የመንገድ ላይ መብራቶች፣ የፈጠራ ጥበብ ያረፈባቸው መዳረሻዎች የመዲናዋ ፀጋዎች ናቸው፡፡

ዛሬ የኮሪዶር ልማቱ በደረሰባቸው ጥጎች ሁሉ ሕይወት የሚያድሰውን አየር የሚተነፍሱ በርክተዋል። በነዚህ ቦታዎች አሮጌው በአዲስ፣ ጨለማው በብርሃን እየተተካ ነው። የአዲስ ኑሮ ብስራት፣ የመልካም ሕይወት ጅማሬን የተላበሱ ነፍሶች ነገን ባሻገር እያዩ ተስፋን መሰነቅ ይዘዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪዶር ልማት መካሄድ ከጀመረ ጥቂት ጊዜያት ተቆጥረዋል። ይህ አጋጣሚ የፈጠረው ታላቅ ለውጥም የቀድሞ ገጽታዋን በመለወጥ ለከተማዋ አዲስ ማንነትን አላብሷል። ትናንት ለአፍሪካ መዲናነት ‹‹አትበጅም›› የተባለችው ‹‹ኢትዮጵያ›› የመቻሏን ትንሣዔ በገሀድ እያሳየች ነው፡፡

ዛሬ በአዲስ አበባ ድንቅ ውበት የሚደመሙ፣ የፈጠነ ለውጧን ሊደርሱበት አልተቻላቸውም። በርካቶችም ለቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ መሆኗን በማየት አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ አሁናዊ ማንነት የኋላ ታሪኳን የመሻር እውነታን ይዟል ። የመኪና መንገድ፣ የሳይክልና የእግረኞች ጎዳና የሥልጣኔ ማሳያዎች መሆን ከጀመሩ ሰንብተዋል። የመበረታት፣ የስልክና ኤሌክትሪክ ዘርጋታዎች ከተማዋን የሚመጥኑ ናቸው፡፡

የኮሪዶር ልማቱ ሰው ተኮር እንደመሆኑ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው። ለነዋሪው ምቹ የሚባል አካባቢን በመፍጠርም መሠረታዊ የሚባሉ አስገዳጅ ሁኔታዎችን አሟልቷል። ይህ የልማት እንቅስቃሴ በከተማዋ ብቻ አልተገደበም። ጥንካሬው ለክልል ከተሞች ጭምር ተጋብቷል፡፡

አዲስ አበባ ልክ እንደስሟ አዲስ ሆና ታብብ ዘንድ የቀን ተሌት ልማቱ አልተቋረጠም። በኮሪዶር ልማት ዘመን በፒያሳና ካዛንቺስ ጎዳናዎች እንቅልፍ ይሉት ተረት ሆኗል። ክንደ ብርቱ ባለሙያዎች፣ ከግንባታ ማሽኖችና ከባድ ተሽከርካሪዎች ጋር በሥራ ትጋት ያነጋሉ። ይህ እውነት አዲሷን አዲስ አበባ በጥረት አዋልዶ ደማቅ ብርሃን ፈንጥቋል፡፡

ዛሬ የትናንት ማንነቷን በእጅጉ የለወጠችው ከተማ መገለጫዋ ውበት፣ ዕድገትና ልማት ሆኗል። ከአፍሪካ መቀመጫነት አልፎ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በደማቅ ዐሻራዋ አትማለች። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህ የኮሪዶር ግንባታ በርካታ እውነታዎችን እየጠቆመን ነው። ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አይተንበታል። በጥረት የሚመዘገበውን ታላቅ ውጤትና ከውጤቱ የሚታፈሰውን ድንቅ በረከትም እንዲሁ፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ለውጥ ጋር ተያይዞ የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓት ተለውጧል። የመኪኖች ተለምዷዊ አካሄድም በሕግ አግባብ ተወስኗል። አብሮን የቆየው የቆሻሻ አወጋገድ ልማዳችን ሕገ- ደንብ ተበጅቶለት መተግበር ከያዘ ሰንብቷል።

ትናንት በየጥጋጥጉ በመጸዳጃነት የሚታወቁ ሥፍራዎች ዛሬ ገጽታቸው በውበት ተተክቷል። ቀድሞ በቆሻሻ ማከማቻነት የሚለዩ ቦታዎች አሁን ውብ መናፈሻ ሆነው ስያሜያቸው የስፖርት ማዘወተሪያ፣ የህጻናት መጫወቻ፣ የሕዝብ መናፈሻና የአረንጓዴ ፓርኮች መገኛ በሚል ተለውጧል፡፡

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ የተከፈተው አዲሱ የካዛንቺዝ ውብ ከተማ የኮሪዶር ልማቱ ድንቅ ማሳያ ሆኖ ተመዝግቧል። የካዛንቺዝ ኮሪዶር ልማት በከተማዋ እስካሁን ከተገነቡት ሁሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ የተለየ መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡

ቀድሞ በካዛንቺዝና አካባቢዋ የነበረው ገጽታ አሁን ላይ ዕውን ከሆነው አዲስ ከተማ ጋር ሲነጻጸር ብዙዎች እንደሚሉት ‹‹እጅን በአፍ›› በሚያስጭን አድናቆት ይገለጻል። ካዛንቺዝ ቀደምት ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በርካታ ነዋሪዎችን አቅፋ ያዘች ዕድሜ ጠገብ መኖሪያ ናት። ከዚህ አኗኗር ጋር ተያይዞም ፍጹም ለኑሮ የማይመቹ፣ ለጤናማ ኑሮ የማይታሰቡ፣ በምስቅልቅልና ፈታኝ ማንነት ውስጥ የነበሩ በርካታ ወገኖች ሕይወት ይገለጽባታል፡፡

ካዛንቺዝ በውስጧ ስንጥቃት አቅፋ ከያዘቻቸው ነዋሪዎቿ ባሻገር ዕድሜ በበላቸው የንግድ ቤቶቿ ጭምር ትታወቃለች። አብዛኞቹ ለበርካታ ዓመታት ዕድሳት ያላገኛቸው፣ የቀለም ጠብታ ያልነካቸው ጎስቋላ መኖሪያዎች እንደሆኑም በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡

እነሆ! የካዛንቺዝን ትንሣዔ ያወጀው የኮሪዶር ልማት አካባቢውን ባገኘው ጊዜ ታሪክ ሊለወጥ ፣ የነበረ ማንነት ሊቀየር ግድ ሆነ። መልከ ጥፉ ገጽታ ፣ ለዓይን የማይበጅ፣ ለአፍንጫ የማይመች፣ አሮጌ ማንነት ተለውጦ በአዲስ ገጽታ ተተካ። መንገዶች ተቀይሰው፣ ሹልክታዎች ተገናኝተው ሰፊው ጎዳና ተዘረጋ። ደማቅ ብርሃን፣ ሥፍራውን አስውቦም በመልካም እይታ ተገለጠ፡፡

የኮሪዶር ልማቱ ካዛንቺዝን ቀዳሚ የዘመናዊነት ማሳያ በመሆን ይገለጻል። አስፈላጊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶች መሟላታቸው ሰው ተኮር የሆነውን አገልግሎት እውን ለማድረግ የሚያስችል ማሳያ ሆኖ ተረጋግጧል፡፡

በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትስስር ገጻቸው ላይ እንደገለጹት ይህ ውጤት ‹‹ሰው የድካሙንና የላቡን ፍሬ ይበላል ይሉት አባባልን በትክከል የሚገልጽ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የአካባቢው ቀዳሚ ገጽታ ከአሁናዊ መልኩ ሲነጻጸር ጋር ፍጹም የተራራቀ ነው። ለእይታና ለኑሮ መገለጫዎችም ምቹ የሚባል ሥፍራ አልነበረም፡፡

በኮሪዶር ልማቱ ሁለተኛ ዙር ላይ በአመርቂ ውጤት የተመዘገበው የካዛንቺስ አዲስ ከተማ ለሌሎች አካባቢዎች ጭምር በቀዳሚ አርአያነት የሚጠቀስ ነው። የሥፍራው ማሳያዎች በጥንካሬ አንድነት እውን መሆናቸውን ይቀጥላሉና፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You