ለተሻለ የግብርና ምርት የተሻለ ዝግጅት

በሀገራችን የክረምቱ ወቅት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ይጀምራል። ይህ ጊዜ ለአርሶ አደሮችና ለመላው ኢትዮጵያዊ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የምግብ ዋስትናን የምናረጋግጥበት የሰብል ዘር የሚዘራበት ወቅት ነው። የሚቀጥለው መከር ስኬት አሁን በተወሰደው በቂ ርምጃና ዝግጅት ላይ የተመሰረተ ነው።

አርሶ አደሩና መንግሥት ቀድመው ከተዘጋጁ ጥሩ ውጤት ልንጠብቅ እንችላለን። በእርግጥ ከግብርና ሚኒስቴር የሚወጡ መግለጫዎች ይህንን ያመለክታሉ። እንደተባለው ሳይሆን ቀርቶ በተቃራኒው በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ከቀረ የሚገኘው ውጤት እንደ ሀገርም እንደ ግለለሰብም ከፍተኛ ኪሳራ የሚያስከትል ነው።

ለግብርና ዘርፍ (ለእርሻ) ስኬታማነት ዋናውና ቀዳሚው ቁልፍ ጉዳይ ቅድመ ዝግጅት ነው። እንደሚታወቀው ብዙ ነገሮች በግብርና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንደ ዝናብ፣ ዘር፣ አፈር፣ መሳሪያ እና እውቀት በበቂ ሁኔታ ካልተቀናጁ ውጤታማ መሆን አይታሰብም። በዚህ ረገድ አርሶ አደሮች ዝግጁ ከሆኑ እና የሚያስፈልጋቸውን ካገኙ ሰብላቸውን በጊዜ በመዝራት በቂ እህል መሰብሰብ ይችላሉ።

ይህ ካልሆነ ግን ብዙ ጣጣ ተከትሎ ይመጣል። የምግብ ምርት ይቀንሳል፤ የኑሮ ውድነት ይባባሳል፤ ሀገሪቱ ከሌላ ቦታ ምግብ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለመግዛት ትገደዳለች። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ክፉኛ ይጎዳል፤ ድህነትን ያባብሳል። ለዚህም ነው ሁሉም ሰው የዝናብ ወቅት ከመጀመሩ በፊት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት በዚህ ፅሁፍ ላይ ለማሳሰብ የወደድኩት።

ለግብርና ወቅት ቅድመ ዝግጅት መንግሥት ትልቅ ሚና አለው። እንደሚታወቀው ጥራት ያለው ዘር ለማግኘት ገበሬዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የተሻሻሉ የምርጥ ዘሮች በፍጥነት ውጤታማ ያደርጋሉ፣ ከፍተኛ ምርት ይሰጣሉ እንዲሁም በሽታን መቋቋም ይችላሉ። በመሆኑም ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በየግዜው ማቅረብ ይኖርበታል።

ለምሳሌ እንደ ሕንድ እና ኬንያ ባሉ በብዙ አገሮች መንግሥታት የተሻለ ዘር በማቅረብ ገበሬዎችን ይደግፋሉ። እነዚህ ሀገሮች በሰብል ምርታማነት ላይ መሻሻሎችን ማሳየታቸው ለእኛም ትልቅ መነሳሳት ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያም ይህንን አርአያ ልትከተል የምትችለው የተሻሻሉ ዘሮችን በየክልሉ በአርሶ አደሮች በቀላሉ እንዲደርሱና እንዲገኙ በማድረግ ነው።

ማዳበሪያ አቅርቦት ሌላው የስኬታማ የእርሻ ውጤት አስፈላጊ አካል ነው። እንደሚታወቀው ሰብሎች ለማደግ የሚያስፈልጋቸውን ንጥረ ምግቦች ማዳበሪያ ይሰጣል። ገበሬዎች በማሳዎቻቸው ላይ በቂ ማዳበሪያ በማይጠቀሙበት ጊዜ ሰብላቸው ደካማ ይሆናል። እንደ ሕንድ ያሉ አንዳንድ ሀገሮች ድጎማ በመስጠት ይህንን ችግር ይፈታሉ። ኢትዮጵያም ይህንኑ እያደረገች ነው። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት አነስተኛ ገበሬዎችን ለመርዳት ተጨማሪ አማራጮችን መከተል አለባት።

በሌላ በኩል አርሶ አደሮችም ስልጠና ያስፈልጋቸዋል ብዬ አምናለሁ። አብዛኛው የኢትዮጵያ ገበሬ አሁንም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ባሕላዊ ዘዴዎችን ይጠቀማል። በእርግጥ እነዚህ ዘዴዎች ቀደም ብለው ይሠሩ ነበር። ነገር ግን ዛሬ ላይ ዓለም እየተለወጠ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰብል ተባዮች እና የአፈር ባሕሪ መቀያየር ያለው አዳዲስ ፈተናዎች እየደቀኑ ነው።

ለዚህ ነው ገበሬዎች አዲስ እውቀት ያስፈልጋቸዋል የምለው። ለምሳሌ በቅርቡ ያነበብኩት መጣጥፍ እንደሚያሳየው በኬንያ የስልጠና መርሃ ግብሮች ገበሬዎች የሰብል ምርታቸውን እንዲያሳድጉ እና ብክነትን እንዲቀንሱ ረድቷቸዋል። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በዘመናዊ የግብርና ቴክኒኮች ላይ ስልጠና ከወሰዱ እነሱም እንዲሁ ማድረግ እንደሚችሉ አምናለሁ።

ሌላው ቅድመ ዝግጅት የሚፈልገውና ትልቅ ችግር የመንገዶች እና የመጋዘን ችግር ነው። ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ በፍጥነት ወደ ገበያ መውሰድ አለበት። ነገር ግን የትራንስፖርትና የመጓጓዣ መንገዶች በቂ አለመሆን ሰብሎች ከመድረሳቸው በፊት እንዲበላሹ ምክንያት ይሆናል።

በተጨማሪም ብዙ አርሶ አደሮች ትክክለኛ የማከማቻ ቦታ ስለሌላቸው አዝመራቸው ይበላሻል። መንግሥት የገጠር መንገዶችን ካስተካከለ እና ማከማቻ ማዕከላት ካቋቋመ ችግሩን ሊቀንሰው ይችላል ብዬ አስባለሁ። ለዚህ ሩዋንዳ ጥሩ ምሳሌ ነች። አገሪቱ በመንገድ እና በማከማቻዎች ላይ ኢንቨስት አድርጋ በብክነት የሚደርስን የምግብ ኪሳራ ቀንሳለች፤ ኢትዮጵያም እንዲሁ ማድረግ ትችላለች።

አርሶ አደሮች የክረምት ወቅት ከመግባቱ አስቀድሞ የመዘጋጀት ኃላፊነት አለባቸው። ዝናቡ ከመድረሱ በፊት መሬታቸውን አስቀድመው ማዘጋጀት አለባቸው። መሬቱን ማረስ እና ማጽዳት ጊዜ ይወስዳል። ቀድሞ መሬት ማዘጋጀት ሰብሎች በተሻለ ሁኔታ እንዲበቅሉ እና በመዘግየት የሚመጣ ኪሳራን ለመቀነስ ያግዛል።

በእርግጥ ለታታሪው የኢትዮጵያ ገበሬ ይሄ የሚነገር አይደለም። ሆኖም አርሶ አደሮችም ለአካባቢያቸው የአየር ፀባይ የሚመጥን ተገቢውን ሰብል መምረጥ አለባቸው ብዬ አስባለሁ። እንደሚታወቀው አንዳንድ ሰብሎች ተጨማሪ ዝናብ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ በደረቅ ቦታዎች በደንብ ያድጋሉ። ቀደም ብሎ መዘጋጀት የግብርና ባለሙያዎችና ገበሬዎች እነዚህን ውሳኔዎች እንዲወስኑ እንዲረዱ ያስችላቸዋል።

በዓለማችን ላይ ውሃ አሳሳቢነቱ እየጨመረ ነው። በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ዝናብ ዘግይቶ ሊመጣ ወይም ቀደም ብሎ ሊቆም ይችላል። ይህ ሰብሎችን አደጋ ላይ ይጥላል። ለዚህ ነው አርሶ አደሮች እንደ ኩሬ መቆፈር ወይም የማጠራቀሚያ ታንኮችን መጠቀም ያሉ ውሃን ለመቆጠብ የሚያስችሉ መንገዶችን መፈለግ የሚኖርባቸው።

ለዚህ ደግሞ ቅድመ ዝግጅት ይጠይቃል። ውሃ በጣም ውስን በሆነባቸው እንደ እስራኤል ባሉ አገሮች ገበሬዎች የሚንጠባጠብ መስኖ ይጠቀማሉ። ይህ ዘዴ ውሃን ቀስ ብሎ እና በቀጥታ ወደ ተክሎች ሥሮች ማቅረብ የሚያስችል ነው። ስልቱ ውሃን ይቆጥባል እና የተሻለ ውጤትንም ያስገኛል። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችም ከዚህ በመማር ውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ምክረ ሀሳብ አለኝ።

ሌላው ቅድመ ዝግጅት የሚጠይቀው ጉዳይ ትብብር ነው። አብሮ መሥራት ከኪሳራና ከአላስፈላጊ የጉልበት ወጪ ያድናል። ለምሳሌ አርሶ አደሮች በቡድን ወይም በሕብረት ሥራ ሲሰሩ ዘር እና መሳሪያ በጅምላ እና በዝቅተኛ ዋጋ መከራየት ወይም መግዛት ይችላሉ። እንዲሁም ሰብላቸውን በጋራ በመሸጥ የተሻለ ዋጋ ማግኘት ይችላሉ።

የሕብረት ሥራ ማሕበራትም አርሶ አደሮች እርስ በርሳቸው እንዲማሩ እድል ይሰጣቸዋል። ጥሩ ተሞክሮና ሀሳቦችን ማጋራት እንዲሁም የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት መተባበራቸው ትልቅ ሚና አለው። በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሕብረት ሥራ ማሕበራት አነስተኛ ገበሬዎችን ውጤታማ አድርገዋል፤ በሀገራችን አንዳንድ ቦታዎችም ተሞክሮው ውጤት ያሳየ ነው።

ሌላው ቴክኖሎጂ ነው። እንደሚታወቀው ቴክኖሎጂ ግብርናን ከማዘመን አንስቶ ብዙ ጠቀሜታ አለው። በአንዳንድ ሀገሮች አርሶ አደሮች ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘትና የግብርና ሥራቸውን ለማዘመን ሞባይል ስልኮችን ይጠቀማሉ። የአየር ሁኔታ ትንበያ፣ የአዝርት አይነት ለመምረጥና የገበያ ዋጋ ምክር ያገኛሉ። ይህም የተሻሉ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

ለምሳሌ በሕንድ እና ናይጄሪያ የሞባይል መተግበሪያዎች ለአርሶ አደሮች የተለመደ መሳሪያ መሆኑን አውቃለሁ። ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲያገኙ ኢትዮጵያ እነዚህን አይነት ዲጂታል መሳሪያዎች ማስተዋወቅ አለባት። ለዚህ ደግሞ ቅድመ ዝግጅት ወሳኝ ነው።

የኢትዮጵያን እድገት ለማረጋገገጥ የግብርና ሥርዓቷን ማዘመን አለባት። ይህ ማለት የተሻሉ የግብርና መሳሪያዎችን፣ እውቀትና ምርምርን ያጣመሩ ሀሳቦችን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ማለት ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ገበሬ እስካሁን ድረስ ለእርሻ ሥራ የእጅ መሳሪያዎች ወይም እንስሳት ይጠቀማል፤ ይህ ለእድገት አዝጋሚ እና አስቸጋሪ ነው።

እንደ ትራክተሮች እና የሰብል አጫጅ ማሽኖች መጠቀም ፈጣን እና ቀላል ነው። በመሆኑም የተጀመረውን ግብርናውን በሜካናይዜሽን የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በባንግላዲሽ ውስጥ በአነስተኛ ማሳ ላይ የሚያርሱ ገበሬዎች ተሰባስበው በአንድነት ማሽኖችን ይከራያሉ። ኢትዮጵያም ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ አርሶ አደሮች ዘመናዊ መሣሪያዎችን በከፍተኛ ወጪ መግዛት ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ ተመሳሳይ አሰራር ብትጀምር መልካም ይሆናል እላለሁ።

ከላይ እንዳነሳሁት የአየር ንብረት ለውጥ እየተባባሰ በመጣ ቁጥር አርሶ አደሮች አዳዲስ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። አንዳንድ አካባቢዎች በጣም ብዙ ዝናብ ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ በጣም ትንሽ ያገኛሉ። አዳዲስ ሰብል አውዳሚ ነፍሳት እና በሽታዎችም እየታዩ ነው። እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት አርሶ አደሮች ስማርት ግብርና የሚባለውን ዓለም አቀፍ የግብርና ዘዴ መለማመድ አለባቸው።

ይህ ማለት በተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ ውጤታማ የሚሆኑ ትክክለኛውን ሰብል መምረጥ፣ የተሻሉ ስልቶችን መጠቀም እና ሀብታቸውን በጥበብ መቆጣጠር የሚችሉበት እውቀት ማዳበር አለባቸው። እነዚህ ዘዴዎች አርሶ አደሮች መሬታቸውን ከጉዳት እንዲከላከሉ እና በአስቸጋሪ ጊዜያትም ብዙ የሰብል ምርት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።

ሌላው የቅድመ ዝግጅት አካል መሆን አለበት ብዬ የማምነው፤ ሳይንሳዊ ምርምር ነው። የግብርና ምርምር ለገበሬዎች ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች መሥራት ይችላሉ። የምርምር ማዕከላት የአፈር፣ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ፍላጎቶችን በማጥናት የተሻሉ ዘሮችን እና የእርሻ ዘዴዎችን መፍጠር አለባቸው።

ብራዚል ይህን እያደረገች በመሆኑ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ ምግብ አምራቾች አገራት አንዷ ሆናለች። ኢትዮጵያ የምርምር ማዕከላት አሏት ነገር ግን ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። መንግሥትና ማሕበረሰቡ በምርምር ላይ ኢንቨስት ካደረገ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንችላለን።

ብዙ አርሶ አደሮች ገንዘብ ስለሌላቸው ዘር፣ ማዳበሪያ ወይም መሣሪያ መግዛት አይችሉም። በዚህ ምክንያት የፋይናንስ አቅርቦት በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው የክረምት ወቅት ሲመጣ ባንኮች ለገበሬዎች ልዩ ብድር መስጠት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አለባቸው የምለው።

ለምሳሌ በጋና አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ከሸጡ በኋላ የሚከፍሉት ብድር ያገኛሉ። ይህ ያለምንም ጭንቀት እንዲያርሱ ይረዳቸዋል። ኢትዮጵያም ይህንን ሥርዓት መሞከር ትችላለች። አርሶ አደሮች የበለጠ እንዲያድጉ እና በራስ የመተማመን ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።

እንደሚታወቀው በማንኛውም ሰዓት ያልታሰበ የተፈጥሮ አደጋ ችግር ሊያጋጥም ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አርሶ አደሮች ሁሉንም ነገር በትክክል አድርገውና በቅድሚያ ተዘጋጅተው እንኳን ነገሮች የተሳሳተ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ። ድርቅ፣ ጎርፍ ወይም ያልተጠበቁ የሰብል አውዳሚ ተባዮች የአንድ ወቅትን ሙሉ ጥረት ሊያበላሹ ይችላሉ። ለዚህም ነው የሰብል ኢንሹራንስ አስፈላጊ እንደሆነ የማስበው። ይህ ስልት አርሶ አደሮችን ሁሉንም ሀብታቸውን በአንድ ግዜ ከማጣት ይጠብቃል።

ከሌሎች አገሮች ምን መማር እንችላለን? እንደሚታወቀው በሕንድ መንግሥት ለገበሬዎች በዘር እና በማዳበሪያ ፕሮግራሞች ይደግፋል። እንዲሁም ለገበሬዎች ምክር ለመስጠት ዲጂታል መሳሪያዎችን ይጠቀማል። በብራዚል መንግሥት በግብርና ምርምር እና አዲስ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ያደርጋል፤ አሁን ሀገሪቱ ብዙ ምግብ ወደ ውጭ ትልካለች።

በእስራኤል ገበሬዎች ውሃን በዘመናዊ የመስኖ ዘዴዎች ይቆጥባሉ፤ በበረሃ ውስጥ እንኳን ምግብ ያመርታሉ። በኔዘርላንድስ ገበሬዎች ምግብን በብቃት ለማምረት የግሪን ሃውስ እና ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፤ ሀገሪቱ ትንሽ ብትሆንም በዓለም ላይ ትልቅ ምግብ ላኪ ነች።

እነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ መለወጥ እንደሚቻል ያሳያሉ። ነገር ግን ትብብርን እና ጠንካራ ሥራን ይጠይቃል። ይህንን ስኬት አርሶ አደሮች ብቻቸውን ሊያመጡት አይችሉም። የመንግሥትን፣ የንግድ ድርጅቶችን፣ ሳይንቲስቶችን እና የመገናኛ ብዙሀንን ሳይቀር ድጋፍ ይፈልጋሉ። ትምህርት ቤቶች ጭምር ከስር ከመሰረቱ ለውጥ ለማምጣት ልጆችን ስለ ግብርና ማስተማር አለባቸው። የአካባቢ መሪዎች ማሕበረሰባቸውን ማበረታታት አለባቸው። የተሻለ የግብርና ሥርዓት ግንባታ ላይ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።

ኢትዮጵያ ምርታማ መሬት፣ ታታሪ ሕዝብ፣ ሺህ ዘመናትን የዘለቀ የግብርና ታሪክ አላት። እነዚህን ሀብቶች አቀናጅቶ ውጤት ለማምጣት ሀገሪቱ ደፋር እርምጃዎችን መውሰድ አለባት ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው ኋላ ቀር ዘዴዎች በፍጥነት ማሻሻል ነው። ሌላው አዳዲስ ሀሳቦች መቀበል የሚችል ማሕበረሰብ መፍጠር ነው። የግብርና የወደፊት ዕጣ ዛሬ በእነዚህ ነጥቦች ላይ በምንወስደው እርምጃ ላይ ይወሰናል፤ ጊዜው አሁን ነው።

የዝናብ ወቅት በቅርቡ ይመጣል። አርሶ አደሮች መዘጋጀት አለባቸው። መንግሥትም እንዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ስለ ሰብል ምርት ብቻ አይደለም ስለ መጪው ትውልድ ሕይወት፣ ጤና እና የሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ ጭምር ነው። በየዓመቱ በዚህ ልክ ከሰራን ኢትዮጵያ ራሷን መመገብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገሮችን ጭምር መመገብ ትችላለች። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሚሳካው አስቀድሞ በመዘጋጀት ነው። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You