
በቻይናውያን ቱሪስቶች ልብ ውስጥ አፍሪካ “ምስጢራዊ አሕጉር” እንደሆነች ተደርጋ የምትወሰድ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን የበርካታ ቻይናውያን ቱሪስቶች መዳረሻ በመሆን ላይ ትገኛለች። ከጥንታዊና ባህላዊ ቦታዎች እስከ ውብ የተፈጥሮ መልክዓ ምድሮች፣ ከዱር እንስሳት ፍልሰት እስከ ዘመናዊ የከተማ መልክዓ ምድሮች አፍሪካ በዓይነቱ ልዩ በሆነ ውበትዋ ቻይናውያንን እየሳበች ነው።
የቻይናውያን አፍሪካን የመጎብኘት ፍላጎት መጨመር የወቅቱ የቻይና አፍሪካ ግንኙነት ማደግ የፈጠረው እንደሆነ ይታመናል። ይህም ቻይናውያን አፍሪካን እንዲጎበኙ የተሻለ እድል የፈጠረ ሲሆን ፤ በቻይና ቱሪዝም አድናቂዎች ላይ ያሳደረው ተጽእኖም ከፍ ያለ ነው።
በተለይም የ “ሰቅ እና ጎዳና (Belt and Road)” ተነሳሽነት ጅማሬና ትግበራ በቻይና እና በአፍሪካ መካከል የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እተጫወተ ነው:: በዚህ ረገድ በቻይና ሚዲያ ዘገባዎች ውስጥ የአፍሪካን የዕድገት እውነታ እና የቻይና አፍሪካን የትብብር ስኬቶች በተደጋጋሚ በመቅረባቸው የአፍሪካን “ተደራሽነት” በማጉላት የቱሪስቶችን ቀልብ ለመሳብ አስችለዋል::
ይህም የ”ሰቅ እና ጎዳና (Belt and Road)” ተነሳሽነት የአፍሪካን ባህላዊ እሴቶች በማስተዋወቅም ረገድም ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው። ለአብነት ያህል “አፍሪካ” የተሰኘው የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶችና ፀጋዎች የሚተርከው ዘጋቢ ፊልም በቻይና ሴንትራል ቴሌቪዥን (CCTV) ዌብ ሳይት ላይ በሚሊዮኖች ተደጋግሞ ተለቋል ። በሳን ማኦ (Sanmao) የተፃፈው የሰሃራ ታሪክ እና የቢ ሹሚን (Bi Shumin) “ሰላሳ ሺህ ሊ በአፍሪካ” ወጣት የባህል አድናቂዎችን ቡድኖች ቀልብ መሳቡን ቀጥሏል።
የፎቶግራፍ ባለሙያው ሉኦ ሆንግ (Luo Hong) የአፍሪካ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ከአሥር ዓመታት በላይ እየታየ ዘልቋል። በቻይና ታዋቂ በሆኑት ሲያኦሆንሹ (Xiaohongshu) በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያ እና በቲክቶክ ላይ ሰዎች የሚጋሩት የአፍሪካ የጉዞ ልምድ፣ እንዲሁም በአንዳንድ ፊልሞች እና የጨዋታዎች ምርቶች ላይ ያሉ አፍሪካዊ ዐሻራዎች የቻይናውያን የቱሪዝም አፍቃሪዎችን በተለይም የወጣቶችን ቀልብ በመግዛት አፍሪካን የመጎብኘት ፍላጎታቸውን እያበረታታና እያነሳሳ ይገኛል።
የአፍሪካን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማነቃቃትና ቻይናውያን ጎብኚዎች እንዲጎርፉ ለማድረግ አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ ግድ ይላል:: ይኸውም ቻይናውያን ቱሪስቶች በአፍሪካ ምን ማየት ይፈልጋሉ? የሚለው ነው:: እዚህ ላይ መሳጭ የሆኑት የአፍሪካ ተፈጥሮአዊ መስህቦችና ድንቃ ድንቆች በመጀመሪያ የሚጠቀሱ ናቸው።
በታንዛኒያ የሚገኘው የሴሬንጌቲ ሳር ምድር (Serengeti Grassland)፣ በናሚቢያ የሚገኘው የሱስሊ ቀይ በረሃ (Susli Red Desert)፣ በኢትዮጵያ የሚገኘው የኤርታሌ እሳተ ገሞራና መልክዓ ምድር፣ የቪክቶሪያ ፏፏቴ እና በማዳጋስካር የሚገኙ የባኦባብ (baobab) ዛፎች ቻይናውያን ቱሪስቶች በማህበራዊ ድረ-ገጻቸው ላይ ሊለጥፏቸው የሚፈልጓቸው ውብ ገጽታዎች ናቸው።
በሁለተኛ ደረጃ አፍሪካ የሰው ልጅ መገኛና የሥልጣኔ መፍለቂያ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ቻይናውያን ቱሪስቶች ከአፍሪካ ሥልጣኔ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶች ጋር በስፋት ለመተዋወቅ ይጓጓሉ:: ከአፍሪካ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች አኳያ የግብፅ ፒራሚዶች እና ስፊኒክስ (sphinx) ለቻይናውያን ቱሪስቶች ታዋቂ የጉብኝት ቦታዎች ሆነው ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ድንቅ የተፈጥሮ መስህቦች፣ የጥንታዊቷ የሞሮኮ ፌዝ (Fez) ከተማ የባህል አድናቂዎችን ቀልብ ይገዛሉ። በተጨማሪም ቻይናውያን ቱሪስቶች ስለ ማሳይ ሰዎች መንደር ለማወቅ ከመጓጓት ባሻገር አፍሪካ እያካሄደች ያለችውን የዘመናዊነት ሂደት ከሥፍራው በመገኘት ለመለማመድም ይፈልጋሉ።
እ.ኤ.አ. በ2021 በዳካር የተካሄደው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ጉባዔ እና በ2024 የተካሄደው በቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ጉባዔ ቱሪዝምን ወደ ትብብር የድርጊት መርሃ ግብር በማካተት ተጨማሪ የአፍሪካ ሀገራት የቻይና ቱሪስቶች መዳረሻ እንዲሆኑ በንቃት ያስተዋወቀ ነበር። አንዳንድ ሀገራት ተግባራዊ ያደረጉት የነፃ ቪዛ እና የኤሌክትሮኒክ ቪዛ ፖሊሲም የቻይናውያን ቱሪስቶች ወደ አፍሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ አፋጥኗል።
ቻይናውያን ጎብኚዎች በረጅም ርቀት ምክንያት የሚፈጠረውን ከፍተኛ ወጪ እና የአካባቢውን የአቀባበል ሁኔታ አሳሳቢነት ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ጉዳይ ነው:: በተለይ በሰፊውን ማህበረሰብ ክፍል የሚያካትት በመካከለኛ ክፍል ደረጃ ያሉት ቻይናውያን ወደ አፍሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ ለመወሰን የመንገዶችን ምቾት እና ወጪ ቆጣቢነትን ሙሉ በሙሉ ከግምት ውስጥ ያስገባሉ። ስለዚህ ከጉዞ ኤጀንሲዎች በኩል የሚመቻቹን የቡድን ጉብኝቶች እና ፓኬጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተመራጭ እያደረጉ መጥተዋል።
ባለንበት በዚህ በግሎባላይዜሽን ዘመን ሰዎች የተለያዩ ልምዶችን ለመቅሰምና ለመከታተል ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆንና ቻይናውያን ቱሪስቶችን የአፍሪካን መስህብነት መረዳት በዋናነት ትኩረታቸውን ወደ አፍሪካ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው:: ከመጀመሪያዎቹ አሳሾች እስከ ዛሬዎቹ ዋነኛ ተጓዦች፣ ቻይናውያን ቱሪስቶች የአፍሪካን እሴት እንደገና እየገለጹት ይገኛሉ።
ለአፍሪካ ሀገራት የቱሪዝም ልማትን እና የሥነ- ምህዳር ጥበቃን እንዴት ማመጣጠን እንደሚችሉ እና “የቻይና አፍሪካን ወዳጅነት” ወደ ገበያ ተጠቃሚነት እንዴት መቀየር እንደሚችሉ በመገንዘብ ከቱሪዝሙ መስክ ተጠቃሚ ለመሆን ይህን ታሪካዊ እድል መጠቀም ቁልፍ ጉዳይ ይሆናል።
ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያም ቻይናውያን ጎብኚዎችን በብዛት ለመሳብ በዋናነት በሀገር ውስጥ ሰላምና ፀጥታን ማስፈንና ለጎብኚዎች ከስጋት ነፃ ሀገር መሆን ቁልፍ ጉዳይ ይሆናል:: በሌላ በኩል ከቪዛ፣ ከክፍያ፣ ከጉዞ ታሪፍ ጋር የተያያዙ ችግሮችን መፍታት፣ ጎብኚዎች ጉብኝታቸውን እንዲያራዝሙ የሚንቀሳቀሱባቸውንና የሚያድሩባቸውን ቦታዎች ምቹ ማድረግ እና የመሳሰሉትን ሥራዎች አስቀድሞ መሥራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ነው::
ጉብኝት ባህላቸው የሆነውን የቻይናውያን ጎብኚዎችን ቀልብ ለመግዛት መቻል ለሚታሰበው የተፋጠነ የኢኮኖሚ ልማት እና የተሻሻለ ሕይወት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝቦ ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ መስህቦች ለማስተዋወቅ መጣር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን አዳዲስ እድሎችን ያመጣል የሚል እምነት አለን።
(ፕሮፌሰር ሊ ሆን ፈንግ እና ዶ/ር ስንቅነሽ አጣለ፣ የአፍሪካ ጥናት ተቋም፣ ቤጂንግ የውጪ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ፣ ቻይና)
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም