ወዳጅ መልካም ካልሆነ ሁነት ውስጥ ይመልሳል አይደል? እንድትመልሱኝ ፈለኩ። ያለሁት የማልፈልገው ፈፅሞም ሊሆን ይችላል ብዬ የማልገምተው ቅዥት ውስጥ ነኝ። ወዳጆቼ ቀስቅሱኝ። መቀስቀስ እፈልጋለሁ፤ የማየው፤ የምሰማው፤ ሰመመናዊ ያልተገራ፤ ህልም ውስጥ መቆየቱን አልፈልገውም። ደግሞም እርግጠኛ ነኝ:: እናንተ ከዚህ መልካም ያልሆነ ህልም ከተዘበራረቀው ቅዠቴ ታወጡኛላችሁ፤ ትቀሰቅሱኛላችሁ። አዎ ከዚህ ቀስቅሱኝ በሰመመን እየተናጥኩ ነው።
እንዴት ይሄን ልቀበል እችላለሁ? ስለዚህ እስክትቀሰቅሱኝ የማየውን እየተናገርኩ ልቀጥል ነው። እንዴት ነበር ወደ መደቤ ያቀናሁት ትዝ አለኝ፤ የተደራረበ ስራ አሰልችቶኝ፤ ጉልበቴ ዝሎ፤ አካሌ ተዳክሞ፤ እቤት እንደገባሁ ሶፋ ላይ ልብሴን እንኳን ሳልቀይር ቦርሳዬን አስቀምጬ ጋደም ባልኩበት እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ። መነሳት እፈልጋለሁ፤ ግን አቅም አጣሁ። በተዳከመ መንፈስ በተሰላቸ ስሜት በሰመመን እየቃተትኩ ነው። የሰሞኑ ሀሳብ ተደራርቦ አድክሞኝ፤ ሁሉ ሸክም ሆኖውብኛል መሰል የሆነ ምስል እፊቴ ድቅን ብሎ ታየኝ።
ሌላ አለም ውስጥ ገባሁ፤ ህልም ላይ ነኝ። ግን ይሄን ህልም የማልፈልገው ስለሆነ መንቃት ፈለኩ ቀስቅሱኛ። በርቀት ይመስለኛል ወሬ እየሰማሁ። ወሬዎቹ የተሳኩ የተሰደሩና መልዕክታቸው ግልፅ የሆነ ነው። ሰው አለመሆኑ ገባኝ ሚዲያዎች ከየ አቅጣጫው የሰሙትን ያሰማሉ፤ ያዩትን በምስክርነት ያቀርባሉ። ሀገራዊ መገናኛ ብዙኋን ካለም ጋር አንድ ያደረጋቸው ጉዳይ ላይ ተጠምደዋል ርዕሰ ጉዳያቸው አንድ ሆኖ ጉዳዩን በተለያየ መልኩ ያቀርቡታል። ጉዳዩ ምንድነው? በደንብ ለማድመጥ ሞከርኩ። ጆሮዬ የወሬው ምንነት ለመስመት ይበልጥ ተለጠጠ።
በሰመመን ውስጥ አዲስ ተከሰተ ባሉት ወረርሽኝ የሰዎች ተጎዱ አለም ተናወጠች የሰው ልጅ ህይወት እንደዘበት ረገፈ ይላሉ። የሰው ልጅ ህልፈት፤ የሰው ልጆች እልቂት እየዘገቡ ነው። ኮሮና ወይም ኮቪድ 19 የሚባል ስያሜ ተሰጠው ወይ ቅዠት ? እንዴ በ21 ክፍለ ዘመን ዓለም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥግ ደረስኩ ዓለም በእጄ ናትና አሾራታለሁ ባለበት በዚህ ዘመን የምን ወረርሽኝ? የምን እልቂት ነው። ኧረ ወገን የምን ቅዤት ነው? ቀስቅሱኝ የማይመስል ነገር እያሳየኝ ነው ይሄን መስማት ምን ይሉታል። ቅዤት ወደ ኋላ ይመልሳል እንዴ? አቦ ቀስቅሱኝ! አልፈልግም፤ አልወደድኩትማ። ከአንዱ ጣቢያ ጎልቶ የሚሰማኝ ድምፅ ከቻይና ተነስቶ እዚያ የተወሰኑ ሰዎችን አርግፎ በማለፍ አውሮፓ ላይ ጉልበቱን አጠንክሮ በእጥፍ ሰዎችን መጨረሱን፤ ወደ ሀያሏ ምድር አሜሪካ ደረቱን ገልብጦ የገባው ወረርሽኝ ሀያሏን አገር ምስቅልቅሏን እንዳወጣ ይተርካል። ቀስቅሱኝ አለም በዚህ ገፅታዋ አላውቃትማ ወደ ድሮ ማንነትዋ መመለስ እፈልጋለሁ። እየተንፏቀቅኩ ተነሳሁ፤ የመገናኛ ብዙኃኑ ዜና ከሰዎች ለማረጋገጥ።
ወደ አንድ ሱቅ አጠገብ ቀረብኩ ሱቁ በር ላይ የነበሩት ሰዎች ገለል አሉ። ምንድነው ብዬ ስጠጋቸው የሚሸሹኝ? እንዴ! ምንድነው ግራ የተጋባ ነገር። እራሴን ተጠራጠርኩት፤ ምንድነው የተፈጠረው አካባቢውን ቃኘው ከወትሮ በተለየ ጭር ብሏል። ሱቁን ትቼ ሄድኩ። አልፈ ትንሽ አለፍ ብዬ አንዱ ወዳጄ ሳይ ፈገግ ብዬ እየሆነ ስላለው ነገር ለመጠየቅ ተጠጋሁት። ጎንበስ ብዬ እጄን ለሰላምታ ዘረጋሁለት፤ እሱ በተቃራኒው ኮስተር ብሎ እጁን ሰበሰበ። እየገላመጠኝ “ታሾፋለህ እንዴ ልትገለኝ ነው?” አለኝ። እህ! ማለት እኔ አንተን ልገድል ምንድነው ነገሩ? ግራ እንደተጋባሁ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ምን ተፈጥሮ ነው ሰው ምን ሆኖ ይሆን? ቴሌቪዥኔን ከፍቼ ሁኔታውን ለማወቅ ጓጉቼ አይኔን መስኮቱ ላይ አማተርኩ፤ እስካሁን ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መጠቃታቸውን ከ 50 ሺህ በላይ ደግሞ መሞታቸውን ያወራል። ለዚያውም ሞቱ የከፋው ሞት ብርቅ በሆነባቸው ብዙ ኖረው መጨረሻ ላይ በሚሞቱት ሀገር ላይ በሰለጠነው አለም ላይ ሞት መበርከቱ ይናገራል።
እንዴት ይሄ ሊሆን ይችላል፤ የምር ማመን ይከብዳል። ዓለምን እያመሰ ያለው ነገር ምንድነው? ኮሮና… ኮሮና ምንድነው? ገዳይ ተላላፊ በቫይረስ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ አሁን አለምን እያሸበረ ያለ በሽታ። እኮ በ21 ክፍለ ዘመን ! አለም ሁሉ ነገር ተቆጣጠርኩ ባለበት ሰው የሚጨርስ ደቃቅ ፍጥረት ለዚያውም ነብስ የሌለው እንዴት ?ኧረ ተው! ምን አለ ከዚህ ቅዤት ብትቀሰቅሱኝ ግን? ቀስቅሱኛ እባካችሁ። ስልኬን አውጥቼ የቅርብ ጓደኛዬ ጋር ደወልኩ ሀሎ ሰላም ነው? ጓደኛዬ አልኩት ”እ.. ሰላም ነው? ነው ያልከው ?” ሲለኝ እህ ምንድነው ጓደኛዬ ሰላም አይደለህም እንዴ? የምን ሰላም፤ ከኮሮና በፊት የነበረው ሰላም ነው ? ወይስ ያ ሰላም የሚባለው ጓደኛህን ነው የምትጠይቀኝ” ሲለኝ ይበልጥ ተደናበርኩ። “ባክህ የምን ሰላም የት አለና በፍረሃት እየተናጥኩ ነው ቤቴን ዘግቼ ነው ያለሁት ሰላም የሚባል የለም።
” የሚል ሌላ ዓረፍተ ነገር አከለልኝ። ምን ሆነህብኝ ነው ጓደኛዬ ምንድነው ነገሩ ልምጣ እቤት? የኔ ጥያቄ ነበር ”ኧረ በህግ አምላክ… ወዴት ነው የምትመጣው?” እራሴኑ ጠየቀኝ። “አንተ ቤት ነዋ” የኔ የኔ ምላሽ ነበር። “በል እዚያው ወዳጄ ኮሮና ተነጠሉ ብሏል እዚያ ባለህበት አትምጣ” ብሎ ስልኩን ጠረቀመብኝ። ሰው ሚዲያው ምን ሆኖ ነው? ቀስቅሱ የምለው ለዚህ እኮ ነው። አቦ ቀስቅሱኝ! የምን ቅዤት ነው? እኔ ቅዤት አልወድም ቀስቅሱኝ። እየተንፈራገጥኩ ነው የሆነ ሰመመን ውስጥ ሆኜ የሰዎችን ውክቢያ እመለከታለሁ።
ይሄን ሁሉ ልመናዬ ሰምቶ የቀሰቀሰኝ ሰው ግን አንድም የለም ምንድነው ምን ውስጥ ገብቼ ነው። ስተኛ እንዲህ አይነት ጉዳይ ፈፅሞ አልገጠመኝም አሁን ምን ተፈጥሮ ነው የአለም ሁኔታዋ የተለዋወጠው። ድሮ ሰላም ካላልኳቸው የሚያኮርፉኝ አሁን እጄን ስዘረጋ ገዳዬ የሚሉኝ ለምንድነው ?ድሮ እቤቴ ካልመጣህ በሞቴ የሚሉኝ ጓደኞቼ ዛሬ ጨንቆኝ ልምጣ ወይ ስል ስልክ የሚዘጉብኝ ለምንድነው? ቤቴ ሰው ሞልቶ አየው የነበረው ሰው የጠፋበት ለምድነው? ኧረ ይሄን ቅዤት አልወደድኩትም ቀስቅሱኝ እባካችሁ አንቁኝ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2012
ተገኝ ብሩ