በዚች ሀገር የ3 ዓመት ጥንታዊ የሀገረ መንግስት ታሪክ እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንግስት በኃይለኛ የውቅያኖስ ማዕበል (ሱናሚ) መካከል እንደምትቀዝፍ ታንኳ ከየአቅጣጫው የተናወጠ፣ የተፈተነ የለም ማለት እችላለሁ::ይህ የሆነው በእሳቸው ወይም በለውጡ አፈጻጸም ድክመት አለመሆኑን ሊሰመርበት ይገባል::ምንም እንኳ ለውጡን ተከትሎ ለከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች የለውጡ ኃይል በልካቸው የመመዘን ውስንነት እንዳለበት ቢያምንም::በዚህ አጋጣሚ በአንድም በሌላ በኩል ለለውጡ ስኬትም ሆነ ውድቀት የሁላችንም አዎንታዊና አሉታዊ ተሳትፎ እንዳለበት ልብ ማለት ያሻል::ወደ ተነሳሁበት ሀሳብ ስመለስ፣ በቀደሙት አገዛዞች የሕዝቡ ጥያቄዎችና ተቃርኖዎች ከ100 ዓመታት በላይ በስዩመ እግዚአብሔርነት፣ በኃይልና በአፈሙዝ ታምቀውና ታፍነው ሲብላሉ እንዲኖሩ በመደረጉ፤ ከለውጡ ማግስት አንስቶ ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ብርግድ ብሎ በመከፈቱና ሌሎች ” አስቻይ ” ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ልዩነቶች ሲጋጋሉ ኖረው መጦዛቸውና ከፍታቸው ላይ መድረሳቸው በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት እዚህም እዚያም ግጭቶች እንደ ሰደድ እሳት ሊዛመቱ ችለዋል፡፡
የለውጥ ኃይሉ ገጥሞት የነበረው ተግዳሮትና ፈተና በሀገረ መንግስት ታሪካችን የሚስተካከለው የለም በሚል የሰነዘርሁት ግምገማ በጥናትና በምርምር ስለአልተረጋገጠ ሙሉ በሙሉ በእርግጠኝነት ድምዳሜ ላይ እንደማያደርስ በወጉ እረዳለሁ ::የአብይን መንግስት አይደለም ከአክሱም በፊት ከነበሩት መንግስታት ራሱን የአክሱም ዘመነ መንግስት ከቀደሙት ጥንታዊ መንግስታት ጋር ማነጻጸር የተገቢት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል::በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ አይደለም ከእነ አክሱም ጋር ከትላንቱ ቀዳማይ ትህነግ / ኢህአዴግ ጋር ማነጻጸር የአመክኖ’ዊነትና የተጠየቃዊነት ሙግት ከማስነሳቱ ባሻገር ከአንጻራዊ ንጽጽር መርህ ጋርም ሊጣረስ ይችላል::የዘመነ ጓዴነት (ኮንቴምፓራሪስ) ጥያቄ ማስነሳቱም አይቀርም::የለውጥ ኃይሉን ማነጻጸር ካስፈለገ በተመሳሳይ ወቅት እና አውድ ላይ ካለ አቻ መንግስት ጋር እንጂ ከቀደመው መንግስት ጋር ማነጻጸር ዘመነ ጓዴነት ስለማይኖረው ንፅፅሩ የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡
ይሁንና ታሪክ ካለፈው ስኬታችንና ውድቀታችን የምንማርበት፤መልካሙን የምናዘልቅበት መጥፎው እንዳይደገም አበክረን የምንጠነቀቅበት ስለሆነ፤ በኃይለኛ ማዕበል ከወዲህ ወዲያ እየተላጋ በአሳር በመከራ 2ኛ ዓመቱን ሰሞኑን ስለደፈነው ለውጥ ከቀደሙት ጋር መንግስታት ጋር አጮልቄ እያስተያየሁ የተረዳሁትንና የተገነዘብሁት ያህል ዘካሪ ሀሳብ አነሳሳለሁ፡፡
እነ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ዶ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ፣ ወዘተ ከሀገር ውስጥ፤ ከ300 ዓመታት በላይ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ያደረጉ የውጭ ሀገራት ተመራማሪዎች፤ ከቅርቦቹ ኮንቲ ሮዚኒ እና ሪቻርድ ፓንክረስት ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን በስራዎቻቸው መሰክረዋል:: አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮኣና ማንቴል – ኒየችኮ ” የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያ እስከ አሁን ዘመን ” በሚል በአለማየሁ አበበ በተተረጎመ መጽሐፋቸው፣ ኢትዮጵያ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያላት በተለይ ከ1 ሺህ 700 ዓመታት ወዲህ ደግሞ በደረጀ ጹሑፍ የተደገፈ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ዋቢ ማስረጃዎችን ጠቅሰው አትተዋል ::በዚህ ጥንታዊ የታሪክ ሒደት ሀገሪቱ በብዙ ውጣውረዶችና ውስብስብ ፈተናዎች ማለፏን ሁሉም የታሪክ ተመራማሪዎች ይስማማሉ::የሀገራችን ታሪክ ከካም ይመዘዝ ከኩሽ ወይም ከኢትዮጲስ ይሁን ከሳባ አልያም ከባዚን፣ ከአብርሀ ወ አጽብሀ ይሁን ከድልነአድ፣ ከመራ ተክለ ሀይማኖት ይሁን እስከ ይትባረክ፣ ከባዲት ቢነት ማያ ይሁን ከአብዳላህ ኢብን፣ ከይኩኖ አምላክ ይሁን እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣ ከደርግ ይሁን እስከ ቀዳማይ ትህነግ /ኢህአዴግ፤ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው በየዘመናዎች የፈተናው ክብደትና ውስብስብነት ይለያይ ይሆናል እንጂ በፈተና ማለፋቸው ሁሉንም ያመሳስላቸዋል::የአጼ ቴዎድሮስ፣ የአጼ ዩሐንስን፣ የአጼ ምኒልክና የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ አገዛዞች የገጠሟቸውን ፈተናዎች በአንድ በኩል፤ የደርግና የቀደማይ ትህነግ /ኢህአዴግ አገዛዞችን በሌላ በኩል መለስ ብለን በስሱ እንመለከት፡፡
የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ” A History Of Modern Ethiopia ,1855 – 1991 ” በተሰኘው ድንቅ መፅሐፍ ላይ ደጃች ካሳ ሀይሉ / ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ / የዘመነ መሳፍንት የስልጣን ሽኩቻንና የቱርኮች ወረራ በመመከት የዘመናዊ ኢትዮጵያ ጥንስስ እንደጣሉ ያወሳሉ::ስለሀገራቸው ያላቸው ሕልም መልካም ቢሆንም እውን ለማድረግ የሄዱበት መንገድ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሊቋቋሙት የማይችሉት ባላንጣዎችን አስነስቶባቸዋል::እንደ ክሩሜ ያሉ አጥኝዎች አፄ ቴዎድሮስን የኢትዮጵያ ስልጣኔ ፋና ወጊ አርገው ቢያዯቸውም ይህ ግምገማው እስካከሁን ድረስ አወዛጋቢ መሆኑን ፕሮፌሰር ባህሩ ያወሳሉ::በጀኔራል ናፒር እና በሌሎች የውጭ ኃይሎች እገዛ በእግራቸው የተተኩት ደጃች ምርጫ /አፄ ዩሐንስ የሀገሪቱን አንድነት ለማረጋገጥ የተለየ ስልት መከተልን መርጠው ነበር:: ከፈላጭ ቆራጭነት ይልቅ ለየአካባቢው መሳፍንትና ነገስታት እውቅና በመስጠት ራሳቸውን ርዕሰ መኳንንት፣ ንጉሰ ነገስት አድርገዋል:: ሆኖም ተቃውሞው አልቀረላቸውም::ግብጾችን ጉንደትና ጉራ ላይ ድል ቢነሱም በደርቡሾች ወረራ ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ ሆነው መተማ ላይ ወድቀዋል::በተፈጠረላቸው ምቹ ታሪካዊ አጋጣሚና ጉልህ በነበረው ከባቢያዊ ተፅዕኗቸው በአፄ ዩሐንስ ዙፋን የተተከቱ አፄ ምኒልክ በቀደሟቸው ነገስታት ተጀምሮ የነበረውን የአንድ ሀገረ መንግስት ግንባታ ከማሳካታቸው ባሻገር ግዛታቸውን ማስፋፋት ችለዋል:: አንጸባራቂው የአድዋ ድል ደግሞ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተቀባይነታቸውን በእጅጉ ጨምሮታል::ሀገራችንን ከዘመናዊ አስተዳደርና ከስልጣኔ ጋር በማስተዋወቅ ረገድም የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል::እስካሁን ባየናቸው አገዛዞችም ሆነ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣ በደርግ በመጨረሻም በቀዳማዊ ትህነግ/ኢህአዴግ፣ በሁሉም ውስጣዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶባቸዋል፤ የውጭ ወራሪም፣ ጥቃትም ተሰንዝሮባቸዋል::ሆኖም እንዳለፉት ሁለት መራርና ፈታኝ መላ ሀገሪቱን ዳር እሰከ ዳር ለለየለት ብተና እና የእርስ በርስ ግጭት እስከ መዳረግ የሚደርሱ አልነበሩም፡፡
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሪነት የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት በነበሩ ሶስት ዓመታትና ከለውጡ ማግስት ደግሞ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ያህል በመላ ሀገሪቱ ነግሰው የነበሩ ጎሳንና ማንነትን መሰረት አድርገው የተቀሰቀሱ ግጭቶች፣ የሕግ የበላይነት ጥሰቶች፣ ሚሊዮኖች ከቀያቸው ያፈናቀሉ ጥቃቶች፣ ሀገር በቀል ሽብሮች፣ መንግስታዊ መዋቅሮችን ሽባ የማድረግ ደባዎች፣ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች፣ ስራ አጥነት፣ የፌዴራል መንግስቱን በሀሰት የማሳጣት ዘመቻዎች፣ በለውጥ ኃይሉ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ የተፈጠረ ልዩነት፣ ወዘተ. ዛሬ ላይ ሆነን ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት በመግቢያዬ ላይ ለመግለፅ እንደሞከርሁት ሀገራችን በታሪኳ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይ ለውጡ ከባተ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት የገጠማትን አይነት ፈተና በታሪኳ ገጥሟት አያውቅም ማለት እችላለሁ::ለዚህ ነው እነዚህን ፈተኛ የለውጥ ሁለት ዓመታት በንፋስ ሊጠፉ በተቃረቡና በሚስለመለሙ ሁለት ሻማዎች ወክዬ የአብይ ሁለት ሻማዎች ያልኋቸው::ያው ሻማዎቹን የአብይ ብላቸውም በውስጠ ታዋቂ መላው የለውጥ ኃይል፣ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ አለን::ሆኖም ከንፋሱ ጋር እየታገሉ በሚሰጡት የብርሀን ፀዳል ጨለማውን አሸንፈው ወገግ ማለታቸው አልቀርም፡፡
የሚስለመለሙት እነዚህ ሁለት ሻማዎች በድቅድቅ ጨለማው ብርሀን ፈንጥቀው ተስፋን አሰንቀውናል::በሀገሪቱ ታሪክ ታይተው ተሰምተው የማያውቁ፤ እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ለውጦች፣ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ሆነዋል::ከእነዚህ ውስጥ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት መደረጉ፣ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሰላም የኖቤል አሸናፊና ተሸላሚ መሆናቸው ሀገሪቱ ለምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተደማሪ ጉልበት መሆኑ፤ ፖለቲካዊ ምህዳሩን የሚያሰፉ፣ ሀሳብን የመግለፅና የሚዲያ ነጻነትን የሚያረጋገጡ፣ ለነጻና ገለልተኛ የዳኝነትና የፍትሕ ተቋማት ግንባታ መሰረት የሚጥሉ፤ እንዲሁም ነጻ የምርጫ ቦርድና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መቋቋሙ፤ አፋኝ የነበሩ ሕጎች መሻሻል፣ ለውጡን ተቋማዊ የሚያደርጉ፣ ሰላምን እርቅን የሚያጠናክሩ፣ የውጭ ግንኙነቱን የሚያሻሽሉ፣ የኢኮኖሚውን ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያግዙ ሀገር በቀል ማሻሻያዎች መደረጋቸው፤ ለዚህ ማሻሻያ መተግበሪያም በተሰራ ውጤታማ የፋይናንስ ዲፕሎማሲ ከአለምማቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ከልማት አጋሮች ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ፤ በኢፌዴሪ ካቢኔ የሴቶችን ተሳትፎ ወደ 50 በመቶ ማደጉ፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በሀቀኛ ውስጠ ዴሞክራሲ የተካ፤ በአባልና በአጋር ድርጅቶች መካከል የነበረን ቀይ መጋረጃ የቀደደ፤ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን የሚያጠና እና የእርቀ ሰላም ኮሚሽኖችን ማቋቋም፤ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው የሰላም ሚኒስቴር መቋቋም፤ ዜጋ ተኮር የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ በመተግበሩ በአረብ ሀገራት በእስር ላይ የነበሩ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማስፈታት ከመቻሉ ባሻገር ከሀገራቱ ጋር ሕጋዊ የስራ ስምምነት መፈራረም መቻሉ፤ ስንዴንና ዘይትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ጥረት መደረጉ፤ የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች መጀመር፤ ኢትዮጵያ የራሷን ሳታላይት ማምጠቋ፤ በአረንጓዴ አሻራ ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከል፤ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት፤ የአንድነት ፓርክ እውን መሆን፤ የእንጦጦ ፓርክ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ፤ በተለይ የታላቁ ህዳሴን ግድብ ከውድቀት መታደግ በመቻሉ የግድቡ አፈጻጸም 72 በመቶ መድረሱ፤ በድምሳሳው የዛሬው መሰረት ለነገው ጉልላት መነሻ ነው ፡፡
እንደ መውጫ
ወራሪ፣ ወረርሽኝና ቸነፈር፣ ድርቅና እርሀብ፣ በአጠቃላይ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ሀገራዊ አደጋዎች ሲከሰቱ ጠብቀን አንድ እንደምንሆነው በሰላምና በጥሩ ጊዜም አንድ መሆን ብንችል እንደ አጀማመራችን የት በደረስን::ባለፉት ጥቂት ወራት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ከግብፅ ጋር ውጥረት ሲከሰት፤ ካለፉት ሶስት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ የኖቨል ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን መግባቱ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ያለ ምንም ልዩነት በሚያስገርም ሁኔታ ሀገራዊ አንድነት ተፈጥሯል::የጎሳን፣ የሀይማኖትንና የፓለቲካ አመለካከት ድንበሮችን የተሻገሩ ሀቀኛውን ኢትዮጵያዊነትን የገለጡ፤ በአድናቆት እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ልግስናዎችን፣ መተሳሰቦችን፣ ደግነቶችን፣ እርህራሄዎችንና በጎነቶችን ከመመልከታችን ባሻገር ካለፉት አምስት ዓመታት በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ተፈጥረው የነበሩ ሰው ሰራሽ ግጭቶችና ቀውሶች በአጠቃላይ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው ውጥረት እንደ አረፋ ከስመዋል::ይህ ለለውጡ ኃይሎችም፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሆነ ለሀገር ወዳድ ዜጎች ከሰማይ የወረደ መና ነው ማለት ይቻላል::ሁሉም ቆም ብሎ ትንፋሽ ለመውሰድ እና ቀልቡን ለመመለስ ጊዜ ያገኛል:: በተለይ ዜጎች ይህን አስገዳጅ አጋጣሚ በመጠቀም በጥሞና ስለሀገራቸው ሰላምና ስለአንድነት የሚያንሰላስሉበት፤ ያለፉትን አምስት ዓመታት ከነበራቸው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተዋጾ አኳያ ራሳቸውን በመመርመር ተሳትፏቸው አውንታዊ ከነበር አጠናክሮ ለመቀጠል አሉታዊ ከነበረ ለማቃናት በቂ ጊዜ ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ::
የለውጥ ኃይሉ በእነዚህ ፈታኝ እና እልህ አስጨራሽ ሁለት አመታት በርካታ ተስፋ የሚጣልባቸው እና በቀጣይ ዓመታት ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ ጽኑ መሰረት በመሆን ያገለግላሉ:: መቼም እንደቀደሙት ዘመናት ጠላት ሲመጣ ሆ ብለን በአንድነት እንመክትና ድል እንቀዳጅና በአግባቡ ሳናጣጥመው ወዲያው ወደ ልዩነታችን፣ አለመተማመን፣ ጥላቻ፣ የጎሳ ዛጎላችን (ሼል)እንደማንሸበለል ተስፋ አደርጋለሁ::በእነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ሳምንታት አንድ ስንሆን ምን አይነት ታምር ልንፈጥር እንደምንችል በአይናችን በብረቱ እየተመለከትን ነውና::
ከኮሮናቫይረስ እራሳችንና ወገናችንን እንጠብቅ !
ግድቡን እንደ ጀመርነው እናጠናቅቀዋለን !
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com