ትዝታ አያረጅም፤
ጊዜው ነጉዷል። ለአራት ዐሠርት ዕድሜ ሁለት ፈሪ ብቻ ቢቀረው ነው። 1974 ዓ.ም የሰኔ ወር ግድም። ቦታው አዲስ አበባ፣ ስድስት ኪሎ ግቢ፣ አምስተኛው በር አካባቢ በሚገኘው የተማሪዎች ካፊቴሪያ ውስጥ ነው። ጸሐፊው ዳግላስ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበር። ከትምህርት ሰዓት ውጭ አብዛኛው ተማሪ ኪሱ ውስጥ ያለችውን ሳንቲም ቋጥሮ በካፊቴሪያው ውስጥ ሻይ ቡና ማለት የተለመደ ነበር፤ ዛሬም ዑደቱ አልተለወጠም። የዑደቱ ያለመለወጥ ብቻ ሳይሆን ወንበርና ጠረጴዛዎቹም ስለመለወጣቸው ጸሐፊው ይጠራጠራል። የወቅቱን የሻይ ቡና ዋጋ የዛሬው ዘራፊ ገበያ ቢሰማው ጥርስ በሌለው ድዱ እያሾፈ ስለሚገለፍጥ ያለመጥቀሱ ይመረጥ ነበር። ግዴለም “በዱሮ በሬ ባይታረስም” ጨካኙን የዛሬ ገበያና ኑሮ አምርረን ለመታዘብ እንድንችል ዋጋው ይገለጥ ከተባለም በወቅቱ አንድ ፍንጃል ቡና ወይንም ሻይ ዋጋው ከሃያ አምስት ሣንቲም እንደማይበልጥ በትዝታ እንደሰጠምን ማስታወስ ይቻላል። ትክክለኛው ዋጋ ተዘንግቶኝ እንጂ ከስሙኒም ዝቅ የሚል ይመስለኛል።
የዓመቱ ትምህርት ማጠቃለያ ተቃርቦ የፈተና መንፈስ ግቢውን መቆጣጠር በጀመረበት በዚያ ሰሞን ጸሐፊው የተለመደውን የቡና ሱሱን ለማርካት ወደ ካፊቴሪያው ጎራ እንዳለ የሂሳብ ተቀባዩዋ ባልኮኒ ካለበት የፊት ለፊት ግድግዳ ላይ ከአሁን በፊት ያልታየ አንድ ሥዕል ተሰቅሎ ስለነበር በርካታ ተማሪዎች ዙሪያ ከበው ሥዕሉን እየተመለከቱ ሲወያዩ ይህ ጸሐፊ እግር ይጥለዋል። ዛሬም ሥዕሉን ለመመልከት የሚወድ ሰው ጎራ ቢል እዚያው ቦታ ያገኘዋል።
ጸሐፊው ዳግላስም ከስብስቡ “ሠራዊት” ጋር ተቀላቅሎ ልብ ተቀልብ በመሆን ሥዕሉን ትክ ብሎ መመልከቱን ተያያዘው። ግሩም ስዕል ነበር። በሥዕሉ ግርጌ የተጻፈውን የሠዓሊውን ስም ሲመለከት ይበልጥ አድናቆቱ ጨመረ። “አሰፋ ጉያ -1973” ይላል። ለሥዕሉ የተሰጠው ርዕስ ደግሞ “የሕይወት አሻራ” የሚል ነበር። ከሠዓሊው ጋር የነበረን እውቂያ በትምህርት አቀባበሉ ብቻ ሳይሆን በጠባዩ ጭምር በተመሠገነው የጋራ ጓደኛችን በነፍሰ ሄር ቴዎድሮስ ፍሰሃ አማካይነት ነበር። አሰፋና ቴዎድሮስ ለኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘመናቸውን ለማስገዛት የወሰኑ ሲሆኑ ጸሐፊው ዳግላስ ደግሞ ቀልቡንም ፍላጎቱንም ጠቅልሎ ለወደፊቱ እንጀራው ጭምር አደራ የሰጠው ለሥነ ጹሑፍ ትምህርት ነበር።
የአሰፋ ጉያን “የሕይወት አሻራ” ሥዕል በዚያን እለት የተመለከትኩት በተራ ዓይን ብቻ አልነበረም። ከሥዕሉ ፊት ለፊት ወንበር ስቤ በመቀመጥ ግጥም ብጤ ልሞነጫጭር ወረቀትና ብዕሬን አዋደድኩ። ሥዕሉም ሆነ ርዕሱ ወስጤ ዘልቆ ስለነበር የቃላትና የሃሳብ ምጥ አልገጠመኝም። በአጭር ደቂቃ ውስጥ ከውስጤ የፈሰሰው ሃሳብ ግጥም ሆኖ በወረቀት ላይ ታተመ። የግጥሙን ርዕስ “የሕይወት አሻራ”ን የተዋስኩት ከራሱ ከሥዕሉ ርዕስ ነበር። በዝርዝር ሀረጋትና ስንኞች የተጻፈውን ግጥም ሰብሰብ አድርጌ ለአንባቢያን በመጋበዝ ሃሳቤን እቀጥላለሁ።
“የሕይወት አሻራ”
የተሸረሸረ ማሣ፤ የሕወይት ጎርፍ የሄደበት፣
የአባባ ግንባር አሻራ በፊቱ ላይ ተጋድሞበት፣
እርከን ይመስላል ዙሪያው፣
የዕድሜው ማሳያ ሽብሽቦሽ።
አንድ ቀን . . .
ከማለዳው ጋር ነቅተን፣
የዕለታችንን አቦስቶ ልንከውን ስንጣደፍ፣
አየሁ ባባባ ግንባር ድርብርቡን የዓመታት ንድፍ።
ልጅነትን አስተናግዶ፤ ጉልምስናን አልፎ መጥቶ፣
ከእርጅና ጋር ውል ፈርሟል፤ ጥቁሩን ፀጉር አሸብቶ፤
በቃል ኪዳን ተፈጣጥሞ፣
ለእድሜም ንብረት ባንክ ሆኖ።
. . . ሰነድ ትቷል በቆዳው ላይ፤ ለእማኝነት ተመዝግቦ።
ያ አሻራ ያ የዕድሜ ቦይ፤ ለሕይወት ወንዝ መውረጃነት፣
አገልግሏል ብዙ ዘመን ፤ ምንጭም ሆኖ ሲቀዳለት፤
“ሥራ! . . .” ላቡ እንደ ውሃ ሲወርድበት።
ይህንን ግጥም ጽፌ እንደጨረስኩ ሠዓሊ አሰፋ ጉያን ፈልጌ አድናቆቴን ከገለጽኩለት በኋላ የግጥም ስጦታውን በአክብሮት አስረከብኩት። በዚያ ብቻ አላበቃም ልክ የዛሬ ሰላሳ አራት ዓመት (ግንቦት 8 ቀን 1978 ዓ.ም) ከሳንሱር ተሸሽጌበት በነበረው (?) ዳግላስ ጴጥሮስ በሚለው የብዕር ስሜ በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የባህል አምድ ላይ ታትሞ ለንባብ ቀረበ። አከታትሎም በዚያው ዓመት “ስሞተኛው” በሚል ርዕስ ባሳተምኩት የመጀመሪያ መጽሐፌ ውስጥ ያው ግጥም ተካቶ ታተመ። እነሆ ለሦስተኛ ጊዜ ከሰላሳ ስምንት ዓመታት በኋላ ሠዓሊ አሰፋ ጉያ ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ ከዚያ ድንቅ ሥዕል ጋር ተቆራኝቶ ታተመ። ዕድለኛ ግጥም ይሏል እንዲህ ነው።
“ሰምና ወርቅ” – የሠዓሊው ሦስተኛ መጽሐፍ፤
ብዙ የሀገራችን ሠዓሊያን የሚያጀግኑት ብሩሻቸውን እንጂ የብዕራቸውን ትሩፋት ሲያስነብቡ እጅግም አይስተዋልም። እርግጥ ነው ከአንጋፋዎቹ ሠዓሊዎቻችን መካከል ገብረ ክርስቶስ ደስታ (“መንገድ ስጡኝ ሰፊ” – የግጥም መድብል) እና ስዩም ወልዴ (“ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” – ግለ ታሪክ) በሚሉ ርዕሶች ሥዕሎችን ብቻም ሳይሆን ግሩም መጻሕፍትን ጭምር አበርክተውልናል። ከቅርቦቹና ከታዳጊ ሠዓሊያን መካከልም አገኘሁ አዳነን (“ጨለማን ሰበራ” እና “ግን ለምን?”)፣ ቸርነት ወ/ገብርዔል (“ኤፍራጦስ” – የግጥም መድብል፣ “ዲና” እና “ጽዋው ሲሞላ” በሲዲ የቀረቡ ግጥሞችን) ከሥዕል ሥራዎቻቸው ጎን ለአንባቢያን በረከታቸውን አድርሰዋል። እሸቱ ጥሩነህ፣ በቀለ መኮንን፣ ምህረት ከበደን የመሳሰሉ ባለ ጥምር ተሰጥኦ ባለቤቶችም ብሩሻቸውን ብቻ ሳይሆን የብዕራቸውንም አሻራ በየመድረኩ ለጀማ ስብስብ በንባብ ማቅረባቸው አይዘነጋን። በመጻሕፍት ገጾች የብዕራቸውን ጉልበት በቅርቡ እንደሚያስነብቡን ተስፋ እናደርጋለን።
ሠዓሊ አሰፋ ጉያ ግን ከላይ ከተዘረዘሩት የብዕርና የብሩሽ ልሂቃን ሁሉ የሚለይበት ጉልህ ምክንያት ስላለ በተለየ ሁኔታ ሊወደስና ሊዘመርለት ይገባል ባይ ነኝ። ምክንያቱን ላብራራ። እርግጥ ነው አሰፋ ጉያ እንደ ታላላቅ ወንድሞቹ ሠዓሊ ለማ ጉያና ቱሉ ጉያ የሥዕልን ጸጋ የታደለው በተሰጥኦ እንጂ ሥዕል ትምህርት ቤት ገብቶ ስለተማረ አይደለም። ምናልባትም ቤተሰባዊ ዳራውን እየጠቀስን የጥበቡን ተሰጥኦ ያገኘው “በደም ውርስ ነው” ብለን ልንከራከርበት እንችል ይሆናል። በግሌ አይመስለኝም። አሰፋ የሥዕልን ጥበብ አስገብሮ ሀብቱ ያደረገው በትምህርት ተደግፎ ሳይሆን በአታካች ልምምድ ብሩሹ ስለለዘበለት ነው።
ኢኮኖሚስቱ ሠዓሊ አጠንክሮ የጨበጠው የሥዕል ብሩሽ ብቻ ሳይሆን ሕይወትን በጥበብ የሚተረጉመው በብዕርን ጭምር ነው። ሥነ ጽሑፉንም ቢሆን ከግል ንባብ ውጭ መሰረታዊ ስልጠና እንኳ ስለመውሰዱ እጠራጠራለሁ። ከአሁን ቀደም ለአንባቢያን ያቀረበው “ራህማቶ” የረጅም ልቦለድ ሥራውና “የከንፈር ወዳጅ” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃው የግጥም መድብል ሁለት መጻሕፍቱ የብዕሩን በሳልነት ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ የኅትመት ውጤቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ከኢትዮጵያ ደራስያን ተርታ እንዲሰለፍ ጭምር አስችለውታል። ቀን ቀን የዕለት እንጀራውን የኃላፊነት ወንበር ሳያቀዘቅዝ (ምናልባትም በአንድ የመንግሥት የሥራ ገበታና ኃላፊነት ላይ ስኬታም ሆነው ረጅም ዓመት ካገለገሉ ሲቪል ሰረቫንቶች መካከል ከአሰፋ ጉያ እኩል የሚጠቀሱ ሌሎች ሰዎች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም)። ማታ ማታ ደግሞ በግራ እጁ ብሩሹን፣ በቀኝ እጁ ብዕር እየጨበጠ የአንድ ብዙ ሆኖ ለሕይወታችን በጥበቡ ትርጉም ለመስጠት በመትጋቱ በእጅጉ ሊመሰገን ይገባል። ለዚህም ነው ሊወደስም ሊዘመርለትም ይገባል ያልኩት።
ብዕርና ብሩሽን በሰም ያጣበቀበት ሥራው፤
“ሰምና ወርቅ” የደራሲ አሰፋ ጉያ ሦስተኛ መጽሐፉ መሆኑ ከላይ ተጠቅሷል። ሁለት መቶ ገጾች ያሉትና 185 ብር የተቆረጠለት ይህ መጽሐፍ ለሀገራችን ሥነ ጽሑፍ አዲስ የአቀራርብ ስልት ያስተዋወቀበት ሥራው ሳይሆን አይቀርም። መጽሐፉ በአዲስ ስልትነት እንዲመሰከርለት ያስቻለበት ምክንያት ይዘቱ ብቻ ሳይሆን ቅርጹም ጭምር ስላልተለመደ ነው። መጽሐፉ አራት ክፍሎች ሲኖሩት በመጀመሪያው ክፍል ደራሲው ያለፈበትን የዘመነ ወጣትነት የፖለቲካ ጦስና ጣጣ የተረከበትና የውሎ አምሽቶው ዜና መዋዕል በስፋት የተካተተበት ነው። ትረካው ቃላት እየተመረጠ የተዘገበ ብቻ ሳይሆን ከእለት ውሎው ማስታወሻ ላይ በእጁ የጻፋቸው ጽሑፎች ሳይቀሩ እንዳሉ ኮፒ ተደርገው ቀርበዋል።
ሁለተኛው ክፍል ለ25 ዓመታት ያህል ስንኞችን እያሳካ ከጻፋቸው ግጥሞቹ ቆንጥሮ ያቀረባቸው ሥራዎቹ ሲሆኑ፣ ሦስተኛው ክፍል በአብዛኛው በሞዛይክና በተለያዩ የአሳሳል ስልቶች አምጦ ከወለዳቸው ሥዕሎቹ መካከል በጽሑፍ ማብራሪያ አዳብሮ ያቀረባቸው ሥራዎቹ የተካተቱበት ምድብ ነው። አራተኛው ክፍል በጽሑፍና በሥዕል ሥራዎቹ ዙሪያ በመገናኛ ብዙኃን የተሄሱትንና ወዳጆቹ ስለ ጥበብ ሰውነቱና ተሰጥኦው የመሰከሩባቸው ማስታወሻዎችና ሃተታዎች የተዘረዘሩበት ክፍል ነው።
“የሰምና ወርቅ” ግርድፍ ሂሳዊ ቅኝት፤
በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ጽሑፎችም ሆኑ ሥዕሎች በአብዛኛው ለሕይወት ትርጉምና ፍቺ ለመስጠት ሲቃትቱ ይስተዋላል። “ኪዳን” የሚል ርዕስ በተሰጠው የደራሲው የመንደርደሪያ ገጽ ውስጥ ይህንኑ ጉዳይ በራሱ የእጅ ጽሑፍ አጠንክሮ እንዲህ በማለት ገልጾታል። “ሕይወቴን ለብሩሼ ሰጠኋት፣ ሕይወቴ ከሕይወቷ – ሕይወቷም ከሕይወቴ ይዋሃዱ ዘንድ። ቃሌም ተግባሬም ይህ ነው፤ ብዕሬም ትታከልበት ‹ዘንድ› ወሰንኩ።” (ገጽ 15)።
ሠዓሊውና ደራሲው አሰፋ ጉያ ከሰለጠነበት የኢኮኖሚክስ ትምህርት “ሕገ አእምሮ” ትዕዛዝ በማፈንገጥ በጥበብ ሥራዎቹ ከመጠን በላይ ቸር በመሆን በመጽሐፉ ውስጥ ሥራውን ያበረከተልን ለነገ ይሉት ምንም “ስቶክ” ሳያስቀር ዝርግፍ አድርጎ ነው። እንዴታውን ላብራራ። በመጽሐፉ ውስጥ አጭር ልቦለድ አለ፣ ግጥሞችም በሽበሽ ናቸው። እጅግ የምናከብረው የጋራ ወዳጃችን ነፍሰ ሄሩ አብደላ ዕዝራ በ“ራህማቶ” መጽሐፍ ላይ ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት በጋዜጣ ላይ ያቀረበው የሁለት ክፍል ሂስም አልቀረም። የደራሲው ከፊል ግለ ታሪክም ተቆንጥሮ ቀርቧል። ራሱ ደራሲው በተለያዩ ጋዘጦች ላይ ያቀረባቸው መጣጥፎች ቁርጥራጮች ቅጂም በበርካታ ቁጥር ተያይዘዋል። ስለ መደበኛ ሙያዊ ተግባሩም ብዙ ጉዳዮች ተጠቃቅሰዋል። የብፌው ይዘት ይህ ቀረህ የሚባል አይደለም። በረጅም ዓመታት ውስጥ ብሩሹና ሸራው የተወደዱባቸው ሥዕሎችም ከበቂ ማብራሪያዎች ጋር አብዛኞቹ በመጽሐፉ ውስጥ ቀርበዋል። የጥበብ ሀብቱን አሟጦ ከመስጠት የበለጠ ምን ቸርነት ይኖራል?
ሠዓሊው፣ ደራሲውና ኢኮኖሚስቱ አሰፋ ጉያ ፈላስፋም ነው። ፈላስፋነቱ በግልጽ የሚንጸባረቀው በሥራዎቹ ውስጥ ነው። ሥዕሎቹን ለመሄስ ዕውቀቴ እጅግም ስለማያወላዳ ስለ ጥቂት ግጥሞቹ ጥቂት ማሳያ ልጠቋቁም። በአራት ቃላት የተዋቀረውና “ብቸኝነት” የሚል ርዕስ የሰጠው ባለ አራት ቃላት ግጥሙ በአንድ ተቋም መጽሔት ላይ ቀርቦ እንደነበር የጋዜጠው ቁራጭ አብሮ ታትሟል።
“ራስ ማማጥ፣
ራስ መዋጥ”
እውነት ነው ብቸኝነት ሌሎች ሊያነቡት በማይችሉት የውስጥ የስሜት ሰሌዳ ላይ ቆዛሚው የሚቸከችከው ቋንቋ አልባ ትካዜ ነው። በአጭሩ ራስን እያማጡ፣ ራስን መውለድ። “የዘመን ጣር” ለሚለው ሥዕሉ በተዘጋጀው የመግለጫ ጽሑፍ ውስጥም የተካተተው የፍልስፍና ግጥም ብዙ ሊባልለት የሚገባ ነው።
ከፈገግታ ይልቅ – ጨለ ምታ፣
ከጥርታ ይልቅ – ብርቅርቅታ፣
ከዕልልታ ይልቅ – ዋይታ፣
ከምጥቅታ ይልቅ – ዝቅጥታ።
በተቃርኖ ቃላት የተዋቀረው ይህ ግጥም በርግጥም የአንድን ዘመን ጣር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በተለይም ብዙ ዜጎች በስቅቅ ያለፍንበትን ዘመነ ደርግን በማስታወስ። የሠዓሊውና የደራሲው “የዘመን ጣር” ሥዕልና ግጥም ያስታወሰኝ የደራሲ በዓሉ ግርማን አንድ አጭር ግጥም ነው።
“እንባ እንባ ይለኛል፤ ይተናነቀኛል፣
እንባ ከየት አባቱ፤ ደርቋል ከረጢቱ።
ሳቅ ሳቅም ይለኛል፤ ስቆ ላይስቅ ጥርሴ፣
ስቃ አያስለቀሰች፣ መከረኛ ነፍሴ።”
ደራሲው “የዘመን ጣር” ግጥሙን የጻፈበትን መነሻና ዝርዝር ለጊዜው አቆይቶ “ተናገር አንተ አፈር” የሚል ርዕስ በሰጠው አንድ ተመሳሳይ ባለ አራት ስንኝ አጭር ግጥሙ ውስጥ ፈላስፋነቱን አድምቆ የገለጸበትን ሃሳብ መመልከት ይቻላል።
ካንተው ከሆነ ፍጥረቱ፣
ያዳም የሰው ልጅ ግኝቱ፣
ወደአንተ ከሆነ ምልሰቱ፣
ምነው አፈር ላፈር፤ ባፈር መፋጀቱ።
ፈጣሪ የሰው ልጆችን ሁሉ አባት አዳምን (አደምን) “አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ” ብሎ የወሰነበትን የዘፍጥረት ታሪክ ከዘመናችን ጎጠኝነትና ራስ ወዳድነት ጋር አሰናስሎ ማቅረቡ የብዕሩ አቅም ምን ያህል የደደረ እንደሆነ ጥሩ ማስረጃ ነው። ኢትዮጵያ ጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍን ሃሳብ በመዋስም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፀባኦት መዘርጋት ብቻ ሳይሆን ወደ ምድርም ለሥራና ለልማት ትዘርጋ” የሚለው ፍልስፍናዊ ሃሳቡም አበጀህ የሚያሰኝ ነው።
ማሳረጊያ፤
መልካም የቤተሰብ አውራ “በሞቴ” እያለ አንዳች በሚያህል የፍቅር ጉርሻ በማዕዱ ዙሪያ የተሰበሰቡትን የቤተሰብ አባላት እንደሚያስጨንቅ ሁሉ ደራሲውና ሠዓሊው አሰፋ ጉያም እንዲሁ ዘውጋቸው የበዛ የጥበብ ሥራዎቹን ያለ ስስት በመጽሐፉ ማዕድ ውስጥ አጭቆ ጉረሱልኝ ብሏል። በምርጫው ቢያስብበት መልካም በሆነ ነበር። በይዘት አመራረጡ ላይ ውሱንነቱ ጎላ ብሎ ይታያል። በተለይም ዘመነ ወጣትነቱን ያስገዛለትን የፖለቲካ ውጣ ውረዶችና የመከራ ቁልሎች በጥቂት ገጾች ብቻ ቀንጥቦ ማቅረቡን አልወደድኩለትም። ብዙ ሊጻፍለት የሚችል ታሪክ ነበር። በማስረጃነት ያቀረባቸው በርካታ የጋዜጣ ቁርጥራጮችና ጽሑፎችም አንዳንዶቹ ያለቦታቸው እንደገቡ አስተውያለሁ።
በተረፈ ግን አሰፋ ጉያ የጥበብ አምላክ ሳይሰስት ያፈሰሰለትን ፀጋ እርሱም ያለ ስስት ዘርግፎልናል። ወዳጄ ሆይ! “ከሺህ ቃላት አንድ ሥዕል የበለጠ ይናገራል” በማለት ለብሩሽህ ብቻ ከማዳለት ይልቅ “እርግጥ ነው ከሺህ ቃላት አንድ ሥዕል የበለጠ መናገሩ አይካድም፤ ቢሆንም ግን ከሺህ ቃላት አንድ ሥዕል መናገሩን ለመግለጽ ሺህ ቃላት እንደሚያስፈልግ እንዳይዘነጋ” የሚለውን የቆየ የጠቢባን ብሂል በተግባር ስላረጋገጥክልን ብዕሬ አመስግኖሃል። በነገው አዲስ ቀን አዲስ ሥራዎችህን እንጠብቃለን። ሰላም!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com