በማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፏቸው ይታወቃሉ። በገጠራማ አካባቢዎች ድልድይ በማሰራት እና ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት የባለሀብቱን የገንዘብ ድጋፍ በሚጠይቅበት ወቅት ያላቸውን በመለገስ ለሀገር ተቆርቋሪ መሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል። ተግባብቶ የመስራት እና የንግድ ሸሪኮችን ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ በጋራ የመስራት ባህልን አዳብረዋል። ለፈረስ ግልቢያ ልዩ ፍቅር አላቸው እናም የሚያሳድጓቸው በርካታ ፈረሶች አሏቸው። ከስራ እና ድካም አረፍ ለማለት ሲፈልጉ ፈረሶቻቸው ላይ ተፈናጠው ሽምጥ በመጋለብ መዝናናትን ያዘወትራሉ።
ሼክ አሊ ሁሴን መሐመድ ሙሉ ስማቸው ነው። በኦሮሚያ ክልል ጅማ ሊሙ ገነት አካባቢ ነው የተወለዱት። ቤተሰባቸው ንግድ ላይ የተሰማሩ እና ጥሩ ገቢ የነበራቸው መሆኑን ይናገራሉ። በአካባቢያቸው ኳስ ጨዋታ እና ፈረስ ግልቢያን ያዘወትሩ እንደነበር ያለፉበትን የልጅነት ጊዜ ወደኋላ ተጉዘው ያስታውሳሉ። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸን ሊሙ ገነት ከተማሩ በኋላ ተኩረታቸው ሁሉ ወደ ንግዱ ዓለም ተሳበ። ለዚህ ደግሞ የቤተሰባቸው የስራ ሁኔታ ተጽእኖ እንዳደረገባቸው አይሸሽጉም።
ቤተሰባቸው ካላቸው ሀብት ላይ የተወሰነውን ሰጥተዋቸው ጅማ ላይ እንዲኖሩ ቢፈልጉም እርሳቸው ግን የግል ስራቸውን ጀምረው እራሳቸውን ችለው ለመኖር በመፈለጋቸው ወደ አዲስ አበባ መጡ። በ1980ዎቹ ላይ ወደ ከተማዋ ሲመጡ ግን ከቤተሰብ ይዘውት የመጡት ሀብት እንዳልነበረ ይናገራሉ።
አዲስ አበባ መጥተው መርካቶ አካባቢ የስራውን ሁኔታ እያጠኑ ለጥቂት ወራት ተቀመጡ። ከዚያም በአነስተኛ ገንዘብ የመኪና መለዋወጫ ንግድ ውስጥ አንድ ሁለት እያሉ እቃዎችን በመሸጥ ገበያውን መቀላቀል ጀመሩ። የመለዋወጫ ንግዱ እየተጠናከረ ሲሄድ ደግሞ አቅማቸውም በመጠኑ እየተጠናከረ መጣ። እናም ወደ ሳኡዲ አረብያ ጉዞ በማድረግ ለስራ የሚያስፈልጓቸውን ዕቃዎች ለማምጣት አቀኑ። ሳኡዲ አረብያ ሲሄዱ በመጀመሪያ የተዋወቁትን የመኪና ዕቃዎች መለዋወጫ ንግድ ባለቤት በእንግሊዘኛ ነበር ያናገራቸው።
በጥቂት ወራት ውስጥ ግን ተመልሰው ሲሄዱ ቀደም ሲል የተዋወቁትን ሰው በአረብኛ አናገሩት። በዚህ የተደነቀው የንግድ ሰው ሼህ አሊ በአጭር ጊዜ እንዴት ቋንቋውን እንደለመዱት ተገርሞ እንደነበር አይዘነጉትም። እርሳቸው ከሰዎች ጋር መግባባት እና ለንግድ ቅልጥፍና ቋንቋ ወሳኝ በመሆኑ በመረዳታቸው በየጊዜው ሲሄዱ በማጥናት እና ተናጋሪዎችን በማግኘት አረብኛውን ለመልመድ ከላቸው ፍላጎት የተነሳ በአጭር ጊዜ መላመዳቸውን ያስረዳሉ።
ሼህ አሊ ከቋንቋ በተጨማሪ የንግድ ሰዎችን ለማግኘት የሚጠቀሙበት ብልሃትም አላቸው። ወደ ሳኡዲ አረቢያ በሚጓዙበት ወቅት ገንዘብ ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም አውሮፕላን ውስጥ ቢዝነስ ክፍሉ ውስጥ መሳፈርን ነው የሚመርጡት። ይህንንም የሚያደርጉት አብዛኛውን ጊዜ ከመደበኛው የአውሮፕላን መቀመጫ ክፍሎች በበለጠ በቢዝነስ ክፍል ውስጥ የንግድ ሰዎች እንደሚገኙ ስለሚያውቁ ነው። እናም አብረዋቸው ተሳፍረው የንግድ ሽርክና ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት እድል እንዲፈጠርላቸው በሚል ተጨማሪ ክፍያ አውጥተው ከከፍተኛ ባለሀብቶች ጋር እየተጨዋወቱ ይጓዛሉ። ይህ ብልሃታቸው ታዲያ አንድ ቀን ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት ከሚፈልግ የውጭ ዜጋ ጋር ያገናኛቸዋል።
ትውውቃቸውንም አጠናክረው የስጋ ንግድ ላይ ለመስራት ስምምነት ላይ በመድረሳቸው አዲሱን የሙያ ዘርፋቸውን ከአጋራቸው ጋር ጀመሩ። በመጀመሪያ ቢሾፍቱ ከተማ የእንስሳት ማረጃ ቄራ በማዘጋጀት የበግ ስጋ ለመላክ ዝግጅታቸውን አጠናቀቁ። ለመጀመሪያ ጊዜ 2 ሺህ 800 ኪሎ ግራም የበግ ስጋ አሳርደው ለውጭ ገበያ በሚሆን ጥራት አዘጋጅተው ወደ ሳኡዲ አረብያ መላካቸውን ያስታውሳሉ። በዚያ ጊዜ በርካታ የስጋ ምርቶችን በመላክ ጥሩ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር በማስገባታቸው በ1989 ዓ.ም ላይ መንግስት የማበረታቻ ዋንጫ ሽልማት እንዳቀረበላቸውም አይዘነጉትም።
ከስጋ ንግዱ ጠቀም ያለ ገቢ በመገኘቱ ሼክ አሊ ጅማ አካባቢ የቤተሰብ መሬት ላይ ተጨማሪ ስራ ለመስራት በሚል የቡና እረሻ ንግድ ላይ ተሰማሩ። ቡናው ደርሶ ሁለት ኮንቴይነር ሙሉ ምርት ታሽጎ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ቡናው አዲስ አበባ ሲደርስ ግን አንድም የሚገዛ ሰው ጠፋ። በነገሩ የተገረሙት ሼህ አሊ እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጥ ግን አልፈለጉም። ይልቁንም የቡናውን ናሙና ይዘው ገበያ ለማፈላለግ ቀድሞ ወደሚያውቋት ሳኡዲ አረቢያ አቀኑ።
አዲስ አበባ ላይ ያልተገኘው ገበያ ሳኡዲ ላይ ቡናው ተፈላጊ በመሆኑ ወዲያውኑ ገዥ አገኘ። ቡናውም ተልኮ ተወዳጅነት በማትረፉ በተከታታይ ዓመታት ምርቱን በመላክ ገቢያቸውንም አሳደጉ። ከቤተሰብ መሬት በመውጣት የራሳቸው መሬት አዘጋጅተው በየጊዜው የውጭ ምንዛሬዎችን በማስገባት ከስጋ ንግዱ በተጨማሪ የተዋጣላቸው የቡና ላኪ መሆን ችለዋል።
በመሃል ግን የስጋ ንግዱ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ማቆሙ ሄደ። በዚህ ወቅት ሼህ አሊ እርሻ ላይ አተኩረው ቡናውንም በመላክ እና የመኪና መለዋወጫ ንግዳቸው ላይ በማተኮር መስራታቸውን ቀጠሉ። ይሁንና የመንግስት አካላት የስጋ ንግዱ እንደ ሀገር ሲቀንስ ችግሩ ምንድነው ብለው ወደ አረብ ሀገራት ሲያቀኑ የአረብ ሀገራት የቀድሞ ደንበኞቻቸው የሼህ አሊ ምርት ጥራት ያለው ነው የእርሱ ተወዳጅ ነበር የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ። በዚህ ምክንያት በመንግስት ጥያቄ በተለያዩ ችግሮች ቆሞ የነበረው የቄራ ስራ ከአራት ዓመታት በፊት ዳግም መጀመሩን ሼህ አሊ ሁሴን ይናገራሉ።
የአረብ ሀገራት ስራ በህግ እና በአሰራር ብቻ አይደለም የሚመራው የሚሉት ሼህ አሊ ግለሰባዊ ግንኙነት እና መተዋወቅ ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። እርሳቸውም ጥራት ያለው ምርት ከማቅረብ ባለፈ ነጋዴዎቹን እንደየፍላጎታቸው በመያዝና ስህተት እንዳይኖር ጥንቃቄ በማድረግ በመተማመን ላይ ተመስርተው እንደሚሰሩ ይገልጻሉ።
በመሆኑም ዳግም በተጀመረው የስጋ ንግዳቸው አማካኝነት ጥራት ያላቸው የስጋ ምርቶች ወደ ተለያዩ አረብ ሀገራት እና ግብጽ ጨምሮ የሚልክ ድርጅት ባለቤት ናቸው። ከአርብቶ አደሩ ገዝተው በማደለብ ኤክስፖርት እያደረጉ ይገኛል።ከዚህ ባለፈ ግን የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገንብተው ለእንስሳቶቻቸውም የሚሆን መኖ ከማቅረብ ባለፈ ለሌሎችም የሚተርፍ ምርት እያዘጋጁ ይገኛሉ።
የመኪና መለዋወጫ ንግዳቸውን ወደ ከባድ ማሽነሪዎች ንግድ በማሸጋገር የተለያዩ ማሽኖችን እያስመጡ ይሸጣሉ። በተለይ ለኮንስትራክሽን አገልግሎት የሚሆኑ ዶዘር ተሽከርካሪዎች እና ገልባጭ ከባድ ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት በዘርፉ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው። ከኮንስትራክሽ ዘርፉ ጋር በተያያዘ ደግሞ በቅርቡ 700 ሚሊዮን ብር ወጪ ያለው የገበያ ማዕከል አዲስ አበባ ውስጥ ገርጂ አካባቢ አስገንብተዋል። በገበያ ማዕከሉ አቅራቢያ ቢሯቸውን አድርገው ዘርፈ ብዙውን የንግድ ስራቸውን እየመሩ ይገኛል። በቀጣይም በሪል እስቴት ዘርፉ ሰፊ ስራ ለማከናወን ውጥን አላቸው።
በሌላ በኩል ሼህ አሊ የቡና ምርታቸውን ጃፓን እና የተለያዩ የአለም ሀገራት ድረስ በመላክ የሚያገኙትን ገቢ ለማሳደግ ምን ጊዜም ጥረት እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ። በተለይ ቡናን ከማመረት ባለፈ ቆልቶ እና ፈጭቶ እንዲሁም አሽጎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የፋብሪካ ግንባታ እና የማሽን ተከላ አካሂደዋል። የተፈጨ ቡና ወደ ጃፓን በኮንቴይነር በመላክ ጥሩ የንግድ ሰው መሆናቸውን አስመስክረዋል። በ2012 ስድስት ወራት ብቻ 10 ሚሊዮን ዶላር የቡና ገበያ ማስገባታቸው ደግሞ በዘርፉ እየሰሩ ምን ያህል እንደሚገኝ ማሳያ ነው።
በድሬዳዋና በአዲስ አበባ፣ ያላቸው እያንዳንዳቸው 30 ሺህ ቶን ቡና መያዝና ማደራጀት የሚችሉ መጋዘኖቻቸው ደግሞ አልፎዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ብለው ለሰየሙት ድርጅታቸው ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥሩ ንብረቶች ናቸው።
ሼህ አሊ በአሁኑ ወቅትም የንግድ ዘርፋቸውን ለማስፋት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በተለይ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ የሚረዳ የሆቴል ህንጻ ግንባታ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ የስራ ሁኔታ መኖሩን ለተለያዩ የውጭ ሀገራት ባለሀብቶች በማስተዋወቅ አብረው ለመስራት የሚያስችል ውይይት በማካሄድ ላይ ናቸው። በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት ከውጭ ሀገራት ባለሀብቶች ጋር በጋራ ንግድ ስምምነት በርካታ ኢንቨስትመንቶችን ለማከናወን ሂደት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ሼህ አሊ ከንግድ ስራቸው በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ በመሰማራት ማህበረሰቡን ለመጥቀም ጥረት ያደርጋሉ። ኢንቨስትመንት በሚያከናውኑባቸው በተለይ ደቡብ ክልል እና ኦሮሚያ የውስጥ ለውጥ መንገድ ግንባታ ላይ ሰፊ እገዛ ያደርጋሉ። በተለይ በቡና ምርታቸው ጥራት አማካኝነት ዓለም አቀፉ ስታርባክስ ኩባንያ ሽልማት ሲያበረክትላቸው ውጤቱ የአርሶአደሮች ነው በሚል ይርጋጨፌ አካባቢ ግማሽ ሚሊዮን ብር በመስጠት ድልድይ አሰርተዋል። ለተማሪዎች የደብተር እና ቦርሳ ልገሳ በማከናወን አጋርነታቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል።
ዘርፈ ብዙው የንግድ ሰው ለሀገሬ ገና ብዙ መስራት አለብኝ የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። በአጠቃላይ ሼህ አሊ በፈጠሯቸው ስራዎች ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ ዕድል ባለቤት መሆን ችለዋል። በቀጣይ ደግሞ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ሆቴል ሲጠናቀቅ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
ያለችን ሀገር አንድ ስለሆነች፣ እድገት እንድታሳይ ሁሉም ሊታትር ይገባል የሚሉት የጅማው ሰው፤ በዚህ ረገድ ሰላሟ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ወጣቱ ትውልድ ከግጭት እና ከረብሻ ወጥቶ ስራ ላይ እንዲያተኩር መንግስትም የበኩሉን ጥረት የመወጣቱን ስራ ማጠናከር እንዳለበት ያስረዳሉ።
ስራ ማለት ለእርሳቸው፤ ለእራስ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ብሎም ለሀገር የሚተርፍ ውጤት የሚያመጣ ክንውን ነው። በዚህ ረገድ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከስህተት የጸዳ እና ጥራት ላይ ያተኮረ ስራ በማከናወን ቤተሰቡን እና ሀገሩን መጥቀም የሚችልባቸው በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በኢትዮጵያ ይገኛሉና እድሉን መጠቀም አለበት የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012
ጌትነት ተስፋማርያም