የትምህርት ቤት አፍላ ወጣቶች ለአገራዊ ጥሪ ቅድሚያ ተሰላፊዎች ናቸው። በዚህ የተነሳም የመንግስታቸውን ጥሪዎች በመቀበል ወቅቱ የፈቀደውን መስዋዕትነት በየዘመኑ ከፍለዋል።
አሁን ላይ ለወጣቶች የቀረበው የእናት አገር ጥሪ፣ ብረት ወልውሎ መፋለምን የሚጠይቅ ሳይሆን አንድነት በመፍጠርና በሥነምግባር ልዕልና ድል መንሳትን የሚጠይቅ ነው። በዚህ አግባብ በአንድነት ሲሰራም አገርን እና ዜጎችን የዓለም መቅሰፍት ከሆነው ኮሮና ወረርሽኝ መታደግ ያስችላል።
የዓለምን ኃያላን ከጫፍጫፍ ያስጨነቀውን ወረርሽኝ አስቀድሞ በብልሃትና በጥንቃቄ መከላከልና ማለፍ እንዲቻል መንግስት ጥረት እያደረገ ይገኛል። የአገራትን ተሞክሮዎች እግር በእግር እየቀመረ ዜጎች እንዲተገብሯቸው ጥሪ ያቀርባል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የትምህርት ተቋማትን በጊዜያዊነት በመዝጋት ጥንቃቄ ተማሪዎች በቤት ሆነው እንዲቆዩ ማድረግ ነው።
በዚህም መሰረት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ወረርሽኙን እና ትምህርታቸውን እንዴት ማሳለፍ እንዳለባቸው በውሳኔዎቹ ተመላክቶ ነበር። በዚህ ወቅት በምን ሁኔታ እንዲያሳልፍ ይጠበቃል? ወረርሽኙን በመከላከል በኩል ምን ያበረክታሉ? ተማሪዎችና ወላጆችስ ተግባራቱን ተቀብሎ በተገቢው በማከናወን በኩል የተለየ ፋይዳ ይኖረዋል? የሚሉትን ለመቃኘት ሞክረናል።
በመንግስት በኩል የተላለፉት መልዕክቶች ምን ነበሩ? የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከመጋቢት ሰባት ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በሁሉም የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት መወሰድ ያለባቸው ርምጃዎችና ጥንቃቄዎች አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፎ ነበር። በዚህም ከመጋቢት ስምንት ጀምሮ ተማሪዎች ለሁለት ሳምንት ባሉበት እንዲቆዩ፤ የንጽሕና መጠበቂያዎች እንዲቀርቡላቸው፣ እንዳይተፋፈጉ ተጨማሪ ዶርሞች እንዲዘጋጁ ተደርጎ ነበር። በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች በዶርሞች አካባቢ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት መስጠት እንደተጀመረም ይነሳል።
ነገር ግን በፕሬዚዳንቶች የሚመራ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ፤ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የመሄድ ፍላጎታቸው በመጨመሩ፣በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ከ50 በመቶ በላይ ግቢውን ለቅቀው በመሄዳቸው፣ ለወረርሽኙ መከላከል የሚያደርጉት ጥንቃቄ አናሳ ሆኖ በመገኘቱ የተነሳ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻው ጋር በጥንቃቄ እንዲያሳልፉ እንዲሸኙ ተደርጓል።
ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዳይዘናጉ ምን ታስቧል?
ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርስቲዎች ድረስ የትምህርት ተቋማት ተዘግተዋል። ተማሪዎችም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያሳልፉ እየተደረገ ነው። ከኮሮናን ወረርሽኝ እንዴት ራሳቸውን ሊከላከሉ ይችላሉ? የትምህርት ሁኔታቸውስ እንዴት ተጣጥሞ ይሄዳል? ለሚለው የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐረግ ማሞ እንዳሉት፣ ወረርሽኙን ምክንያት በማረግድ በመንግስት ውሳኔ ተማሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ተደርጓል።
የትምህርት ቤቶች መዘጋት ዋናው ዓላማም ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች ሲውሉ በአንድ ይተፋፈጋሉ። በዚህ የተነሳም ለቫይረሱ መዛመት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል። ይሄን ታሳቢ ያደረገ ርምጃ ነው። ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ፤ በተጨማሪም ወላጆቻቸውን ጭምር ከዚህ ቫይረስ እንዲከላከሉ ለማድረግ ሲባል ትምህርት መዘጋቱን አብራርተዋል።
ትምህርት ተቋረጠ ወይም ተዘጋ ሲባል እረፍት ነው ማለት አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሐረግ፤ ተማሪዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ እንዲያጠኑና እንዲያነቡ ይፈለጋል። ትምህርት ሚኒስቴር የቴሌቪዥን ጣቢያ አለው፤ በሱ አማካኝነት ትምህርቱ ይሰጣል። በተመሳሳይም በየክልሎች የሬዲዮ ትምህርት በመኖሩ መከታተል ይችላሉ። ይህ ማለት ግን የገጽ ለገጽ ትምህርቱን ይተካል ማለት አይደለም። ተማሪዎች ከትምህርት ስርዓት ውጪ እንዳይሆኑ፣ ራሳቸውን እንዲያበቁና እንዲያዘጋጁ ለማድረግ ነው። እውቀቱንም ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲከታተሉ ማድረግ ስለተፈለገም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።
መደበኛ የትምህርት ሂደትን የሚተካ ግን አይደለም ይላሉ። ጎበዝ ተማሪዎች መምህራን ከዚህ ቀደም ያስተማሯቸውን መነሻ በማድረግ እጃቸው ላይ ከሚገኘው መጽሐፍ፣ ከበድ ከበድ የሚሉ የትምህርት ምዕራፎችን ለማጥናት ይረዳቸዋል ባይ ናቸው።
በቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን መከታተልና ማጥናት እንዲችሉ ወላጆች ሊከታተሏቸውና ሊደግፏቸው እንደሚገባ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ ተናግረዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል ምን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ?
ተማሪዎች ወረርሽኙን በመከላከል በኩል ከፍተኛ ሚና አላቸው። ምክንያቱም ጽዳታቸውን በተገቢው ለመጠበቅ እድል ያገኛሉ። የግብዓት ችግሮቻቸው ይቃለሉላቸዋል። ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር ያስተምራሉ። የበሽታውን መንስኤዎች፣ መተላለፊያ መንገዶች እና መከላከያ ስልቶች ለአርሶ አደር ቤተሰቦቻቸው ያስተምራሉ፤ግንዛቤም ይፈጥራሉ ነው ያሉት ወይዘሮ ሐረግ።
ዶክተር ዮሐንስ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤት ዝግ ሲደረግ እዚያ አካባቢ የበሽታው ወረርሽኝ አለ ማለት ሣይሆን ለስርጭቱ አመቺ ሁኔታ ላለመፍጠር ሲባል ነው። ተማሪዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሆነው ለወረርሽኑ መከላከል የራሳቸውን ሚና መጫወት አለባቸው።
ወላጆችም ትምህርት ቤቶች የተዘጉባቸው ምክንያቶች የበሽታውን መዛመት ለመግታት ሲባል መሆኑን ተገን ዝበው ልጆቻቸው ከቤት እንዳይወጡ ሊጠብቁ ይገባል። ልጆቻቸውን ሊመክሩና ሊቆጣጠሩ አደራ አለባቸው። የወረርሽኙን መዛመት በዋናነት መቆጣጠር የሚቻለው ንጽሕናን በመጠበቅና እንቅስቃሴን በመግታት እንደሆነ በደንብ መታወቅ አለበት። ልጆች ከቤታቸው በሚወጡበት ጊዜ ለንክኪ የተጋለጡ ናቸው። በመሆኑም ተማሪዎችም፣ ወላጆችም ራሳቸውን ከንክኪ በማራቅ ወረርሽኙን ሊከላከሉ ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎች ከመመለሳቸው በፊት ወላጆች በየአካባቢያቸው የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን ንጹህ ማድረግ አለባቸው። ወረርሽኙ ከንጽሕና ጋር የሚቆራኝ በመሆኑ የትምህርት ግቢዎቹን ጽዱ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ ዶክተር ዮሐንስ በንቲ።
ምን ሊደረግ ይገባል?
ዶክተር ዮሐንስ እንዳስረዱት፤ ችግሩ አለም አቀፍ ነው። በመላው ዓለም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተለይተዋል። ስለዚህ ተማሪዎች ትምህርት ተቋርጧል በሚል ለሐሳብ መጋለጥ የለባቸውም። ይልቁንም ራሳቸውን በጥናትና በተለያዩ ስራዎች መጥመድ አለባቸው።
በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የትምህርት ፕሮግራሞችን መከታተል፤ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መልዕክቶችን በተገቢው አዳምጠው በተግባር ላይ ማዋል፣ ከአሉባልታና ካልተጣሩ መረጃዎች ራሳቸውን ማራቅ፣ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተቀብለው መፈጸም አለባቸው። ወላጆቻቸውም እንዲተገብሩ ማድረግና ማስተማር ይገባቸዋል። ምክንያቱም የአብዛኛው ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው የተማሩ እንዳልሆነ ይታወቃል። በዚህ የተነሳ ተማሪዎች በርካታ ኃላፊነቶች እንዳሉባቸው ገልጸዋል።
በቀጣይ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና እንዴት መወጣት እንዳለባቸው እያሰቡ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው። በርግጥ የትምህርት ተቋማቱም ያለፉ የትምህርት ጊዜያት እንዴት ሊካካሱ እንደሚገባ ሊያስቡበት ይችላሉ። መምህራንም በዚሁ ሁኔታ ራሳቸውን እያዘጋጁ እንደሚቆዩ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንቱ እምነታቸውን ተናግረዋል።
እዚህ ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ መምህራንን ተግባር መጥቀስ ጠቃሚ ይሆናል። የኮሮና ወረርሽኙን በተመለከተ መጋቢት 21 በከተማዋ ዋናዋና መንገዶች የእግር ጉዞ በማድረግ ማህበረሰቡን አስተምረዋል። ተራርቀው እንዲ ቀመጡ፣ ተራርቀው እንዲሰለፉ እና እንዳይጨባበጡ በመግለጽ ማህበራዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ግንዛቤ ፈጥረዋል። በተጨማሪም የዓለም የጤና ድርጅት ባስቀመጠው ምጥጥን መሰረት ሳኒታይዘር በማምረት ለአቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ለማሰራጨት እየሰራ እንደሚገኝ የቴክኖሎጂ አንስቲትዩት የኬሚካልና ባዮ ምህንድስና ትምህርት ቤት ገልጿል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25/2012
ሙሐመድ ሁሴን