ጤና ይስጥልኝ!
እንዴት ከረማችሁ ውድ የሀገሬ ልጆች? እንዲህ በከፋ ዘመን የእግዜር ሠላምታን እንኳ በቅጡ ለመለዋወጥ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ወገኖቼ። አምላክ ካልታረቀን ምንም ማምለጫ እንደሌለን መቸም አሁን አሁን ያልተገለጠልን ሰዎች አለን ብዬ ማመን እጅግ ከባድ ነው። አምላክ “እኔ ዘንዳ ያሎት ቀሪ ሂሳብ አነስተኛ ነው” ያለን ለታ ክፉ ቀን እንደሚመታን አለመገንዘባችን ወይኔ ያስብላል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ከተቀረው ዓለም ለየት ከሚያደርጉን ከብዙ ትውፊታዊ እሴቶቻችን አንዱ ጥልቅ ስሜትን ለመግለጽ የምንጠቀምበት የሰላምታ ልውውጣችን ነው። እንዲህ እንደ ሰሞነኛው የምፅአት ቀን የደረሰ እስኪመስለን ዓለም ከጫፍ ጫፍ ስትናጥ በምናይበት ወቅት የሠላምታ ልውውጣችንን ዋጋ በሚገባ እንረዳዋለን። “ጤና ይስጥልኝ”ን በችጋር እና በወረርሽኝ ወቅት ብቻ ከተሰቀለበት አውርደን እንደ መኸር ወቅት ማጭድ የምንጠቀምበት ሳይሆን ወትሮውንም በእለት ተእለት የኑሮ እንቅስቃሴዎቻችን ጋር የተሳሰረ እና በመደበኛነት የምንገለገልበት የግንኙነታችን ቡራኬ መስጫ ድንቅ ሐረግ ናት። ከሀገሬ በቀር በሌላኛው ዓለም ይህን መሰል የግብረገብነት እና የሰብዓዊነት ርኅራኄ ማሳያ ቋንቋ ስለመኖሩ ወይ እርግጠኛ አይደለሁም አልያም በሀገሬ ባህል ጭፍን ፍቅር ውስጥ ወድቄ መሆን አለበት ማለት ነው። የሆነው ሆኖ የሀገሬ ሰው ጤናን ከምንም ነገር በላይ የመኖሩ ትርጉም፣ የኅልውናው ምሰሶ እና ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕይወትን ከተሟላ ጤንነት ጋር ለሰው ልጆች ሁሉ ያላንዳች አድልዎ ለሰጠን አምላክ ያለውን መንፈሳዊ ተገዢነት እና ረቂቅ መስተጋብርን የሚያረጋግጥበት ብቸኛ ሀብት አድርጎ የሚወስደው ምድራዊ ምስጢር ነው። ጤና ከሌለ ምን አለ? ምንም! የትም መሄድ ሳያስፈልገን ይኸው በአይናችን እያየን እኮ ነው። የቱን ያክል የተከማቸ ሀብት፣ የወታደር ብዛት፣ ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃያልነት አንድ ላይ ተሰባስቦ አንድ ጤናን ማምጣት እንደተሳነው እኮ በየዕለቱ የምንመለከተው ሐቅ ሆኗል። በሰላሙ ጊዜ ጥጋብ ልባቸውን አውሮ ደሃ ሊታያቸው ያልቻሉ የናጠጡ የቁስ ሀብታሞች፤ ይኸው የጥጋብ ስካር ከሰውም አልፎ የአምላክን መኖር እስከ መካድ ያጀገናቸው የመሰይጠን ስሪቶች ጤና እንደ ሰማይ ርቋቸው የኛኑ የድሆቹን ከንፈር ምጥጫ መሻት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
አሁን ማነው እስቲ አንድ በምጣኔ ሀብታዊ አቅሟ እጅግ የበለፀገች የምትባል፤ በወታደራዊ አቅሟም የአለምን ሆድ የምታርድ፤ በአንድ ወቅት ደሃ ሀገራትን በጉልበት ስትገዛ የነበር፤ የሰው ልጅን እንደ ሸቀጥ ገበያ አውጥታ የምትሸጥ ሀገር ገዢ አልያም ንጉሥ የነበረ ሰው እኛኑ መልሶ “አደራ በፀሎታችሁ አትርሱን” ሲል የሚያምነው? ማንም! ቀደም ሲል እንደገለፅኩት የአምላክን መኖር እስከናካቴውም ረስተው በየትኛውም ቤተእምነት የተወገዙ ድርጊቶችን በሃላልነት ብይን ሰጥተዋቸው የተቀረው ዓለምም የሰይጣናዊ ባህሎቻቸው ተገዢ እንዲሆን በሚችሉት ሁሉ የጥመት ጥዋ ሲያጠምቁን የነበሩ የስም ኃያላን ዛሬ ደርሰው የአምላክ ቁጣ ሲለበልባቸው እንዲሁም ቁጣው ከእነሱም አልፎ ለእንደኛ አይነቱ ደሃ ሲተርፈን እውነት ወደ አምላካቸው በስተመጨረሻ ይመለሳሉ ብሎ የገመተ ማን አለ? በግሌ እኔ እንጃ! የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በያዝነው ሳምንት ያደረጉት አጭር ንግግር ለዚህ ዋቢ ነው። ከደረሰባቸው አደጋ ያን ልብ ሰባሪ ንግግር ማድረጋቸው የሚጠበቅ ነበር። ወረርሽኙ በተለይም በእነርሱ ላይ ያሳረፈው በትር እጅግ አስከፊና አሳዛኝም ነበር። የአምላክ ቁጣ ሲመጣ ዶላርና ዩሮ ተክተው መስራት እንደማይችሉ ተመለከቱ። ወታደርም ሆነ የህክምና ስፔሻሊስት ሊያተርፏቸው አልቻሉም። እንኳንስ ሊታደጓቸው እነርሱም እራሳቸው በእሳቱ ነበልባል መገረፍ ጀመሩ። በዚያች ቅፅበት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ነፍስ ረገፈ። አለም በአንድ አይን አነባች። በአንድ ልብም አዘነች። በዚህን ጊዜ ያሁሉ አቅም ዋጋ ማጣቱን ተገነዘቡ። ደካማነት ተሰማቸው። አቅመቢስነታቸውን ወደ ማስተዋል ወደ ልቦናቸው ተመለሱ። ወደ ፈጣሪ!
የኮሮና ቫይረስ
የኮሮና ቫይረስ በሽታ ወይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠራሩ COVID-19 የዘመናችን አዲስ እንግዳ በሆነ ቫይረስ የሚከሰት እጅግ አስፈሪ ተላላፊ በሽታ ነው። አለም ስለዚህ በሽታ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም ማለት ይቻላል። የአስፈሪነቱም ምንጭ ይኸው አዲስ ክስተት መሆኑ ነው። በሽታው በዋናነት የመተንፈሻ አካላችንን በማጥቃት በአፋጣኝ ለሞት የሚዳርገን የዘመናችን ቀሳፊ ጠንቅ ከመሆኑ በዘለለ የተሟላ ማብራሪያ ሊሰጠን የሚችል የጤና ሊቅ እስከአሁን አልተገኘም። ሆኖም ሀገራትና ምሁራን ከዚህ ወረርሽኝ ለመዳን ሌት ተቀን እየተጠበቡ ይገኛሉ። እሳቱ ግን የሰው ልጅን ሕይወት በሚዘገንን ፍጥነት እየቀጠፈ መጓዙን ቀጥሏል። በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መግቢያ ላይ አንድ ብሎ ከወደ ሩቅ ምስራቅ አካባቢ ስራውን እንደ ጀመረ የሚነገርለት ይኸው ወረርሽኝ ዛሬ ያልነካው የዓለማችን ክፍል የለም። ድንበር ሳይበግረው፣ ሀብት ሳያቆመው፣ ስልጣንም ሳይከላከለው፣ እውቀትም ሳያረክሰው ከሀገር መሪ እስከ ተራ ዜጋ ወንድ ሴት፣ ወጣት አረጋዊ፣ እስላም ክርስቲያን፣ ሀብታም ደሀ፣ ጥቁር ወይም ነጭ ሳይል የእያንዳንዱን ቤት በፍጥነት እያንኳኳ ይገኛል። አሁን ባለንበት ሁኔታ መቼ ይደርሰን ይሆን ከማለት በቀር አንዳች ምድራዊ ኃይል ደርሶ ሊያቆመውም ሆነ ሊታደገን እንደማይችል የተገነዘብን ይመስለኛል። ምክንያቱም በሽታው አሁን ላይ ምንም አይነት መድኃኒት ወይም የህክምና ፈውስ አልተገኘለትምና። በየቀኑ የሟቾችን እና የተጠቂዎችን አኃዝ መቁጠር ብቻ ሆኗል ስራችን።
የአለም የጤና ድርጅት ባሰፈረው ሪፖርት መሠረት በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በጃንዋሪ 20፣ 2020 ዓመተ ምህረት ከወደ ሩቅ ምስራቅ አካባቢ በቀድሞዋ የቻይና ግዛት የነበረችው የኮሪያ ሪፑብሊክ በአንዲት የሰላሳ አምስት ዓመት እድሜ ቻይናዊት እንስት ላይ እንደተገኘ ይፋ አድርጓል። ሴትዮዋም ሪፖርቱ በዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ከመሆኑ ሁለት ቀን ቀደም ብላ በምትኖርበት የሁቤ ክፍለ ሀገር ዉኃን ከተማ ባደረባት ህመም ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ በተደረገላት ምርመራ መጠነኛ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት እና የጡንቻ ህመም ስሜት ተገኘባት። በዚህን ወቅት ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ኮሪያ የበሽታ መከላከያ ማእከል ተወሰደች። እዚያም በተደረገ ሰፋ ያለ ምርመራ ሴትዮዋ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆኗ ተደረሰበት። በእርግጥ ሴትዮዋ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት እንደ አዲስ በተቀሰቀሰ እና ዛሬ ላለንበት ደረጃ ላደረሰን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመጀመሪያዋ ተጠቂ ይሁኑ እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ ለበሽታው አራተኛ ታማሚ ናቸው።
በሽታው ቀደም ብሎ በተጠናቀቀው 2019 የፈረንጆች ዓመት በዲሴምበር 31 እዚያው በሀገረ ቻይና ነበር የመጀመሪያው ምልክት መገኘቱን የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው። ከዚህ በመነሳትም በሽታው የዛሬ ስያሜውን አገኘ። ወደ ሀገሬ ስመጣ እንግዲህ የሀያላኖቹን አወዳደቅ እንዴት እንደሆነ እያየን ነው። በህክምና የተራቀቁት እጅ ሰጥተው ባሉበትና ተረኛ መሆናችንን እያወቅን፣ አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ፣ ወባ ያጠቃውን እና ምጥ ላይ ያለችን ሴት ዛሬም በአልጋ ተሸክመን ወንዝ የሚነጥቀን ጭራ ሁዋላ ቀር መሆናችንን፣ አስፈሪው ሞት እየመጣ እየሆነ ገና ጊዜ ሰጥቶን እያለ በዚህች ሰዓት የሟቹን ቁጥር እንዴት እንቀንስ ብሎ ሌት ተቀን የሚለፉትን ከማንጓጠጥ ውጭ አንድ ለሀገር እና ለወገን የሚረባ ተግባር የማያከናውኑ ድኩማን “ኢትዮጵያዊያንን” ከማየት በላይ ህመም ያለ አይመስለኝም። በመንግሥት በኩል የሚታየው ግዴለሽነት በቅርቡ ውድ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ምንም ጥርጣሬ አይግባችሁ። ይህንን ባዮሎጂካል ጦርነት የምንገጥመው ፌጦና ዳማከሴን ይዘን አይደለም። በእርግጥ የእነሱን ዋጋ ለማሳነስ ተደርጎ እንዳይወሰድብኝ ከወዲሁ ተማፅኖዬን አቀርባለሁ። አሁን ላይ ገና ምኑም የማይጨበጥን መቅሰፍት ልንቆጣጠረው የምንችለው በአንድ እና በአንድ መንገድ ብቻ ነው። እርሱም ስርጭቱን በመግታት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ምናልባትም ከፈረንጆቹ በብዙ እጥፍ ወደ አምላካችን ማንጋጠጥ ግድ የሚለን እኛን ነው። በዚህ ረገድ በግላቸው ተነሳሽነት ያላቸውን ማህበራዊ ተሰሚነት ተጠቅመው ህዝባችንን በበሽታው ዙሪያ ለማንቃት እየደከሙ ያሉትን ውድ የሀገሬ ልጆች በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም።
ሰይጣንና ኮሮና ከገዳይነታቸው ባሻገር አንድ ነገር በጣም ያመሳስላቸዋል። ብርታታቸው አለመታወቃቸው ላይ!! ሰይጣን በጣም ደካማ ነው፣ ብርታቱ አለመታወቁና እያታለለ እየሸነገለ በስጋ ላይ ነግሶ ነፍስን ማጥፋቱ ነው።
ኮሮና ቫይረስም ብርታቱና አደገኛነቱ አለመታወቁ ነው። በቻይና መረጃው እንዳይታወቅና እንዳይሰማ ኮሚኒስቶቹ የገዛ ዶክተሮቻቸውን አስረው የቫይረሱ ሰለባ እስከሚያደርጉ ድረስ ጨክነውባቸዋል። የነርሱ ዳፋም ምዕራቡን አለም፣ ሩቅ ምስራቅን፣ አፍሪካን፣ ላቲንን፣ መካከለኛውን ምስራቅ በጠቅላላ እያናወጠ ነው። ይህ ደዌ ከጅምሩ እንዳይታወቅ ያደረጉ ኮሚኒስቶች የኮሮና ባለ ውለታ፣ የትውልድ ባለእዳ ናቸው።
በአውሮፓ በተለይ ሰሜን ጣልያን መንግስታቸው አስቀድሞ ቢያስጠነቅቅም የእለት ተእለት ኑሯቸውንና ወጋቸውን ትተው ለተወሰነ ጊዜ ዋጋ መክፈል ዳገት ሆኖባቸው ይኸው አሁን በዓለማችን ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የቫይረሱ ምት አርፎባቸዋል።
ህዝቤ ስማኝ፣ ለአንድ ወር ከቤት ባትወጣ አትሟሟም፣ ኢትዮጵያዊን ጥጋብ እንጂ ችግርና ረሀብ እጅ አሰጥቶት አያውቅም። በቃ ወጉና ባህሉ፣ ሀይማኖትና እምነቱ ለጊዜው በልብህ ይሁን!!! ቤትህ ክትት በልና ጸሎት አድርግ። ከአምላክህም ከትዳርህም፣ ከቤተሰብህም የተሀድሶ ጊዜ ይሆንልሀል። እጅህን አካላትህን ሙልጭ አድርገህ ታጠብ። ውሀ አይገድልም። ግን ደግሞ የትኛው ውሀ ልትለኝ ነው። ግዴለም ለእጅ የሚሆን አይጠፋም።
ይሄንን በሽታ ሚስጥሩን ካወቅከው ታስወግደዋለህ። 26°c ብቻ ነው የሚቋቋመው። በበጋው ወራት አዳማ ላይ ህይወት የለውም። ሎሚ፣ ዝንጅብል፣ ነጭ ሽንኩርት አድርገህ እያፈላህ ፉት ብትል ናዝሬትን ራሷን ዋጥካት ማለት አይደል!!!
የፖለቲካ ሰዎችና ካድሬዎች አንዳች ማርክ ትሰጠኛለች ብላችሁ ላንቃችሁ እስኪሰነጠቅ ስለ ፖለቲካ የምትበጠረቁ እስኪ አሁን እንኳ ሰው ሁኑ። ሰው መሆን ልክ እንደመታጠብ ነው። አይገድላችሁም።
የሞቀ ውሀ ለብዙ ነገር መድሀኒት ነው። የታሸገ ውሀ እየተሸከምክ ከምትገባ የቧንቧውን ውሀ አሙቀህ ቀምቅም። ኪስህም ስላም ያገኛል። ትራስ ስር አስቀምጠህ ያሻገትከውን ወንጌልና ቁርአን አንብበው። የአምላክ ቃል ቀጥ አድርጎ ያቆምሀል። ይሄ ደዌ ደረጃ አንድ ላይ ከሆነ በአንድ ብርጭቆ የሎሚና የነጭ ሽንኩርት ውህድ የሞቀ ውሀ ድራሹን ታጠፋዋለህ። ደረጃ ሁለትም ግማሽ ግማሽ እድል ይኖርሀል።
ኋላቀር የጤና ፖሊሲ ያላት ሀገር ውስጥ እየኖርን እርስበርሳችን በመሰማመት መደጋገፍ እና የበሽታውን መዛመት መግታት ስንችል ግማሹ በኑሮ ውድነት፣ ገሚሱ የፖለቲካና የስልጣን ቅርሻቱን፣ ገሚሱ የውሸት የሞት ዜና፣ ገሚሱ ቧልት እና ግብዝነትን ይሰብካል። “ ሀገር ማለት ሰው ነው አይደለም ወንዙና ተራራው” እንዳለው ባለቅኔው በእኛ ሞት ላይ ንግድ ለመነገድ፣ ኪሳራና ትርፍ ለማትረፍ ነው ይሄ ሁሉ እሩጫ? በእውነት ዘንድሮ ኢትጵያውያን በጣም ነው የተዛዘብነው። የሰለጠነው ዓለም እውቀቱንና ሀብቱን በጋራ አድርጎ መከላከል ያልቻለውን የኮሮና ቫይረስ እንዴት እኛ በሀሳብ ያልተስማማነው፣ ሀገርን በእያንዳችን ሆድ ልክ የሳፋን ሰዎች በሽታውን እንቋቋማዋለን? የሰሜኑ ፖለቲከኛ፣ የመሀል ሀገሩ ፖለቲከኛ፣ የደቡቡ ፖለቲከኛ በሀሳብ ወድቆ ቢሸነፍ እና ኢትዮጵያን መምራት ባይችል የሀገሩ ዜጋ መሆኑና በጋራ መቆሙን እንዴት ይዘነጋዋል። በዚህ ቀውጢ ወቅት ከህዝብና ከመንግስት ጎን ያልቆመ ሰውም መቼስ ቢሆን ይታመናል። ወንድሞች ትርፍም፣ ኪሳራም፣ ደስታም ሀዘንም በወገን ውስጥ ነው። ሰው ደሴት አይደለም ብቻውን አይኖርም። ይሄን ቀውጢ ወቅት ለማለፍ ብርቱ መደጋገፍና መሠማማት ይጠይቀናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ