የአለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ለሚደረገው ጥንቃቄ እያሳየነው ያለነው ዝግጁነት እንደ ጣሊያን ዋጋ እንዳያስከፍለን እሰጋለሁ። ብዙዎችም ሊመጣ የሚችለውን ችግር ቀድመው በመተንበይ እያስጠነቀቁን ነው። ነገር ግን አፍንጫው ላይ ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚና ጤናዳምን እስከነቅጠሉ አስሮ ከመሳለቅ በዘለለ ንክኪን ለማቆም የደፈረ የለም። ብዙዎቻችን ኮሮና ኢትዮጵያ አይገባም፤ ቢገባም አይጎዳንም የሚል ፌዝ ይዘን እራሳችን እያታለልን ነው። ማታለል ብቻም ሳይሆን ለሚመጣው ሰደድ እሳት ብዙዎችን አሳልፈን እየሰጠን ነው። ኋላ በኮሮና የተያዝኩት በማንነቴነው ምናምን አይሰራም። በሚገርም ሁኔታ ኮሮና የሚባል ነገር እንኳ በኢትዮጵያ በተቀረው የዓለማችን ክፍልም አለ ብሎ የማያምን ብዙ ሰው አለ።
አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ ኮሮናን ለማስደሰት እስኪመስል ድረስ እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ድረስ የሚጮህ የእጅ ሰላምታ ሲለዋወጡ እየተመለከትን ነው። ሌላው ደግሞ ኮሮናን ለመከላከል ከሥራ ቀርቶ ካፌ ሲያሞቅ ይውላል። አንዳንዱ ሥራ አይገባም ነገር ግን በሠራተኞች ማመላለሻ ሰርቪስ ነጠላውን አጣጥፎ ይገባና ቤተክርስቲያን ያሳልፋል። የተቀረው ከመገናኛ እስከ ሜክሲኮ፤ ከአውቶቡስ ተራ እስከ ቃሊቲ ሰው በብዛት የሚሰበሰብበትን እየመረጠ ሲዘዋወር ይውላል። በሽታው ከሚሰራ ሰው ጋር ነው እንዴ ጥሉ? ይህ እኮ አግባብ አይደለም ስትላቸው መልሳቸውና ራሳቸውን የማታለያ መንገዳቸው «ፈጣሪ አለ» የሚል ነው። «ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትፈርስም። ይህ የአውሮፓውያን ሴራ ነው» ብለው ይመልሳሉ። እኔም አምናለሁ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃል። ግን ደግሞ «አትፈታተኑኝ» ብሏል። ክፉ ቀንንና ጥምዝምዝን ማሳለፍ ጎንበስ ብሎ ነው ይባል የለም? ምን ችግር አለው ፈጣሪያችንን እያመንን ቤታችንን ብንዘጋ? ችግሩ ከየትም ይሁን ከየት ማንም ያምጣው ማን የሚጎዳን ከሆነ በመጠንቀቅ ፈንታ ሌሎችን መኮነን አግባብ አይደለም። ቤትን መዝጋት ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል። መጥፎ ከማየትና ክፉ ከመስማት በጥቂቱም ቢሆን ይቆጥበናል። ፈጣሪን መማፀኛ ሰፊ ጊዜም ይኖረናል።
ፈጣሪ ሁሌም አለ። ግን ሰዎች በራሳቸው ስህተትና በማያውቁት ነገር ይሞታሉ። እና የሚሞቱ ኢትዮጵያውያን ፈጣሪ አያውቃቸውም ማለት ነው? ብዙ አታስወሩኝ ከፈጣሪዬ ጋር ታጣሉኛላችሁ። አንዳንድ ሰዎችማ ኮሮናን ደስ ለማሰኘት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ከተጣሉት ሰው ጋርም ሳይቀር ሰላምታ ሳይለዋወጡ አይቀሩም። እናም እላለሁ እባካችሁ መመሪያ እናክብር። የኤሲያ ሀገራት ለቻይና ቅርብ እንደመሆናቸው በከፍተኛ ሁኔታ የመጠቃት ዕድል ነበራቸው፤ እነሱ ግን የበላይ አካላትንና ሕግን የማክበር ጠንካራ ባህል አላቸው። ይህም ጠቅሟቸዋል። መንግሥት ያወጣውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው በሽታው ሳይስፋፋ ብዙም ሳይጎዱ ማለፍ ችለዋል። አያችሁ ቤታቸውን ዘግተው ፈጣሪያቸውን የሚለምኑ እንዲህ ናቸው። እውነት እናውራ ካልን ብልህነት ይህ ነው! ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› በቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ከፈጣሪ ጋር መቀራረብ እንዲሁም ከበሽታው መትረፍ።
‹‹ስንቱን አስታወስኩት ስንቱን አሰብኩት
ልቤን በትዝታ ወዲያ እየላኩት
አንዴ በመከራው አንዴ በደስታየ
ስንቱን ያሳየኛል ይሄ ትዝታየ›› አይደል ያለው መሀሙድ አህመድ ።
መሀሙድን ትዝታው ብዙ ነገርን እንዳሳየው ሁሉ እኔንም ኮሮና ብዙ ፀባይ ያላቸው ሰዎችን አሳይቶኛል። አንዳንድ ሰዎችማ ግርም እኮ ነው የሚደርጉት በግድ ስለ ኮሮና ብዙ እንድታስብ ያደፋፍሩሃል። ጣሊያን በቫይረሱ በጣም ብዙ ሰዎች ሞቱ ሲባል «ኢትዮጵያ ስለወረረች ነው» ይላሉ። ግብፅ ሦስት ጀነራሎቿንና በርካታ ዜጎቿን በበሽታው መነጠቋ ታውቋል ሲል ዜናው ሰው ቀበል ይልና ማን ኢትዮጵያን ተንኩሽ አላት። የማይገባትን የአባይን ውሃ ለምን ለእኔ ብቻ ልጠቀም አለች?…ሲል ይጠይቅና ቀጠል አድርጎም አያችሁ አይደል ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይወዳታል ይላል።
በአንድ የቴሌቪዥን መስኮት ደግሞ በአሜሪካ የሟች ቁጥር ከአንድ ሺ በላይ ደረሰ። በቫይረሱም ከ60 ሺ በላይ ሰዎች ተይዘዋል ሲል ወንድሜ ምን ቢል ጥሩ ነው «አይ ትራምፕ በማያገባህ ገብተህ ሕዝብህን አስጨረስክ አይደል» አለ። ዞር አልኩና ምን ማለት ነው ስለው? «ለምን በግድቡ ዙሪያ ከግብጽ በኩል ወገነ። » ሲል ሳልወድ ፈገግ አልኩ። ስለእውነት ከሆነ ይህ የዋህነት ነው። ፈጣሪ የሁሉም እንጂ ጥቂቶች እንደምናስበው አንዱን ደግፎ ሌላውን የሚበቀል አይደለም። ይህ ሁሉ ምክንያት ድርደራ እራስን ማዘናጊያ ነው። ግን ሁሉንም ትተን እንጠንቀቅ፤ መመሪያዎችን እንተግብር። አሁን ራስን መደለል አቁመን ወደ መጠንቀቁ ካልገባን ተያይዘን ማለቃችን ነው።
በቦሊቪያ ከአንድ ቤተሰብ ከቤት እንዲወጣ የሚፈቀድለት አንድ ሰው ነው። ይህ የሆነው ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ታስቦ ነው። ደግሞም ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን በእዛ ሰው አማካኝነት እንዲያገኙ ነው። በእኛ ሀገርስ ይህ ሕግ ቢተገበር የሚቀበለው ስንቱ ነው? ከእንትና ብሔር ከአንድ ቤተሰብ ሁለት ሰዎች እንዲወጡ ተፈቅዶላቸዋል። የእንትና ሃይማኖት ተከታዮች እንደልባቸው እየተንቀሳቀሱ ነው። እኛ ተከለከልን መብታችን ተነፈገ ብሎ አቤቱታ የሚያቀርብ አይጠፋም። ግን ሁሉም አይሆንም ከሳሽም ተከሳሽም የማይሰማው ኮሮና ቫይረስ ለወሬ ነጋሬ ሳያስቀር እንዳይጨርሰን መጠንቀቁ ይበጃል። በማንነቴና የእንትን ብሔር ተወላጅ በመሆኔ ማለት ኮሮና ላይ ዋጋ የለውም፤ ዋጋ ያስከፍላል እንጂ። እራስን ፃዲቅ ሌላውን ሀጢአተኛ በማድረግ ኮሮናን ማምለጥ አይቻልም። ኮሮና ቫይረስን ማምለጫው ዋና መንገድ የሚሰጡ መመሪያዎችን በትክክል መተግበር መቻል ነው። ከሁሉም በላይ እግራችንን ሰብስበን ደጃፋችንን ዘግተን የኮሮናን ማህበራዊ ተጽዕኖ እንቋቋም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም
ሞገስ ጸጋዬ