በባህሪያቸው ረጋ ያሉ ሰው መሆናቸውን የሚያው ቋቸው ይናገራሉ። ስደት የሚያስከትለውን ችግር ደግሞ በተግባር የተመለከቱ ሰው ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ግን በሚያጋጥሟቸው የተለያዩ መሰናክሎች ላይ ትኩረት አድርገው ከማማረር ይልቅ ተመስገን ብሎ ለተሻለ ሥራ መነሳትን ይመርጣሉ። የሰከነ የሰላም አየር እና ጥሩ የማስተዋወቅ ሥራ የሚፈልገውን የሥራ ዘርፋቸው ከጊዜ ወደጊዜ ለማሻሻል የሚጥሩ ሰው መሆናቸውን ደግሞ አብረዋቸው የሰሩ የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። በሙያቸው አማካኝነት መላ ኢትዮጵያን ተዟዙረው አይተዋል ቢባል ደግሞ ማጋነን አይሆንም።
አቶ ኤርሚያስ ኃይሉ ይባላሉ። አዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት ጀርባ በሚገኘው ትንባሆ ሞኖፖል አካባቢ ነው የተወለዱት። ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ፍሬሕይወት የተሰኘው ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ግን ቤተሰባቸው በሥራ ምክንያት ወደ አዳማ ከተማ በመዘዋወሩ እርሳቸውም አብረው ተጓዙ።
በአዳማ ከተማ ቆይታቸው ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን በአፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በወቅቱ ለሒሳብ ትምህርት ልዩ ትኩረት እንደነበራቸው አይዘነጉትም። ይሁንና የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ቢወስዱም ውጤቱ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አላስቻላቸውምና ፊታቸውን ወደሥራ አዞሩ።
ወደተወለዱባት አዲስአበባ ተመልሰውም በ1979 ዓ.ም ላይ ቃሊቲ አካባቢ የነበረ የግንባታ ሳይት ላይ የሰዓት ተቆጣጣሪ ሆነው መስራት ጀመሩ። አንድ ዓመት ተኩል በሰዓት ተቆጣጣሪነት ካገለገሉ በኋላ ግን ወደአልባሳት እና የተለያዩ ዕቃዎች ሽያጭ ንግድ ተሰማሩ። የተለያዩ አልባሳትን እና ዕቃዎችን ከጅምላ አከፋፋይ ጓደኞቻቸው ላይ ተረክበው ለባለሱቆች እና ለነጋዴዎች በማድረስ መጠነኛ ገቢ ይሰበስቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ሥራ አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ዘመዳቸው ጋር ሄደው ለመስራት በሚል ስደትን ምርጫቸው አደረጉ።
ፓስፖርት አውጥተው ሞያሌ ድረስ በተሽከርካሪ ከተጓዙ በኋላ ወደኬንያ በአውሮፕላን ገቡ። ኬንያ ደግሞ ሌላ ዘመዳቸው ጋር ነበር ያረፉት። የደቡብ አፍሪካ ጉዟቸው እንዲሰምር የተለያዩ ሀገራትን ማቋረጥ እንዳለባቸው የተገነዘቡት አቶ ኤርሚያስ በኬንያ ጥቂት ጊዜ ለመቆየት ቢያስቡም ዓመታትን መቆየታቸው ግን ግድ ሆነ።
በኬንያ የሚገኘው የአክስታቸው ልጅ ጋር አርፈው የኮምፒዩተር አጫጭር ሥልጠና እየወሰዱ የጉዞውን ጉዳይ ሲያመቻቹ ከጊዜ ወደጊዜ የደቡብ አፍሪካው ጉዟቸው ሊሳካ እንደማይችል እየተገነዘቡ መጡ። እናም ኬንያ ላይ ቱር ኤንድ ትራቭል ትምህርትን ለአንድ ዓመት ተከታትለው ስለአስጎብኚነት ሙያው ያላቸውን ዕውቀት ማዳበር ጀመሩ።
በወቅቱ ግን ኬንያ ላይ በአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራሙ ተዘጋጅቶ ሲሸልስ ላይ በሚገኘው ጣቢያው አማካኝነት ዝግጅቶቹን የሚያሰራጭ የክርስቲያን የሃይማኖት ሬዲዮ ጣቢያ ነበር። በሬዲዮው ማዘጋጃ ክፍል ደግሞ ዘመዳቸው ይሰራ ነበርና እርሳቸውን በአንባቢነት እንዲገቡ አደረጋቸው። በዚህም ምክንያት ለሁለት ዓመታት ኬንያ ላይ በአንባቢነት ሬዲዮ ጣቢያው ላይ የመስራት ዕድልን አግኝተዋል። በመጨረሻ ግን የጣቢያው ፕሮግራሞች ማሰናጃ ክፍል ከኬንያ ወደአዲስአበባ እንዲዘዋወር በመደረጉ አቶ ኤርሚያስም አዲስ አበባ መጥተው በተማሩበት መስክ አስጎብኚ ድርጅት ውስጥ ለመስራት ይወስናሉ።
ለሦስት ዓመታት የዘለቀውን የኬንያ ቆይታቸውን አጠናቀው በ1992 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የግል አስጎብኚ ድርጅት ውስጥ በቱር ኦፕሬሽን ባለሙያነት ተቀጥረው መስራት ጀመሩ። ይሁንና አቶ ኤርሚያስም ለሁለት ወራት በድርጅቱ እንደቆዩ ጣልያናዊው የአስጎብኚ ድርጅቱ ባለቤት እና ወኪል ሆኖ ከሚሰራ ሰው ጋር በመጋጨታቸው አለመግባባት ተፈጠረ፤ በመጨረሻም ድርጅቱ ተዘጋ። አቶ ኤርሚያስም ወደክራውን ሆቴል ተዘዋወሩ። በክራውን ሆቴል የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ኤጀንት ሆነው መስራትም ጀመሩ። በተለይ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ሰዎች በክራውን ሆቴል አርፈው እንዲስተናገዱ የማስተዋወቅ እና የማግባባት ሥራቸው ከብዙ የውጭ ሀገራት ሰዎች ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል ፈጠረላቸው።
በሆቴሉም የምሽት ማናጀር ሆነው አገልግለዋል። በትርፍ ሰዓታቸው ግን የውጭ ዜጎችን እያነጋገሩ የከተማ ጉብኝት ማዘጋጀት ጀመሩ። በሆቴሉ የሚቆዩ ጥቂት ሰዎችን አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚገኙ ሙዚየሞችን እና ታሪካዊ ስፍራዎችን እያስጎበኙ ለአንድ ዓመት በተጓዳኝነት ሰሩ። በዚህ ወቅት ታዲያ ወደሆቴሉ ከሚመጡ የቱር ኦፕሬተሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥረው ነበር። የቱር ኦፕሬተርነት ትምህርት መውሰዳቸውን እና ፈጣን መሆናቸውን የተገነዘበ አንድ ሰው ኤባ የተሰኘ አስጎብኚ ድርጅት ውስጥ እንዲገቡ እርሳቸውን ጠቆመ።
ኤባ አስጎብኚ እና የጉዞ ወኪል ድርጅትን ተቀላቅለው ከቱር ኦፕሬተርነት ጀምሮ እስከ ቱር ኦፕሬሽን ማናጀርነት በማገልገል መላ ኢትዮጵያን ተዟዙረው የመጎብኘት ዕድል አግኝተዋል። ለ10 ዓመታት በድርጅቱ ሲሰሩ ከተለያዩ የውጭ ዜጎች ጋር ታሪካዊ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል፤ ቢሮ ውስጥም ሆነው የጉዞ፣ የሆቴል እና ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎችን በማቀናጀት ጥሩ ልምድ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
በድርጅቱ በሚሰሩበት ወቅት ግን ልምዳቸውን ከማካበት ባለፈ ጥቂት ጥሪትም መቋጠር ጀምረው ነበርና ኑሯቸውን የሚደጉሙበት ሚኒባስ ተሽከርካሪ ገዙ። እየሰሩ ቁጠባቸውን በማጠናከርም የሚኒባሶቻቸውን ቁጥር ሁለት አደረሱ። ከዚህ በኋላ የግላቸውን ሥራ መጀመር እንዳለባቸው ከባለቤታቸው ጋር ምክክር ማድረግ ጀመሩ። ከስምንት ዓመታት በፊትም እንጦጦ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ብለው የሰየሙትን ድርጅት ከፈቱ።
አስፈላጊውን ፈቃድ አሟልተውም ሚኒባሶቻቸውን ለድርጅታቸው ሥራ አውለዋቸዋል። አዲስ አበባ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ አንዲት ጠባብ ቢሮ በሦስት ሺህ ብር ተከራይተው እና የድርጅታቸውን ሥራ በዓለም የሚያስተዋውቅ ድረ-ገፅ ከፍተው እንግዶቻቸውን መጠባበቅ ጀመሩ። የተለያዩ በራሪ ጽሑፎችን እና ማስታወቂያዎችን አዘጋጅተውም ቀድሞ በሥራ ላይ እያሉ ለሚያውቋቸው አስጎብኚዎች እና ከሥራው ጋር ግንኙነት ላላቸው ሰዎችም የግል ሥራ ስለመጀመራቸው በሰፊው አስተዋወቁ።
የግል ሥራ ከፍተው አንድ ወር እንደቆዩ ደግሞ ከወደኬንያ ቸር ወሬ ደረሳቸው። ኬንያ እያሉ የሚያውቃቸው አንድ «የውጭ ሀገር ዜጋ» አስጎብኚ ድርጅት መክፈታቸውን ሰምቶ አስር የውጭ ሀገራት ጎብኚዎችን ይዞ ሊመጣ መሆኑን በኢሜይል አበሰራቸው። አቶ ኤርሚያስም ዕድሉን በአግባቡ ተጠቀሙበት። አስፈላጊውን የጉዞ፣ የሆቴል እና የጉብኝት መርሃ ግብሮች በማቀናጀት የውጭ ዜጎቹን ኢትዮጵያ ላይ አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።
ጉብኝቱ በአውሮፕላን ነበርና አክሱም፣ ላሊበላ እና ጎንደር ላይ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ቀድመው የሚያውቋቸውን በየአካባቢው የሚገኙ አስጎብኚዎችን መድበው፤ ጥሩ የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤት መሆናቸውን አስመሰከሩ። አብዛኛዎቹ ጎብኚዎች ደግሞ ከኖርዌይ ሀገር የመጡ ነበሩና ወደሀገራቸው ሲመለሱ የአቶ ኤርሚያስን ድርጅት ሥራ በማስተዋወቅ በርካታ ኖርዌጃውያን ወደኢትዮጵያ ሲመጡ በእንጦጦ አስጎብኚ አማካኝነት እንዲስተናገዱ መልካም አጋጣሚን ፈጠሩ።
አቶ ኤርሚያስም ከዕለት ዕለት ግብዓቶችን እያሟሉ እና የውጭ ምንዛሬም ለሀገር እያስገቡ አምስት ዓመታትን ካገለገሉ በኋላ ያረጁ ሚኒባሶቻቸውን ወደመቀየሩ ተሸጋገሩ። ዱባይ ድረስ ተጉዘው ለሥራቸው የሚሆኑ ሁለት ዘመናዊ ሚኒባስ ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት ድርጅታቸውን ማዘመኑን ተያያዙት።
ሁሉም ጎብኚዎች በቆይታቸው ወቅት ስለኢትዮጵያ መልካምነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው የበኩላቸውን መወጣታቸውን ያስረዳሉ። በድርጅታቸው አማካኝነት በብዛት የተስተናገዱ የውጭ ዜጎች ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ በተለይም ከእስካንዴኔቪያን ሀገራት የመጡ ጎብኚዎችን መሆናቸውን ይናገራሉ።
ለስምንት ዓመታት በዘለቀው የግል አስጎብኚ ድርጅት ሥራቸው የቱሪዝም ሥራ ፈተና የሚበዛበት ነውና ብዙ ትርፍ ያገኙበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ በተቃራኒው ሥራ የጠፋበት ወቅትም እንዳለ ይናገራሉ። በተለይ ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በየአካባቢው በነበረው አለመረጋጋትና እና አሁን ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሥራው ክፉኛ እንደተጎዳ ያስረዳሉ። ይሁንና ኮሮና ሁሉም ሀገር የተከሰተ ችግር በመሆኑ ሲቀረፍም ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ብቻ ተብሎ የተለየ ሥራ የማያስፈልገው ዓለም አቀፍ ችግር በመሆኑ በቀጣይ ሥራው እንደሚነቃቃ ተስፋ አድርገዋል።
ግጭት በነበረበት ወቅት ግን ብዙ ጎብኚዎች ለመምጣት ፍላጎት የማያሳዩ በመሆኑ ችግሩ መስተካከሉን ለማሳየት እና ለማስተዋወቅ ሰፊ አቅም እንደሀገር ያስፈልግ እንደነበር ይገልጻሉ። አቶ ኤርሚያስ ችግር መጥቷል ብለው ግን እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ይልቁንም ድርጅታቸውን ሊያስፋፉ የሚችሉባቸውን አማራጮች በማስፋት ላይ አተኩረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት የሊዝ ፋይናንስ ብድር ዕድል በመጠቀም ሦስት ላንድ ክሩዘር የመስክ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበዋል። ጥያቄያቸው ሂደት ላይ ቢሆንም ተሽከርካሪዎቹን የማግኘት ዕድል ካላቸው ነገ ላይ ለኢትዮጵያም ሆነ ለእርሳቸው ሰፊ የውጭ ምንዛሬን እንደሚያመጣላቸው እምነት ጥለዋል፡፡
ከአንድ የውጭ ዜጋ ጋር በጋራ በመስራት ኢትዮጵያ ውስጥ በ20 ሚሊዮን ብር የሎጅ ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል ጥናት ላይ ናቸው። ሎጁ እውን ሲሆን የበለጠ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገባ እና የቱሪዝም ዘርፉን የሚያሳድግ እንደሚሆን ተስፋ ሰንቀዋል። የአቶ ኤርሚያስ ድርጅት አሁን ላይ ላፍቶ አካባቢ መዳረሻውን ባደረገው ቢሮ ስር በቋሚነት አምስት ሰዎችን ቀጥሮ የሚያሰራ ቢሆንም ሥራ በሚገኝበት ወቅት ግን በየአካባቢው ከሚገኙ አስጎብኚዎች እና ተሳታፊዎች ጋር 15 ጊዜያዊ ሠራተኞችን የማሳተፍ አቅም አለው። የሎጂ ግንባታ ሲጨመር ደግሞ ለተጨማሪ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል።
«እኔ በአምላክ እርዳታ ከስደት ተመልሼና ልምድ አካብቼ፤ ለሌሎችም የሚተርፍ ሥራ በመጀመሬ ደስተኛ ነኝ» የሚሉት አቶ ኤርሚያስ፤ ማንኛውም ሰው የሚያዋጣውን የሙያ ዘርፈ ፈልጎ ጠንክሮ ከሰራ የማይለወጥበት ምክንያት እንደሌለ ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው፤ አንዳንዶች ሰርቶ መለወጥ የሚቻለው ለተመረጡ እና ለሆነላቸው ሰዎች ብቻ ነው የሚል አመለካከት ይዘው እራሳቸውንም ሀገራቸውንም ይጎዳሉ። ይህ አስተሳሰብ ግን ፈጽሞ የተሳሳተ እና ለችግር የሚያጋልጥ በመሆኑ ማንኛውም ወጣት በሚችለው መልኩ ዛሬን በሥራ ካሳለፈ ነገላይ የሥራውን ፍሬ ሊያገኝ እንደሚችል የእርሳቸው ሕይወት ምስክር ነው። አዲስ ዘመን መጋቢት 19 / 2012
ጌትነት ተስፋማርያም