አፍሪካን እስከነ አካቴው ለመቀራመት የተወሰነበት የጀርመኑ ጉባኤ (1884-1885) ሲሆን እሱን ተከትሎም እንዴት አህጉሪቱን መቀራመትና “ማሰልጠን” እንዳለባቸው 13 የአውሮፓ ሃያላን የተፈራረሙት የመተግበሪያ ሰነድ (The Berlin Act of 1885) ለዚህ ሁሉ ደባና የጥቁር ህዝብ ሰብአዊ መብት ጥሰት መነሻዎች ናቸው።
እንደሚታወቀው አፍሪካ በሃያላን ጉዳዮች ውስጥ አንዳችም ጥልቅ የሚያደርግ ጉዳይ የላትም። እንኳን የሰው ድንበር ጥሳ አገር ልትወርና ልትዘርፍ የራሷንም ለመከላከል ሳትችል የቀረች እንደነበረች ይታወቃል። በ1960ዎቹ ነው ነጮቹን ከተደላደሉበት ወንበራቸው መነቅነቅ፤ መፈንገል የጀመረችው። ደቡብ አፍሪካን ለ300 ዓመት የገዛው አፓርቲይድ ሳይቀር ዞር በል የተባለው ገና አሁን በ1990ዎቹ ነው።
የዛሬው አቢይ ጉዳያችን አፍሪካ በማያገባት፣ በማይመለከታት፣ ፍፁም የእሷ ባልሆነ ጉዳይ እየገባች ፍዳዋን ስታይ የምትኖርበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ሲሆን፤ ለዚህም በማይመለከታት የአንደኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ተሳትፋ የከፈለችውን ያልተፈለገና ከድሉም በኋላ ምንም አይነት ምስጋናና እውቅና እንኳን ያልተቸረውን ታሪክ ለማስታወሻ ያክል ማንሳት ነው።
‘ጦርነቶችን ሁሉ ሊያስቆም የሚችል ጦርነት /A war to end all wars’ የተባለለት አንደኛው የዓለም ጦርነት አፍሪካውያን በቀኝ ገዥዎቻቸው አማካኝነት በማይመለከታቸው ጦርነት ውስጥ እንዲማገዱ አድርጓል። ከ1914 እስከ 1918 (1915 እና 1916 ሁሉም ነገር እጅግ የከፋባቸው ሁለት ዓመታት ናቸው) ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ፈረንሳይ የጀርመንን ጦር ይዋጉ ዘንድ ከምእራብና ከሰሜን አፍሪካ 450,000 አፍሪካውያንን (troops) በመላክ ማግዳለች።
ይህ ብቻ አይደለም፤ በዚህ በ1914 የተጀመረው ጦርነት 70,000 አውሮፓዊ ደቡብ አፍሪካውያን (European South African)፤ በአጠቃላይ በአህጉሪቱ ሶስት የጦርነት ቀጠናዎች 135,000 የአፍሪካ ወታደሮች የዘመቱ ሲሆን፤ የእነዚህን 10 እጥፍ (1,465,000 አካባቢ) የሚሆኑ የጉልበት ሰራተኞች የጦር ስንቅ በማቀበልና በመሳሰሉት ስራ ላይ ተሰማርተው አልቀዋል። ሌላውና በ”African Theatre” በሚል ስያሜ የሚታወቀው (… ካሜሩን፣ ቶጎላንድ፣ ጀርመን ደቡብ ምእራብ አፍሪካ እና ጀርመን ምስራቅ አፍሪካ ያካተተው) ሲሆን ይህም የየአካባቢው ነዋሪዎች ከቅኝ ገዥዎች ጋር የተካሄደውን ጦርነት የሚገልፅ ስያሜ ነው። በድርጊቱም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ቤልጂየም እና ፖርቹጋል ሲሆን ሁሉም አፍሪካውያንን አስጨርሰዋል።
እንግሊዝ ጦሯን ያዋቀረችው ከአፍሪካ በአስገዳጅነት በመለመለቻቸው አፍሪካውያን ወታደሮች ሲሆን፤ በተለይም ከናይጄሪያ፣ ጎልድ ኮስት (የዛሬዋ ጋና)፣ ሴራሊዮን፣ ጋምቢያ፣ ዩጋንዳ፣ ኒያሳላንድ (የዛሬዋ ማላዊ)፣ ሮዴዥያ (ዚምቧቡዌ) እና ከኬኒያ በከፍተኛ ቁጥር አግዛ ማግዳለች።
ፈረንሳይ ብቻ በቅኝ አገዛዝ ወጥመዷ ስር ከጣለቻቸው አፍሪካ (ከምእራብና ሰሜን) አገራት ጀርመንን እንዲወጉላት 450,000 በጦርነቱ የመጀመሪያው ረድፍ (frontline) አሰልፋለች። ከ10,000–15,000 ከአፍሪካ የተመለመሉ ወታደሮች የደረሱበትም ሆነ ስለማንነታቸው/ ዜግነታቸው እስካሁን ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። የፍራንኮ-ቤልጂያን ወታደሮች ተብለው የሚታወቁትና በጀነራል ጆሴፍ አይመሪች ከሚመሩት መካከል 1,685 በጦርነቱ ሲያልቁ፤ 117 ያህሉ ደግሞ ባልታሰበ፣ አፍሪካዊ ባልሆነና ከውጪ በገባ በሽታ (ኢንፍሉዌንዛና ሌሎች) ምክንያት አልቀዋል።.
የጆን ኢሊፌ ጥናት እንደሚነግረን ጀርመን በ1916 ብቻ 15,000 አካባቢ ወታደሮችን ያዘመተች ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ጀርመናውያኑ 3ሺህ ብቻ ሲሆኑ 12,000ዎቹ ስማቸው እንኳን ያልተመዘገበላቸው ታንዛናውያን ናቸው።
የF. J. Moberly “Togo and the Cameroons” ጥናት እንደሚነግረን በአንደኛው የዓለም ጦርነት የአንድ እለት አውደ ውጊያ ላይ ከተሰማሩት ወታደሮች መካከል 11,596 ያህሉ አፍሪካውያን ናቸው፡፡ ከ10,000–15,000 የሚሆኑት ከአፍሪካ ተመልምለው የተወሰዱ ሲሆን እስካሁን ስለ እነሱ ያወራም ሆነ ማንነታቸውንና ዜግነታቸውን እንኳን የተናገረ የለም።
አፍሪካ ምንም በማታውቀው ምክንያት ስትቀጣ ኖራለች ስንል ዝም ብለን አይደለም፤ ጀርመን በያዘቻቸው ምስራቅ አፍሪካ (German East Africa) ከ10–20 በመቶ፤ ከሰሀራ በታች (ኢትዮጵያን አይጨምርም) ከ1,500,000– 2,000,000 ወገኖች በተለያዩ ወረርሽኞች (epidemic እና pandemic) ምክንያት አልቀዋል።
ስትራቻን (2001) እንዳሰፈረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን፣ የአፍሪካን 30% ህዝብ በቅኝ አገዛዝ ክንዷ የተቆጣጠረችው እንግሊዝ በምስራቅ አፍሪካ ባካሄደችው ጦርነት 100 ሺህ 002 ወታደሮች ሲሞቱ ከእነዚህ መካከል 90,000 ያህሉ በቅኝ ግዛት ከያዘቻቸው አገራት የመለመለቻቸውና ያዘመተቻቸው አፍሪካውያን ወታደሮች ናቸው። ፓይሴ (2007) በበኩሉ በ1917 1,000,000 የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች እንዲጠፉ መደረጋቸውን ጠቅሷል፡፡
ኦስዋልድ ማሴቦን ከጠቀሰውና “The African soldiers dragged into Europe’s war” በሚል ርእስ ከተዘጋጀው የቢቢሲ ጥናት እንደምንረዳው በመጀመሪያው የአለም ጦርነት ከምስራቅ አፍሪካ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን በጦርነቱ አልቀዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ አፍሪካ ተገቢው ዋጋ ሊከፈላት ቀርቶ ተገቢውን ምስጋና እንኳን አለማግኘቷ የብዙዎች ቁጭት እንደ ሆነ ዛሬም ድረስ አለ። (ብዙዎች እንደሚያምኑበትና እንደሚነግሩን የአንደኛውንና ሁለተኛውን የዓለም ጦርነቶች ሰንዶ በመያዝ በኩል የቢቢሲን አርካይቭ፤ በተለይም “Imperial War Museums”ን የሚያክል የለምና እድሉን ላገኘ እሱን መጎብኘት ተገቢ ነው።)
አንደኛው የዓለም ጦርነት እጅግ ዘግናኝ ነበር። ግዛቶች ተጨፍልቀዋል፤ ሩሲያን የመሳሰሉ አገራት በአብዮት ተጥለቅልቀዋል፤ አሜሪካ የዓለም የልእለ ሀያልነት ቦታዋን ወደ መያዝ ደረጃ መጥታለች፤ እንግሊዝ ገለልተኝነትን የመረጠችበት ዘመን፤ ሩሲያና ፈረንሳይ በአንድነት የተደመሩበት፤ በጀርመን መርዛማ ጋዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ ያዋለችበትንና 1000 የራሺያ ወታደሮችን የጨረሰችበት፣ 3 ጃንዋሪ 1915፤ 25 April 1915፣ 7 ሜይ 1915፣ 27 ጃንዋሪ 1916፣ 21 ፌብሯሪ 1916 የተካሄዱ ውጊያዎችን ብቻ እንኳን ስንመለከት ጦርነቱ ምን ያህል አስከፊ፣ ውስብስብና እውነትም የዓለም ጦርነት እንደነበር ይገልፅልናል።
የ”The Gallipoli campaign” የተካሄደበትን 25 ኤፕሪል 1915፤ ጁላይ 18 1918 “Hundred Days Offensive.” በሚል በአሜሪካ የበላይነት የተከናወነውን ድል፣ በመጀመሪያው ቀን ብቻ 20,000 የእንግሊዝ ወታደሮች ያለቁበትን ጁላይ 1916፤ አፍሪካውያን ፀረ- ቀኝ አገዛዝ ተጋድሎ ያደረጉባቸው – Volta-Bani War, 1915–1917፤ ማርች 8 1917 በሩሲያ ከፍተኛ ህዝባዊ አመፅ በመነሳቱ፣ በኖቬምበር ወር በሌኒን የሚመራው ቦልሼቪክ በ”ሰላም፣ ዳቦ፣ መሬት” መፈክር ተመርቶ ስልጣን መያዙን ተከትሎ ሩሲያ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወጣች። ይህም ለጀርመኗ በምስራቅ አውሮፓ በከፍተኛ ደረጃ የመንሰራፋት እድልን ማጎናፀፉ ሁሉ ጦርነቱና ዘመኑን ልዩ ያደርጉታል።
በዚህ ጦርነት ውስጥ አንዴ ሲገጥሙ አንዴ ሲጋጠሙ የምናገኛቸው አገራት በርካታ ሲሆኑ ጀርመንና እንግሊዝም የዚሁ አካል ናቸው። እነዚህ ሁለቱ አገራት ሲዋጉ አውደ ውጊያቸው ያደረጓት ፈረንሳይ ሳትሆን አፍሪካዊቷ ቶጎ ነበረች። በመሆኑም ጦርነቱ ቶጎን አይሆኑ ያደረጋት ሲሆን ዝቅ ብለን እንደምናየው ዜጎቿንም የጦርነቱ ሰለባ አድርጎ አልፏል።
በ1917 በሩዋንዳ ብቻ በተለያዩ ጦርነቱ ባስከተላቸው ምክንያቶች ከ300,000 በላይ ንፁሀን /ሲቪሊያንስ/ አልቀዋል። እንግሊዝ በያዘቻቸው ምስራቅ አፍሪካ (British East Africa) ከ160,000 እስከ 200,000፤ በደቡብ አፍሪካ ከ250,000–350,000፤ ንፁሀን ዜጎች ረግፈዋል። ታዲያ በጦርነቱ ማነው የተዋጋው? ማንስ ነው ያሸነፈው ይላሉ?
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ግርማ መንግሥቴ