«ቡና መጠጣት ያለው የጤና በረከት»፣ «ሙዝ መመገብ የሚኖረው ጥቅም»፣ «በሞቀ ውሃ በየቀኑ መታጠብ ለጤና የሚኖረፍ ፋይዳ»፤ «ፎርፎርን ለማጥፋት በቤት ውስጥ የሚሰሩ መድሃኒቶች»፣«ብጉርን በቀላሉ ለማጥፋት የሚረዱ ቅጠሎች»፣«የጥቁር አዝሙድ የጤና በረከቶች»…ወዘተ እየተባሉ በድረገጽ የሚለቀቁ መረጃዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ከብዛታቸው አልፎም እርስ በርሳቸው የሚጋጭ ሃሳብ ያላቸው ናቸው። በርግጥ የጤና በረከት ስለመሆናቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ የላቸውም።
በማህበራዊ ድረገጾች የሚለቀቁት የመድሃኒቶች ጥቅማቸው እንጂ የሚያስከትሉት ጉዳት፣ ተመጣጣኝነታቸው አብሮ ባለመጠቀሱ በርካቶች ለጉዳት ይዳረጋሉ። ታዲያ ይህ እንዳይሆን ምን ይደረግ? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሆኗል።
በጅማ ዩኒቨርስቲ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል የምርምር ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሱልጣን ሱሌይማን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በድረገጽ መድሃኒት እንዲተላለፍ በአዋጅ፣ በፖሊስም ሆነ በህግ ደረጃ የተደነገገ ነገር የለም። በመሆኑም ማንም እንደፈለገው በመጣለት ልክ መድሃኒቶችን ያስተዋውቃል። ይህ ደግሞ ጠቃሚና ወሳኝ የመድሃኒት መረጃዎችን በትክክል ለመለየት ያስቸግራል።
የሚደነግግ ህግ ባለመኖሩ ተአማኒ ምንጮች በራሳቸው የማይታመኑበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ደግሞ በጤና ላይ አደጋ የሚያደርሱ መድሃኒቶች እንዲበራከቱ በር እንደሚከፍቱም ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ መድኃኒት አስተዳደርና ፕሮክላሜሽን አዋጅ 1/2009 ላይ በድረገጽ ላይ የሚተላለፉ መድኃኒቶችን በተመለከተ ምንም አይነት ማብራሪያ አይሰጥም። በዚህም ህብረተሰቡ ራሱን የሚጠብቅበት መስመር ካልዘረጋለት ካለጥንቃቄ መጠቀሙ ስለማይቀር ችግር ማስከተሉ አይቀርም ይላሉ።
ህበረተሰቡ በተለምዶ የሚከተላቸው ነገሮች በመኖራቸው በተለይም ማህበረሰቡ መድኃኒቶችን ሲመርጥ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚወጡ፣ ከታዋቂ ባለሙያዎች የሚመከሩና ተያያዥ ችግሮቻቸው በደንብ የተገለጠ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም የድረ ገጽ መድሃኒት አምኖ መጠቀም እንደሌለበት ያሳስባሉ።
«በአገር አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ናቸው ተብለው የሚያገለግሉ ድረገጾችም ቢሆኑ ገቢ ለማግኘት እስከቆሙ ድረስ የመድኃኒቱን ፈዋሽነት የሚያጣጥሉበት ሁኔታ አይኖርም» የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሱልጣን፤ አይደለም በድረገፆች የሚተዋወቁትን ይቅርና በትልልቅ ገበያዎች ውስጥ ገብተው ማህበረሰቡን እያታለሉ እንደሆነ በጥርስ ሳሙና ብቻ መመልከት በቂ መሆኑን ለአብነት ይጠቅሳሉ። ስለሆነም ህብረተሰቡ ከመጭበርበር ራሱን መጠበቅ አለበትና ያለባለሙያ ምክር ምንም አይነት መድኃኒት መጠቀም እንደሌለበት ያሳስባሉ።
ማንኛውም በድረገጽ ላይ የሚለቀቁ መረጃዎች የራሳቸው የሆነ ህግ ሊኖራቸው ይገባል። ለአብነት የአውሮፓ መድኃኒት ኤጀንሲና የአሜሪካው «ኤፍዲኤ» መድኃኒቶች በድረገጾች ሲተዋወቁ ማሟላት ያለባቸውን ጉዳዮች ያስቀምጣሉ። ችግር ሲፈጠርም ተጠያቂ ያደርጋሉ። ይህ አሰራር በአገራችን ባለመኖሩ በድረገጽ የሚለቀቁ መድኃኒቶችን አለመጠቀሙ ይመረጣል። ካልሆነ ግን ማህበረሰቡ ፈዋሽነታቸው ባልተረጋገጡ መድኃኒቶች ምክንያት ለካንሰር፣ ለልብ፣ ለኩላሊት፣ ለጨጓራና መሰል በሽታዎች ሊጋለጥ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
በድረ ገጽ የሚለቀቁ መድኃኒቶች እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑና የሚምታቱ ናቸው። ይህ ደግሞ ተጠቃሚውን ውዝግብ ውስጥ ይከተዋል። በዚህም ማንኛውም መድኃኒት ያለህክምና ትዕዛዝ መጠቀም ተገቢ አይደለም። መጠቀም አለብን ብሎ ከታመነ ደግሞ የምናውቀው ልክና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን ድረገጾች ብቻ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ።
«መድኃኒቶችን በኩሽና፣ በምግብ አቅራቢያ፣ በማይክሮዌቭ ምድጃ፣ ምግብ ማብሰያ እና ሌሎች በኤሌክትሪክ ወይም በጋዝ እቃዎች አካባቢ ማስቀመጥ በጥብቅ የተከለከለ እንደሆነ መድኃኒቶችን ቤት ውስጥ ለማከማቸት በወጣው ህግ በግልፅ ተቀምጧል። አንድ እሽግ እና መመሪያዎችን በግልፅ ከተጠቀሰ ስም ጋር፣ ጊዜው የሚያልፍበት ቀን፣ የመጠን እና የማከማቻ ሁኔታዎች ሊኖረው እንደሚገባም ህጉ ይናገራል። ይሁንና በድረገጽ የሚለጠፉ መድኃኒቶች ግን ከዚህ ማሳሰቢያ የራቁ ለመሆናቸው በተለያየ ጊዜ የሚያዙ መድኃኒቶች አብነት ናቸው። የሚቀመጡባቸው እቃዎችም ከውጫዊ ሁኔታዎች የበለጠ ተከላካይ መሆን እንዳለባቸው መመሪያ ቢኖርም ተጠቃሚውንም ሆነ መልዕክት አስተላላፊው ይህንን ሳያስብ ነው ተግባራዊ የሚያደርገው ስለዚህም መረጃ መውሰድ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል» የሚሉት ደግሞ በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታቸው በቀለ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በድረገጾች ላይ በሁለት መልኩ የመድኃኒት አይነቶች ሊቀርቡ ይችላሉ። የመጀመሪያው ሙሉ ገለጻ የሚይዙና አምራቻቸው የሚታወቁ ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ለማስታወቂያና ገቢ መሰብሰቢያ ተብለው ብቻ የሚለጠፉት ናቸው። በዚያው ልክ ዘመናዊና ባህላዊ የመድኃኒት አይነቶች ተግባራቸው ሊለያይ ይችላል። ስለሆነም አጠቃቀሙም በዚያው ልክ ልዩነት እንደሚኖረው ያብራራሉ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ ዘመናዊ የሚባሉትን መድኃኒቶች በድርጅታቸውና በሚደረገው ገለጻ መጠቀም የሚቻልበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ይህ እንኳን ባይሆን ድርጅቱ ስለ መድኃኒቶቹ ሰፊ ማብራሪያ ስለሚሰጥ ድረገጹን በመክፈት ተያያዥ ችግሮችን ማንበብና መጠቀም ይቻላል። ነገር ግን በባህላዊ መድኃኒቶች ላይ ሰፊ ክፍተት ሊታይ ይችላልና በሚገባ የሚታወቁትን መምረጥ ቀዳሚ ምርጫ መሆን አለበት። በድረገጾች ስለተነገረና በማስታወቂያ ስለተላለፈ ብቻ መድኃኒቶች ናቸው ብሎ መውሰድ ጤናን ሊያጓድል እንደሚችልም ይናገራሉ።
በባህላዊ መንገድ እንድንጠቀምባቸው በድረገጾች የሚለጠፉ መድኃኒቶች የመጀመሪያው ጉድለታቸው ተጠቃሚው ምን ያህል መጠን እንደሚጠቀም አለመንገራቸው ነው፤ ከዚያ በፊት የተጠቃሚው ጤንነት ምን እንደሚመስልና ህመሙ ያለበት ሰው መጠቀም የሌለበትን የሚጠቅስ መመሪያም አይሰጡም። በተመሳሳይ ተጠቃሚው በምን መልኩ መድኃኒቱን ማስቀመጥና በምን ያህል ጊዜ መጠቀም እንዳለበትም ማብራሪያ የላቸውም። ይህ ደግሞ በተለይም ይህንን ሳያገናዝቡ ለሚጠቀሙ ሰዎች አደገኛ የጤንነት ቀውስ ውስጥ እንደሚከተው ይናገራሉ።
በድረገጽ ብቻ ተመርቶ ያለ ባለሙያ እገዛ መድኃኒቶችን መጠቀም ለቆዳ ህመም፣ ለአንጀት ቁስለት፣ ለኩላሊትና መሰል በሽታዎች ያጋልጣል የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ማህበረሰቡ ሳያውቀው ማንኛውንም በድረገጽ ያለ መድኃኒት መጠቀም እንደሌለበት ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 5/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው