
አዲስ አበባ፡– የአኅጉሪቱ ወጣቶች በኢኮኖሚ፣ በልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚተሳሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።
አቶ አደም ፋራህ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሔድ የቆየው የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም ትናንት የማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ሲካሄድ እንዳሉት፤ ፎረሙ ለአፍሪካ ወጣቶች ዘላቂና ትርጉም ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያመላከተ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገሮች በልማት በሚተሳሰሩባቸው ምቹ ሁኔታዎች ላይ በትኩረት እየሠራች ትገኛለች። በተለይም የአኅጉሪቱ ወጣቶች በልማት፣ በኢኮኖሚና በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚቀናጁበትን ሁኔታ ማመቻቸት አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።
አፍሪካውያን የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ በክህሎት ልማት፣ በሥራ ፈጣሪነት፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በትብብር ልንሠራ ይገባል ያሉት አቶ አደም፤ የሥራ ዕድል ፈጠራን በመንግሥት አቅም ብቻ ማስፋፋት ስለማይቻል የግሉ ሴክተር፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ወጣቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በፈጠራ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሥራ ዕድልን ለማሳደግ የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ አመልክተው፤ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችም የወጣቶችን፣ የሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
አቶ አደም እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ ትልቁ ሀብት መሬቷ ብቻ ሳይሆን፤ የፈጠራ አቅም፤ አይበገሬነት፤ እና አጠቃላይ የሕዝቡ አቅም የሚያካትት ነው፡፡ በኢትዮጵያም በክህሎት ልማት፤ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በጥቃቅን እና አነስተኛ እና በተለያዩ ዘርፎች ለውጤታማ የሥራ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
አንድ ሀገር ለብቻው ፍላጎቶቹን እንደማያሟላ በኢትዮጵያ በኩል ግንዛቤ መኖሩን አንስተው፤ ከዚህ አንጻር የሥራ ፎረሙ አኅጉራዊ አንድነት እና ትስስር ትልቅ አቅም እንዳለው በተለያየ መልኩ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ራስን ከመቻል እና ለውጭ ገበያ ከማቅረብ አልፋ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ ለመሆን በቅታለች፡፡
የግብርና በአፍሪካ የኑሮ መሠረት እና የአኅጉሪቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም 60 በመቶ የሚሆነው የሥራ ዕድል የሚፈጠረው በግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያም ግብርና ለአጠቃላይ ሀገር ውስጥ ምርት 32 በመቶ እንዲሁም፤ 65 በመቶ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የግብርናን ምርታማነት ለማሳደግ የተንዛዛ የገበያ እሴት ሰንሰለት፤ የተከፋፈለ የእርሻ መሬት እና የአየር ንብረት ለውጥ እንደ ትልቅ ተግዳሮቶች መሆኑን አመልክተው፤ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እና ለአርሶና አርብቶ አደሩ የገበያ ዕድል ለመፍጠር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ እንደ አኅጉር በጋራ መወያየት በሥራ ዕድል ፈጠራ አማካኝነት ለማምጣት የታሰበው የጋራ የብልፅግና ግብ ለማሳካት ይረዳል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደግብ የተያዘ ሲሆን፤ ለዚህም የወጣቶችን አቅም እና ክህሎት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ በውይይቱ ለተሳተፉ እና ፎረሙን ለማዘጋጀት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዓመለወርቅ ከበደ
ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም