ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ 91 ቢሊዮን ብር ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ አውጥቷል

አዲስ አበባ– ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ከያዘው 230 ቢሊዮን ብር በጀት 91 ቢሊዮን ብር ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ማውጣቱን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ አስታወቁ፡፡

ወይዘሮ እናትዓለም እንደተናገሩት፤ በከተማዋ የተከናወኑት ፕሮጀክቶች ኅብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜያት በውይይት ወቅት ሲጠይቃቸው የነበሩ ናቸው፤ የልማት ሥራዎቹ የኅብረተሰቡ ፍላጎት ከመሆናቸውም ባሻገር ለከተማዋ አስፈላጊ መሆናቸው በጥናት ተለይቶ የተከናወኑ ናቸው። በከተማዋ በበጀት ዓመቱ በርካታ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፤ ለዚህም 91 ቢሊዮን ብር ወጥቷል፡፡

በተሠሩት የልማት ሥራዎች ውስጥ ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንደነበረው አስታውሰው፤ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ሥራዎችን ማከናወኑን አመልክተዋል፡፡

15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ እናትዓለም፤ 13 የመንገድ፣ 35 የውሃ፣ አንድ ግዙፍ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የጤና፣ የትምህርት፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚፈቱ 561 ፕሮጀክቶች መሠራታቸውንም ገልጸዋል።

የከተማዋን የቤት ፍላጎት ለማሟላትም 10 ሺህ 476 ቤቶችን እና በመልሶ ማልማትና ኢኮኖሚ መነቃቃት የሚፈጥሩ 3ሺህ 288 ሱቆችን መገንባት መቻሉን ኃላፊዋ ገልጸዋል። 122 የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ እና 1ሺህ 155 የሕፃናት ማቆያና መጫወቻዎች መገንባታቸውንም ጠቁመዋል።

በሁለተኛው የኮሪዶር ልማት ሥራ 135 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ፣ 246 ኪሎሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 141 ኪሎ ሜትር የብስክሌት እንዲሁም 43 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክ የተሠራ መሆኑንም ኃላፊዋ አስታውቀዋል። በእነዚህ ሥራዎችም ለ366 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። ከአጠቃላይ የከተማ ልማት ሥራው 30 በመቶ አረንጓዴ ዐሻራ እንዲሆን ይጠበቃል ያሉት ኃላፊዋ፤ በዚሁ መሠረት 517 ሄክታር ላይ 245 ፕሮጀክቶችን ሠርቶ ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል።

እነዚህ የልማት ሥራዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቁ የከተማዋ አስተዳደር ሠራተኞችና ኃላፊዎች በትጋት መሥራታቸውን ተናግረው፤ ይህም ለከተማዋ አዲስ የሥራ ባህል ያበሰረ እንደሆነና እየተከናወኑ ለሚገኙ የድህነት ቅነሳ ሥራዎችም በር የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ለድህነት ቅነሳ እና የኅብረተሰቡን ጥያቄ የሚመልሱ ፕሮጀክቶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ መሥራቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።

በራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You