
ዜና ሐተታ
ትዕግስት እንቻለው፤ ዓይነስውር ነች። ራሷን ለውጣ፤ ሀገሯንም የመጥቀም ተስፋ ሰንቃ የምትታትር ለግላጋ። የእናቷን ፍቅር በወጉ ሳታጣጥም በሞት የተነጠቀች ብላቴና። እናቷን በሞት ካጣቻት በኋላ የእናቷን ንብረት ለመጠቀም የፈለጉ ዘመዶቿ ወደራሳቸው አስጠግተዋት ከአባቷ ጋር እንድትራራቅ አደረጓት። እስከ ዘጠኝ ዓመቷ ድረስ ትምህርት የመማር ዕድል እንኳን ሳታገኝ ቆየች።
አሁን ግን አባቷን አግኝታ ተስፋዋ ለምልሟል። እርሱ ከሌሎቹ ልጆቹ አስበልጦ ይንከባከባታል። ጋሪ ጎትቶ ከሚያገኛት ገቢ ላይ ምንም ሳይሰስት ፍላጎቷን ለማሟላት ይጥራል። እርሷን ለማስተማር ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ግን አልተሳካለትም። በዚህም ለዓመታት ተሰቃይቷል። ግን ደግሞ ትናንት ማንም እንደሌላት ሆና ሲሰማት የቆየች ልጁን ››አለሁልሽ›› እያለ የአዕምሮ ዕረፍት እንድታገኝ በማድረጉ ተደስቷል።
በእንዲህ ዓይነት የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ላሉት አባትና ልጅ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ‹‹ድጋፍና እንክብካቤ ለአካል ጉዳተኞች ማኅበር›› አዲስ ተስፋ ይዞላቸው መጥቷል። ማኅበሩ ለ11 ዓመታት ያህል ዓይነስውራንን ተቀብሎ የቅድመ አንደኛ ትምህርትን በብሬልና መሰል ትምህርቶች ሲያስተምር የኖረ ነው። አዳሪ ትምህርት ቤት በመሆኑም ዓይነስውራኑ ምንም ሳይጎልባቸው የፈለጉትን እያገኙ የሚያድጉበት መኖሪያቸውም ጭምር ነው።
የመቀበሉ ምጣኔ አናሳ ቢሆንም ለአቶ እንቻለው ጌታነህ ልጅ ግን ይህንን ዕድል አልነፈገም። ለዓመታት የትምህርት ጉጉት ለነበራት ልጃቸው ደርሷታል።
አቶ እንቻለው እንደሚሉት፣ ‹‹ማኅበሩ የብዙ ዓይነስውራንን ተስፋ ያለመለመ ነው። በተለይም እንደእኔ አይነት ችግር ውስጥ ያሉና በምንም መልኩ ልጆቻቸውን ማስተማር ያልቻሉ ሰዎችን ቀና ብለው እንዲራመዱ ያደረገ ነው። ከማኅበረሰቡ ጫናም እንድንላቀቅና ልጆቻችን እንደማንኛውም ዜጋ ተምረው መለወጥ እንደሚችሉ ያሳየን ነው። እናም ዘለዓለም አመሰግነዋለሁ ነው ያሉት።
ዓይነስውራን ልጆች በተለያየ ምክንያት ሳይማሩ እድሜያቸው የትምህርት መግቢያ ጊዜያቸው ያልፋል። በዚህም ትምህርት ቤት ገብተው ለመማር እንዲሸማቀቁ ይሆናሉ። ከጓደኞቻቸው እኩል መማርም አይችሉም። ማኅበሩ ውስጥ ገብተው የሚማሩት ግን ይህንን ሁሉ ማለፍ እንደሚችሉ ከልጄ ለውጥና ነፃነት አንጻር ተረድቻለሁ›› የሚሉት አቶ እንቻለው፤ ልጃቸውን በቀጣይ በትምህርት ቤቱ የማትቆይ በመሆኑ ይህ የለመደችው ተግባር እንዳይቀርባት አድርገው ለማስተማር እንደሚሞክሩ ነግረውናል።
‹‹እኔም እንደእናቷ አፈር እስኪጫነኝ ድረስ ፍላጎቷን ለማሟላት እተጋለሁ። ከእህትና ወንድሞቿ በበለጠም እንከባከባታለሁ። በአካል ጉዳቷ የተነሳ በትምህርት ቤት ውስጥም ከእድሜ እኩዮቿ እንዳታንስ ለማድረግ የተቻለኝን ሁሉ አደርግላታለሁ›› ሲሉ በአደባባይ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ቃል የገቡት አቶ እንቻለው፤ ሌሎች ወላጆችም ልጆቻቸውን በዚህ ልክ መንከባከብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የድጋፍና እንክብካቤ ለአካል ጉዳተኞች ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ አስፋው በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ‹‹ማኅበሩ ለመመሥረቱ ምክንያት የራሴው ተሞክሮ ነው። እኔ በዓይነስውራን ትምህርት ቤት ተምሬ ለዛሬ እንደበቃሁ ሁሉ ሌሎች የሀገሬ ልጆች የሆኑ ዓይነ ስውራንም ይህንን ዕድል እንዲያገኙ ከማሰብ አንጻር ነው አዳሪ ትምህርት ቤቱን ከዛሬ 12 ዓመት በፊት እንዲመሠረት ያደረኩት። በዚህም ለ11 ጊዜ ተማሪዎችን አስተምሮ አስመርቋል።
ዓይነ ስውራን ተማሪዎች እንዲህ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው መማራቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። አንዱና ዋነኛው በራሳቸው እንዲቆሙና ለሀገራቸው ማበርከት የሚገባቸውን እንዲያደርጉ ማስቻል ነው። ሌላኛው ደግሞ ከማንኛውም ጫና ራሳቸውን አላቀው ሀገር በምትፈልጋቸው ቦታ ላይ እየገቡ ዐሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግ ነው።›› በተለይም የብሬል ትምህርትን ጠንቅቀው መማራቸው ዘመኑን የዋጁ ተግባራትን በቴክኖሎጂ እንዲያከናውኑ ከማስቻል አኳያ የማይተካ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በተለያዩ ቦታዎች በመከራየት ሥራውን ያከናውኑ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ወንድሙ፤ አሁን በቢሾፍቱ በአግባቡ ትምህርት የሚሰጡበት ሰፊ ቦታ አግኝተው ትምህርት ቤቱንም ገንብተው ወደ ሥራ በመግባታቸው በስፋት ዓይነስውራን ተማሪዎችን ተቀብለው እንዲያስተምሩ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አሁን በተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ መደበኛ ዓይነስውራን ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከፊል እይታ ያላቸውም ተማሪዎች ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች እንዲመጡ በማድረግ የብሬል ትምህርት እንዲወስዱ ተደርጓል። በዚህም በዘንድሮው ዓመት 10 መደበኛና 11 ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የመጡ ከፊል እይታ ያላቸው ተማሪዎችን ማስመረቅ ተችሏል። ለዚህም ግብረሠናይ ድርጅቶቻችን ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
አቶ ተመስገን ቶሌራ ከቢሾፍቱ ከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራ ጽሕፈት ቤት የመጡ ናቸው። ከማኅበሩ ጋር በቅርበት እንደሚሠሩና በርካታ የትምህርት ቤቱን ሠልጣኞችን አደራጅተው ወደ ሥራ እንዳስገቧቸው ያነሳሉ።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ብዙ ጊዜ ዓይነስውራን የትምህርት ዕድል አያገኙም። ካልተማሩ ደግሞ ምርጫቸው ጎዳና ላይ መውጣት ይሆናል። እንደነዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች መበራከታቸው ደግሞ ይህንን ችግር ከማስቀረት አኳያ ሚናቸው የማይተካ ነው። በተለይም የብሬል ትምህርት የብዙዎችን ዓይነስውራን ተማሪዎች ተስፋ የሚያለመልም ነው። ከዘመኑ ጋር ተዋደውና ተወዳድረው እንዲራመዱ ያስችላቸዋል። የኮምፒውተር እውቀታቸውን ከፍ ስለሚያደርገው ጥሩ የፈጠራ አቅም እንዲኖራቸውም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርላቸው ነው ይላሉ።
አሁን የተማረና በቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን የሚሠራ የሰው ኃይል ነው ሀገር የምትፈልገው። ከዚህ አንጻር ምንም እንኳን አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከሦስተኛ ክፍል ያልተሻገረ ቢሆንም ብዙዎቹ ተማሪዎች እድሜያቸው ከፍ ያሉ በመሆናቸው ለሥራ ዕድል ፈጠራው የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። በዚህ ደግሞ ተቋማችን ሁሌም እገዛውን የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።
በጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም