በደራሲነት፣ በመምህርነትና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል፤ በመቀሌ ከተማ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዲግሪ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነጽሁፍ ተመርቀው በሰመራ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋና ስነጽሑፍ አግኝተዋል። ከዚህ በኋላ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የማስተማር ስራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፤ ወደ መቀሌ በማምራትም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግለዋል። ከመምህርነት ባሻገር የስነጽሑፍ ስራ የሚከውኑ ሲሆን፤ ታሪካዊ ልቦለዶችን ይጽፋሉ።
እስካሁንም ሶስት መጽሃፍን ለአንባብያን ያበረከቱ ሲሆን፤ በቅርቡ ለንባብ የሚበቃ ተጨማሪ አንድ መጽሃፍም ጽፈዋል። ሥነጽሑፍን፣ ፖለቲካን፣ ታሪክና ፍልስፍናን እንዲሁም ሶሾሎጂ ስነ ማህበረሰብን አፍቃሪ ስለሆኑም በስፋት ያነባሉ፤ ይሄም በታሪካዊ ልቦለዶቻቸውና ፖለቲካዊ ሁነቶችን በትንታኔዎቻቸው ሲንጸባረቅ ይስተዋላል፤ በፖለቲካው ላይም በትኩረት የሚሳተፉ ሲሆን፤ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪዝም፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችና የህዝብ ጥያቄዎችን በማንሳትም መፍትሄ እንዲያገኙ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይህን ሲያደርጉ ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውላቸው አልነበረም።
ይልቁንም በርካታ ውጣ ውረድና እንግልቶችን አሳልፈው እንጂ። ይሄንንም ሲያስረዱ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጥያቄ መጠየቅ፣ የህዝብን ብሶት ማሰማትና መታገል ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ ቆይቷል። ይሄም የተገነባው ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ የተፈጠረ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዴሞክራሲና ነጻነት ትግል ውስጥ የራሱን አሻራ አሳርፏል ብዬ ነው የማምነው። እኔም እንደ አንድ ወጣትና መምህር ተመሳሳይ ስራ መስራት ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር በመሆን የራሴን ሚና ስጫወት ቆይቻለሁ ይላሉ። ዴሞክራሲ በታጣበት ሁኔታ ደግሞ ሰው ሲታገል ብዙ ችግሮች ይደርሱበታል። ሆኖም ትግል ነበርና በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍን የጠየቁ፤ ችግርና ግፍን ተቋቁሞ የማለፍ ጽናትም የታየባቸው ከቃላት ዘለፋ ጀምሮ እስከ መደብደብ፣ መታሰርና በሀሰት ክስ እንዲንገላቱ እስከማድረግ የደረሰ ችግርና ግፍን እንደደረሰባቸው ይገልጻሉ።
ከዚህ ባለፈም ወደ 18 ዓመት የሚስቀጣ የሀሰት ክስ መዝገብ እንደተመሰረተባቸው፤በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ስለ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊነት ብሎም ትግራዋይነት ከመናገር፤ ስለ ህዝቦች ጥያቄዎች ምላሽ ለመሻት ከመሟገት እንዳልተቆጠቡ ያመለክታሉ። ኢትዮጵያዊነትን በእናት እና መሰረቱ ጽኑ በሆነ ቤት የሚመስሉት አቶ ነብዩ ስሑልሚካኤል፤ በትግራይ የነበሩ መሰረታዊ አራት ያህል ስልጣኔዎችም በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ግንባታ ላይ ቀዳሚ መሰረት የጣለ ስለመሆኑ፤ ኢትዮጵያዊነትና ትግራዋይነት በረዥሙ የስልጣኔ ጉዞ ውስጥ እየተገነባቡ የመጡ ሳይነጣጠሉም የሚዘልቁ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ዛሬ ላይ ለትግራይ ህዝብ የዴሞክራሲና ልማት ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከቃል ባለፈ በተግባር እንዲገለጽ የድርሻቸውን ለማበርከት በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ተቀላቅለው እየሰሩ፤ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።
እኛም በወቅታዊ አገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች፤ በፓርቲያቸው ቀጣይ ጉዞና በክልሉ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎቶች ላይ በማተኮር ያደረግነውን ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊነትና ትግራዋይነት ሲናገሩ፤ ስለ ትግራይ ህዝብ ትግል ሲመሰክሩ፤ ትግራይና ኢትዮጵያ የታሪክ ሰንሰለት መስርተው ያሉና የሚኖሩ ስለመሆናቸው ሲገልጹ ይሰማል። እስኪ ቃለ ምልልሳችንን ይሄን ሀሳብዎን በማብራራት እንጀምር?
አቶ ነብዩ ፡- እኔ ኢትዮጵያን የምገልጸው መሰረቱ ጽኑ በሆነ ቤት ነው። የትግራይ ህዝብ ደግሞ የቤቱ መሰረት ነው። የመደመር እሳቤም ትልቅ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ይህ ታሪካዊ ምክንያቱ ነው።
ኢትዮጵያም ስትፈጠር በመደመር እሳቤና ፍልስፍና ነው የተፈጠረችው። ከሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል የጀመረው የአገረ መንግስት ግንባታ ወደ ደቡብ እየገሰገሰ ሄዶ ብዙ ህዝቦችን እያቀፈ የስልጣኔ ውርርስ እየተደረገ፤ የህብረተሰብ ውህደት እየተፈጸመ ይህች ትልቅ አገር እንድትፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህ ሂደት ደግሞ የመደመር ሂደት ነው። እናም መደመር የሶስት ሺህ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ እንደመሆኑ፤ የኢትዮጵያ የአገረ መንግስት ጉዞ በመደመር እሳቤ ነው መታየት ያለበት። ስለዚህ በዚህ ጉዞ ውስጥ የትግራይ ህዝብ የቤቱ መሰረት በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በቀጣይነትም ይህች አገር ሉዓላዊነቷ እንዲከበር፤ ትልቅ አገርም እንድትሆን ታሪካዊ ሚናውን እየተጫወተ ቆይቷል።
በዚህ ሂደት ግን የሚና መበላለጥ አለ ብዬ አላምንም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ሁሉም ህዝብ የየራሱን አሻራ አሳርፏል። ሆኖም በኢትዮጵያ ታሪክ ችግር እየሆነብን ያለው የኢትዮጵያን ታሪክ በቁንጽል ደረጃ ማንሳት ነው። የ130 ዓመት ታሪክ ብቻ እያነሱ፤ ያውም በዛ ውስጥ ተሰርተው ያሉ ጥሩ ነገሮችን ከማውሳት ይልቅ አንዳንድ የተፈጠሩ ችግሮችን በማቁሰልና በማድማት የህዝቦችን አንድነት የመሸርሸር አደጋ አለ።
ይህ ደግሞ የጽንፈኛ ብሔርተኝነት አካሄድ የፈጠረው ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ታሪክ መነሳት ካለበት በምልዓት ነው። በምልዓት ሲነሳ የዚች አገር ሚስጢርም ይገባናል። ከየት መጣች፣ እንዴት ተገነባች፣ እንዴትስ ነው መተዳደር ያለባት፣ ህዝቦቿ ምን አይነት ህዝቦች ናቸው የሚሉ ነገሮች ሁሉ ግልጽ ይሆንልናል። ስለዚህ የትግራይ ህዝብም የመስራችነት ሚና መታየት፤ በቀጣይነትም ይህች አገር እንደ አገር እንድትቀጥልና ወደተሻለ ደረጃም እንድትደርስ የራሱ የሆነ አስተዋጽዖ እያደረገ የቆየ ህዝብ መሆኑ መነገር አለበት። እናም ትግራዋይነትና ኢትዮጵያዊነት በፍጹም ሊለያዩ የማይችሉ ነገሮች ናቸው ተብሎ ነው መገለጽ ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ መልኩ በኢትዮጵያዊነት የማይደራደርና የኢትዮጵያ መሰረት ነው ብለው የገለጹት የትግራይ ህዝብ ዛሬ ላይ ጽንፍ በወጣ የህወሓት የዘር ፖለቲካ ከኢትዮጵያዊነቱ ለመነጠል እየተሰራበት ነው ፤ ይህ ደግሞ ከትግራይ ህዝብ ሰብዕና ጋር አብሮ የሚሄድ እንዳልሆነ በርካቶች ይናገራሉ። እርሶስ ምን ይላሉ?
አቶ ነብዩ ፡- ከ60ዎቹና 70ዎቹ ጀምሮ እንደ አገርም እንደ አለምም ያለውን እውነት መነሻ በማድረግ በጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ የህወሓት አካሄድ ጊዜው ከፈጠረው የትጥቅ ትግል ጀምሮ ያለው ሁነት በየምዕራፉ ከፋፍሎ ማየት ቢቻልም፤ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ህወሓት የዘረጋው ስርዓት አገራዊ ያልሆነ ‹‹ከየት መጣ›› የሚባል አይነት ስርዓት ነው።
ህወሓትም ሆነ የአገዛዙ ባህሪ ሲታይ የኢትዮጵያንም ሆነ የትግራይን ህዝብ ስነልቡና ያልተገነዘበ፤ ከየት መጣ (ኤሊየን) ሊባል የሚችል አይነት ስነልቦና ይዞ የመጣ ነው። ምክንያቱም በትንሹ እንኳን የዚህችን አገር ታሪክ ለማወቅ ጥረት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ አገራዊ የሆነ መንፈስ ተፈጥሮ ከዚህ የተሻለ ለውጥ ሊመጣ በቻለ ነበር። ነገር ግን በእሳቤም፣ በባህሪም፣ ባካሄድም፣ በብዙ መልኩ የትግራይን ስነልቡና፣ የኢትዮጵያን ስነልቡና የማይወክል፤ መጤ ሊባል የሚችል ሀሳብና ስርዓት ነው የተዘረጋው።
ስርዓቱም የዘር ፖለቲካ ላይ መመስረቱ ፍጹም ከትግራይ ህዝብም ሆነ ከኢትዮጵያ ህዝብ ስነ ልቡና ጋር የማይጣጣም ነው።
ለዛም ነው ትልቅ ውድቀት ያጋጠመው። ዘር የፖለቲካ መዘውር አድርጎ መጠቀምና ፖለቲካን ደግሞ ዘር አድርጎ መቀጠል አይቻልም። ይህ ምናልባት አንዳንድ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለማረም ልትጠቀም ትችል ይሆናል። ነገር ግን አገር ለመገንባት፤ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ግን በፍጹም አያስችልም። እናም የተያዘው ዘርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ መቆየት ከነበረበት ጊዜ በላይ ስለቆየም ነው ይሄንን አደጋ የፈጠረው። ከዚህም በላይ የዘር ፖለቲካ የሴራ ፖለቲካም አለበት።
የሴራ ፖለቲካው በአገር ደረጃም በደንብ ተንጸባርቋል። በትግራይ ደረጃ እንኳን ብናየው የሴራ ፖለቲካው ማቆሚያም አልነበረውም። ምክንያቱም የከፋፍለህ ግዛው ዝንባሌዎች ታይተዋል፤ ይሄም ማቆሚያ ያልነበረው፣ በዞን፣ በወረዳና መሰል አካሄዶች ህዝቡን እየከፋፈሉ ማስተዳደር፤ የትግራይ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲከፋፈል፣ እንዳይተማመንና እንዲጠራጠር ተደርጎ፤ አንዱ ወዳጅ አንዱ ጠላት፤ አንዱ ታማኝ አንዱ ተጠርጣሪ እየተደረገ ለብዙ መከፋፈልና እኩልነት መነፈግ ተዳርጎ ቆይቷል። ስርዓቱ የአፓርታይድ ስርዓት እስኪመስል ድረስ የዘር ፖለቲካው ቀጥሎ እስከ ቀበሌና መንደር የዘለቀ ህዝብን የመከፋፈል ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን አዲስ ለውጥ ወይም ሪፎርም መጥቷል። ይሄን ሪፎርም እንዴት ይገልጹታል? ከትግራይ ህዝብ ጋርስ በምን መልኩ ተገናኝቷል?
አቶ ነብዩ ፡- ጭቆናውና የአፓርታይድ የሚመስለው ስርዓት በአጠቃላይ በአገሪቱ ሰፍኖ ነበር። በተለይ ደግሞ ስርዓቱ መቀመጫዬ ነው፤ መሰረቴ ነው ብሎ በሚያምንበት ትግራይ ላይ ጠንከር ይላል። ሆኖም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለውጥ፤ የተሻለ ስርዓትና ነጻነት፤ የተሻለ ማህበራዊ ፍትህና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ይፈልግ ነበረ። የትግራይ ህዝብም ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም።
ምናልባት አፈናው ጠንከር ስለሚልና ለሚዲያም ቅርብ ስላልሆነ፤ አንዳንዴ የታሪክ ጫናዎችም ሊኖሩት ስለሚችሉ ጎልቶ ያልታየ ሊሆን ይችላል እንጂ እንደውም ስርዓቱ ጫናውን እዛ ህዝብ ላይ ስለሚያበዛ የትግራይ ህዝብ ከሌላው በበለጠ የተሻለ ነገርን ይፈልግ፤ ለዛም በተግባር ሲታገል ነበረ።
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ የለውጡ አካል ነው። እኛም ወደብልጽግና ስንመጣ፣ ብልጽግና የትግራይ ህዝብ መሻትም ነበረ በሚል እሳቤ ነው። እናም ይህ ለውጥ የትግራይ ህዝብም ለውጥ ነው፤ የትግራይ ህዝብም አሻራ አለበት፤ ከዚህ ለውጥም የትግራይ ህዝብ መጠቀም አለበት፤ የትግራይ ህዝብም ለውጡን ደግፎ ወደተሻለ ደረጃ የማድረስ ግዴታም እንዳለበት በማመን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ለውጥ እንደ አገርም እንደ ትግራይ ክልልና ህዝብም ምን ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ? እርሶስ አሁን ላይ የብልጽግና ፓርቲ አባል ሆነው ለመስራት ለምን ፈለጉ?
አቶ ነብዩ ፡- የትግራይ ህዝብም ለውጥ ይፈልግ ነበር። አጠቃላይ በአገር ደረጃም የለውጥ ፍላጎት ነበረ። ይህ ለውጥም እውን እንዲሆን ዜጎች መስዋዕትነት ከፍለውለት ለዚህ ደረጃ በቅቷል። በህዝብ ፍላጎትና ትግል ለዚህ የበቃ ለውጥ ደግሞ በአግባቡ ከተመራና ከተሰራበት ለአገርም ለትግራይም የጎላ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ አለው።
የትግራይ ህዝብ ደግሞ የዚህ ለውጥ አካል ነው ካልን፤ በለውጡም መሳተፍ መቻል አለበት። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ በታሪኩም አገራዊ ሃይል ሆኖ ነው የቆየው። ባለፈው 27 ዓመት ብቻ ነው በሴራ ፖለቲካ በህወሓት መሪነት የትግራይ ህዝብ ለአገር ያለው ተቆርቋሪነት ያነሰ እንዲመስል ሆኖ የተሳለው እንጂ፤ የትግራይ ህዝብ አገራዊ ራዕይ ያለው አገር እየፈጠረና አገር እየገነባ የኖረ ህዝብ ነው።
እናም ይህ ለውጥ የትግራይ ህዝብም ለውጥ ነው፤ በለውጡም ተሳታፊነቱ መረጋገጥ አለበት ካልን፤ ተጠቃሚም መሆን አለበት። ከእሱ የሚጠበቀውን ግዴታም መወጣት አለበት። ስለዚህ ብልጽግና ፓርቲ ህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ የወለደው አገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑና የትግራይ ህዝብም በዚህ ውስጥ ታሪካዊ ሚናውን መወጣት መቀጠል ስላለበት እኛም አማራጭ ሆነን በብልጽግና በኩል መጥተናል። እናም መሰረታዊ ጉዳያችን የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ኃላፊነቱን የሚወጣበት አማራጭ እንዲኖረው ማድረግ ሲሆን፤ መዝኖና የተሻለውን ሀሳብ አይቶ መምረጥ የእርሱ ድርሻ ቢሆንም የትግራይ ህዝብ አንድ መስመር ብቻ ተከትሎ ይኑር መባሉ ትክክል ስላልሆነ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንደ ብልጽግና ፓርቲ አባልና አመራር ከለውጡና ከህዝቦች ተጠቃሚነት አኳያ የህወሓት መስመር ከብልጽግና ፓርቲ መስመር በምን ይለያል?
አቶ ነብዩ ፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያን ያክል የዘመነ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው። እናም ስለመስመርና አቅጣጫ ለማውራት ትንሽ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም አስከፊ ድህነት ውስጥ አለን፤ ሰፊ የሆነ ስራ አጥነት አለ፤ ሌሎችም ብዙ ችግሮች አሉ። ስለዚህ ህወሓት የሚያነሳው የመስመር ጉዳይ፣ የመስመር ጉዳይ ሳይሆን የጥቅም፣ የበላይ የመሆንና የስልጣን ጉዳይ ይመስለኛል። የአስተሳሰብና የመስመር አይመስለኝም። ስለዚህ እነርሱ መስመር የሚሉት በፖለቲካ ፓርቲው ውስጥ ያሉ ግለሰቦች የራሳቸው ስፍራ፣ የራሳቸው ስልጣንና ተጠቃሚነት ጉዳይ ላይ እንጂ ህዝብን በሚጠቅም አጀንዳ ላይ አይደለም። ልዩነቱም እየተፈጠረ ያለው በዚህ ላይ ነው።
ስለዚህ እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም አይነት ካልሆነ በስተቀር መስመሩ ምንድን ነው ተብሎ እስካሁንም በደንብ አልተገለጸም። ህወሓትም በሂደት መስመሩን እየቀያየረ ከጽንፈኛ ኮሚኒዝም ወደ ካፒታሊዝም ባንዴ ሲቀየር፤ የጠራ ፖሊሲ ሳይዝ ሲንቀሳቀስ፤ በርካታ የፖለቲካ ቅርጽ ያልያዙ ጉዞዎች ነበሩ። ስለዚህ ያን ያክል በፖለቲካ ደረጃ ጠርቶ የወጣ ሳይሆን የጥቅምና የስልጣን ጥያቄን ያዘለ መሆኑ ነው እኔ የሚገባኝ።
ምክንያቱም አንድን ነገር እነርሱ ከያዙት ለአገርም ለህዝብም ይጠቅማል ይላሉ፤ እነርሱ ካልያዙት ደግሞ አገር ያፈርሳል፣ ህዝብ ይጎዳል ብለው ፕሮፖጋንዳ ይሰሩበታል።
አዲስ ዘመን፡- እናንተ እንደ ብልጽግና ፓርቲ ወደ ትግራይ ህዝብ ስትሄዱ ከህወሓትም ሆነ በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ኃይሎች በተለየ የህዝቡን ችግር ሊፈታ የሚችል ምን አዲስና የተለየ አማራጭ ይዛችሁ ነው?
አቶ ነብዩ ፡- ብልጽግና አገራዊ ፓርቲ ነው። በአገር ደረጃም የተቀመጠ ፖሊሲና ፕሮግራም አለ። በእርግጥ ሁሉም ነገር ያለቀለት ባይሆንም፤ እኛም የራሳችንን አሻራ ለማሳረፍ እየሞከርን ነው። በቀጣይነትም ለህዝብም ይሄን ሚና መጫወት ለሚፈልጉ ሰዎችም ክፍት ቦታ ያለው፣ አካታች የሆነ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት የሚፈልግ ፓርቲ ነው።
እንግዲህ ህወሓት የትግራይ ህዝብን የሚጠቅም ፖሊሲም የለውም፤ የትግራይ ህዝብንም ለመጥቀም ፍላጎቱም የለውም። ከዛ በተቃራኒ ብልጽግና ፓርቲ አገርን መሰረት አድርጎ፤ ሰውን መሰረት አድርጎ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከጫፍ በአንድነት አሰባስቦ የሁሉንም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማንገስ፤ ከድህነት አረንቋ ወጥተን ወደ ብልጽግና እንድንሸጋገር ትልቅ የሆነ የኢኮኖሚ ራዕይ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው።
የማህበራዊ ፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችንም በደንብ ለመመለስ ቆርጦ የተነሳ ከጫፍ እስከ ጫፍ የኢትዮጵያ ህዝብን በአንድነት ያሰለፈ ትልቅ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን፤ የትግራይ ህዝብም ከዚህ ተጠቃሚ ይሆናል ብለን ነው የምናምነው፤ የምንቀሳቀሰውም። በክልሉ ስንቀሳቀስም በዚያ ካሉ ፓርቲዎች ጋር የፖለቲካ ፓርቲዎችን ህግና ስርዓቱ በሚፈቅደው ደረጃ ተባብረን ለመስራት እንፈልጋለን።
በተለይ ደግሞ በወጣቶች የሚመሩ አዳዲስ ፓርቲዎች አሉ። ብልጽግናም በዋናነት የወጣቱ ፓርቲ ስለሆነ ወጣቱ ነው መታገል ያለበት፤ የለውጥ ኃይል እሱ ስለሆነ ለእሱ ልዩ ትኩረት መሰጠት ስላለበት በትግራይ መፈጠር ከጀመሩ አዳዲስ ፓርቲዎች ጋርም ተቀራርበን የምንሰራበት ማዕቀፍ ይኖረናል።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በተለይም ከብልጽግና ፓርቲ እውን መሆን ጋር ተያይዞ ህወሓት የሚያራምደውና በአሀዳዊነት ምስል በህዝቡ ላይ ፍርሀትና ጥርጣሬን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑ ይነገራል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ? ይሄስ እስከየት ያስኬዳል?
አቶ ነብዩ ፡- አገራዊነትና አሃዳዊነት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለ አገር ማሰብ የሁላችንም ግዴታ ነው። አሃዳዊነት የሚለው በጊዜ ሂደት የተሞከረና የተፈጠረ ነገር ቢኖርም፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ አሃዳዊት ልትሆን አትችልም። አሃዳዊነት ማለት አንድነት ከሆነ ሁላችንም የምንፈልገው ነገር ነው።
አሃዳዊነት ምንድን ነው የሚለው ነገር በደንብ መገለጽ አለበት። ምናልባት አሃዳዊነት የአንድ ብሔረሰብ ወይም አካባቢ የበላይነት የሚል ከሆነ በኢትዮጵያ ይህንን የሚያስተናግድ እውነታ የለም። ከዚህ በፊት ተሞክሮ ከነበርም የራሱ የሆነ ውጤት አስከትሏል።
ከዚህ በኋላ ግን ኢትዮጵያ የአንድ ቡድን፣ ብሄር ወይም አካባቢ ልዕልናን ያነገሰች ልትሆን አትችልም። እንደዛ የሚያስብ አካል ካለም ለእርሱም ለማንም አይጠቅምም። ምክንያቱም ይህች አገር የሁላችንም ናት። ተባብረን ልንሰራላት፣ ልንጠቀምባትና በሰላም ልንኖርባት ይገባል።
ስለዚህ አሃዳዊነት ሊፈጠር አይችልም ምንም፤ ዕድል የለውም። ህወሓቶች በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ነው ይህንን እየቀሰቀሱ ያሉት። አገራዊ አንድነቱ እየገዘፈ መምጣት አለበት ሲባል፣ ወደ አሃዳዊነት ሊወስዱን ነው የሚል ፍርሃት መፈጠሩ አግባብነት የለውም።
እንደዛ ለማድረግ የሚያስብ አካልም ሊኖር አይችልም። የኢትዮጵያ እውነታም ሆኖ ሊቀጥል ስለማይችል፤ ያለው የህዝቦች አብሮ የመኖር ሁኔታ ተጠብቆ አንድ አገር እንድትኖረን ይገባል። ወደ አንድነት መምጣት፤ በብዙ መልኩ እየተዋህድን መምጣት አለብን። ይህ ውህደትም በሶስት ሺህ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ እየታየ ቆይቷል አዲስ ነገርም አይደለም። የመጠፋፋት ሳይሆን በመፈቃቀድ በመደመር ወደ አንድነት እየመጣን የአገረ መንግስት ግንባታን ወደ አንድ ደረጃ የምናደርስበት ወርቃማ ዕድል ነው አሁን የገጠመን።
ስለዚህ በዘር በሃይማኖት በሌላ ነገር ሳንከፋፈል ልዩነታችን እንዳለ ሆኖ ወደ አንድ የምንመጣበት ዕድል መኖር አለበት። ለምሳሌ፣ የኢኮኖሚና የባህል ትስስር እየፈጠርን መሄድ እንችላለን። ለዚህ ደግሞ በአገራችን የተለያዩ ባህሎች አሉ። እነዚህ ባህሎች ደግሞ በጣም ተቀራራቢዎች ናቸው። ለምሳሌ፣ ጥምቀት፣ እሬቻና አሸንዳን ማየት መውሰድ ይቻላል። አሸንዳን ብናይ ማንም ልጃገረድ በዚያ መልኩ መጫወት ትፈልጋለች። የትግራይ ህዝብ ባህል ብቻ ሳይሆን የልጃገረዶች ባህል ነው። ማንም ልጃገረድ አይደለም በአገር ደረጃ በአለም አቀፍ ደረጃ ካየነው በዚያ ደረጃ መቦረቅ መጫወት የማትፈልግ የለችም። ስለዚህ አሸንዳን የአገር ባህል ማድረግ እንችላለን፤ የዓለም ባህልም ማድረግ እንችላለን። እሬቻን ካየን ሰዎች ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው። ሰው በተፈጥሮው ደግሞ አብሮ የሚኖረውን ጭምርአመስጋኝ ነው። ስለዚህ ይህ ባህል ሁላችንም ጋር ያለ እንደመሆኑ አገራዊ አንድነቱን ለማፋጠን እሬቻን የሁላችንም ባህል የምናደርግበት ዕድልም አለ። በዚህ መልኩ የባህልም የኢኮኖሚም መዋሃድ እየፈጠርን ጠንካራ አገር መፍጠር እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ይሄን ጠንካራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደትና ትስስር ለመፍጠር እናንተ እንደ ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ህዝብ ውስጥ ለመስራት ስትዘጋጁ ምናልባትም በህወሓት ያልተነገሩ እናንተ የለያችኋቸው የትግራይ ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ነብዩ ፡- የትግራይ ህዝብ ጥያቄና ፍላጎት ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ አይደለም። አብዛኛው የህዝብ ጥያቄ ተመሳሳይ እንደመሆኑ የትግራይ ህዝብም ተመሳሳይ ጥያቄ ነው ያለው። በዚህ ረገድ እኛም የለየናቸውና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በታሪክ በሁሉም ዘርፎች የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችና ችግሮች አሉ። ለምሳሌ፣ በፖለቲካው ዘርፍ ካየን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አለበት።
ራስን በራስ የማስተዳደር ፌዴራላዊ ስርዓቱ በእውነት እንዲተገበር ይፈልጋል። ምክንያቱም አሁን አሃዳዊነት እየተባለ የሚነሳው ነገር ህወሓት ትግራይ ላይ ሲተገብረው የነበረ በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ ችግር ነበር። በአገር ደረጃም ካየን አሃዳዊ የሚመስል ስርዓት የተገበረው ህወሓት ነው። እንደውም በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተብሎ ያንድ ሰው አምባገነንነት እንዲፈጠር፤ ስልጣን አንድ ሰው ላይ እንዲከማች የማድረግ፤ ክልሎችን በእጅ አዙር የማስተዳደር፤ ፌዴራሊዝም ተብሎ ግን የውሸት ፌዴራሊዝም እየተተገበረ ቆይቷል።
ስለዚህ መጠየፍ ካለብን አሃዳዊ ተብሎ ሊፈረጅና ሊወገዝ የሚገባው እንቅስቃሴ ካለ ህወሓት የተንቀሳቀሰበት መንገድ ነው። በተለይ በትግራይ የአንድ አካባቢ የበላይነት ተፈጥሮ አስተዳዳሪዎች እኛ ብቻ ነን የሚል ተፈጥሮ የፌዴራል ስርዓቱ በከፋ ደረጃ እንዲተገበር ተደርጓል። የትግራይ ህዝብም በአካባቢ እንዲከፋፈል ተደርጎ የዚህ አካባቢ ሰው አስተዳዳሪ፣ የዚህ አካባቢ ሰው ደግሞ አሜን ብሎ ነገሮችን የሚቀበል፤ አንደኛው ታማኝ ሌላኛው ደግሞ በጥርጣሬ የሚታይ፤ እንዲህ እየተደረገ የመከፋፈል ስራ እየተሰራ ቆይቷል።
ስለዚህ በትግራይ ደረጃም እንኳን ፌደራላዊ ስርዓቱ በትክክል አልተተገበረም፤ በኢትዮጵያ ደረጃም በተመሳሳይ ሁኔታ ማለት ነው። ቅድም እንዳልኩ የመልካም አስተዳደር ችግርን ጨምሮ ይሄ ፖለቲካዊ ችግር ነው። በኢኮኖሚ ደረጃ ካየን የስራ ማጣት የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ይነሳሉ። በታሪክም እንደዛው የትግራይ ህዝብ ታሪክ በምልዓት እንዳይነሳ፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለው ቁርኝት በእውነተኝነት እንዳይወሳ በማድረግ የተነጣይነት አዝማሚያ ያለበት የታሪክ ትርክት ሲደረግ ቆይቷል።
ስለዚህ እነዚህ ሁሉ በደሎች ናቸው። እነዚህ በደሎች ደግሞ በአገር ደረጃም የተፈጸሙ ናቸው። እና ለዛ ነው የትግራይ ህዝብ የተለየ ጥያቄ የለውም የተለየ ፍላጎትም የለውም፤ እኛም እንደ ብልጽግና ፓርቲ በአገሪቱ ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው፤ ስለዚህ በተመሳሳይ መንገድና በተባበረ ክንድ ነው መፈታት ያለበት ብለን ያስቀመጥነው። ከዚህ ባለፈ ግን የትግራይ ህዝብ በተለየ መንገድ ተጠቅሟል የሚለው ተራ ፕሮፖጋንዳ ነው።
እንዲያውም የትግራይ ህዝብ በተለየ ተበድሏል በህወሓት። የስርዓቱም ባህሪ እንደዛ ነው። የራሴ የሚለውን ህዝብ በጣም የመጨቆን ባህሪ ነበር እያሳየ የቆየው። ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች እንዳሉ እሙን ነው። በኔትወርክ በቡድን ተደራጅተው አገር ሲዘርፉ የቆዩ ሰዎች እንዳሉ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው። ስለዚህ መሰረታዊ ልዩነቱ መታየት አለበት ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ናቸው ፤አንድ ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሲገፋ ሲጨቆን የኖረ ህዝብ ነው። በእሱ ስም ሲነገድ የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ነው በማለት የትግራይ ህዝብ ለጥቃት እንዲጋለጥ እየተደረገ ቆይቷል። ስለዚህ ጥቂቶች በትግራይ ህዝብ ነግደው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የትግራይ ህዝብ እንዲያውም ከሌላው በከፋ ደረጃ ተበዝብዟል፤ ተጨቁኗል። የህወሓት የሴራ ፖለቲካ ተጠቂ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ህዝብ ለዴሞክራሲና ነጻነት የታገለ ህዝብ ቢሆንም መጨረሻው አማራጭ ሀሳብ ሊቀርብለት በማይችልበት አፈና ውስጥ መውደቅ ሆኗል፤ ለዚህ ደግሞ ለውጡን ተከትሎ በሌሎች ክልሎች የታዩ የሀሳብ ብዝሃነቶችና ነጻነቶች በክልሉ ሊደፈጠጡና ግለሰቦችና ድርጅቶችን ለእንግልት ሲዳረጉ መታየቱ አብይ ማሳያ ነው፤ የሚሉ አካላት አሉ። እርሶ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ነብዩ ፡- ህወሓት ሲፈጽመው የቆየው አፈና በባሰ ደረጃና መልኩ የተፈጸመው የትግራይ ህዝብ ላይ ነው። የትግራይ ህዝብ ከህወሓት መሪነት ውጭ ሌላ መሪ እንዳያይና እንዳይፈጠር፤ አማራጭ ሀሳብ እንዳይኖር ሌላ ሀሳብ እንደ የጠላት ሀሳብ የሚፈርጅ በጣም ኋላ ቀር የሆነ ፖለቲካ ሲራመድ ቆይቷል። የዚህ ትልቁ ገፈት ቀማሽ የሆነው የትግራይ ህዝብ ነው። ይህ አፈናም ቀጥሏል።
ስለዚህ በህወሓት ፖለቲካ በጣም ኋላ ቀር ከመሆኑ የተነሳ ሀሳብ የማያስተናግድ፤ ሀሳብ የሚፈራ፤ ሀሳብ ሲመጣም ብዙ እንግልትና ፕሮፖጋንዳ በመክፈት አማራጭ ሀሳብ እንዳይፈጠር የመደፍጠጥ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፤ አሁንም እየተሰራ ነው። ይህን ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ታግለን ካላሸነፍነው ተመሳሳይ ተግባሩን መፈጸሙ አይቀሬ ነው ። ስለዚህ ይህ አካሄድ መቆም መስተካከልም ስላለበት ነው የምንታገለው።
እንደዛ ለማድረግም አማራጭ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ይዘን በመምጣት ነው መታገል ያለብን፤ የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዲኖረው ነው ትልቁ ስራችን። አማራጭ ኖሮ ራሱ ገምግሞ አይቶ ከፈለገ ህወሓትን መቶ አስር ፐርሰንት ቢመርጥ ለእኛ ትልቅ ድል ነው። መንቀሳቀስ የምንፈልገውም በዚህ መልኩ ነው። ቅድም እንዳልኩትም አፈናው የትግራይ ህዝብ ላይ የበረታ ነበረ፤ አሁንም እየበረታ ያለው የትግራይ ህዝብ ላይ ነው። ለምሳሌ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአሁኑ ግዜ ተፈጥረዋል። ነገር ግን እነዚህ ፓርቲዎች በጣም ብዙ ችግር አለባቸው። ስብሰባ ለማካሄድ እንኳን አዳራሽ ሲከለከሉና የተለያየ እንግልት ሲደርስባቸው እያየን ነው።
በተለይ አረና ፓርቲ ቀደም ብሎ የተቋቋመ እንደመሆኑ በርካታ እንግልትና ብዙ አባሎቹ ላይ እስከ ግድያን የደረሰ ግፍ እንደተፈጸመበት ፓርቲው ብዙ ጊዜ ይናገራል። በዚህ ደረጃ የማንገላታትና የማሸማቀቅ ስራ እየተሰራ ቆይቷል። የትግራይን ህዝብ ደግሞ ነጻነት ይፈልጋል፤ የእኩል ተጠቃሚነትና በሰላም አብሮ መኖር ይፈልጋል። እንደ ብልጽግና ይህንን ሁኔታ በመቀየር እነዚህን ህልሞቹን እውን እንዲያደርግ የማገዝ ስራ ነው የምንሰራው።
አዲስ ዘመን፡- ቁጥራቸው ቢለያይም ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ጉዞ ውስጥ በሁሉም ቦታ አጥፊዎችና ሙሰኞች ነበሩ። እነዛን የመያዝና እርምጃ የመውሰድ እንቅስቃሴ ሲወሰድ በህወሓት በኩል ‹‹ትግራዋይ ተነጥሎ እየታደነና እየተሳደደ ነው›› በሚል ፕሮፖጋንዳ በህዝቡ ውስጥ ጥርጣሬን የመፍጠርና የፖለቲካ ቁማር ዓላማ ማሳኪያነት ሲጠቀምበት ይስተዋላል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ነብዩ ፡- ኢህአዴግ የመጣበት የራሱ ታሪክ አለ፤ ከትግራይ ህዝብ ጋር የተቆራኘ ታሪክ መኖሩም ለሁላችንም ግልጽ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትግሉ አልቆ መንግስትነት ሲፈጠርም ሀይሉ ከትግራይ እንደመምጣቱ መጠን ከዛ አካባቢ የመጡ ሰዎችን በመንግስት ኃላፊነት እንዲያገለግሉ የተደረጉበት ሁኔታ ይኖራል። ከዛ በኋላም ህብረ ብሄራዊ ሀገር እንመስርት ተብሎ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት በብዙ መልኩ እንዲሳካ በሰራዊቱ በቢሮክራሲው ላይ ያለው ሰራተኛ በሁሉም መስኩ ሽግሽግም እንዲደረግ የተመጣጠነ ሁኔታ እንዲፈጠር እየተደረገ መቆየቱ እውን ነው። እዚህ ላይ መለየት ያለብን አንድ ነገር አለ። የትግራይ ህዝብና ህወሓት ለያይተን ማየት አለብን።
ምናልባት የህወሓት ሰዎች ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ላይ በዛ ብለው ታይተው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የመጀመሪያ ግምገማው የታሪክ ሂደቱ የፈጠረው ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ይሄ ማለት ግን የትግራይ ህዝብ የበላይ ሆነ ማለት ላይሆን ይችላል። የህወሓት አመራሮች የሚሰማቸው ስሜት ሊኖር ይችላል፤ ታግለናል በማለት ክሬዲቱን መውሰድ ሊፈልጉ ይችላሉ።
በመሆኑም የህወሓት አመራሮች ከበዙ እነሱ በዙ ነው መባል ያለበት እንጂ ተጋሩ በዙ፤ የትግራይ ህዝብ ልእልናውን አረጋገጠ ሊያስብል አይችልም። የትግራይ ህዝብ ለራሱ ፍትህ የሚፈልግ በጣም የተጨቆነ ህዝብ ነው። የህወሓት አመራሮች የበላይነት ካለ መታገል ያለብን እሱን ነጥለን ነው። የትግራይ ህዝብም ይህንን አይፈልግም በእኩልነት መኖር ነው የሚፈልገው። ሆኖም በኔት ወርክ በትስስር የተፈጠሩ በርካታ መዋቅሮች አሉ። አሁን ደግሞ ከህዝቡ ስንት እጅ እንደራቁ መገንዘብም ይጠበቃል።
ከህወሓትም በላይ፤ ከድርጅቱ በላይ ኔት ወርኮች ተፈጥረው እነዛ ኔት ወርኮች ባጠፉት ጥፋት ህዝብ በፍጹም መወቀስ የለበትም። ስለዚህ የትግራይ የበላይነት የሚል ፕሮፖጋንዳ ነው እንጂ የበላይነት የለም። የትግራይ ህዝብ እንደማንኛም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት መኖር ለራሱም ፍትህ የሚፈልግ ህዝብ እንጂ የማንኛውንም ልእልና የማይቀበል በመፈቃቀድ አብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። ፓርቲና ህዝብ መለየት አለባቸው። ምን አልባት እነዛ በኔትወርክ በቡድን የተሳሰሩ ሰዎች የፈጠሩት ችግር በህግ መታየት አለበት ብለን እናምናለን።
ይህቺን ሀገር ሲያስተዳድር የቆየ ሀይል ኔት ወርክና ቡድን ለዚች ሀገር የሰራው መልካም ነገር ታይቶ ለዛ መሸለም፤ መሞገስ መመስገን፤ ባጠፋው ጥፋት ልክ ደግሞ መጠየቅ መቻል አለበት። ይህም ሆኖ የትግራይ ህዝብ እየተነጠሉ እየታደኑ ነው የሚል ግምገማ የለንም ። የሚያስጠይቅ ነገር ካለ ኃላፊነት ላይ የነበረ ሰው ሊጠየቅ ይገባል። ከተጠረጠረም ህጉ በሚፈቅደው መልኩ መሄድ አለበት፤ ንጹህ ከሆነ ንጽህናው ነጻ ያወጣዋል። ትግራይ ተነጥሎ እየተጠቃ ነው የሚለው የለውጡ መፈጠርና መፍጠን የተደራጀ ስላልነበር የህዝብ ስሜት ገንፍሎ ስለወጣ አንዳንድ ሰዎች ያልሆነ ስእል አስይዘውት ሊሆን ይችላል።
እንደዚህ አይነት ችግር ሲፈጠርም ወደ ለቅሶ ፖለቲካ ሳይሆን መገባት ያለበት የለውጡ አንድ አካል በመሆን ክፍተቱን እያረምንና እያስረዳን ነው መሄድ ያለብን። ነገር ግን እዚህ ላይ ትልቁ ተጠያቂ መሆን ያለበት ህወሓት ነው። ህወሓት፤ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው እያለ ሲሰብክ ስለነበር፤ የለውጥ ሀይሉ ሲመጣ አንድ ነን በሚለው ልክ ቢንቀሳቀስ ባህሪያዊ ነው። ስለዚህ የመጀመሪያ ችግር ፈጣሪው የህወሓት ፕሮፖጋንዳ ነው።
ህዝብና ፓርቲ አንድ ነው እያሉ ኢሳይንሳዊ ኢፖለቲካዊ የሆነ ጽንሰ ሃሳብ ሲያራምድ ቆይቷል። በዚህም የትግራይ ህዝብ ለችግር እንዲጋለጥ ምክንያት የሆነው ራሱ ህወሓት ነው። ለዚህም በቅድሚያ መወቀስም መጠየቅም ያለበት ህወሓት ነው። የለውጥ ሀይሉ ደግሞ ህዝብና ፓርቲ ለይቶ ቆፍጠን ባለ መልኩ መንቀሳቀስ ነበረበት። ነገር ግን የተደራጀ ስላልነበር የተለያዩ ኃይሎች የራሳቸው ፍላጎት ሊያንጸባርቁበት ችለዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ የትግራይን ህዝብ ከሌላው ለመነጠል ከሚደረገው ጥረት መካከል ከአማራ ህዝብ ጋር ግጭት እንዳለ አድርጐ ማቅረብና ይሄንን አጉልቶ የማሳየት ተግባር መሆኑን ይጠቀሳል። የዚህ ችግር ምክንያቱ ምንድን ነው? መፍትሄውስ ምን ሊሆን ይገባል?
አቶ ነብዩ ፡- የአማራና የትግራይ ህዝብ ሁለት አድርገን ልንገልጻቸው የማይገባ፤ በታሪክ በባህል በብዙ መልኩ የተዋሀደ ህዝብ ነው። ይህ ህዝብ ለዘመናት ሲፋቀር ሲዋለድና በአንድነት ሀገር ሲጠብቅና አገር ሲያለማ የኖረ ህዝብ ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ ሊጣላበት የሚችል ምንም አይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም። ከዚህ አኳያ ህዝብ እየተጣለ ነው ብለው የሚሰብኩ ግለሰቦችና ሀይሎች አሉ። ስለዚህ ጥሉ ከእነዚህ ሀይሎች ጋር ነው እንጂ ህዝብ ለህዝብ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም።
እናም የአማራና የትግራይ ህዝብ አብሮ የኖረ አብሮም የሚኖር ባህሉም በቋንቋውም የሚቀራረብ ህዝብ ነው። አንዳንድ ሀይሎች በፈጠሩት ግርግር ህዝብ ተጣላ ማለት በጣም አጸያፊ ነገር ነው። ይህ ደግሞ ለውጥ ሲፈጠር ብዙ ነገሮች የተበላሹ ሊመስሉ ይችላሉ፤ አሁን ግን እየተስተካከለና በጣም ጥሩ ስሜቶች ተፈጥረው ወደ ቀደመው ወንድማማችነት በደንብ ተመልሰናል። ለምሳሌ፣ በስፖርቱ ላይ ላለፉት ሁለት አመታት አንዱ አንዱ ጋር ሄዶ እንዳይጫወት የሚያሰጉ አንዳንድ ነገሮች ነበሩ።
አሁን እነዚህ ነገሮች ተቀርፈው ሁለቱ ቡድኖች እስፖርታዊ ውድድሮቻቸውን እያደረጉ ፍቅራቸውን እየተገላለጹ ደስ የሚል እውነተኛ የህዝቦች ግንኙነት እየታየ ነው። ቀድሞ የተፈጠረውም ጥቂት ሰዎች የፈጠሩት የተሳሳተ ምስል እንጂ የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ሊጣላና ሊቃረን የሚችልበት ምክንያት የለም። መፍትሄውም ይሄንኑ ሀቅ ለህዝቡ እያሳወቁ መሄድ፤ አንድነቱን ማጠናከር ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው በትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ተንቀሳቅሳችሁ የምርጫ ቅስቀሳ ለማከናወን አስባችኋል? ምን ውጤትስ ትጠብቃላችሁ?
አቶ ነብዩ ፡- በትግራይ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ይዞ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በዛው ልክ የሚቻልበት ሁኔታም አለ። ምክንያቱም ህዝቡ ከአፈና መላቀቅና አማራጭ ሀሳብ እንዲኖረው ይፈልጋል። ለዚህም ነበር የትግራይ ህዝብ የታገለው። እኛ ጦር አዝምተን እንሂድ አላልንም፤ ሀሳብ ይዘን ነው።
የትግራይ ህዝብም በሀሳብ የሚያምን ነው። የትግራይ ህዝብ ባህልና ስሜት በትክክል ሲታይ በትግራይ አማራጭ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቀላልና ምቹ ነው። በሌላ መልኩ ከህወሓት ባህሪ አንጻር አማራጭ ሀሳብ ከመፍራትና ከመጥላት የተነሳ ጫናዎችና አፈናዎች ይደረጋሉ’። ስለዚህ መጥፎ ምስሉ የህወሓት ነው፤በጎ ምስሉ ደግሞ የህዝቡ ነው፤ እኛ ደግሞ የምናከብረው የምንፈራው የምንታገልለትን ህዝብ እንጂ ሌላ ሀይል አይደለም። በመሆኑም ህወሓት የፈለገውን ሀሳብ ሊይዝ ይችላል። እኛ ይህንን ሃሳቡንና አቋሙን ታግለን ህዝባችንን ይዘን እናሸንፈዋለን።
የህዝቡ ስሜት መልካም እስከሆነ ድረስ ከዛ ውጪ ሊሆንም ስለማይችል የህዝባችንን ስሜት ተከትለን ህዝባችንን አምነን ህዝባችንን ይዘን አማራጭ ሀሳብ አቅርበን ተቀባይነት እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለንም። በዚህ መልኩ የብልጽግና ፓርቲ ተወዳድሮ ትልቅ ድል እንደሚገኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ። ለዛ የሚሆንም ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፤ ከዚህ በኋላም በዛ ልክ ቀጣይ ይሆናል።የሚያስቸግሩ ነገሮችም ካሉ ታግለን እንደምናሸንፋቸው ጥርጥር የለንም።
አዲስ ዘመን፡- የብልጽግናን ፓርቲ በትግራይ ቅርንጫፍ መክፈትን ተከትሎ በህወሓትና ተከታይ አክቲቪስቶቹ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ መጀመሩ ይነገራል። ታዲያ እናንተ የህዝብን ፍላጎት እና የህወሓትን ጭንቀት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ምን ለመስራት አስባችኋል?
አቶ ነብዩ ፡- ህወሓት በትግራይ ህዝብ ታቅፎ ያለው የተሻለ ሀሳብ ኖሮት የተሻለ ስራ ስለሰራ ሳይሆን የተበላሸ አካሄድ ስላለ ነው፡፡ ያ የተበላሸ አካሄድ ደግሞ እስኪስተካከል ድረስ በጊዜያዊነት የተፈጠረ መግባባት ነው እንጂ ህዝቡ ከህወሓት አገዛዝ መላቀቅ ይፈልጋል። ስለዚህ ህዝቡ የለውጡ ሂደት ሰከን እስኪል ድረስ ነው እየጠበቀ ያለው። ህዝቡ ሰከን ባለበት ሁኔታ የሚጠብቀውም ሌላ አጀንዳ መጨመርም ተገቢ አይደለም በሚል የትግራይ ህዝብ ነገሮችን በጥሞና እየተከታተለ ያለው።
ህወሓት ከዚህ በኋላ ሀሳብ ማመንጨት የሚችል ፓርቲም አይደለም። የትግራይ ህዝብም ህወሓትን መጠየቅ የሚፈልገው ብዙ ጥያቄ አለው። ምክንያቱም ከሌላው ህዝብ በላይ የትግራይ ህዝብ በህወሓት ተበድሏል። የሴራ ፖለቲካ ሰለባ እየሆነ ቆይቷል። ስለዚህ አሁን ህወሓት በትግራይ ህዝብ ተቀባይነት ያለው የሚመስለው በሴራ ፖለቲካና ፕሮፖጋንዳ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በራሱ ሰዓት መስራቱን ያቆማል።
የኢትዮጵያ ህዝብን በማጠልሸት ያልተፈጠሩ ግጭቶችን የተፈጠሩ በማስመሰል መኖር አይቻልም። በተለይም በዚህ ዓመት ፕሮፖጋንዳው የትግራይ ህዝብን ማስተዳደር አይችልም፤በመሆኑም አሁን ላይ ሁሉም ነገር ያለቀለት ነው። ህወሓት ከዚህ በኋላ ለትግራይ ህዝብ አማራጭ ሆኖ መቀጠል አይችልም። በሀሳብም በአደረጃጀት፣ በባህሪም ሆነ በሌሎች ጉዳዮችም ከትግራይ ህዝብ ጋር የማይሄድ እንደውም የህዝቡን ገጽታ ያጠለሸ ነው። በብዙ መልኩም አሁን ላይ ፈርሷል፤ ህወሓት ያለቀለት ደርጅት ነው፤ ስለዚህ አማራጭ ሊሆን አይችልም፤ ከዚህ በኋላም ታሪኩ እንዴት እንደሚወሳ ነው መጨነቅ ያለበት። ጉዞውም በጣም ረዥም ነው፤ ከ60 ዎቹ ተነስቶ እስከ አሁን ልቀጥል ማለት አንዱ የውድቀቱ ምንጭም ነው።
አሁን ላይ ሀሳብ ስለሌለው መዋጋት የሚፈልገው በሌላ መልኩ ሊሆን ይችላል። ግን እሱም ቢሆን ከፍተኛ ተጠያቂነትን የሚያመጣና ለትዝብት የሚዳርግ ነው። እኛው ከዚህ በፊት የተፈጸሙትን የስም ማጥፋትና ሌሎች ጉዳዮችን በማንሳት ፍትህ እንዲሰፍን ከፍተኛ የሆነ ትግል እናካሂዳለን። አዲስ የወጣት አደረጃጀት በብልጽግና ፓርቲ አማካይነት መጥቷል፤ እስከ አሁንም ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴን እያደረገ መጥቷል የትግራይ ህዝብም ይህ ፓርቲ የኔ ነው ብሎ ማመን የጀመረው ከመጀመሪያ ጀምሮ ነበር።
ከፕሮፖጋንዳው ባሻገር የህዝቡ እውነተኛ ስሜትን መመልከት የሚቻልበት እድልም አለ። እናም ፕሮፖጋንዳው ለጊዜው የተፈጠረ ምናልባት በዚህ ፕሮፖጋንዳ የተሸወደም ካለ ለእሱ ትክክለኛውን መንገድ ማሳየትና ለውጡም በትክክለኛ መስመር ላይ እንዳለ እናሳያለን። ትልቁ ነገር የሚሰማ እውነትን የሚፈልግና ፍትህ የናፈቀ ህዝብ አለን። አሁን የተፈጠሩት አንዳንድ ሁኔታዎች በአጭር ጊዜ ተቀይረው በአገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ ከጫፍ እስከጫፍ ለማድረስ እንሰራለን። ይሄም እውን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ የትግራይ ህዝብ በዘመናት ሂደት ውስጥ በከፈለው መስዋዕትነት ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን በመፍጠር ውስጥ የራሱን አሻራ አሳርፏል፤ እያሳረፈም ይገኛል። በቀጣይም ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባትና የሚጠቀምባትን አገር ዕውን ለማድረግ ምን መሰራት ይገባል? ከማንስ ምን ይጠበቃል በሚለው ላይ መልዕክት ካለዎት?
አቶ ነብዩ ፡- የኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ታሪክ ነው፤ ትልቅ አገርና ትልቅ ህዝብም ነው ያለን። በብዙ መልኩ የአገር ሀብታምና የህዝብ ሀብታሞች ነን። ይሄን ጸጋ በደንብ ልንረዳውና ልንጠቀምበት ይገባል። በዚያም ልክ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀላልም አይደለም። ሰፊ ታሪክ ስላለን ያ ታሪክ የሚፈጥረው የራሱ የሆነ ውስብስብነት ይኖረዋል። ስለዚህ መደረግ ያለበት የመጀመሪያ ትኩረታችን ታሪክ ላይ መሆን አለበት።
ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ ይህች ሀገር የታሪክ ውጤት ናት። እኛም በዛ ያለፍን በዛ የተገነባን፤ በዛ ያለፍን ነን። ስለዚህ ብዙ ግዜ ታሪካችን ይጫነናል። እናም ታሪካችንን በደምብ መረዳት ማወቅ አለብን። በምልአት መረዳት አለብን። ከ3ሺ አመት በላይ ታሪክ ያላትን ሀገር የ130 አመት ታሪኳን ማንሳት ብቻ ፍትሀዊ አይደለም። በዛ ላይ ደግሞ ብዙ የተፈጠሩ መልካም ነገሮች እያሉ ቁስል ብቻ እየፈለጉ ሰው ለማጋጨት ሕዝብ ለማራራቅ መሞከሩ በጣም አሳዛኝ ተግባር ነው። ታሪክ ላይ በደምብ መሰራት አለበት። መሰነድ አለበት።መተረክም አለበት። የመጀመሪያው ትኩረታችን መሆን ያለበት ይሄ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አካታች የሆነ ፖለቲካ ማስፈን አለብን።
ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አለብን። አብዛኛውን ግዜ በታሪክም የተፈጠሩት ቅራኔዎች ስልጣንን መሰረት ያደረጉ ነበሩ። ክብርን መሰረት ያደረገ ነበር። ይሄ ትርክት ሆን ተብሎ የሴራ ፖለቲካን ለማራመድ የተፈጠረ እንጂ በኢትዮጵያ የተፈጠሩት ግጭቶች መሰረታቸው ስልጣን ነው። ስልጣን መፈለግ ደግሞ ባሕርያዊ ነው።እኔ ላስተዳድር፤ እኔ ኃላፊነት ልውሰድ፤ ማለት የሚበረታታ ነገር ነው።
ስለዚህ የስልጣን ፉክክሩን ለማለዘብ መፍትሄው ዲሞክራሲ ነው። ይህች ሀገር የሁላችንም ናት። አቅም ያለው ሁሉ ሊያስተዳድራት ይችላል። ሕዝብን ብቻ ያገልግል እንጂ ወደ ስልጣን ለመውጣት ብሄር፤ ኃይማኖት፤ ሌላ ነገር አያስፈልግም። የተሻለ አማራጭ ይዞ መምጣት መቅረብ ለዚያ የሚያስፈልገውን ዲሞክራሲያዊ ትግል ሰላማዊ ትግል ማካሄድ በዚህም የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ነው። ዴሞክራሲ ለሁላችንም ያግባባናል። ይህቺ ሀገር የሁላችንም ናት። ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲኮራ ለማስቻል ፖለቲካችንን ዘመናዊና አካታች ማድረግ አለብን። ለዛ ነው አሁን ብልጽግና ይሄን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘመናዊ ለማድረግ ጥሩ ጅማሮና ጉዞ ጀምሯል። በሂደት ይፈታሉ። ፖለቲካ ነው። የለውጥ ሂደት ውስጥ ነን ያለነው። በትናንሽ ችግሮች መደንገጥ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። እንደ ሕዝብ እንደ ሀገር ብዙ ነገር አሳልፈናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰከን ብሎ ባለው የዳበረ የሰላምና የመግባባት ባህሉ ለውጡን ይዞት እንጂ ወደሌላ ትርምስምስ ልንገባ እንችል ነበር። የባሰ አለመምጣቱ አንድ ነገር ነው። ለውጥ ደግሞ በቀላሉ አይመጣም።
ለውጡ በአይነቱም እስከአሁን የተለየ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው እኮ ተገዳድለን የመጣ ለውጥ ነው። አሁን ላይ ሊያሳፍረን ይገባል። ስንት ሺህ ወጣት ገብረንበት የመጣ ለውጥ ነው። እናም ይሄኛው ከዛኛው የተሻለ ነው። ነገ ጠዋት ደግሞ የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ይሄ ሂደት ነው። ሂደቱን መቀበል አለብን። ሂደቱን ደግሞ የበይ ተመልካች ሳንሆን፤ እኛንም ይመለከተናል ሀገራችን የሁላችንም ነች ብለን የየራሳችንን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን። እዚህ ወቃሽ ተወቃሽ፤ አሳዳጅ ተሳዳጅ፤ የሚሆን ሰው ፍጹም ሊኖር አይገባም። አይችልምም። ስለዚህ አንዳንድ ዝም ብሎ በሞቅታ የተፈጠሩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ የዛሬ ሁለት አመት የነበሩ ነገሮችና ዛሬ ያሉት በብዙ መልኩ ይለያያሉ። ስለዚህ በሆደ ሰፊነት፤ በአርቆ አሳቢነት ለአንዳንድ ችግሮች ጥግ ይዘን በመውቀስ በማኩረፍ ሳይሆን እኛም የመፍትሄው አካል መሆን አለብን። የኩርፊያ ፖለቲካ ምንም ሊጠቅመን አይችልም። መስራት የሚቻለው በማኩረፍ፣ በመውቀስና በመጠላላት ሳይሆን በመቀራረብ ነው። አይደለም በሀገር ደረጃ እንኳን ከጎረቤትህም ጋር በቀላል ሁኔታ አትኮራረፍም። በዛ ልክ የተዋሀድክ ነህ። አጥሩ ተፈጥሮአዊ የሆነ ድንበር አይደለም። ሰው ነህ። የሰው ህመምም ሊያሳምምህ፤ የሰው ችግርም ሊገባህ ይገባል። በትልቁ ደግሞ መደማመጥ አለብን። ሌላኛው ሰው የሚያስበው ምንድነው፤ ችግሩስ ምንድነው፤ ብለን መቀራረብ መደማመጥ መተሳሰብ ከቻልን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በጣም ዘመናዊ እናደርገዋለን። ሶስተኛው ደግሞ፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማስፋት ነው። ሁሉም ሰው የተሻለ ኑሮ ለመኖር ይፈልጋል። የእኛ ሀገር ሁኔታ ደግሞ ይታወቃል። ከዚህ ካለንበት የድህነት አረንቋ ወጥተን የተሻለ ሕይወት እንድንኖር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥለት ፍትሀዊ ማድረግ ይገባል። ይህ ደግሞ የመንግስት ስራ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ራሱን ለመለወጥ መትጋት፤ መንግስት ደግሞ እድሎችን ማስፋት መቻል አለበት። ለዚህ መንግስትና ሕዝብ ተቀናጅቶ፤ ጥረቱን ደምሮ፤ ሕዝቡ የተሻለ ሕይወት እንዲኖርና ወደ ብልጽግና እንድንሸጋገር የማስቻል ስራ መቀጠል አለብን። አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ። አቶ ነብዩ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም
ወንድወሰን ሽመልስ