
ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የማምረቻ መሣሪያዎች ተሠራጭተዋል
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለሥልጣን ባለፉት ሦስት ዓመታት ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የማምረቻ መሣሪያዎችን ማሰራጨቱን አስታወቀ።
በባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለስ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የማምረቻ መሣሪያዎቹ ከልማት ባንክ እና ከካፒታል ዕቃ ንግድ ሥራ ኪራይ አክሲዮን ማኅበራት ጋር በመሆን ሲሆን፣ በዚህም 3ሺ98 ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ በተከናወነው በዚህ ሥራ 9ሺ902 መሣሪያዎች መሰራጨታቸውን አቶ አሸናፊ ጠቅሰው፣ ለመሣሪያዎቹ ግዥም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መደረጉን አብራርተዋል። በካፒታል ዕቃ ንግድ ኪራይ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መሣሪያዎች መሠራጨቱ መንግሥት የኢንዱስትሪዎቹን የማምረቻ ዕቃ ማነቆ ችግር ለመፍታት የሚያደረገውን ጥረት እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ አሠራሩ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በአገራችን የተተገበረ መሆኑን አስረድተዋል።
አገሪቱ የካፒታል ዕቃ ንግድ ኪራይ አዋጅ 103/1990 መውጣቷን አስታውሰው፣ በካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ላይ በትኩረት የሚገባ ሳይገኝ መቆየቱን አመልክተዋል። አዋጁ እንደገና በአዋጅ 807/2005 ማሻሻያ ተደርጎበት መውጣቱን ገልፀው፣ ይህም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት እንደሚያመለክት ተናግረዋል።
እንደ አቶ አሸናፊ ገለፃ፤ በልማት ባንክ በኩል በ2009 በጀት ዓመት አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ትግራይን ጨምሮ በአዲስ አበባ ለሚገኙ 1ሺ 624 ኢንዱስትሪዎች 2ሺ926 መሣሪያዎች ተሰራጭተዋል፤ መሣሪያዎቹም 158 ነጥብ4 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ናቸው። በተጠቀሱት ክልሎች ድሬዳዋን ጨምሮ ለ35 ኢንዱስትሪዎች 213 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መሣሪያዎች በካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበራት ተሰራጭተዋል።
በ2010 በጀት ዓመትም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች ለሚገኙ ለ827 ኢንዱስትሪዎች 2ሺ243 መሣሪያዎች መሰራጨታቸውን ጠቅሰው፣ የማምረቻ መሣሪያዎቹም ከ189 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውንና በካፒታል ዕቃ ንግድ ፋይናንስ አክሲዮን ማኅበራት አማካኝነት መሰራጨታቸውን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ዓመት በልማት ባንክ በኩል በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በሶማሌና ጋምቤላ ክልሎች እና አዲስ አበባ ለሚገኙ 106 ኢንዱስትሪዎች 1ሺ350 መሣሪያዎች ከ550 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የማምረቻ መሣሪያዎች መሠራጨታቸውን ገልፀዋል።
በ2011 በጀት ዓመትም በልማት ባንክ እና በካፒታል ዕቃ ንግድ ማኅበራት በኩል ለ1ሺ 107 ኢንዱስትሪዎች ከ545 ነጥብ7 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 3ሺ148 ማምረቻ መሣሪያዎች ተሠራጭተዋል ብለዋል።
ለካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ኪራይ የሚገባ የማምረቻ መሣሪያ ከውጭ ሲገባ ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ እንደሆነ አቶ አሸናፊ ገልፀው፣ ተከራዩ ለአከራይ ክፍያ በሚፈፅምበት ጊዜም የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍል እንደማይደረግ አስታውቀዋል። የካፒታል ዕቃውን ያለ ተጨማሪ ዋስትና በኪራይ መጠቀም እንደሚቻል ተናግረው፣ ዘርፉን ለማበረታታት በመንግሥት ከሚሰጡ ድጋፎች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ