አቶ ታደለ ካሳ ይባላሉ። በኢንቨስትመንት መዳረሻነቷ በምትታወቀው ደብረብርሃን ከተማ ጠባሴ አካባቢ በ1967 ዓ.ም ነው የተወለዱት። ለቤተሰባቸው ሰባተኛ ልጅ ናቸው። አባታቸው ወታደር ናቸውና እርሳቸውም ያደጉት በወታደር ካምፕ ውስጥ ነው። በልጅነታቸው ወላጅ አባታቸውን ቢያጡም አጎታቸው እንደአባት ሆነው አሳድገዋቸዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዘርዓያዕቆብ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በወቅቱ ደግሞ መሆን የሚገፈልጉት ወታደር መሆን ነበርና የሚሊተሪ አልባሳትን ሲያድጉ እንደሚለብሱ ነበር ህልማቸው። በተጓዳኝ ግን ኤሌክትሮኖክስ እቃዎችን መፈታታትና መገጣጠም ያስደስታቸው ነበር።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ሲገቡ ግን የሒሳብ ትምህርት ፍላጎታቸው ከፍተኛ መሆኑን ይረዳሉ። እናም 12ኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት ሲያጠናቅቁ ወደዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት እድል ተፈጠረ።
ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲመደቡ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግን ምርጫቸው አደረጉ። ለአምስት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ደግሞ አዲስ አበባ የሚገኙ አጎታቸው እና ባለቤታቸው ትምህርቱን ለቅጥር ስራ ብቻ ሳይሆን የግል ንግድ ጀምረው እንዲተገብሩትም ምክራቸውን ይለግሷቸዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ እንዳገኙ አዲስ አበባ የሚገኝ የብራዚል የቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ ተቀጠሩ። በወቅቱ የማይክሮሶፍት ኩባንያ ስልጠና በመውሰድ ከዋና ስራቸው በተጓዳኝ በሚያገኙት የእረፍት ጊዜ በግላቸው የኔትወርክ ዝርጋታ ላይ ተሰማሩ። የተለያዩ የትምህርት ተቋማትን እና የግል ድርጅቶችን የኔትወርክ ዝርጋታ በማከናወን መጠነኛ ገንዘብ አጠራቅመዋል።
በመቀጠልም የቅጥር ስራቸውን ለቀው በግላቸው የኮምፒውተር ማሰልጠኛ ለመክፈት ተነሱ። በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በ600 ብር ህንጻ ላይ የሚገኝ ቢሮ ተከራይተው በ1995 ዓ.ም <<ሀ>> ብለው የማስተማር ስራቸውን ጀመሩ። በወቅቱ አንድ ኮምፒውተር በ13 ሺ ብር ገዝተው አስፈላጊውን የስልጠና መስጫ ፈቃድ ኖብል ኮምፒውተር ማሰልጠኛ በሚል አወጡ።
የማስተማር ስራው ግን እንዳሰቡት አልተሳካም። 1 ሺህ 800 ብር እየከፈለ ኮምፒውተር የሚማር ሰው ጠፋ። እናም አቶ ታደለ አንድ መላ ዘየዱ። ክፍያውን በመቀነስ ብዛት ያላቸውን ተማሪዎች ለመሳብ በመወሰን ክፍያውን ለአራት ወራት 180 ብር አደረጉ። ቅናሹን የተመለከቱ ከ200 በላይ ተማሪዎች ደግሞ በሰልፍ ተመዘገቡ። የመመዝገቢያ 20 ብር ከእያንዳንዱ ተማሪ ተቀብለው ጠቀም ያለ ገንዘብ ሰበሰቡ።
ባገኙት ገንዘብም በገነት ሆቴል በ1ሺህ 800 ብር ሰፋ ያለ ቢሮ ተከራይተው አነስተኛ የመማሪያ ቁሳቁሶችን ማሟላት ቀጠሉ። ከዚያም በየሁለት ሰዓት ልዩነት ተማሪዎቻቸውን እያቀያየሩ ማስተማሩን ተያያዙት። በወቅቱ እስከምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ በሚያስተምሩበት ጊዜ አንድ ጓደኛቸው ያግዛቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ጥቂት ቀናት የንድፈሃሳብ ትምህርት ብቻ ከሰጡ በኋላ ከተማሪዎች ክፍያ በተገኘው ገንዘብም 20 ኮምፒውተሮችን ገዝተው የተግባር ስልጠናውንም አከሉበት። ኮምፒውተሮቹን የተገዙት ደግሞ በግማሽ ክፍያ 35ሺህ ብር አውጥተው ግማሹን ደግሞ በዱቤ ግዥ ተዋውለው ነበር።
አድካሚ የሆነውን የማስተማር ጊዜ ለሶስት ወራት ከጓደኛቸው ጋር እንደከወኑ ግን የነበራቸው ገንዘብ በማለቁ ለቤት ኪራይም የሚሆን ገንዘብ አጠራቸው። የመጀመሪያው ዙር ተማሪዎች ሊያጠናቅቁ አንደ ወር ሲቀራቸው ግን ሌላ ዙር ምዝገባ አድርገው ተጨማሪ ገንዘብ አገኙ። እናም የኮምፒውተሮቹን ዱቤ እዳ ከፍለው ማሰልጠኛቸውን አጠናከሩ። ከመሰረታዊ ኮምፒውተር ስልጠና ባለፈ አውቶካድ እና ሌሎች ተጨማሪ ስልጠናዎችን አከሉበት።
አቶ ታደለ አቅማቸው ሲጠናከር ደግሞ አንድ ተጨማሪ የንግድ ስራ እድል ተከፈተላቸው። ወቅቱ የአሜሪካን ዲቪ በኮምፒውተር መሞላት የተጀመረበት ጊዜ ነበርና በሚያስተምሩባቸው ኮምፒውተሮች አማካኝነት ዲቪ እንደሚሞሉ አሳወቁ። እናም ለሁለት ወራት ያክል ሰው ተሰልፎ ምዝገባውን አከናወነ። ይህ ወቅት ለእርሳቸው ጥሩ ገቢ የተገኘበት እና ተቀማጫቸውንም ያሳደጉበት ነበር።
ከጥቂት አመታት በኋላ የዲቪውን እና ከማስተማሩ የተገኘውን ገቢ አጠራቅመው አነስተኛ የኮምፒውተር እና ኤሌክትሮኒክስ መለዋወጫዎችን ወደሀገር ውስጥ ወደ ማስገባቱ ተሸጋገሩ። ዱባይ ሄደው ጥቂት የኮምፒውተር መለዋወጫዎችን ሲሸምቱ ደግሞ የፕሪንተር ቀለም አሞላል ሂደትን ይመለከታሉ። ወደኢትዮጵያ ሲመለሱ በ45 ሺህ ብር የፕሪንተር ቀለም መሙያ ማሽን ገዝተው ወደስራው ገቡበት።
የቀለም ሙሌቱ ስራ በአጭር ጊዜ ታዋቂነቱ እየናረ ገቢውም እያደገ ሲመጣ ለአራት አመታት የከወኑትን የማስተማር ስራ አቁመው ወደቀለም መሙላቱ እና የጥገና ስራዎች አተኮሩ። በዚህ ወቅት ወደዱባይ እና ቻይና ይመላለሱ ነበር። አቶ ታደለ በሚሄዱባቸው ሀገራት ግን አዳዲስ አውደርዕዮችን እና አዳዲስ ፈጠራዎችን ተመልክተው ወደኢትዮጵያ ስለማምጣት ነበር ፍላጎታቸው። በተጨማሪ ኢንተርኔት ላይ ብዙ ዕውቀቶችን በመፈለግ ስራ ላይ ለማዋል ሁሌም ይጥራሉ። እናም ወደውጭ ሀገር ሲሄዱ የተመለከቱት የህትመት ቴክኖሎጂ ይስባቸዋል።
የቀለም ሙሌቱን ሳያቋርጡም ካሳንቺስ አካባቢ ማተሚያ ቤት ይከፍታሉ። በወቅቱ ለማሽን ግዥ ሶስት ሚሊዮን ብር በማውጣት የተደራጀ ማተሚያ ቤት ከፈቱ። የህትመት ስራው እየተጠናከረ ሲመጣ ደግሞ አሁንም በሌላ ቴክኖሎጂ ቀልባቸው ይሳባል። እቃዎችን ለማስመጣት ወደውጪ ሀገራት ሲሄዱ ኤግዚቢሽኖች ላይ ያዩት የካርቶን ማምረት ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር ቆርጠው ተነሱ።
በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተመስርቶ በየጊዜው የሚያድገው ካፒታላቸውን ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት በማዋል በ1999 ዓ.ም ሰንዳፋ ከተማ ላይ በ 13 ሚሊዮን ብር ካርቶን ፋብሪካ አቋቋሙ። የህትመት ድርጅቱን ለቤተሰብ አባላት በመተው እርሳቸው ካርቶን ፋብሪካው ላይ በማተኮር ንግዱን መስመር አስያዙት። ነገርግን የካርቶን ማምረቻ ጥሬ እቃው ከውጭ የሚመጣ በመሆኑ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ስራው ተቀዛቀዘ።
የቻይናዎችን ጥበብ ለመማር ሁልጊዜም ዝግጁ የሆኑት ባለሃብት በቻይና ሀገር በተዘጋጀ ኤግዚቢሽን ላይ የሚታደሙበት አጋጣሚ ተፈጠረ። በኤግዚቢሽኑ ላይ የተመለከቱት የማግኒዥየም ቦርድ አሰራር ደግሞ ሊተገበሩት የሚችሉት አይነት ቴክኖሎጂ መሆኑን አውቀዋል። እናም በካርቶን ፋብሪካቸው ውስጥ ማሽኖችን አስገብተው ማግኒዥየም ቦርድ ማምረቱን ተያያዙት። የማግኒዥየም ጥሬ እቃው ደግሞ የሚመጣው ቀንጢቻ ከተባለ ስፍራ ነበርና የመንግስት ተቋማት ጥሬ እቃውን በብዛት በሚፈልጉበት ወቅት አሁንም የግብዓት እጥረት ተፈጠረ።
አቶ ታደለ የአዲሱ ስራቸው እንቅስቃሴ በቀነሰበት ወቅት ታዲያ ፒያሳ አካባቢ ሲዘዋወሩ አንድ ሰው የጂፕሰም የቤት ውስጥ ጌጣጌጦችን ከመኪና ሲያስወርድ ይመለከታሉ። ከየት ነው የመጣው ጂፕሰሙ ብለው ቢጠይቁ ደግሞ ከቻይና መሆኑ ይነገራቸዋል። በነገሩ ተገርመው ሀገር ውስጥ ሊሰራ የሚችል ዲዛይን መሆኑን ይናገራሉ። እናም ጂፕሰሙን ሰርተው እንደሚያመጡለት ለሰውዬው ነግረው ይለያያሉ። ሳይደግስ አይጣላምና ነው ነገሩ ለማግኒዥየም ማምረቻ ያመጡትን ማሽን ጂፕሰሙም ቅርጽ ለማስያዝ ተጠቅመው ጥሩ የቤት ውስጥ ማስዋቢያ አምርተው ያቀርባሉ። ምርቱንም የተወሰነ ማሻሻያ ቢያደርጉበት ከውጭ የሚመጣውን ጂፕሰም እንደሚያስቀር በርካቶች ሃሳብ ሰጥተዋቸው ወደማምረቱ ተሸጋገሩ።
በአጋጣሚ የሞከሩት የጂፕሰም ጌጣጌጥ እና የቤት ውስጥ ማስዋቢያ ምርት ግን ከውጭ ከሚመጣውጋር ሲነጻጸር በጥራት ብዙም የማያንስ ነገር ግን በዋጋ ከሶስትና አራት እጥፍ በላይ የቀነሰ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተመራጭነቱ አደገ። በተለይ በ2002 ዓ.ም ላይ በርካታ ኮንዶሚኒየሞች እና የተለያዩ ህንጻዎች ሲገነቡ የአቶ ታደለ የጂፕሰም ምርቶች በከፍተኛ መጠን ተመርተው ተሸጠዋል። በርካታ ግለሰቦችን ምርቱን ገዝተው በቤታቸው ተጠቅመውታል። ይህ ንግድ ለባለሃብቱ ሰፊ ገበያን የፈጠረ ዘርፍ ነው። በወቅቱ በዓመት እስከ አራት ሚሊዮን ብር ያገኙ ነበር። እስከአሁንም ድረስ ስራው እየተስፋፋ ሄዶ 75 ሰራተኞች የሚሳተፉበት ግዙፍ ማምረቻ ሆኗል።
የጂፕሰም ገበያው ደግሞ አቶ ታደለን ይበልጡኑ ወደኮንስትራክሽን ዘርፉ እንዲሳቡ አድርጓቸዋል። እናም ወደቀለም ምርቶችም ዘርፍ ለመግባት ፍላጎት አሳዩ። በዚህ ወቅት ታዲያ ከቻይና የሚመጣው ግራናይት ቀለም ለግላቸው ለማሰራት ሲፈልጉ በካሬ 800 ብር እንደሚፈጅ ይነገራቸዋል። የዋጋው ውድነትን በመቀነስ በሀገር ውስጥ ለማምረት ስለሚቻልበት መንገድ ኢንተርኔት ላይ መፈለግ እና ወደቻይና ተጉዘው ስለአመራረቱ ጥናት ማድረግም ጀመሩ።
ለሁለት ወራት ቻይና ውስጥ ስለቀለም ቴክኖሎጂ አስፈላጊውን ትምህርት ወስደው ገጠራማ አካባቢዎች ድረስ በመሄድ ስለ ቀለም አመራረት ዕውቀት መቅሰማቸውን ያስረዳሉ። ወደአዲስ አበባ ሲመለሱም የቤተዘመድ ንብረት የሆነ ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ቀለም ለማምረት የሚያስፈልጉ ማሽኖችንና መትከል እና ሙከራዎችን ማካሄድ ቀጠሉ።
በአነስተኛ መጠን ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ጥራት ያለው ቀለም ለማዘጋጀት ለሁለት ዓመታት ሙከራ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በመጨረሻም የሚፈልጉትን አይነት ደረጃ ላይ ሲደርስ የዛሬ ዓመት ላይ «የን» ብለው የሰየሙትን የቀለም ፋብሪካ በይፋ ስራ አስጀምረው የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ አቅርበዋል። በተለይ አርት ፔይንት የተሰኘውን በዲዛይኖች እና በቀለማት ያጌጠውን የቀለም ቅብ አይነት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ።
በተለያዩ የብሩሽ አይነቶች አማካይነት ልዩ ዲዛይን ያላቸው የህንጻ ቀለም ቅብ እና የቤት ውስጥ ዲዛይኖችን መከወን እንደሚቻል አሳይተዋል። አሁን ላይ ኳርትር፣ ለግራናይት የሚሆኑ በወፍራምና በቀጭኑ የተዘጋጁ ፈሳሽ ቀለሞችን እና የዱቄት ቀለሞችን እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ። 25 ኪሎግራሙን ኳርትዝ ቀለም በ1ሺህ200 ብር ለገበያ ያቀርባሉ፤ በአንጻሩ አንድ ኪሎግራሙን የዱቄት ቀለም በ80 ብር ነው የሚሸጡት። ነገር ግን ምርቶቻቸው ከውጭ ከሚመጡት የተሻለ ጥራት እና በካሬ ሜትር ከፍተኛ መጠን ያለው ቦታ መቀባት የሚያስችሉ መሆናቸውን አቶ ታደለ ይናገራሉ።
በቀለም ምርቶቹ ላይ ያለው የህብረተሰቡ ተቀባይነት ጥሩ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ታደለ፤ ሀገር ውስጥ ሰፊ የገበያ ድርሻ ያላቸው የቀለም አይነቶች ባሉበት መድረክ ገበያውን ሰብሮ ለመግባት የአርት ቅብ ላይ ያተኮሩ ምርቶችን ማቅረባቸው አስፈላጊ እንደነበር ይገልጻሉ። የተለያዩ ብሩሾችን ተጠቅሞ ለሚዘጋጁ የአርት ቅቦችም በየሳምንቱ ቅዳሜ ዕለት በነጻ ለማንኛውም ሰው ስልጠና በመስጠት ዕውቀታቸውን እያካፈሉ ይገኛል።
ዘርፈ ብዙው ሰው አጠቃላይ ሃብታቸው 80 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ይናገራሉ። ለእርሳቸው ስራ የማይቆም የፈጠራ ውጤት ነው። እናም በቀጣይ ፎም ጀነሬት በተባለ ቴክኖሎጂ አማካኝነት በአነስተኛ ወጪ የሚገጣጠሙ ቤቶችን ገንብተው በአነስተኛ ወጪ ለነዋሪዎች ኪራይ የሚሰጡበት ዘርፍን ለመቀላቀል ዝግጅት ጀምረዋል። ፎም ጀነሬት ማሽኑ በሲሚንቶ የሚዘጋጅ በአንድ ሰው የሚነሳ ነገር ግን ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው ግድግዳ ለማምረት ያስችላል። ማሽኑን ገዝተው ሙከራ እያደረጉ የሚገኙት አቶ ታደለ፤ ሰፋ ባለ ቦታ ላይ የቤቶቹን ግንባታ አከናውነው በቤት ኪራይ ውድነት የሚሰቃየውን ዜጋ በአነስተኛ ወጪ ችግሩን እንዲያቃልል ለማድረግ አልመዋል። ነገር ግን ሃሳባቸውን ይዘው ወደመንግስት ቢሮዎች መሄድ እንደትልቅ እዳ የሚያዩት ጉዳይ በመሆኑ በእራሳቸው ወጪ መሬቶችን ገዝተው ለመስራት ነው የወጠኑት።
<<እኔ ስራ ሳልመርጥ እዚህ ደርሻለሁ>> የሚሉት አቶ ታደለ፣ በተለይ ወጣቱ ማንኛውም ለሀገር በሚጠቅም ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ በፈጠራ የታጀበ ንግድን ቢተገብር አዋጭ እንደሚሆንለት ይናገራሉ። ማንኛውም ሰው ከለፋና ስራውን ለማሳደግ ከጣረ ስኬታማ የማይሆንበት ምክንያት የለምና ስንፍናን ብቻ እንጠየፍ የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 28/2012
ጌትነት ተስፋማርያም