አማረች ዳመና ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በአዊ ዞን ባንጃ ሽኩዳድ በሚባል አካባቢ ነው። ረጅም ቁመናና ጠይም መልከ አላት። መቃ የሚመስለውን አንገቷን እንደዘለቃችሁ በጠባብ የልጅነት ድንቡሽቡሽ ፊት ላይ ቀስት የመሰለ አፍንጫዋ የሚወረወር ዓይንን ተቀብሎ ያሳርፋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ብዙም የከፋ ችግር ሳይኖርባት ጓደኞቿን ተከትላ እንደዋዛ ካደገችበት ቀዬ መሰስ ብላ ወጥታ መቅረቷን ታነሳለች። አዲስ አበባ እንደናፈቀቻት አዲስ ልትሆንላት ቀርቶ የልጅነት አበባዎቿን በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እንደነጠቀቻት የምትናገረው በምሬት ነው። እየዋለ ሲያድር ያደገችበትን ሰፈር የሚያስናፍቁ ብዙ ሁኔታዎች ቢገጥሟትም የሰው አፍ እንዴት ብሎ ያስኖረኛል? ስትል በይሉኝታ ተሰቅዛ ፊቷን ላታዞር ማለች።
በወቅቱ ሁለት እግሮቿ የአውቶብስ ተራውን ግቢ በወጉ ሳይረግጡ ጩልሌዎች ተቀብለው በሴተኛ አዳሪነት ሥራ እንዳስጀመሯት የምትናገረው አማረች፣ ልጅነቷን ሳትጨርስ እሷም በተራዋ የልጅ እናት የሚያደርጋት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበር ታስታውሳለች። ነገር ግን በወቅቱ አማራጭ ያልነበራት አማረች ራሷን ለሞት አጋልጣ እርግዝናውን አጨናገፈችው።
ተስፋ፣ ወግ ማዕረግ፣ ትዳር፣ ክብር፣ ገንዘብ፣ጤና፣ መውለድ፣ መክበድ ለእሷ እንዳልተፈጠሩ ትናገራለች። ዝም ብሎ መዋል፣ ማደር፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መጨፈር እጣፋንታዎቿ እንደሆኑ ታስባለች፤ የሕይወት ጣዕሙ ጎምዝዞባታል፤ አዲስ ነገር አጥታበታለች፤ ዛሬ ላይ ግን አትፈልገውም፤ ረስታዋለች። ሕይወቷን በዚሁ ቦይ እስከመጨረሻው ይፈስ ዘንድ የፈቀደችለት ይመስላል። አውቶብስ ተራ አካባቢ ዛሬ የእሷ ግዛት ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የጤና ማጎልበትና በሽታ መከላከል ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ቢሳ እንደሚሉት፤ በከተማዪቱ የማህበረሰቡን ጤና በመጠበቅና በመከላከል በኩል መጠነ ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። ለምሳሌ በኤች አይ ቪ ኤዲስ መከላከል ዙሪያ በዋናነትም ‹‹የአር ቲ ›› መድኃኒት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውን የጤና ድርጅቶችን ለማስፋት እየተሰራ ነው። በ154 የጤና ተቋማት አገልግሎቱ ተደራሽ መሆን ችሏል።
የኤች አይ ቪ ኤድስ ሕክምና በግልም ሆነ በመንግሥት በነጻ እንደሚሰጥ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ስርጭቱን ለመግታት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ይሰራል። የፊት ለፊት የምክር አገልግሎትና የጤና ትምህርት ይሰጣል። በሚዲያዎችና በተለያዩ የመልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶች አገልግሎቱን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ ጌቱ እንዳብራሩት፤ ባለፉት ስድስት ወራት 296 ሺ 784 ሰዎች እንዲመረመሩና ራሳቸውን እንዲያውቁ የታቀደ ቢሆንም 366 ሺ 385 ተመርምረዋል። ሰባት ሺ 56 ያህሉ ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቷል። እነዚህ ሰዎች የጸረ ኤች አይ ቪ ሕክምና እንዲከታተሉ ለማድረግ ቢታቀድም ተጠቃሚ የሆኑት ስድስት ሺህ 433 ናቸው፤ አፈጻጸሙም ካለፉት ተመሳሳይ ወቅቶች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ በ2020 የተቀመጡ የሶስቱን ዘጠናዎች ግቦች ለማሳካት ከሚሰሩ ተግባራት መካከል የመጀመሪያው ምርመራ ነው። በዚህም ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 90 በመቶ የጸረ ኤች አይ ቪ ሕክምና ተደራሽ ማድረግ፤ ሁለተኛው ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው 90 በመቶ ሕክምና ማስጀመር እና የመጨረሻው ሕክምና ከጀመሩት 90 በመቶ የቫይረስ መጠናቸውን ከሚፈለገው (ከአንድ ሺ) በታች ማውረድ እንዲቻል መሰራቱን አብራርተዋል።
የክፍለ ከተማ የዘርፉ አመራሮች፣ ሆስፒታሎች እና ባለድርሻ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቅንጅት በሳምንት ሥራው ያለበትን ደረጃ፣ በምን አቅጣጫ እየሄደ እንደሆነ፣ ያሉበት ክፍተቶች ምን እንደሆኑ እና መወሰድ በሚገባቸውን መፍትሄዎች ላይ በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል።
ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም በሁሉም አገልግሎት መስጫ ጤና ተቋማት 115 ሺ 471 ሰዎች የአር ቲ መድሐኒት ማድረግ እንዲችሉ ቢታቀድም ክትትል 101 ሺ 713 (88 በመቶ) ተፈጽሟል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም ከአምስት ሺ በላይ ብልጫ አሳይቷል ብለዋል።
ከኤች አይ ቪ አድስ መከላከልና መቆጣጠር ጋር በተያያዘ በማህበረሰቡ ዘንድ ሥራው ተቀዛቅዟል የሚሉ አስተያየቶች እንደሚነሱ ገልጸው፤ ትኩረት አልተነፈገውም፤ እንደውም በትኩረት እየተሰራ ነው። የአስተያየቱ መነሻም እንደቀደመው (ሲጀመር አካባቢ እንደነበረው) ያለ አሰራር በየሚዲያዎች በሰፊው ሽፋን ስለማይሰጠው እንደሆነ ተናግረዋል።
የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሰው እንዳሉት፣ በአዲስ አበባ ማህበረሰቡ ከ90 በመቶ በላይ ስለኤች አይ ቪ ኤድስ ግንዛቤው አለው። ነገር ግን ችግሩ የባህሪ ለውጥ ማምጣት አለመቻል ነው። በመሆኑም ተደጋጋሚ ሥራዎችን መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በሥርዓተ ትምህርት ተካትቶ የሚሰጥ እንደመሆኑም ስለ በሽታው ሲነሳ ከሕጻን እስከ አዋቂ ድረስ ያውቃል፤መረጃው አለው፣አዲስ የሚሆንበት የለም ይላሉ።
የበሽታው ስርጭትም ቢሆን ከአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ወጥቷል። በተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተወስኗል። ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተለይተዋል። ቀደም ሲል መቶ ሰው ቢመረመር አምስት ስድስት ሰው ቫይረሱ በደሙ ያለበት ሊገኝ ይችላል። ዛሬ ላይ ግን በተለዩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ካልሆነ ምንም ላይገኝበት እንደሚችል ያስረዳሉ። በመሆኑም በውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ የሚመጣ ግብዓትንም ማባከን ይሆናል።
ካለፉት ረጅም ዓመታት የተለየ ውጤታማ የሚያደርጉ አሰራሮችን እየተተገበሩ እንደሆነ ገልጸዋል። ‹‹ኪት›› ውስዶ ሰው ራሱን መመርመር ይችላል። ተጋላ ጮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል። በዚህ የተነሳም ተግባሩ የተቀዛቀዘ እንደሚመስል አስገንዝበዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት በኤች አይ ቪ ስርጭት ዙሪያ ያስቀመጠው መዳረሻ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ ከ2021 በኋላ ሶስቱ ዘጠናዎች ወደ ሶስቱ ዘጠና አምስት ግቦች እንደሚቀየሩ ተመላክቷል። በመሆኑም ውዝፍ ሥራዎችን አናሻግርም ይላሉ አቶ ጉቱ። በ2030 ስርጭቱን በአጠቃላይ ለመግታት የተቀመጠ ትልም ነው።
ሴተኛ አዳሪዎች፣ የከባድ መኪና ሾፌሮች፣ የቀን ሰራተኞች፣ ለቫይረሱ የተጋለጡ ሰዎች ቤተሰቦች በተጋ ላጭነት ከተለዩት የሚጠቀሱ ናቸው። ስለሆነም በሥራ ባህሪያቸው እና በጾታ ባህሪያቸው የሚጋለጡ ይኖራሉ። ስለዚህ በጅምላ ከሚሆን ይልቅ የተለዩት ላይ ሰፊ ሥራዎች ቢሰሩ የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠርና መግታት ይቻላል ብለዋል።
በአጠቃላይ የበሽታው መገኛ እየተሰባሰብ ሲሄድ ክትትልና ቁጥጥሩ እየተጠናከረ ሊቀጥል ይገባል። የኃይማኖት አባቶች፣ታዋቂ ግለሰቦች እና እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የሚገኘው ባለሙያ በቅንጅት ያሳየውን ቅንጅታዊ ተሳትፎ መቀጠል አለበት። አሁን ባለው ተጨባጭ ማሳያ በኤች አይ ቪ ኤድስ ምክንያት ሕይወቱን የሚያጣ እና የአልጋ ቁራኛ የሆነ ሰው የለም።ይሄ የለውጥ ተግባር በመንግሥት ቁርጠኝነት ነው። ሁሉም የመን ግሥት የጤና ተቋማት ሕክምናውን የሚሰጡ ሲሆን በግሎቹ የተሟላ ግብዓት ያላቸው እና የተመረጡ የጤና ተቋማት እንዲሰጡ መደረጉን አብራርተዋል።
ጤናማ ማህበረሰብ በአገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጦች የሚያበረክተው ፋይዳ ቀላል አይደለም። በመሆኑም ማህበረሰቡ የራሱንና የቤተሰቡን እንዲሁም የአካባቢውን ጤና በመጠበቅ የዜግነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ሙሐመድ ሁሴን