እናት የጡቷን ወተት፣ የእጇን ጉርሻ ለልጇ እንደምተለግስ ሁሉ አዲስ የጀመሩትን የስራ ዘርፍም ወደልጃቸው አሸጋግረዋል። ከታሸገ ምግብ ጋር የተያያዘው የንግድ ዘርፋቸው በበርካቶች ዘንድ ታውቆ ገቢ ማስገኘት እንዲችል አድርገዋል። የማታ የማታ ግን የለፉበትን ውጤት ፍሬ አፍርቶ ማየታቸው አልቀረም። ልጃቸውም በእርሳቸው እግር ተተክቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ካፒታል ያለውን ንግድ እየከወነ ይገኛል።
ልጅ አቶ ወሰን ገብረመድህን ነው ሙሉ ስማቸው እናት ደግሞ ወይዘሮ አምባነሽ ከበደ ይባላሉ። አቶ ወሰን የተወለዱት ጎንደር ከተማ ነው። ወይዘሮ አምባነሽ የመጀመሪያ ልጃቸውን ወሰንን የሀገራቸውን ባህል እያስተማሩ አሳድገዋል። ብላቴናው ወሰን ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት ሲደርስ ግን በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የሚሰሩት አባታቸው በስራ ምክንያት ወደኮትዲቯር የሚሄዱበት አጋጣሚ ተፈጠረ። እናም መላ ቤተሰቡ ጥቂት አዲስ አበባ ቆይቶ ወደምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አቀና።
በኮትዲቯርም እናት ልጃቸውን ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛን ቋንቋ ጭምር እንዲላመድ በማድረግ ወደትምህርት ገበታ እንዲቀላቀል አደረጉ። በድጋሚ ደግሞ አባት በስራ ምክንያት ወደሌላኛዋ የምዕራብ አፍሪካ ሀገር ካሜሩን ሲዘዋወሩ አሁንም መላ ቤተሰባቸውን ይዘው መጓዝ ግድ ሆኖባቸው ነበር። አቶ ወሰንም እስከ 9ኛ ክፍል ድረስ በካሜሮን ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የአባታቸው የካሜሮን የስራ ዘመን ሲጠናቀቅ ደግሞ ቤተሰባቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። አቶ ወሰንም በአቃቂ ቃሊቲ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው አስረኛ ክፍልን ቀጠሉ። እናታቸው ደግሞ ከባህር ማዶ መግባቢያ ቋንቋዎች ባለፈ አማርኛንም በወጉ እንዲይዙ ስላደረጉ አቶ ወሰን በትምህርት ቤት እምብዛም አልተቸገሩም። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በጥሩ ውጤት አጠናቀው ወደዩኒቨርሲቲ ገቡ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታስቲክስና ኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ተቀላቅለው የከፍተኛ ትምህርት እውቀታቸውን ቀስመዋል። በ1992 ዓ.ም ደግሞ እንደተመረቁ በቀጥታ ወደስራ የገቡት ወደ አንድ የግል ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ተቋም ነው። የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱን በተግባር በመቀየር በተቋሙ ለአንድ ዓመት ተኩል ያክል አገልግለዋል። ከዚያም ወደመምህርነቱ ተሸጋገሩ።
በማይክሮሊንክ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ተቋም በማስተማር ለአንድ አመት ተኩል ያክል ሰርተዋል። በወቅቱ ደግሞ ከህንድ ሀገር የትምህርት እድል በግላቸው ያገኛሉ። እናም በህንድ የኮምፒውተር ሳይንስን ትምህርት እየተከታተሉ ለሁለት ዓመት ከስድት ወራት ቆይተዋል። በጊዜው ትምህርቱ የሚሰጠው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቢሆንም ከአካባቢው ማህበረሰብ የተማሩት ህንድኛ ቋንቋን በመጠኑ መናገር ችለው ነበር።
ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ደግሞ ከጓደኞቻቸው ጋር በመጣመር ‹‹ፓዝኔት›› የተሰኘ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ኩባንያ አቋቋሙ። በወቅቱ ደግሞ እናታቸው የፋርማሲ ሙያ ባለቤት ነበሩና አምባ የተሰኘ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ከፍተው የተለያዩ መድኃኒቶችን ከውጭ ሀገራት እያስመጡ ለገበያ ያቀርቡ ነበር። በኢትዮጵያም ከመጀመሪያዎቹ ሴት የመድኃኒት አቅራቢዎች መካከልም ይመደባሉ።
እናት ወይዘሮ አምባነሽ ለስራ ጉዳይ ወደዱባይ ወይም ወደሌሎች አረብ ሀገራት ሲያቀኑ ግን ለቤተሰባቸው ምግብነት የሚውል የእንጉዳይ ምርት ያመጡ ነበር። ምርቱም ለጤና ጠቃሚ መሆኑን በመረዳታቸው በዱቄት ወይም በተለያየ መልክ የተዘጋጀውን እንጉዳይ ምግብ ውስጥ በመቀላቀል ለቤተሰብ ያቀርቡ ነበር። እናም ይህንን ምግብ ለምን ወደ ገበያ አላቀርበውም የሚል ሃሳብ መጣላቸው።
ከ12 ዓመታት በፊት በጣት የሚቆጠሩ እና በፕላስቲክ ብልቃጥ የታሸጉ የእንጉዳይ ምርቶችንም ማስተዋወቅ ጀመሩ። እንጉዳዩ በዱቄት መልክ የሚዘጋጅ እና በምግብ ውስጥ ተነስንሶ የሚበላ ብዙ ንጥረ ነገሮች የያዘ ጠቃሚ ምግብ መሆኑንም እያስረዱ ለሸማቹ አቀረቡ።
በወቅቱ ከመድኃኒት ንግዱ በተጨማሪ ‹‹ፕራይም እንጉዳይ›› የተሰኘ ድርጅት ከፍተው ነበር ምርቱን የሚያቀርቡት። የህብረተሰቡ ተቀባይነት ግን እምብዛም አልሆነላቸውም። ስለምግብነቱ የማያውቁ ሰዎች እንኳ ገንዘብ አውጥተው ለመግዛት የሚደፍሩ አልነበሩም።
‹‹የጅብ ጥላ ነውና እንዴት ብር አውጥተን እንገዛዋለን?›› የሚሉም ሰዎች አጋጥመዋቸዋል። በዚህ ምክንያት ከውጭ ሀገራት ያመጡት ምርት ገበያ በማጣቱ ምክንያት የአገልግሎት ዘመኑ እያለቀ ወደቆሻሻነት የሚቀየር ምርት ሆኖ ነበር።
ምርቱ ደንበኛ እንዲያፈራ በሚል የተለያዩ ቢሮዎችን በመቀያየርም ብዙ ተጠቃሚ ያለበትን ስፍራ መፈለጉን ግን ችላ አላሉትም። ሜክሲኮ፣ 22 አካባቢ እና ሌሎች ቢሮዎችንም ተከራይተው ሰርተዋል። በመጨረሻ ቦሌ ቲኬ ህንጻ ላይ ተከራይተው መስራት ሲጀምሩ የአካባቢው ማህበረሰብ የተሻለ የእንጉዳዩን ምርት እንደሚጠቀም ተረዱ። በዚያም ስለእንጉዳዩ ምርት ተጨማሪ ግንዛቤ በመፍጠር እና ሰዎች እንዲሞክሩት በማበረታታት ጥቂት ገቢን መፍጠር ቻሉ። ይሁንና ምርቱ በአንድ ጊዜ ተቀባይነት ለማግኘት አልቻለም።
የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ዜጎች አዲስ ነገር ለመጀመር እና ለመጠቀም ድፍረት አላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልምድ ግን ለሌች ሰዎች እንድን ነገር ሞክረውት ከተመለከቱ በኋላ የመጀመር ሂደት ነው ያለው። በዚህ ምክንያት እንጉዳዩን መመገብ የሚፈሩ ሰዎች በርካቶች ነበሩ። በጊዜ ሂደት ግን ሰው ከሰው እየተነጋገረ እና ምግብነቱን እየወደደው መምጣቱ አልቀረም።
ስራውን በጀመሩበት ወቅት አንዷን 22 ግራም የምትመዝን የእንጉዳይ እሽግ በ100 ብር ያቀርቡ ነበር። ዕለት ከዕለትም ለችግሮቻቸው ሳይበገሩ መስራታቸውን እንደቀጠሉ ግን የምርቱን ምግባዊ ንጥረነገር የተረዱ ሰዎች በብዛት ይጎርፉ ጀመር። በወቅቱ ደግሞ ወይዘሮ አምባነሽ ከዱባይ የሚያመጡት ምርት ምንጩ ከማሌዥያ በመሆኑ ከዋናው አምራች ለምን አላመጣም ብለው ይነሳሉ።
ወደ ማሌዥያ በማቅናት ከፋብሪካው ባለቤቶች ጋር በመነጋገር አብረው መስራት ስለሚችሉበት ሁኔታ ተነጋግረው ተመለሱ። በቀጣይም ከመንግስት ዶላር እየተቀበሉ ምርቶቹን በንግድ ተቋማቸው አማካኝነት እያስመጡ መነገድ ጀመሩ።
የእንጉዳይ ምርቱ ተወዳጅነቱ በመጨመሩ ደግሞ በክፍለ ሃገራትም ከተሞች ጭምር የአቅርቡልን ጥያቄ ይመጣ ጀመር። ከአዲስ አበባው ቢሮ በተጨማሪ በአዳማ እና ሀዋሳ ከተሞች መሸጫዎች ተከፍተው አምስት ሰራተኞችም ተቀጠሩ። እንጉዳዩንም ከአዲስ አበባ ውጪ ወደሚገኙ ከተሞች ለማቅረብ ተሽከርካሪዎችን ተከራዩ።
ልጃቸው አቶ ወሰንም ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የግል ስራቸው በተጨማሪ የእናቱን ፈር ቀዳጅ የንግድ ዘርፍ ላይ በመሳተፍ ያግዙ ነበር። በመጨረሻም እናት ወደመድኃኒት አቅርቦቱ ስራ ሲያተኩሩ ልጅ ስራውን ተረከቡ። ጥሩ ገበያ በነበረበት ወቅትም በወር እስከ ሶስት መቶ ሺ ብር ድረስ ገቢ ይገኝ እንደነበር ልጃቸው አቶ ወሰን ይናገራሉ።
አቶ ወሰን አሁን ላይ የእንጉዳይ ምግብ ተፈላጊ ቢሆንም በውጭ ምንዛሬ ምክንያት በቂ ምርት ከማሌዥያ እየመጣ አለመሆኑን ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከአዳማው እና የሀዋሳ ምርት ማቅረቢያ ሱቆች በእንጉዳይ እጥረት ምክንያት ከስራ ውጪ ሆነዋል።
ይሁንና ምርት በሚገኝበት ወቅት በተለይ ሱፐርማርኬቶች እና ግለሰቦች በብዛት እንደሚጠቀሙት ያስረዳሉ። በአሁኑ ወቅት ለማኪያቶ መስሪያነት እና በዱቄተ መልክ ተዘጋጅቶ ምግብ ውስጥ የሚጨመር ወይም በውሃ ተበጥብጦ የሚጠጣ የእንጉዳይ ምርቶች እያቀረቡ ይገኛሉ። ለማኪያቶ ማዘጋጃ የሚሆነው ባለ 20 ፍሬ የሚይዘው እና እያንዳንዳቸው 22 ግራም ያላቸው የታሸጉ እንጉዳዮች በ475 ብር ለገበያ ያቀርባሉ። ሌላኛው ምርት ደግሞ ቀይ እንጉዳይ ነው፤ ቀዩን የታሸገ 22 ግራም የእንጉዳይ ዱቄት በ650 ብር ይሸጣሉ።
አቶ ወሰን በአሁኑ ወቅት በፕይም እንጉዳይ አቅራቢ ድርጅት ውስጥ የፋርማሲ ባለሙያዎችን ጨምሮ ለየተለያዩ ሰራተኞቻቸው በወር አንድ መቶ ሺህ ብር ይከፍላሉ። በተጨማሪነት ደግሞ ለቢሮ ኪራይ በአጠቃላይ 300ሺ ብር ያወጣሉ። አጠቃላይ ካፒታላቸው ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው። የእናታቸው መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ በስሩ 43 ሰራተኞችን ይዟል። የእንጉዳዩ ንግድ የተሻለ ገበያን ለኢትዮጵያ እንዲፈጥር በማሰብ የማሌዥያው ኩባንያ ባለቤቶች በኢትዮጵያ አምርተው እንዲሸጡ እናትና ልጅ ጥረት አድርገዋል።
በዚህም ምክንያት የማሌዥያዎቹ እንጉዳይ አምራቾች ጋምቤላ ክልል መሬት ተረክበው ማምረት ከጀመሩ በኋላ በአካባቢው በተከሰተ ግጭት ንብረታቸው በመውደሙ ወደመጡበት ለመመለስ ተገደዋል። ይሁንና አቶ ወሰን ዳግም ባለሀብቶቹን ወደኢትዮጵያ አምጥተው በጋራ ለመስራት አሊያም ሌላ የገበያ አማራጭ ለመፈለግ በዝግጅት ላይ ናቸው።
በእንጉዳይ ምርት ከኢትዮጵያ ህዝብ አንድ በመቶውን እንኳን ማዳረስ አልተቻለም የሚሉት አቶ ወሰን፤ ምግቡን በብዛት አምርቶ በጥንቃቄ የማሸግ ሂደቱ ከተከናወነ ሰፊ የገበያ አማራጭ እንዳለ ይገልጻሉ። በመሆኑም ከማሌዥያው ኩባንያ ጋር በመነጋገር ምርቱን ኢትዮጵያ ውስጥ በማሸግ ስራ ለመሰማራት አቅደዋል።
ለእንጉዳይ ንግዱ ማደግም ሆነ መነሳት ግን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ ወሳኝነት አለው። በመሆኑም መንግስት ተጨማሪ ድጋፍ አድርጎ እንጉዳይ ያለውን ጥቅም በመረዳት ለመድኃኒት የሚሰጠውን ትኩረት ያክል ቅድሚያ ትኩረት ቢሰጠው የተሻለ ምርት ለህብረተሰቡ ማቅረብ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።
እናትና ልጅ የተቀባበሉት የእንጉዳይ ምርት ከእራሳቸው አልፎ ለሌሎችም የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በምግብ ጥንረ ነገሮች እጥረት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል የእራሱ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ቤተሰቡ ደስታ ይሰማዋል። ስራ ማለት ለእነርሱ ለግላቸው ገቢ የሚያስገኝ ንግድ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ ጥቅም የሚተርፍ ውጤት ያለው ነው። ማንኛውን ሰው ሰርቶ መለወጥ ካሰበ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት የሚችል ንግድ ላይ ቢሰማራ ሀገርንም እራስንም የበለጠ መጥቀም ይችላል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ጌትነት ተስፋማርያም