ቅድመ- ታሪክ
ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ስር ያሉ ቀበሌዎች አብዛኞቹ ገጠራማ የሚባሉ ናቸው። በነዚህ ስፍራ ያሉ በርካታ ነዋሪዎችም ህይወታቸው በግብርና ላይ ተመስርቷል። ጠዋት ማታ አፈር ገፍተው ፣በሬ ጠምደው የሚውሉበት ማሳ ከዓመት ዓመት የልፋትና ድካማቸውን አይነሳቸውም። በዋሉበት ልክ ምርት እያሳፈሰ ነገን በጥንካሬ እንዲዘልቁ ምክንያታቸው ነው። ላባቸውን አንጠፍጥፈው፣ ጉልበታቸውን ገብረው የሚያገኙት ፍሬም ብዙሃኑን መልካም ገበሬ አድርጎ ብርታታቸውን አሳይቷል።
ወይዘሮ ማሚቴ ሰብለና ባለቤታቸው አስራት ወልደማርያም የዕድሜያቸውን ግማሽ ያህል በዘለቁበት ትዳር ልጆችን በወጉ አሳድገው የልጅልጆችን አቅፈው ስመዋል። ጎጇቸውን ለማቅናት ሲለፉ የኖበሩት ዋንኛ ሀብት ደግሞ የእርሻ መሬታቸው ነው። ይህ መሬት ለእነሱ ለዓመታት የህይወታቸው መሰረት ሆኖ ዘልቋል።
እስከዛሬ ከእርሻ መሬቱ የሚያገኙት ምርት ከልጆቻቸው ጉሮሮ አልፎ ለገበያ ጭምር ሲውል ኖሯል። ከሸመታና ግዢ ሲሳይ በሚገኘው ገንዘብም ጎዶሎዎችን ሞልተው የጎጇቸው አቅም ጠንክሯል። በቋጠሩት ጥሪት ለየጉዳያቸው ገንዘብ የመመንዘራቸው ምክንያቱ ይኸው የእርሻ መሬት ነበር። መሬቱ የመላው ቤተሰብ ህልውና ነው። ምርትና ፍሬው ደግሞ የጎጇቸው መቆም ደምና አጥንት።
አቶ አስራት ብርቱ የሚባሉ ገበሬ ናቸው። ከዓመት ዓመት ጎተራቸው ሞልቶ እጃቸው ሳይነጥፍ የመኖራቸው ምክንያት መሬቱን ገምሰው፣ ሞፈር ነቅንቀው የማረሳቸው እውነታ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክራሉ። በሻከረው እጃቸው ሲያፍሱት የኖሩት ምርት የልጆቻቸው ጥጋብ፣ የእሳቸው ኩራትና የመንደሩም መነጋገሪያ ሆኖ ዘልቋል።
ሁሌም ደከመኝን የማያውቁት አባወራ ከእርሻ ውለው ከቤት ሲደርሱ የሚስታቸው ፈገግታ ከልጆቻቸው ፍቅር ተደምሮ ድካማቸውን ያስረሳል። የአምናውን ምርት ከዘንድሮው፤ የዘንድሮውን ለከርሞ እያወጉም ለመጪው ዘመን አርቀው ያቅዳሉ። የመኖራቸው ዋስትና የሆነው መሬትና የእሳቸው ጉልበት ተነጣጥለው አያውቁም። ከዓመት ዓመት ለፍተው ነጭ ከጥቁር በያሚፍሱበት እርሻ መልካሙን ፍሬ እንዳለሙ ዘመናትን ተሻግረዋል።
ሰሞኑን ግን ገበሬው አስራት ከእርሻ መሬታቸው እየታዩ አይደለም። ለወትሮው ከበሬዎቻቸው ጋር ሲያዘምሩ የሚሰሙት ብርቱ ሰው አሁን እርሻቸው በጭርታ ውሎ ማደር ጀምሯል። ጠንካራው አርሶ አደር እንደዋዛ ከቤት ያዋላቸው ህመም በቀላሉ የሚያላውሳቸው አልሆነም። ከዛሬ ነገ በይሻላቸዋል ተስፋ የቆየው ቤተሰብ ከመላው ወዳጅ ዘመድ ጋር መዳናችውን ናፍቆ ቆሞ መሄዳቸውን እየጠበቀ ነው። የአባወራው ሁኔታ ግን ለዚህ የሚያበቃ አልሆነም። በህመም የተረታ አካላቸው አቅም አጥቶ ተዳከመ። ጠንካራው ማንነታቸው ዳግም ከሞፈር ቀንበር ላይገናኝ ሆኖ እስከወዲያኛው ተለያየ። የብርቱው ገበሬ የሞት ዜናም ለሚያውቋቸው ሁሉ አውን ሆኖ ተሰማ።
አባወራው ከሞቱ በኋላ የቤተሰቡ ህልውና ሊፈተን ግድ አለው። በሬዎቹ ሜዳ ውለው የእርሻ መሳሪያዎች ቦዘኑ። ከዓመት ዓመት ምርት የሚታፈስበት ለም መሬትም ያለአመሉ ሊነጥፍ እጁን ሰጠ። ይህኔ እማወራዋ ጨነቃቸው። ትናንት ጎተራ ሙሉ ምርት ይፈስበት የነበረው ጓዳ ዛሬ በባላቸው ሞት በችግር መፈታቱን ለማሰብ ተቸገሩ።
የመላው ቤተሰብ ሃላፊነት በእሳቸው ትከሻ መውደቁ ቢገባቸው በሃሳብ ውጣ ውረድ ባዘኑ። አሁን ወይዘሮዋ ህይወት ይቀጥል ዘንድ አፋጣኝ መላ እንደሚያሻ ገብቷቸዋል። ከቀናት በኋላም እንደ አገሬው ወግና ባህል መሬታቸውን የእኩል ሰጥተው ሊያሳርሱና የሚገኘውን ለልጆቻቸው ሊያተርፉ መወሰናቸው የግድ ነበር።
የእኩሌታው እርሻ
ማሚቴ ከአባወራው ሞት በኋላ የግል መሬታቸውን የእኩል እያሳረሱ የሚገኘውን ምርት መካፈል ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ወይዘሮዋ ይህን የእርሻ መሬት ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ከሟች ባለቤታቸው የተረከቡት ነው። በወቅቱ አርሰው ይጠቀሙበት ዘንድ እውቅና ከሰጣቸው አካልም የባለቤትነት ማረጋገጫን ይዘዋል።
እማወራዋ መሬቱን የእኩል እያሳረሱ ከሚያገኙት ምርት ለቤት ለጓዳቸው የሚሆን አላጡም። ባለቤታቸው ሲሞቱ ራሳቸውን ያልቻሉ ልጆቻቸው ዛሬ ላይ የኔ ያሉትን ጎጆ ቀይሰዋል። ይህ መሆኑም ህይወት እንደትናንቱ ላይከብዳቸው ሆኖ መኖርን ቀጥለዋል።
አንዳንዴ ብቸኝነቱ ሲያይልባቸው እማወራዋ በትካዜ ይዋጣሉ። አሁን ዕድሜያቸው እየገፋ በመሆኑ በርከት ያለ ጉዳዮች ያሳስባቸው ይዟል። ይህን በቅርበት ሆኖ የሚያስተውለው ወርቁ የተባለው ልጃቸው አንድ ቀን ወደ እናቱን ቀረብ ብሎ መላ ነው ሲል ያቀደውን ሃሳብ አማከራቸው።
ወይዘሮ ማሚቴ ልጃቸው ባመጣው ሃሳብ አልተከፉም። እንደስከዛሬው ለሌላ ሰው በእኩል ማሳረሱን ትተው የእርሻ ስራውን ለእሱ እንዲሰጡትና እንዲጦራቸው ሲጠይቅ በሙሉ ልብ ተስማሙ። ይሁንታቸውን አጽድቀውም መሬቱን ከሰውዬው ተቀብለው ለልጃቸው አስረከቡ።
ወርቁ የእርሻ ስራውን ከግለሰቡ ተቀብሎ የሚያመርተውን ለወላጅ እናቱ ማስገባቱን ያዘ። ወይዘሮዋም በልጃቸው ሃሳብ ተደስተው ምርቱን ከእናትነት ምርቃት ጋር እያከሉ ሲቀበሉ ቆዩ። ይህ ልማድ ለዓመታት ዘልቆም በተለመደው መንገድ ያለችግር ቀጠለ።
ዳግም ኀዘን
አንድ ቀን በእናትና ልጅ መካከል ዘልቆ የቆየው ሰጥቶ የመቀበል ሂደት ሊቋረጥ ግድ አለው። ልጃቸው ወርቁ ባደረበት ህመም በሞት መለየቱ ለቤተሰቡ አስደንጋጭ አጋጣሚን ፈጠረ። ወይዘሮ ማሚቴ በእርጅና እድሜያቸው የወረደባቸው የልጅ ኀዘንም ከባድ ሆኖ ሰነበተ።
የኀዘን ጊዜው አልፎ ወዳጅ ዘመድ ወደየመጣበት ሲመለስ አዛውንቷ ዳግመኛ በትካዜ አንገታቸውን ደፉ። አርሶ የሚያጎርሳቸው የጠንካራው ገበሬ ልጃቸው ሞት በችግር ሊፈትናቸው ጊዜው መድረሱንም ተረዱ ። አሁን ስለሳቸው ሆኖ የሚጨነቅ ወገን በቅርብ የለም። ከዚህ ኃሳብ ባሻገር ስጋት ሆኖ በውስጣቸው ውሎ ያደረው ጉዳይም ዕንቅልፍ ከነሳቸው ሰነባብቷል።
ከቀናት በአንዱ ቀን እናት ማሚቴ ልጃቸው በህይወት በነበረ ጊዜ ከመሬታቸው ያገኙት ስለነበረው ጥቅም አንስተው ከምራታቸው ጋር ተነጋገሩ። የሟች ልጃቸው ሚስት ወይዘሮ ሙሉ ጉርሙ ግን ይህ ጉዳይ ሲነሳባት ሃሳባቸውን ልትቀበል አልፈቀደችም። ከአሁን በኋላ መሬቱም ሆነ የሚገኘው ምርት ለእሳቸው እንደማይገባ አስረድታ በቁጣ ወደመጡበት ሸኘቻቸው።
እናት ልጃቸውን በሞት ማጣታቸው ሳያንሰ ከባለቤቱ የሰሙት ያልተገባ ጉዳይ ከመጠን በላይ አሳዘናቸው። ከልጅነት እስከ እውቀት የመኖር ህልውናቸው ከሆነው የእርሻ ይዞታ እንደዋዛ መፈናቀላቸው ያሳስባቸው ያዘ። ይህ እውነት በእስተእርጅና ዘመናቸው ይገጥመኛል ያላሉት ነበርና አለኝ ያሉትን ወዳጅ ዘመድ አማከሩ። ጉዳዩን የሰማ ሁሉ የክስ ዶሴ ይዘው ለሚመለከተው አካል ‹‹አቤት›› እንዲሉ ነገሯቸው።
የክሱ ዶሴ
ወይዘሮ ማሚቴ ለሙሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ‹‹ተበድያለሁ›› ሲሉ ክሳቸውን አቀረቡ። አመልካችዋ በእጃቸው የሚገኘውን ማስረጃና የእማኞችን ምስክርነት ዋቢ አድርገውም ምልልሳቸውን ቀጠሉ። ፍርድ ቤቱ ተጠሪዋን የልጃቸውን ሚስት ወይዘሮ ሙሉ ጉርሙን አቅርቦ በክሱ ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጡ ቀጠረ።
በቀጠሮው ዕለት አማትና ምራት ከችሎቱ ቀርበው ‹‹አለን›› የሚሉትን ሃሳብ አስረዱ። ወይዘሮ ማሚቴ ዓመታትን አርሰው የተጠቀሙበትን መሬት ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ለሌላ ሰው ለእኩል ሰጥተውት እንደነበርና እስከቅርብ ጊዜ ደግሞ ሟቹ ልጃቸው እያረሰ ምርቱን ያካፍላቸው እንደነበር ተናገሩ። ልጃቸው ካረፈ በኋለ ግን መሬትና ምርቱን ሲጠይቁ ከምራታቸው ያገኙት ምላሽ ይህን የመጠየቅ መብት እንደሌላቸውና ንብረቱ የማይገባቸው መሆኑ እንደተነገራቸው አስረዱ።
ወይዘሮ ሙሉ ጉርሙ በበኩላቸው ባለቤታቸው የእርሻ መሬቱን ለአስራሁለት ዓመታት እያረሱ ሲጠቀሙበት የነበረ በመሆኑ የሚገኘውን ምርት ጨምሮ የባለቤትነት መብቱ የእሳቸው ስለመሆኑ በመግለጽና ጥያቄው ተገቢ አለመሆኑን በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ተናገሩ።
የሙሎ ወረዳ ፍርድ ቤት በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲያከራክር የቆየውን የመሬት ይገባኛል ጉዳይ ሲመረምር ቆየ። በመጨረሻም ተጠሪዋ ወይዘሮ ሙሉ ጉርሙ የአመልካችን የወይዘሮ ማሚቴ ሰብለን የእርሻ መሬት መከልከላቸው አግባብ ያለመሆኑን ጠቅሶ ተቃውሟቸውን ውድቅ አደረገ። ተጠሪዋ መሬቱንና የሚገኘውን ምርት ለወይዘሮ ማሚቴ ጉርሙ የማስረከብ ግዴታ አለባቸው ሲልም ውሳኔውን አስተላለፈ።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የዘለቀው የመሬት ይገባኛል ክርክር በዚህ ብቻ አልተቋጨም። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደተሰማ ወይዘሮ ሙሉ በእርሳቸው ላይ የተሰጠው ብይን ተገቢ ያለመሆኑን በመቃወም ለፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት ‹‹ይግባኝ›› ሲሉ አቤቱታቸውን ቀጠሉ ።
የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ወይዘሮዋ ያቀረቡትን የውሳኔ ተቃውሞ ሲመረምር ቆየ። ተገቢ ነው ያላቸውን መረጃዎች ከማስረጃዎች ጋር አገናዝቦም የወረዳው ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በማሻሻል በወይዘሮዋ ላይ ቀደም ሲል የተላለፈውን ብይን ትክክል ነው ሲል አጸና።
ወይዘሮ ሙሉ አሁንም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ አልተዋጠላቸውም። በሟች ባለቤታቸው ጉልበት ይታረስ የነበረ መሬትንና ሲታፈስ የቆየ ምርትን እንደዋዛ ከእጃቸው አውጥተው ለአማታቸው ማስረከብ አልፈቀዱም። ጉዳዩን ለሚቀጥለው የፍርድ ሂደት ለማቅረብ ሲያስቡ ቆይተው ዶሴያቸውን ሰንደው አዘጋጁ። ለጠቅላይ ፍርድቤት አቅርበውም ‹‹በደሌ ይታይልኝ›› ሲሉ አቤት አሉ።
ጠቅላይ ፍርድቤቱ የአመልካችን የክስ ውሳኔ ተቀብሎ ሲመረምር ቆየ። በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤቶቹ የተላለፈውን ውሳኔ አጣርቶም እስከዛሬ እንደነበረው ሁሉ ብይኑ ትክክክል ስለመሆኑ አመነ። በመጨረሻም የአመልካችን ጥያቄ ውድቅ በማድረግና የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቀበል ፍርዱ በድጋሚ እንዲጸና ወሰነ ።
ወይዘሮ ሙሉ አሁንም ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተላለፈውን የውሳኔ ሃሳብ ተቃወሙ። ውሳኔው መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ሲሉም ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን አቀረቡ።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወይዘሮዋ ክርክር በገጠሙበት የእርሻ መሬት ላይ ክስ የማቅረብ መብት ይኖራቸው አይኖራቸው እንደሆነ ጭብጥ ለይቶ መረመረ። መሬቱ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ለአመልካች ልጅና ለወይዘሮዋ ባለቤት ለአቶ ንጉሴ አስራት ተሰጥቶ እንደነበር ከወረዳው የአካባቢና የመሬት ጥበቃ መስሪያ ቤት በማስረጃ አረጋገጠ።
ወይዘሮዋ ክርክር ባስነሳው መሬት ላይ ለአስራ ሁለት ዓመታት እየተጠቀመችበት በመሆኑና በስር ፍርድ ቤቶቹ የተላለፈው የአይገባትም ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ውሳኔው መሻር እንዳለበት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አስታወቀ። በመጨረሻም ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት የሚያስችል ማሳያ አልቀረበም በማለት መዝገቡ በምራቲቱ አሸናፊነት እንዲዘጋ ወ ሰነ።
አቤቱታ
በአማትና ምራት መካከል ሲያከራክር የቆየው ጉዳይ በመጨረሻ በኦሮሚያ ብሄራዊ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትና በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረት ፍርዱ ለወይዘሮ ሙሉ ጉርሙ እንዲወሰን ተደርጓል።
ወይዘሮ ማሚቴ ከሟች ልጃቸው ሚስት ጋር ያደርጉት በነበረው የመሬት ይገባኛል ክርክር በመረታታቸው በእጅጉ ማዘናቸው አልቀረም። በመጨረሻ ግን ‹‹ውሳኔው መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል›› ሲሉ ጉዳዩን ለኢፌዴሪ የህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤት ሲሉ አቅርበውታል።
የኢፌዴሪ ህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የወይዘሮ ማሚቴ ማመልከቻን ተቀብሎ የአቤቱታውን ጭብጥ ከስረመሰረቱ መመርመር ጀምሯል። በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የቆየውን የይገባኛል ጥያቄ በስር ፍርድ ቤቶቹ ከቀረቡ ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብም ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ኮሚቴ አዋቅሮ ም ርመራውን ጀምሯል።
ጉባኤው ባደረገው ጥልቅ ማጣራት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይርጋን መሰረት አድርጎ በአመልካቿ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ ከእርሻ መሬታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉ ህገመንግስታዊ መብትን የጣሰ ስለመሆኑ አረጋግጧል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔውን ተቀብሎ እንዲጸና ማድረጉ የአመልካችን ህገመንግስታዊ መብት የጣሰ ሆኖ በመገኘቱ በአንቀጽ 9/1 መሰረት ተቀባይነት እንደማይኖረው ጉባኤው በሙሉ ድምጽ አረጋግጧል።
ውሳኔ
ጉባኤው የቀረበለትን የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄ ተመልክቶ ሲመረምር ቆይቷል። በመጨረሻ ባሳለፈው ውሳኔም የስር ፍርድ ቤቶቹ በተለያየ አግባብ የሰጧቸው ብይኖች መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመባቸው መሆኑን በማረጋገጥና አሳማኝ የሚባሉ ነጥቦችን በማስቀመጥ ክርክር ያስነሳው የመሬት ባለቤትነት መብት ለወይዘሮ ማሚቴ ሰብለ ይገባቸዋል ሲል የመጨረሻውን ውሳኔ አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
መልካምስራ አፈወርቅ