በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የዘንዘልማ የመዳረሻ ገበያ ማዕከል ግንባታ በ2007ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ በ2009ዓ.ም ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃት ነበረበት፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ተጠናቅቆ ሥራ አልጀመረም፡፡
የገበያ ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ለብልሽት የሚዳረጉ የግብርና ምርቶችን እንዳይበላሹ አድርጎ ማቆየት የሚያስችልና በግብርና ምርቶች የግብይት ሰንሰለት ውስጥ የሚታየውን አላስፈላጊ ደላላ በማስቀረት የዋጋ መረጋጋትን የሚፈጥር በመሆኑ ነው ግንባታው የተጀመረው፡፡
የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አፈወርቅ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሰጡት መረጃ መሠረትም የዘንዘልማ መዳረሻ ገበያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቅቆ በተያዘው በጀት ዓመት ሥራ ሊጀምር ነው፡፡
እንደ አቶ ዮሐንስ በሦስት የግንባታ ምዕራፎች ለአስተዳደር አገልግሎት የሚውል አንድ ባለአራት ፎቅ ሕንጻን ጨምሮ ለገበያ ማዕከል፣ ለጥበቃ ቤቶች፣ ካፍቴሪያና የመሰብሰቢያ አዳራሾች አገልግሎቶች የሚውሉ 68 ሕንጻዎች (ብሎኮች) ይገነባሉ። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ አካል የሆኑ
ግንባታቸው ከ169 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው 22 ሕንጻዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍም እየተጠናቀቁ ያሉት ሕንጻዎች 180 ጅምላ እና 280 ቸርቻሪ ነገዴዎችን የሚያስተናግዱ እንደሆኑም አቶ ዮሐንስ ነግረውናል።
የመዳረሻ ገበያ ቦታውን ሥራ ለማስጀመር የመንገድ፣ የውኃ እና የመብራት መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ብቻ እንደቀሩና እነሱም በቅርብ እንደሚጠናቀቁ ከምክትል ቢሮ ኃላፊው ተረድተናል፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በመጓተቱ የምዕራፍ ሁለትና ሦስት ግንባታዎች እስካሁን አልተጀመሩም፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በምዕራፍ አንድ ወደ ሥራ መግባት የነበረባቸው ነጋዴዎችም በግንባታው መጓተት አልገቡም፡፡
ለግንባታው መጓተት የዲዛይን ክለሳና የዋጋ ግሽበት በግብዓት ላይ ችግር መፍጠሩ በቢሮው በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
ለምዕራፍ አንድ የግንባታ ወጭ ተቋራጮች በ127 ሚሊዮን 643ሺህ 853 ብር ቢያሸንፉም እስካሁን የተከፈለው ግን ለ169 ሚሊዮን 729ሺህ 811 ብር መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 18 ሚሊዮን ብር ያህሉ ለአርሶ አደሮች ካሳ የተከፈለ መሆኑንም መረጃው ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን 23 ሚሊዮን ብር አካባቢ ጭማሪ የተከፈለበትን መረጃ ማግኘት አልቻልንም፡፡
የገበያ ማዕከሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለግብርና ምርቶች ግብይት አገልግሎት፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ምርቶች ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ የሚያስችል የማቀዝቀዣ መጋዝን አገልግሎት እና የምርት ደረጃን በማስጠበቅ አሽጎ ወደ ውጭ የመላክ ሥራ እንደሚከናወንበት ነው ከምክትል ኃላፊው የተነገረን።
የገበያ ማዕከሉ በአካባቢው የሚገኙት አርሶ አደሮችን የገበያ ችግርም መፍታት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ የዘንዘልማ የመዳረሻ ገበያ በሦስት ምዕራፎች በ2007ዓ.ም ግንባታ መጀመሩን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡ የገበያ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በሀገሪቱ በቀዳሚነት የሚቀመጥ መሆኑንም አቶ ዮሐንስ ጠቁመዋል፡፡
ሦስቱ የግንባታ ምዕራፎች ሲጠናቀቁ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚጨርሱ ታቅዷል፤ የግንባታው ወጭ በግብርና የመዋቅራዊ ሽግግር መርሀ ግብር (አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ) እና ‹አግሮ ቢግ› ድጋፍ ሰጭ ፕሮጀክቶች የሚሸፈን ነው። በሦስቱ ምዕራፎች የሚገነባው የገበያ ማዕከሉ 25 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ እንደሆነም የዘገበው አብመድ ነው፡፡