የልጅነት ጣዕሟቸውን በእናትነት ኃላፊነት ለማሳለፍ የሚገደዱ እንስቶች የትየለሌ ናቸው፡ ልጅ እያሉ ልጅ ያዥ ናቸው፤ ታናናሾቻቸውን ተንከባካቢ ናቸው። ይሄ እንግዲህ ቀላሉ ነው፤ ልጅ ናቸውና ከታናናሾቻቸው ጋር እየተጫወቱ ቢያድጉ ችግር የለውም። ችግሩ ልጅ ከመያዝ አልፈው ልጅ ወደ ማርገዝ መሸጋገራቸው ነው ከባዱ ነገር። በልጅነት ሰውነት ሚስትነት፣ በልጅነት ሰውነት ነፍሰጡርነት፣ በልጅነት ሰውነት ምጥ… እነዚህን ሁሉ በልጅነት ይሸከማሉ። በእርግጥ ይህ አይነቱ ሁነት በኢትዮጵያ የሚገኙ የብዙ ታዳጊ ሴቶችን ሕይወት የሚዳስስ ነው።
የችግሩ መነሻ አንድም በቤተሰብ ሙሉ ፈቃድ ነው። ሊያውም ኋላቀር እየተባለ በሚተቸው ያለ ዕድሜ ጋብቻ። ለችግሩ አቻ አረፍተነገር ቢፈለግለት በአደባባይ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደማለት ነው። ችግሩን ለመቅረፍ ‹‹የጎጂ ልማድ አስወጋጅ ኮሚቴ›› እየተባለ በየገጠሩ ቢቋቋምም ችግሩን መቅረፍ ግን አልቻለም። ከኮሚቴዎች ለመደበቅ በጨረቃ ሰርግ ተደርጓል፤ የሰርግ ድምጽ ሳይሰማ ጋብቻ ይፈጸማል፤ ሌላ ቀን ሰበብ ይፈለግና ሰርጉ ይደገሳል። ከቤተሰብና ከምሥጢረኞች ውጭ ያሉ ሰዎች እንዳያውቁት ክርስትና ወይም ሌላ ስም ይሰጠውና ያጭበረብሯቸዋል። ይሄ ሁሉ ልጅቷን ያለ ዕድሜዋ ለመዳር ነው።
አሁን ላይ ችግሩ በከፊልም ቢሆን ቀንሷል፤ የቀነሰው ግን በቁጥጥር ሳይሆን በጊዜ ሂደት የሰዎች አስተሳሰብ እየተለወጠ በመምጣቱ ነው፤ አንፃራዊ ንቃተ ህሊና በመፈጠሩ ነው። የትምህርት ተደራሽነት እየተስፋፋ ስለመጣ ገጠር አካባቢ ያሉ ሴቶችም የተሻለ የትምህርት ዕድል አገኙ፤ አላገባም በማለት ቤተሰብን አሳመኑ። ከአቅም በላይ ሲሆንባቸው ከቤተሰብ ጠፍተው ለመሄድ መንገድና ሌሎች ዘመናዊ መገናኛዎች ምቹ ሁኔታ ፈጠሩላቸው። ልጅና ቤተሰብ መግባባት ላይ እየደረሱ ነው።
ምን ዋጋ አለው! ዘመናዊነቱ ደግሞ ሌላ የከፋ ችግር ይዞ መጣ። ይሄ በየትምህርት ቤቱ የምንሰማው ታሪክ ነው። በቤተሰብ ጫና ይመጣ የነበረው ያለዕድሜ ጋብቻ መልኩን ቀይሮ በልጆቹ ፈቃድ ይፈጸም ጀመር፤ በዚህም አንዳንዶቹ ‹‹ኧረ የድሮው ይሻላል›› እስከማለት ደርሰዋል። ምክንያቱም ይሄኛው የከፋ ነውና! ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ ይፈጸማል፤ ያልተፈለገ እርግዝና ይፈጠራል፤ ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ እንዳይሰማ በሚደረግ የማስወረድ ትግል የራሷ ሕይወት ያልፋል።
ከዚህ ያመለጠች ደግሞ ልጅ ወልዳ ለማሳደግ ትገደዳለች፤ ትምህርቷንም ለማቋረጥ ትገደዳለች። የተቋረጠውን ትምህርት ለመቀጠል የሚያስችል የኑሮ ሁኔታ ደግሞ የለም፤ ልጅ እያሳደጉ ለመማር የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅምም የለም፤ የቀን ሥራ እየሰራች ልጇን ለማሳደግ ትገደዳለች። አጋዥም የላትም፤ ምክንያቱም ልጁ የተወለደው ከጋብቻ ውጭ ነው።
በቤተሰብ ከሚደረገው ያለዕድሜ ጋብቻ ተፅዕኖ የተላቀቁት ተማሪዎች በራሳቸው ፈቃድ የሚደረገው አጉል ዘመናዊነት እየጎዳቸው ነው። ሁሉንም ማለት አይደለም፤ እያወራን ያለነው ስለተጎዱት ብቻ ስለሆነ ነው። ለምንም ነገር ዝግጁ ሳይሆኑ ጓደኛ ይይዛሉ፤ ይሄም ቀላል ነበር፤ ራስ ሳይጠና ጉተና እንዲሉ ከጋብቻ በፊት በሚደረግ የወሲብ ግንኙነት የተወለደውን ልጅ በድህነት ለማሳደግ መውተርተሩ ነው የከፋ ችግር የሚያመጣው።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ጠቅሰን ወደ ዛሬ ባለታሪካችን እንሄዳለን። ባልተፈለገ እርግዝና ምክንያት የብዙ ታዳጊ ሴቶች ሕይወት አልፏል። የአንዳንዶቹ በለጋነት ዕድሜ በሚያደርጉት ወሊድ ምክንያት፤ የአንዳንዶቹ ደግሞ ለማስወረድ በሚጠቀሙት ባዕድ ነገር። ከዚህ ያመለጡት ደግሞ አሰልቺና የተማረረ ሕይወት የሚኖሩ ናቸው። በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ልጅ ታቅፈው የሚለምኑት ናቸው። ባስ ባለባቸው ቁጥር ሞት እየተመኙ የሚኖሩ አሉ። ‹‹ከልመና ይሻል ይሆን?›› ብለው ያሰቡት ደግሞ በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ ሆነው ከህሊናቸው ጋር ትግል ገጥመዋል።
አሳዛኙ ነገር እነዚህ ልጅ ያላቸው ሴቶች ነፃ ሆነው የሰው ቤት እንኳን ተቀጥረው አይሰሩም። ያገኙትን ሰርተው ያገኙትን በልተው ያገኙበት አያድሩም። አሰሪዎች ሰራተኛ ሲፈልጉ አንዱ መስፈርታቸው ልጅ የሌላት የሚል ሆኗል። ይሄውም እንደፈለጋቸው ለማዘዝ እንዲያመቻቸው ነው። የእነዚህ ሴቶች አይነተኛ አማራጭ ደግሞ ልጅ አዝለው የማይሸጥ ሶፍትና ማስቲካ ይዞ መዞር አሊያም ከዕጅ ወደአፍ የሆነውን ኑሮ የሚደጉሙበት ስራቢጤ መፈለግ ነው።
የዛሬ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ዓምድ እንግዳችን ሰናይት ቦጋለ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በከፋ ዞን ቦንጋ አካባቢ በምትገኝ የገጠር መንደር ውስጥ ሲሆን፤ አሁን የምትኖረው ቦንጋ ከተማ ውስጥ ነው።
በቦንጋ ከተማ ውስጥ በዋናው አስፋልት የእገረኛውን መንገድ ይዤ እየሄድኩ ነው። የብዙ ከተሞች መገለጫ የሆነው የጀበና ቡና በየቅርብ ርቀቱ ይታያል። አብዛኞቹ የጀበና ቡናዎች የሚገኙት ከሆቴል በረንዳ ላይ፣ ከትልቅ መስሪያ ቤት አጠገብ፣ ከትልልቅ ንግድ ቤቶች አጠገብ ነው። ለጀበና ቡና ብቻ ተብሎ የተሰራ ቦታ ብዙም አይታይም። ከተገኘም በተደራቢነት ሌላ አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን ጨምሮ ነው። ቢያንስ ብስኩትና ሻይ ይኖር ይሆናል። ይህ የሆነው የጀበና ቡና ብቻውን ስለማያዋጣቸው ነው፤ የተከራዩትን ቦታ ኪራይ ስለማይከፍል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሆቴሎች፣ መስሪያ ቤቶች ወይም ትልልቅ ንግድ ቤቶች አጠገብ ካልሆነ ደንበኛ አያስገኝም።
በዚህ የእገረኛ መንገድ ላይ እየሄድኩ በሸራ የተወጠሩ ማረፊያዎች አየሁ። ከአንዳንዶቹ ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች አሉ፤ ከአንዳንዶቹ ውስጥ ደግሞ በዛ ያለ ሰው አለ። ከቡና ዕቃዎች ውጭ ሌሎች የሻይና የምግብ ዕቃዎችም ይታያሉ። እነዚህን ሸራ ቤቶች ሳልጨርስ ከአንደኛዋ ሸራ ቤት ውስጥ አንዲት ወጣት ብቻዋን አግዳሚው ወንበር ላይ ተቀምጣለች። ወደ ውስጥ ስመለከት ከቡና ዕቃዎች ውጭ የሚታይ ነገር የለም። ቡና የሚጠጣ ደንበኛም የለም። ወደ ሸራ ቤቷ ውስጥ ገባሁ። ቡናም አዘዝኩ፤ ቡናው ከመቆየቱ የተነሳ ጀበናውም ቀዝቅዞ እንደገና ነው ከሰል የተቀጣጠለ። እኔም ለቡናው ሳይሆን ለምን ደንበኛ እንደሌለ፣ ለምን ሌሎች ያደረጉትን አድርጋ ደመቅ እንዳላደረገችውና በአጠቃላይ የሆነ ችግር እንዳለ ስለጠረጠርኩ ብዙ ለመቆየትና ታሪኳን ለማወቅ ይደርሳል ቀስ ቭሎ ይፍላ አልኳት።
ልጅነትና እናትነት
ሰናይት ከድሃ ቤተሰብ ነው የተወለደች። ከድሃ ቤተሰብ ብትወለድም ግን አቅም በፈቀደ እያስተማሯት ነው። የኑሮ ጣጣ አልሞላ እያለ ከትምህርት ቤት ትቀራለች፤ ባስ ሲልም ትምህርቱን ለማቋረጥ ሁሉ ታስባለች። በልጅነት ዕድሜዋ ኑሮን ለማሸነፍ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከቦንጋ ቴፒ እያለች ትንንሽ የንግድ ሥራዎችን ትሰራለች።
በዚህ ሕይወት ውስጥ እያለች ከአንድ ወጣት ጋር ትውውቅ ተፈጠረ። ትውውቁ እየጠነከረ ሄዶ ፆታዊ ግንኙነት ተጀመረ። ጓደኛዋ ‹‹አገባሻለሁ›› ስለሚላት እምነቷን ጥላበታለች። የነገ የትዳር ጓደኛዬ ነው ብላ ስለምታስብ ግንኙነታቸው የባልና ሚስት አይነት ሆነ። ዳሩ ግን ገና ቤተሰብ አላወቀውም፤ የትዳር ቃል አልተገባቡም። እምነቷን የጣለችው ሰናይት አስፈላጊውን ጥንቃቄም አታደርግም። የወሊድ መቆጣጠሪያ አትጠቀምም። በግንኙነታቸው ውስጥ አረገዘች። እርግዝናዋ እየለየ ሲሄድ ግን ጓደኛዋ ጋር በድንገት ተለያዩ።
ሰናይት ነፍሰጡር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ያ ‹‹አገባሻለሁ›› ሲላት የነበረው ልጅ የት እንደሄደ መረጃው የላትም፤ ምን እንደዋጠው አላወቀችም። ለወሲባዊ ግንኙነት ብቻ ይመላለስ የነበረውን ወጣት ከእርግዝናዋ በኋላ የበላው ጅብም አልጮኸም። ቤተሰብ አይጠየቅ ነገር ቤተሰቦቹን አታውቅም፤ የእሷም ሆኑ የእሱ ቤተሰቦች ግንኙነታቸውን አያውቁም። በዚያ ላይ ደግሞ ወጣቱ በአሽከርካሪነት ሥራ ላይ የተሰማራ ነውና በየጊዜው መዳረሻውን ሊቀይር የሚችልበት አጋጣሚ አለው። በተጨማሪም የሚሰራውም እርሷ በምትኖርበት ቦንጋ ሳይሆን ቴፒ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ እሱን የምታፈላልግበት ጊዜም የላትም።
የስነ ልቦና ጥንካሬ
ብዙ ሴቶች ላይ የሚታየው ችግር ከጋብቻ ውጭ እርግዝና ሲፈጠር ለማስወረድ በሚደረግ ጥረት ሕይወትን ማጣት ነው። ይህን ማድረግ ያልፈለጉ ደግሞ የሚወለደውን ሕጻን ሕይወት በማጥፋት የህሊና ቀውስ ውስጥ መግባት ነው። እስከሚወለድ ድረስ ባለው የእርግዝና ወቅት ከህብረተሰቡ የሚደርስባቸውን ከንፈር መጣጣና ሽሙጥ ላለመስማት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ። በማህበረሰባችን ባህል ከጋብቻ ውጭ ያረገዘች ሴት ላይ ጣት መጠቋቆም ያለ ነው፤ በተለይ እንደ ሰናይት ገና ታዳጊ ስትሆን ደግሞ የከፋ ይሆናል።
የሰናይት ጥንካሬ እዚህ ላይ ነው። እርግዝናዋ እየገፋ ሲመጣ ራሷን የሚጎዳ ወይም ሌላ የህሊና ቁስል የሚሆን ነገር አላሰበችም። ራሷን አጠነከረች። በቃ! የሆነው ነገር ሆኗል ብላ ሁሉንም ነገር ለምታማክራቸው ጓደኞቿ ፍርጥርጥ አድርጋ ተናገረች። ጓደኛ እንደነበራትና ካስረገዛት በኋላ የት እንደጠፋ እንደማታውቅ ለሚያውቋት ጓደኞቿ ተነፈሰች።
የሰናይትን ችግር የተረዳ እያጽናና የፈረደም እየፈረደ ይሄዳል። እርሷም ቤተሰብ ቤት ከመሄድ ይልቅ ጓደኛዋ ጋር ሆና የአራስነት ጊዜዋን አሳለፈች። ተገቢውን የአራስነት ወግ ባታገኝም በፈጣሪ ፈቃድ ገና ሳትጠነክር ለዕለት ጉርስ እንኳን የሚሆን ሥራ መፈለግ ጀመረች። ይሻል ይሆን ብላ ጨቅላ ልጇን ይዛ ከቦንጋ ወደ ቴፒ ከተማ ሄደች። እግረ መንገድም የልጇን አባት አገኘው ይሆን የሚል ጉጉት ነበራት፤ ዳሩ ግን እሱም አልተገኘም፤ ሥራም አልተገኘም። እንዲያውም ይባስ ብሎ የልጇ አባት ያለበት ከተማ ውስጥ መንከራተቷ እየረበሻት መጣ። እናም ተመልሳ ወደ ቦንጋ ሄደች።
አሁናዊ ሕይወት
ሰናይት አሁን የልጅ እናት በመሆኗ ደስተኛ ናት። አሁን ላይ ልጇም ያን ያህል አታስቸግራትም። ከሌሎች ልጆች ጋር መዋል ትችላለች። ሁለት ዓመት ሆኗታል። ሰናይት አሁን እየኖረች ያለችው ለልጇ ነው። የፈለገችውን አይነት ሥራ መሥራት አትችልም። ወጪ ለመቀነስ ከጓደኛ ጋር ሆና ቤት መያዝ አትችልም። በቀን አሥር ብር ለማይገኝበት የጀበና ቡና ሥራ በወር 250 ብር የቤት ኪራይ ትከፍላለች። ሥራውን ከዚህ የተሻለ ለማድረግ ገንዘብ የለም። እንኳን ሌላ የተሻለ ሥራ መጀመር ለጀበና ቡናው የሚያስፈልጉ ነገሮች እንኳን አልተሟሉም። የተሻለ በረንዳ እንኳን መከራየት አትችልም።
የጠዋት ማታ ስጋቷና ጭንቀቷ የልጇ የነገ ዕጣ ፋንታ ነው። ልጇ እንደ እሷ እንድትሆን አትፈልግም። ተገቢውን ትምህርት እንድታገኝና ከእሷ የተሻለ ሕይወት እንዲትኖር ነው የምትፈልግ። ለዚህ ደግሞ ዛሬ ላይ መሥራት አለባት። ልጇ ከጠነከረች ሌላ የተሻለ ሥራ ለመሥራት አስባለች። ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች ነውና ብሂሉ እርሷም ልጇን ለማሳደግ ስትል ስትታትር ትውላለች። ልጇ ባትኖር የትም ተሯሩጣ በመስራት ለመለወጥ ብትችልም ልጅ ስላገኘች ግን አምላኳን አታማርርም። ይልቁንም ተስፋ የሰጣትን አምላክ ታመሰግናለች። ፈጣሪ ላይ እምነቷን የጣለችው ሰናይት የልጇን የነገ ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ጥረት ላይ ናት። እኛም ምኞቷን ያሳካለት ዘንድ እንመኛለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ዋለልኝ አየለ