በመምህርነት ሙያቸው የሚያውቋቸው በርካታ ናቸው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋም አብረዋቸው ያስተምሩ የነበሩ ባልደረቦቻቸው ከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን ላይ ይገኛሉ። እርሳቸው ግን ወደግል ሥራ በማተኮራቸው የንግዱን ዓለም ተቀላቅለዋል።
በአብዛኛው ገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የእርሻ መሳሪያዎችን ከውጭ አገር በማስመጣት ቀዳሚ ከሚባሉ ሰዎች መካከል ይመደባሉ። ከሥራ ውጪ ባለው ጊዜያቸው ደግሞ የቱሪስት መስህቦችን መጎብኘት የሚወዱት ሥራ ፈጣሪ መላ ኢትዮጵያን ዞረዋል ማለት ያስደፍራል። በተለይ የሶፍ ኡመርን ዋሻ ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር በመሆን በማቋረጣቸው በአንድ ወቅት የመገናኛ ብዙሃንም መወያያ ጉዳይ ሆነውም ነበር።
አቶ ቾምቤ ስዩም ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ ነው። ለቤተሰባቸው 2ኛ ልጅ ሲሆኑ፣ 12 እህትና ወንድሞች አሏቸው። በሰፊው ቤተሰብ ውስጥ ያደጉት አቶ ቾምቤ የአባታቸውን ጠንካራ የሥራ ባህል ይዘው እንዳደጉ ይናገራሉ።
አባታቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ወቅት በትራክተር እና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎች የታገዘ እርሻ ነበራቸው። እናም ለልጆቻቸው የግብርናውን ሙያ ሳይንስ ማለማመዱ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው። አባታቸው ከስራው ውጪ ደግሞ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ ሰው በመሆናቸው ልጆቻቸው በሙሉ ወደአስኳላው የእውቀት ማዕድ እንዲሳቡ ይገፋፉ ነበር።
ልጀቻቸውንም ያለማንም ገፋፊነት አስተምረዋል። በዚህ ምክንያት በደርግ ዘመነ መንግሥት ብቻ ስምንት ሴት ልጆቻቸውን በዲግሪ ያስመረቁ መሆናቸውን አቶ ቾምቤ ይናገራሉ። የአቶ ቾምቤ እህቶች በአሁን ወቅት በአሜሪካ እና አውሮፓ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አስተማሪ ሲሆኑ፣ የተቀሩትም በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ይገኛሉ።
አንደኛ ደረጃን እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዶዶላ ከተማ የተከታተሉት አቶ ቾምቤም ቀን ቀን ተምረው በትርፍ ሰዓታቸው የአባታቸው ዘመናዊ እርሻ ላይ ሲሰሩ ይውላሉ። በተጨማሪም አባታቸው ወደዘይት መጭመቂያ ሥራ ሲዘዋወሩም ሌሊት ላይ ከወንድማቸው ጋር በዘይት መጭመቂያው በሥራ ያሳልፋሉ። ከዚ ያም ማታ ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስላልነበረ እንደሌሎች ወንድምና እህቶቻቸው ሁሉ በኩራዝ ብርሃን የማጥናታቸው ጉዳይ የእለት ተዕለት ተግባራቸው ነበር።
በትምህርታቸው በርትተው በጥሩ ውጤት 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ደግሞ በ1974 ዓ.ም ወደዩኒቨርሲቲ ገቡ። ከዶዶላው ቤተሰባቸው ተለይተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግን ትምህርት መከታተል ጀመሩ። በክረምት ወቅት ወደቤተሰባቸው ሲመለሱ ግን ሩቅ አሳቢ የነበሩት አባታቸው የሹፍርና ትምህርት እንዲከታተሉ ያደርጉ ነበር። እናም በ1978 ዓ.ም ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመረቁ በጎን ደግሞ የሦስተኛ መንጃ ፈቃድ ባለቤት ሆነው ነበር።
ከዩኒቨርሲቲው እንደተመረቁም ወዲያውኑ በአስተ ማሪነት የተመደቡት በቀድሞው የአርባምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ በአሁኑ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው። በመም ህርነት ቆይታቸው ደግሞ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከአሁኑ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጋር በጋራ ሰርተዋል። በወቅቱ መንጃ ፈቃድ የነበራቸው ወጣት መምህር በመሆናቸው መኪና ተሰጥቷቸው ከመምህርነቱ በተጨማሪ የግንባታ ቁጥጥር ስራ እየከወኑ ይሰሩ ነበር።
ለሦስት ዓመታት በተቋሙ እንዳገለገሉ ደግሞ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል በማግኘታቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዩናይትድ ኪምግደም ስኮትላንድ ተላኩ። በስኮትላንድም በአፈር ሜካኒክስ ፋውንዴሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተከታትለው አጠናቀቁ።
ትምህርቱ ሲጠናቀቅ ግን ያልታሰበው ነገር በኢት ዮጵያ ተከሰተ። የደርግ መንግሥት ወድቆ ግርግር የነበረ በት ወቅት በመሆኑ አቶ ቾምቤ ወደሀገራቸው ለመመለስ አልቻሉም። እናም በዚያው ስኮትላንድ ቆይተው የግድግዳ ወረቀት መለጠፍ፣ የኤሌክትሪክ ምድጃ ሥራ እና የተለያዩ ጥገናዎች ላይ ለአንድ ዓመት እየሰሩ ቆይታቸውን በአውሮፓ አደረጉ።
በመጨረሻ ግን ወደሀገራቸው ለመመለስ ሲያስቡ በትምህርት ወቅት እና በሥራ ጊዜ የቆጠቧትን 70 ሺህ ብር አውጥተው አንድ ትራክተር ገዙ። ቀድሞ አባታቸው በልጅነታቸው ጊዜ የነበራቸው ትራክተር እና የግብርና ሥራ በውስጣቸው ልዩ ስሜት ይዞ ነበርና እርሳቸውም ግብርናው ላይ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ነበር ህልማቸው።
ትራክተሯን ወደተወለዱባት ዶዶላ ልከው የትምህርት እድል ወደሰጣቸው አርባምንጭ የትምህርት ተቋም አመሩ። በዚያም የማስተማር ስራውን ትተው ወደግል ሥራ ለመሰማራት ማቀዳቸውን በመግለጽ መልቀቂያቸውን ወሰዱ። በመቀጠልም ለዶዶላ እና አካባቢዋ ህብረተሰብ ከውጭ ይዘውት የመጡትን ትራክተር በማስተዋወቅ ለግብርና ሥራ የማከራየት ስራቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ።
በወቅቱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በርካታ በመሆና ቸው አቶ ቾምቤ የትራክተራቸውን ዋጋ ለመመለስ የወሰደ ባቸው ጊዜ ሦስት ወራት ብቻ እንደነበረ ያስታውሳሉ። ይህ የገበያ አማራጭ የሳባቸው የዶዶላው ሰው ታዲያ ከባንክ 100 ሺህ ብር ተበድረው እና እቁብ ገብተው ያገኟትን መጠነኛ ገንዘብ ጨምረው ተጨማሪ ትራክተሮችን ለማስመጣት ተነሱ።
ከእንግሊዝ ሁለት ትራክተሮችን ገዝተውም ዳግም ተመለሱ። በመቀጠልም ኮምባይነሮችን ጨምረው ለአርሶአደሩ በኪራይ ማቅረቡን ተያያዙት። እንዲህ እንዲህ እያሉ በዶዶላ እና አካባቢዋ ላይ ታዋቂ የእርሻ መሳሪያዎች አከራይ ሆኑ።
ስራውን ከጀመሩ ከሦስት ዓመታት በኋላ ከትራክተሮቹ ባሻገር 18 የሚከራዩ ኮምባይነሮች (እህል አጭደው የሚወቁ) ባለቤት በመሆን ሃብታቸውን ከፍ አድርገው ነበር። ከ20 ዓመታት በፊት ለኮምባይነር ኪራይ በኩንታል 12 ብር ሲያስከፍሉ በትራክተር ለማረስ ደግሞ በሄክታር 200 ብር ያስከፍሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ስራቸው እየጎለበተ ሲመጣ ግን ወደአዲስ አበባ መጥተው ገደብ ኢንጂነሪንግ የተባለ ድርጅት ከፈቱ። ጎፋ አካባቢ በከፈቱት ድርጅት አማካኝነትም ‹‹ጆን ዲሬ›› የተሰኘውን ለረጅም ዘመናት ትራክተር በማምረት የሚታወቀውን የአሜሪካውን ኩባንያ አጋር ሆኑ። እናም በብቸኝነት ምርቶቹን ወደኢትዮጵያ ለማስመጣት እድል አገኙ።
ከ1990ዎቹ አጋማሽ አንስቶ ለኢትዮጵያ የአፈር እና የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የተለያየ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮችን አስመጥተዋል። ከስኳር ፋብሪካ አንስቶ እስከ አነስተኛ አርሶ አደሮች ድረስ ምርቶቹን ለእርሻ ሥራ ጥቅም ላይ አውለዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ትልቁ የግብርና እቃዎች አስመጪ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
አሁን ላይ በድርጅታቸው አማካኝነት የተለያየ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች፣ የጤፍ አና የተለያዩ ሰብሎች የመስመር መዝሪያዎች እና የኬሚካል መርጫ ዘመናዊ መሳሪያዎች ለገበያ ያቀርባሉ። ለመሳሪያዎቹ የሚሆኑትን መለዋወጫዎች በማቅረብ በእራሳቸው ባለሙያዎች የጥገና አገልግሎትም ይሰጣሉ።
በተጨማሪ ለመንግሥት አብረን እንስራ የሚል ጥያቄ አቅርበው በመገጣጠሚያው ዘርፍ አንድ ድርጅት ከፍተዋል። ሻሸመኔ ላይ ከሦስት ዓመት በፊት ከመንግሥት ጋር በጥምረት በከፈቱት የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትራክተሮችን እያመረቱ ይገኛል።
መንግሥት 51 በመቶ ድርሻ በያዘበት መገጣጠሚያ ፋብሪካ እርሳቸው ደግሞ 49 በመቶውን ድርሻ ይዘው ግብርናን ሜካናይዝድ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እያገዙ ይገኛል። በየማምረቻ ፋብሪካው ከውጭ ለለሚገቡ እቃዎች የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢኖርበትም በቀን ከ100 ፈረስ ጉልበት በታች አቅም ያላቸውን 25 ትራክተሮች መገጣጠም እንደሚቻል ይናገራሉ።
እስከአሁን ድረስም በፋብሪካው አማካኝነት በአጠቃላይ 450 ትራክተሮች ተገጣጥመው ለገበያ ቀርበዋል። አሁን ላይ ደግሞ ከ100 ፈረስ ጉልበት በላይ አቅም ያላቸውን ትራክተሮች ለማምረት ቡራዩ ላይ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ ግንባታ አከናውነዋል።
በመገጣጠሚያው ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው እና ለኢትዮጵያውያን ተስማሚ የሆኑ ትራክተሮች ለማምረት ተዘጋጅተዋል። አቶ ቾምቤ ከግብርና መሳሪያዎች አቅርቦት ውጪ በግብርና ስራውም መሰማራቱን ያውቁበታል። በተለይ በአርሲ ዞን ከመንግሥት መሬት ተቀብለው የተለያዩ ሰብሎችን ያመረቱ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ባሌ ላይ 800 ሄክታር መሬት ስንዴ አልምተው እየተጠቀሙ ይገኛል። በአፋር ክልልም ሦስት ሺህ ሄክታር መሬት ተረክበው የመስኖ ስንዴ በሙከራ ደረጃ የተወሰነው መሬት ላይ እያለሙ ይገኛል። በቀጣይ ደግሞ የጥጥ፣ የድንች እና የሸንኮራ አገዳ ምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችን አስመጥተው ግብርናውን በዘመናዊ መሳሪያዎች ለመደገፍ እቅድ አላቸው።
በኢትዮጵያ ካለው የእርሻ መሬት ውስጥ 95 በመቶው በበሬ የሚታረስ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቾምቤ፣ ጠንካራው አርሶ አደር በባህላዊ መንገድ ተጠቅሞ እሰከአሁን ድረስ ህዝብ እየመገበ ማቆየቱ የሚያስከብረው መሆኑን ይገልጻሉ። ይህንን ጥረት ግን በዘመናዊ የግብርና መሳሪያ በመደገፍ ለሃገርም የተሻለ ውጤት ማስገኘት አላማቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
በአንድ ትራክተር ኪራይ ሥራ የተጀመረው ንግዳቸው አሁን ላይ በሚሊዮኖች ብር ያስገኘ ንግድ ቢሆንም፤ በዘመናዊው የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦት ላይ ለሀገራቸው የበኩላቸውን መወጣት መቻላቸው ደግሞ የመንፈስ እርካታን የሚሰጣቸው ጉዳይ መሆኑን አልሸሸጉም።
ለወደፊቱ ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፉ በመሰማራት የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ግንባታ ላይ ለመሳተፍ ውጥን ይዘዋል። ለግንባታ ኢንቨስትመንቱ የሚሆን ቦታም ከመንግሥት ላይ ጠይቀው በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
የዶዶላው ነጋዴ በሀገራቸው ሰርተው ለሌሎችም ሥራ የመፍጠር ተግባራቸው ሰፊ ነው። ጎባ ከተማ ላይ የዋቢ ሸበሌ ሆቴል ባለቤት በመሆናቸው ለአካባቢው ጎበኚዎች እና ለነዋሪው አገልግሎት ከመስጠታቸው ባለፈ ለበርካታ ሰው ሥራ መፍጠር ችለዋል።
አቶ ቾምቤ፣ በሻሸመኔ ከመንግሥት ጋር ከከፈቱት መገጣጠሚያ ውጪ በእራሳቸው ብቻ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶቻቸው አማካኝነት ለ120 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። በቅርቡ ወደስራ የሚገባው የቡራዩው ትራክተር መገጣጠሚያው ሲታከልበት ደግሞ የሠራተኞቻቸው ቁጥር ወደ 200 እንደሚጠጋ ይናገራሉ።
በትራክተር ጥገና ላይ የተሰማሩ ሰራተኞቻቸው ደግሞ በጆን ዲሬ ኩባንያ አማካኝነት እስከ አሜሪካን ድረስ ሄደው የተግባር እና ትምህርታዊ ስልጠናዎች እንዲያገኙ ይደረጋል። በአዲስ አበባ ቢሯቸው ሆነው የኦንላይን ትምህርት እና ስልጠና የሚያገኙ ባለሙያዎችም በርካታ በመሆናቸው በየጊዜው የሠራተኞቻቸው የዕውቀት ደረጃ እና ልምድ እያደገ እንደመጣ አቶ ቾምቤ ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት ጥገና የሚያስፈልጋቸውን የግብርና መሳሪያዎች በድርጅታቸው የውስጥ አቅም በመጠቀም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።
ለአቶ ቾምቤ አንድ ሰው በውስጡ ያለውን እምቅ ሃይል አውጥቶ ለሌላው ማካፈል እስኪችል ድረስ በትጋት ከስራ የተሻለ ውጤት ማግኘት ይችላል። ጥረት የታከለበት ንግድ ምንጊዜም አዋጭ መሆኑን ይናገራሉ።
ማንኛውም ሰው በሙያው ተሰማርቶ ጥራት ያለው ነገር ማቅረብ ከቻለ ለእራሱም ሆነ ለሀገሩ የሚያተርፈው ነገር ስለሚኖረው ወጣቶች በተለይ ሰርቶ ለመለወጥ ምንጊዜም ሊተጉ ይገባል የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ጌትነት ተስፋማርያም