ዋና ብለን የምንጠራው ብዙ ነገር በቤታችን ፣ በደጃችን ፣ በጎረቤት በመኖሪያ አካባቢያችንና በሐገር ደረጃ አለን ። ለመሆኑ ዋናው አጀንዳችን ምንድነው? እርሱንስ ከየት እናገኘዋለን? ለአብዛኞቻችን ዋናው አጀንዳችን ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስና አለፍም ሲል መጓጓዣ ወይም ሥራው ሊመስለን ይችላል ። እነዚህ ነገሮች በዋናነት ሊፈረጅ የሚያስችል አቅም ሳያጡ የሚያጡት ሰላም በዙሪችን ከሌለ ነው። ሰላም ዋናው የእነዚህ ሁሉ አቅሞች ማሳኪያ የሆነ መሰረት ነው ፤ ለዚህ ነው ዋናውን አጀንዳ ሰላምን እንዳንረሳ ዋናው አጀንዳ ብዬ ርእስ የሰጠሁት።
ሰላምን የማይወድ ሊኖርበት የማይፈልግና የማይናገር ጤናማ ሰው መቼም አይገኝም። በማንኛውም የሃገራችን ቋንቋ ቃሉ አስፈላጊ በመሆኑም ቃሉ ስም ሆኖ እያገለገለ ነው። በያላችሁበት ይህንኑ ቃል በአፍ መፍቻችሁ ቋንቋችሁ እንደምትጠሩት አልጠራጠርም ። ታዋቂው ደራሲ ሆሬስም ስለሰላም የተናገረው ጥልቅ ነገር አለ። “ ሰላምን ካለሰላም ለዘለቄታው ማምጣት አይቻልም።” ስለዚህ ሰላማችንን በሰላም እንዴት እናምጣው? ነው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የምንለው።
ይህንን በቤት ደረጃ በሚነሳ ጸብ ውስጥ፣ ማየት እንችላለን። ታላቅ እህት ታናሹዋን እቃዎቼን አትንኪ በሚል እያስጠነቀቀቻት ነው፤ ታናሽ ግን አንቺ ያሉሽ ነገሮች ስለሌሉኝ፣ ወይም ስለሚያምሩ ባደርጋቸውስ ባይ ናት።እዚህ ጋ፣ የኔና ያንቺ የሚባሉ መለያዎች ያሉትን ነገር እናስተውላለን፤ የታላቅ እህቲቱ (ሣራና ታናሽ እህቷ ግላሴ እንበላቸው) እና የታንሹዋ ንብረቶች በተራራቀ እድሜ ሳቢያ፣ ትልቋ በርከት ያሉ ነገሮች አሏት ። ቅባቴን መዋቢያ እቃዎቼንና ውስጥ ልብሶቼን አትንኪ ትላታለች። ግላሴ ግን ወላጆቿን ግዙልኝ ብላ ከማሸነፍ ይልቅ ታላቅ እህቷን ማስደንገጥ መርጣለች። እንዲያውም ከማስጠንቀቂያዋ ብዛት አንድ ቀን ዝም ብለሽ ከምታስፈራሪን አንድ ቀን ይለይልን ትላታለች። (ጥፍሮቿን እያሳየቻት) ንዴቷን መቋቋም ያቃታት እህት እርሷም እንደተቆጣች ትንሽ እህቷ ላይ ዘፍ ትልባታለች ፤ ንዴትና ኃይል የተቀላቀለበት የሳራ ጉልበት የግላሴን አቅም ይደፍቅና ከመሬት ስታላትማት በዚያው ድምፅዋ አልሰማ፣ ይላል። ከዚያም ከላይዋ ላይ ተነስታ “አስኮናኝ ለዚሁ አቅምሽ አይደል የተፍጨረጨርሽው” ብላ የተበታተነ ፀጉሯን ወደማስተካከሉ ብትመለስም ግላሴ ከተኛችበት አልንቀሳቀስ አለች።
ሣራም ወደ እህቷ በመመለስ ተነሽና ለትምህርት ቤት ተዘጋጅ ፤ ተኝታ ትቀራለች እንዴ ትላታለች ። ዝምታ ሲቀጥልባት እናቷን ከፍ ባለ ድምጽ ትጣራለች ። እናት ሮጣ ስትመጣ ግላሴ አትናገር፤ አትጋገር። ምን ሆና ነው ብላ ስትጠይቅ መጣላታቸውንና እንደመታቻት ትናገራለች። አሁን ታክሲ ጥሪልኝ አምቡላንስ ትልና አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ይወስዷታል። ለካስ በግብግቡ ወቅት ግላሴን የአልጋው ጠርዝ ማጅራቷን ገጭቷታል ። ድንገት የባነነችውም ሐኪሙ በትንሽ ዳበሳ ደም ስሮቿን ከነካካ በኋላ ነው። ቀልቧ መለስ ሲልላት እናቷ ላይ ጥምጥም አለችና ከሣራ ክፍል አውጭኝ፤ እማይዬ ትገለኛለች፤ ስትል በክፍሉ ጠርዝ ላይ ሣራ በጸጸት እያለቀሰች ነበረ።
በሁለቱ እህትማማቾች መካከል የተነሳው ጸብ በሁለት መንገድ ሊቀር ይችል ነበረ። አንደኛው ሣራና ግላሴ ጉዳያቸውን ቁጭ ብለው በመነጋገርና ተገቢውን የንብረት ክፍል በማድረግ ፤ ማለትም በጋራ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉትን (የሚገቡ) እቃዎችን የማይገቡትን በመለየት ፣ ሁለተኛ፣ ጉዳዩ መደማመጥና መናናቅ ከነገሰበትና አንዳቸው ያንዳቸውን ቃል መስማት የማይወድዱ ከሆነ፣ ለወላጆች በመንገር ለጉዳዩ እልባት መስጠት ይቻላል። አለበለዚያ በቀላሉ የሚፈታው የጸብ መነሾ ወደማይፈታ አጥፊና ጠፊነት ሊያድግ ና ቤተሰብ ሊበትን ይችላል።
ለዚህ ነው፤ ቅራኔ አያያዛችን መልክ ይዞ ሊቀጥል የሚችልበትን አግባብ ማጤን የሚገባን ። ይህንን በድርጅቶች ደረጃ ከፍ አድርገን ማየት ከቻልንም ተመሳሳይ ውጤት ልናይ እንችላለን። መደማመጥ፣ የሃሳብ ልዩነት መከባበር፣ አድራሻና መድረሻን መቀበል (ከየት የመጣና መድረሻውን የማያውቅ ላለመባባል) መቻልና በረባው ባልረባው ምክንያት ላለመገፋፋት መጨከንን ይጠይቃል፤ ሰላም!
እንደዘበት “ሰላም ነህ ወይ፣ ሰላም አደርሽ ወይ እና ሰላም ዋል” የሚሉት ቃላት ቀላል ትርጉም ያላቸው አይደሉም። ለአፍ ያህል ሳይሆን ሲቀር የከበደና የጠለቀ ፍች ያላቸው ቃላት ናቸው። ሰላም በመዋል ውስጥ ግጭት የለም አይደለም ፤ ግን የበረደ ግጭትና አዳርን የማያጠራጥር እምነት አለ፤ ማለት ነው። ስለዚህ ነው፣ ሰላምን አቆላምጠንና አስፍተን ለማሳየት ወይም ለቄንጥም ብለን፣ ከራሳችን አልፎ ከዕብራይስጥ ተውሰን “ሻሎም” የምንለው።
ስለዚህ ከግለሰብ አንስቶ ድርጅቶች ራሳቸው ውስጣዊ ሰላማቸውን ማስጠበቅ ይገባቸዋል። ሰላም በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ከተጠበቀ ሰው ይልቅ ከራሱ ጋር ሰላም ያለው ሰው ምንኛ የታደለ ነው። ምክንያቱም አንድም ፀጥ ካለ የመስሪያ ቤት ድባብ ይልቅ ፀጥ ያለ ሰላማዊ ማንነት ያለው ሰው የተባረከ ነውና፤ ሁለትም እውነተኛ ሰላም የሚመነጨው ከሰውየው ከራሱ ነውና። ሰው በራሱ ውስጥ የጠፋውን ሰላም ዘንግቶ፣ “ሰራተኞቹ ሰላሜን ነሱኝ፤ የሥራ ባልደረቦቼ ሰላም አሳጡኝ፤ ሚስቴ ሰላሜን ወሰደችው፤ ” ማለት ለማንም ለምንም አይረባም፤ መጀመሪያ አንተ ከራስህ ጋር ሰላም አለህን? ሰላምህ በውስጥህ የተጠበቀ ሲሆን ለሌሎች ሁካታ የምትሰጠው መልስ ከአንተ ሰላማዊ ሚዛን የተነሳ መሆኑን አትርሳ።
ሰላምን ማምጣት የሚቻለው በሰላም ነው ብለናልና ፣ ይህንን ሰላም በሥርዓት ይዘን የበለጠ የሰላምን ጸጋዎች ማስተናገድ መቻል ምንኛ መታደል ነው። ሰላማዊ ሰው ከራሱ በሚመነጨው ሰላም ቤቱን የሚመራው በሰላም ነው፤ መስሪያ ቤቱም የሚውለው በሰላም ነው፤ ከማህበረሰብ ጋር የሚስተጋበረው በሰላም ነው፤ በሐገር ደረጃ ለሚኖረውም ሰላም በቤቱ፣ በጎረቤቱና በማህበረሰቡ ውስጥ ለሰላም በሚከፍለው ዋጋ መሰረት ይከፍላል ፤ ያካፍላል።
ሰላም ነው፤ ማለት ጸጥ ረጭ ያለ፣ የማይናገር የማይጋገር ማንነት ያለው ነው፤ ማለት ግን አይደለም ። ዋናው ጉዳይ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙት (መቼም ችግር አይጠፋምና ) ወደ መፍትሔው የሚሄደው እንዴት አድርጎ ነው- የሚለው ጥያቄ ምላሽ ነው።
ባል እና ሚስት ይቀያየሙ ያድሩና፣ በማግስቱ “ሰላም አደርክ” ትለዋለች፤ “ሰላሜን ይዛው ጠፍታ፣ አድራ ሰላም ነህ ወይ…. ትለኛለች ፤ እንዴ?” አለ ይባላል። ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ አንዱ ሌላኛውን በመወንጀልና ጣት በመቀሳሰር መቼም መፍትሄ አይገኝም። ዋናውና ተገቢው ጉዳይ፣ የራስን አስተዋጽኦ መመርመር ነው ። ራስን የችግሩም የሰላሙም አካል ማድረግ ተመራጭ ነው።
ህግን በህገ-ወጥ መንገድ ሲመራ የነበረ ኃይል፤ ህግን በሸርና ሸፍጥ ሲደፈጥጥ የኖረ ወገን፣ ህግን በክፋትና በሁከት ያውም ራሱ በሚያቀነባብረው ግፍ መልሶ መዋቲዎችን ሲያንገላታ የነበረን ኃይል በራሱ መንገድ ለመዳኘት መሞከር የሚፈለገውን ሰላም ፤ የሚፈለገውን ፍትህ አያመጣም ፤ ፍትሃዊ ነው፤ ብለን ብናስብ እንኳን ርትዓዊ አይሆንም።
በሰላማዊነቷ በምትታወቀው ኖርዌይ ውስጥ ለበጋ ሽርሽር ወደ ኡቶያ ደሴት ከተጓዙት መካከል 69 ያህሉን የሌበር ፓርቲ አባላትና ለጋ የትምህርት ቤት ተማሪዎችን “ሩገር ሚኒ” በተባለ አልሞ መተኮሻ ጠመንጃ ነጥሎ እየመታና እንዲሁም “አንፎ ቫን በተባለ ቦንብ ደግሞ ኦስሎ ከተማ ላይ 8 ሰዎችን፣ የጨፈጨፈው አንደርስ ብሬቪክ (በ4ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ነው፤ ይባላል) በጠቅላላው፣ 77 ዜጎችን ፣ ገድሎና 319 ካቆሰለ በኋላ ተይዞ ሲጠየቅ ሐገሬ በመጤ ሃይማኖትና ፤ ሴቶችን የበላይ በሚያደርግ (ፌሚኒስት ንቅናቄ) ባህል እየተበከለች ስለሆነ እርሱን ለማጽዳት የወሰድኩት እርምጃ ነው፤ እኔ ከማንም ጋር የግል ጸብ የለኝም ፤ “ወደተሻለ የሐገር ከፍታ ለመሄድ የተወሰደ የማጽዳት እርምጃ” ነው- ነው ያለው። ለሐገር በማሰብ ስም የሐገሩን ሰዎች መግደል፣ ለሃይማኖቴ ስል ነው፤ በሚል ስም የሐገሩን ንብረት ማጥፋት የብዙ አጥፊዎች የጋራ መለያ ነው።
ይህ ሰው ታዲያ፣ ወደ ፍርድ ቤት ሲመጣና ሲሄድ በፍርድ ቤትም ውስጥ በአለባበስም ሆነ በገጽታ አያያዙ መልካም መሆኑን ያዩ ጋዜጠኞች ፣ የሐገሪቱን የፍትህ መስሪያ ቤት ሃላፊ፣ “ይህንን መሰል ጭራቅ ወንጀለኛ ሰው፣ በወህኒ ልብስና አቀራረብ መያዝ ሲገባችሁ፣ እንዳማረበት መቅረቡ እርሱን መሰል ወንጀለኞች እንዲፈለፈሉ ምክንያት ያደርጋል፤ ከዚህም ሌላ፣ የታሰረበትን ክፍልም ስናየው ለታላቁ ሐይቅ እይታ የተመቸና ማራኪ ነው፤ ይህም ወንጀለኞች ወንጀል ሰርተው ተንደላቅቀው መኖር እንደሚችሉ አያመላክትምን፤ አያደፋፍርምስ ትላላችሁ?” ሲል ለጠየቋቸው ጥያቄ ሃላፊው ሲመልሱ ፣ “እርሱን እንደ ጭካኔው አስበን ካሰቃየነው፣ እኛ ከእርሱ ጨካኝ ዝንባሌ በምን እንለያለን?” ሲሉ ያጠይቁና … ከውጭው ዓለም ጋር ያለው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠና ወንጀሉን ደግሞ ሊሰራ የሚችልበትን እድል ሁሉ ያቋረጥን ስለሆነ ምንም አቅም የለውም ። እድሜ ልክ (21 ዓመት ) ለብቻው እንዲታሰር ስለፈረድንበትና 24/7 በኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስ ስለሚጠበቅ የትም አይደርስም ሲሉ መልሰዋል። ለማንኛውም የዚህ የ2017 ዓመተምህረቱ ድርጊት፣ አድራጊውን ለእስር፤ ኖርዌይን ለዕድሜ ልክ ጸጸት ዳርጎ፤ ይህ ክፉ የታሪክ ክስተት ፣ በሐገረ ኖርዌይ “የኡቶያው እልቂት” ሲል ተመዘግቦ ይገኛል።
“ጦርነት እሳት ነው፤ ነዲድና ድቀት፣
እርሳስ እየበሉ ፤ እሣት ሚያገሱበት፣
ወርቅ እያቀለጡ፤ ዓመድ የሚያፍሱበት።” (ያልታወቀ ገጣሚ)
በዚህም፣ ሰላምን ብለው፣ ሰላምን አስበውና ሰንቀው ወደሜዳ የሚወጡትን፣ ወደሥራ የሚሄዱ፣ ለግንባታ ደፋ ቀና የሚሉ ባተሌዎችን ፣ በፍንዳታ ማስደንገጥ፣ ተጓዦች የተሳፈሩበትን አውቶቡስ ጠብቆ ማጋየት፣ ወይም አግቶ ማሰቃየት፣ እና የመሳሰሉትን ስናስብ የሰላምን ዋጋ እንድናስብበትና እንድንቆምለት በጣም ይገፋፋናል።
ሌባ ሰዓት ነግሮ እንደማይሰርቅ ሁሉ አጥፊዎች በቀጠሮ አይመጡም ፤ በቀጠሮ የማይመጣን አጥፊ ደግሞ ያለቀጠሮ በንቃት ይጠብቁታል እንጂ፤ አይዘናጉለትም። በናይጄሪያ ቦኮ ሐራም “ሥልጣኔ እርሙ” ድርጅት፣ በአፍጋኒስታን ጧሊባን፣ በሶማሊያ አልሸባብ፣ በፊሊፒንስና ኢንዶኔዥያ ያሉ መሰል ድርጅቶች፣ ሲያጠፉ ወይም አጥፍተው ሊያጠፉ ሲመጡ ነግረው አይመጡም ፤ የደራ ገበያና የተጧጧፈ የመኪና ጅረት የሚፈስበትን ሰዓት፤ ቱሪስቶች የሚመላለሱበትን አካባቢ፣ እውቅ የሆኑ የገበያ አዳራሾችንና ስፍራዎችን ስመጥር ሆቴሎችን፣ በብዙ ህዝብ ሲጨናነቅ ጠብቀው ያደርጉታል፤ እንጂ።
ይህንን ሰላም በብዙ ንቃትና ትጋት በውስጣዊ ሰላም ነው ፤ ልንጠብቀው የሚገባን። ያንን ውስጣዊ ሰላምም የምንገነባው በይቅርታ ነው። ይቅርታን የምናዳብረው በፍጹም ትእግስት ነው፤ ትእግስቱን የምናንጸውም በትህትና ነው። እነዚህን እርስ በእርስ የሚተናነጹ ንኡድ ጉዳዮች የምናሳድገው በህይወት በሰላም ስንኖር ነው።
እንታገሳለን ስንል ስለማንችል “እስቲ እንግዲህ ይሁን” ብለን ሳይሆን፣ ለማድረግ ወይም ለመበቀል ስንችል፣ ልናደርገው የማንፈቅድ መሆናችንን በማሳየት ነው። የሚጠላህን ሰው ድንጋይ ተረብርቦበት ስታገኝ ሌላ ድንጋይ ጭነህበት መሄድ ስትችል ፣ ወይም “እግዚአብሔር ይቅጣህ” ብለህ ሳትል ፤ የተረበረበበትን ድንጋይ አንስተህ፣ ወደ ህክምና ስፍራው በመውሰድ እንዲድን ስታግዘው ነው፤ ታገስከው ማለት የሚቻለው። እንዲህ ታግሼ አሳልፌው ሳበቃ፣ ተነስቶ ቆሞ ቢያጠቃንስ ብሎ የማይታገስ ፈሪ ነው። ፈሪ ደግሞ እንኳንስ ለሌላው ለራሱም ሰላም የሌለው ቦቅቧቃ ነው። ፈሪ ሰው ደግሞ ሺህ ቢያምጥ የሚወልደው ጭካኔ እንጂ ከቶም ትእግስትን አይደለም። ፍርሃት የሚወጣው መቀርጠፍን እንጂ መሞረድን አይደለም ፤ ስለዚህ ለጋራ ሰላማችን ስንል በታነጽንበት ትዕግስት፣ በቁርጠኛነት፣ በፍቅርና በትህትና ልባችንን በማቅናት ለላቀ ሰላም ዘብ እንቁም!
“ሰላም ውብ ደን ነው፤ የጽናትና ሐሴት፤
በትዕግስት ትሁት ዘር ፍቅር የሚበቅልበት!!” (ያልታወቀ ገጣሚ)
ስለዚህ ዋናውን አጀንዳችንን በጽናት በመያዝና ውስጣችንን በመመርመር ፣ ሌሎቹን ድሎቻችንን ጨብጠን ለመጓዝ እንነሳ! ለዋናው አጀንዳችንም የሚጠበቅብንን ሁሉ በውስጣችን፣ በቤት፤ በሰፈር- በጎጥ፣ በቤተ እምነቶቻችን፣ በተቋሞቻችን፣ በከተማና በገጠር ሁሉ የቤት ሥራችንን በትኩረት ከሰራን ሐገራችንም በተግባር ሰላም የሰፈነባት ምድር ትሆንና የማለዳ ዝማሬያችንም እርሱኑ ማመስገን ይሆንልናል! ሰላም ያክርመን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ