ቅድመ-ታሪክ
ልጅነቱን እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ሲቦርቅ ቢያሳልፍም ትምህርት ቤት ገብቶ ቀለም ለመቁጠር አልታደለም። ወላጆቹን በማገዝ ጊዜውን መግፋት ዕጣ ፈንታው ሆነ። ከፍ ማለት ሲጀምር ግን ወጣትነቱን በስራ ማሳለፍ እንደሚገባ አመነበት። ይህ አመኔታው ሩቅ ቢያሳስበው ደግሞ ምርጫው አዲስ አበባ አደረገ።
ደምስ እንዳሰበው ሆኖ አዲስ አበባ ደረሰ። እግሩ ስፍራውን ከመርገጡ በፊት ስለከተማው ይሰማው የነበረው ሁሉ ሲያጓጓው ክርሟል። አልፎ አልፎ ወደ ቀዬው የሚዘልቁ ወጣቶች ተለውጠውና አምሮባቸው ሲመለከት ራሱን በነሱ ቦታ ተክቶ ልቡን በሀሴት ሲመላው ኖሯል። እነሆ! ዛሬ ደግሞ ህልም ትመስለው በነበረችው ከተማ ተገኝቶ አገሬውን መምሰል ከጀመረ ሰንበት ብሏል።
ደምስ አዲስ አበባ እንደገባ የመጀመሪያ ፍላጎቱ ራሱን መቻል ነበር። ይህን ለማድረግ ስራ ማግኘት እንዳለበት የገባቸው ባልንጀሮቹ ቄራ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ስጋ ቤት አስቀጠሩት። እንግዳው ደምስ ስጋ ቆራጭነቱን አፍታ ሳይቆይ ለምዶ ባለሙያ ሆነ። የሚከፈለው ደሞዝ ማነስ ግን እንዳሰበው አላራመደውም። ኑሮ እየከበደውና በሃሳብ እየናወዘ ከጭንቀት ገባ።
የቤት ኪራይ፣ የዕለት ወጪና ፍላጎቱ አልመጣጠን ቢለው ዘወትር በትካዜ ይብሰለሰል ያዘ። ስለከተማው የሰማውና እሱ እየሆነ ያለው አውነታ አልመሳሰል እያለ ከጥልቅ ሀሳብ ዘፈቀው። የስጋ ቤቱን ስራ ቢወደውም ጾም ሲገባ ስለሚዘጋ ያለደሞዝ መዝለቁ አላዋጣውም።
ደምስ ጥቂት ቆይቶ ሌሎች አማራጮችን ፈላለገ። አጋጣሚ ሆነና በዘመድ የተገኘለት ስራ ከቀበሌ ስጋ ቤት አስቀጥሮ ደሞዙን በእጥፍ አሳደገለት። በዚህ ስፍራ መቆየቱም ልምዱን አዳብሮ ከበርካቶች አስተዋወቀው። ጠቀም ያለ ገንዘብና ጥሪት እንደያዘ ዓይኖቹ ወደሌሎች ስፍራዎች አማተሩ። አሁን ጥሩ እጅ ስላለው ብዘዎች ተደራድረው እንደሚወስዱት ተማምኗል።
ይህ ልበሙሉነት ሲጨምርም ደምስ ቦታ እያማረጠና በደሞዝ እየተደራደረ አቅሙን አጠናከረ። ከቦታ ቦታ እየዞረም ሙያና ችሎታውን አስመሰከረ። ዳቢቱን ከሻኛ፣ ታላቁን ከታናሽ፣ ጮማውን ከአጥንቱ እያማረጠ የሚሰጣቸው ደንበኞቹም በረከቱለት።
በል! ሲለው በአስተናጋጅነት ጭምር ይሰራል። እንዲህ ሲሆንም በግብዣ የሚጎነጨው መጠጥ አያጣም። ይህ ካልሆነም ከኪሱ አውጥቶ ራሱን በማዝናናት በስካር መናወዝን ለምዷል። ይህ ድርጊቱ ግን በሰላም ከሌሎች ጋር ሊያኖረው አልቻለም። በየሰበቡ ከሚጋጫቸው ጋር መጣላቱ ለፖሊስ ጣቢያ ክስ እየዳረገ ለቀናት በእስር ያከርመው ያዘ።
ከዕለታት በአንዱ ቀን የፈጸመው ስህተት ግን ዘወትር ከለመደው ድብድብ አለፍ ብሎ ጥርስ እስከማውለቅ አደረሰው። ጉዳዩ ከበድ ማለቱም ደምስን ለእስር ዳርጎ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት አወረደው። ሁለት አመታትን በቅጣት አሳልፎ አዲስ አበባ ሲመለስ ማንነቱን ለውጦ መልካም ሰው እንደሚሆን ከራሱ ጋር ተስማማ።
ህይወት ከእስር በኋላ
ደምስ የሁለት አመቱን እስር አጠናቆ አዲስ አበባ ሲገባ ወደ ቀድሞው ስራው ተመለሰ። የስካር ልማዱን ተወት አድርጎ ያባከነውን ጊዜ ማካካስ እንዳለበት አምኖም በጥንካሬ ዘለቀ። ይህ መንገዱ እምብዛም አላራመደውም። መጠጥ በተጎነጨ ቁጥር ከሰው እያጋጨ ሰላም አሳጣው።
ጥቂት ቆይቶ ካገሩ ልጆች ተገናኘ። ከእነሱ ጋር መሆኑ የኮንትራት ስራዎችን እንዲያውቅ አገዘው። በሰርግና መሰል ዝግጅቶች እየተገኘ የሚቆርጠው ስጋ ገንዘብ አስገኘለት። ይህ አይነቱ ስራ ተጨማሪ አቅም ሆኖ ብዙዎቹን ያበረታል። ከወር ደመወዝ ልቆም የልብን ያደርሳል። የደምስም ኪስ ለዚህ ሲሳይ በቅቶ ያሰበውን ሲሞላለት ቆይቷል።
ከአገሩ ልጆች አንደኛው ከእሱ ጋር በጋብቻ ይዛመዳል። እሱም ቢሆን ኑሮውን የሚገፋው በስጋ ቤት ተቀጥሮ በሚያገኘው ገቢ ነው። አመታትን በገፋበት የስጋ መቁረጥ ስራ ራሱን ጠቅሞ ዘመዶቹን ጭምር አግዞበታል።
ደምስና መኮንን ሲገናኙ በቀን ውሎ በሚያገኙት የስራ ጥቅም ላይ ይወያያሉ። ዕድል በቀናቸው ጊዜም ከሌላ አካባቢ ሰርተው ገንዘብ ይዘው ይመለሳሉ። ሁሌም ከሚያገኙት ጥቅም በእኩል የሚካፈሉት ባልንጀሮች ሌሎችንም አዳብለው የማሰራቱን ልምድ ዘልቀውበታል።
የጾሙ ወራት በገባ ጊዜ የስጋ ቤቶች ገበያ ይቀዘቅዛል። የበርካቶቹ በር ስለሚዘጋም ደንበኞች በስፍራው ዝር አይሉም። ይህኔ ደምስን የመሰሉ ተቀጣሪዎች የወር ገቢ የላቸውም። እንዲህ ሲሆን ግን አብዛኞቹ ለዕረፍት ወደ ገጠር ሄደው ጊዜን ይገፋሉ። ፋሲካ ሲደርስ ተመልሰውም ወደ ስራቸው ይገባሉ።
ደምስና ጓደኞቹም በነዚህ ጊዚያት ጓዛቸውን ሸክፈው አገር ቤት ይገባሉ። ሁለት ወራትን በገጠር ሲቆዩም ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ አይቦዝኑም። አቅም ላነሳቸው ቤተሰቦች የጎደለውን እየሞሉ፣ የወደቀውን ሲያቃኑ ምርቃትና ምስጋናን ያገኛሉ።
አንዳንዴ ጊዜ ሲተርፍ ደግሞ እነደምስ ቡድን ፈጥረው እግር ኳስ ይጫወታሉ። ጨዋታው ሞቆ ተመልካች ሲበረክትም ላለመሸነፍ ያለው ፉክክር ያይላል። እንዲህ በሆነ ጊዜም ለጠብና ድብድብ መጋበዙ የተለመደ ነው። በዚህ ልማድ በማለፍ ደምስና ባልንጀራውን መኮንንን የሚያህላቸው የለም።
አንድ ቀን ግን የኳስ ጨዋታው በአግባቡ ሳይጋመስ ጅምሩን ለማቋረጥ የግድ ሆነ። እንደተለመደው የኳስ ትግል የጀመሩት ሁለቱ ባልንጀሮች ዓላማቸውን ስተው በጠብ ተፋጠጡ። በጎል መሆን ያለመሆን የተነሳው ግጭትም ጡጫና እርግጫን አስከትሎ አንገት ለአንገት አያያዛቸው።
ሁኔታቸውን የተመለከቱ በርካቶች ከመሀል ገብተው ገላገሉ። በግልግሉ መሀል ክፍተት ያገኘው ደምስም መኮንንን ለማጥቃት ተፍጨረጨረ። ይህ አጋጣሚም የሁለቱን ልብ አሻክሮ የገጠሩን ቆይታ በመቀያየም እንዲያሳልፉት አስገደደ።
የጾም ጊዜው ተጠናቆ ለፋሲካ አዲስ አበባ ሲገቡ በመሀላቸው ንግግር አልተሰማም። ዘወትር ቢገናኙም በኩርፊያ እንደዘለቁ ወራትን ቆጠሩ። በተያዩ ቁጥር አንዳቸው ለሌላቸው ያላቸውን ጥላቻ ለማሳየት ይሞክራሉ። አንዳንዴም የጠብና የድበድብ ፍላጎት ይታይባቸዋል። አንድ ቀን ደግሞ ጉዳዩ ከዚህ አልፎ ዳግመኛ ጉልበታቸውን ፈተሹ።
የሁለቱን ጠብ ያስተዋሉ የቅርብ ሰዎች አሁንም መሀል ገብተው ገላገሏቸው። ይህን አጋጣሚ ሲያስብ የቆየው ደምስ ግልግሉን ተጠቅሞ የመኮንን ጭንቅላት በድንጋይ ፈነከተ። ያልተጠበቀው ድርጊትም የሁለቱን ቂም አባብሶ በመሀላቸው የቆየውን ቅሬታ ያባብሰው ያዘ።
እርቅ
አሁን የባልንጀሮቹ ቅያሜ ገፍቶ ከአንድ አመት በላይ አስቆጥሯል። ዛሬም ግን የሁለቱም ዓይኖች በጥላቻ መተያየታቸውን ቀጥለዋል። በተለይ በድንጋይ የተፈነከተው መኮንን አንድ ቀን ቂሙን እንደሚወጣ እያሰበ ቀንና ቦታ ማመቻቸቱን አልዘነጋም። የሁለቱ አለመግባባት ያሳሰባቸው የቅርብ ሰዎች ግን ቤተሰባዊ ቅርበታቸውን ምክንያት አድርገው ለማስታረቅ ወስነዋል።
በድንገት በሽምግልና የተያዙት ባልንጀሮች የእርቅ ጥያቄውን አለመቀበል አልቻሉም። ‹‹በይቅር ለእዚዓብሄር›› ተብለው ቅያሜያቸውን አነሱ። እንደፊቱ ሊሆኑ ቃል ገብተውም የቀድሞ ህይወታቸውን ቀጠሉ። የሁለቱን በጎ መሆን ያስተዋሉ ጓደኞቻቸው ሰላምና እርቅ በመውረዱ እፎይታ ተሰማቸው ።
ከእርቁ በኋላ በሁለቱ መሀል የሰፈነው ሰላም ጥቂት አለፍ ብሎ ታየ። ከጊዚያት በኋላ ግን የአንዳቸው ንግግር ለሌላቸው አሽሙር እየመሰለ ውስጣቸውን ያጎሸው ያዘ። አንዳንዴ ደምስ እንደቀልድ የሚጥለው ንግግር ለመኮንን ሰላም አይሆነውም። ቃላቱ ሁሉ ትርጉም እየሰጠው ማንነቱን ሲፈትነው ቆየ።
ከጾም ፍቺ በኋላ የጀመሩት የሉካንዳ ቤት ስራ አሁንም አልተቋረጠም። አንዳንዴ በተለየ ዝግጅትና ድግስ ሰበብ በትርፍ የሚያገኙት ገቢም እንደቀጠለ ነው። አሁንም ከሌሎች ጋር የሚያገኙትን ገንዘብ በመተሳሰብ እኩል ይካፈላሉ ።
አንድ ቀን ማለዳ የመኮንን የእጅ ስልክ አንቃጨለ። መልስ ለመስጠት ከመፍጠኑ ከደዋዩ የሰማው መልዕክት ፊቱን በደስታ አብርቶ ገጽታውን በፈገግታ አወዛው። የደወለለት ሰው በቀጣዩ ቀን በአንድ መናፈሻ የድግስ ስራ ስለመኖሩ ነግሮታል። ስለስራው የተረዳው መኮንንም ዋጋ ተነጋግሮ በተባለው ቀን በስፍራው ሊገኝ ተስማምቷል።
መኮንን ይህን የምስራች እንደሰማ ለሁለቱ ጓደኞቹ ስልክ እየደወለ አሳወቃቸው። የእሱን ስልክ ዘግቶም አንድ ሰው መጨመር እንዳለበት አሰበ። ይህን ሲያስብ ግን ለውሳኔው ተጨንቆ በሀሳብ ተመላለሰ። እስከዛሬ ለእንዲህ አይነቱ ስራ ደምስን ነጥሎት አያውቅም። አሁን ግን… በእጅጉ ተጨነቀ። አብሯቸው የዘለቀውን ቅያሜም አስቦ ለይሁንታው ከራሱ ጋር መከረ።
በሀሳብ ውጣውረድ ሲባዝን የቆየው መኮንን በመጨረሻ ደምስን ሊያሳትፍ ውስጡን አሳምኖ ውሳኔውን አሳለፈ። ይህን ዕቅዱን ለእሱ ነግሮም ለስራው እንዲዘጋጅና በቀጠሮው ቦታ በሰዓቱ እንዲደርስ በማሳሰብ ስልኩን ከአደራ ስንብት ጋር ዘጋ።
መስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም
በዚህ ቀን ማለዳ ስልኩ ያቃጨለው መኮንን ደዋዩ ደምስ መሆኑን እንዳወቀ ምክንያቱን ጠየቀው። ለስራው አስቀድሞ ሊቀሰቅሰው እንደሆነ በሰማ ጊዜም ከልቡ እንዳሰበበት በማወቁ በውሳኔው ተደሰተ። ለስራው የሚያስፈልጉ ስል ቢላዎች፣ መከትከቻና አነስ ያለ መጥረቢያ ከነጭ ሽርጥ ጋር አዘጋጅቶ በሻንጣው ከተተ።
ሁሉን አሟልቶ ከቤት እንደወጣ ጓደኞቹ በቀጠሮ ስፍራው እየጠበቁት መሆኑን አውቆ ወደ ቦታው ገሰገሰ። በቦታው ሲደርሰ ከሁለቱ በቀር ደምስን ማየት አልቻለም። ወዲያው ሞባይሉን አንስቶ ደወለ። መልስ አልነበረም።
ሶስቱ ጥቂት ጠብቀውት ባልደራስ አካባቢ ወደሚገኝ መናፈሻ ዘለቁ። በሻንጣ በያዟቸው መጥረቢያዎች ስጋውን ከአጥንቱ አላቀው በስል ቢላቸው እየለዩ የጥብስ፣ የክትፎና የቁርጡን በየመልኩ መድበው ለግብዣው አዘጋጁ። ጥቂት ቆይቶ ደምስ መጣና ተቀላቀላቸው። ሰበቡን ሳይሰሙ ቀሪውን ስራ አጋሩት። በድግሱ የእንግዶቹን ፍላጎት ለመሙላት ነጫጭ ሽርጣቸውን ለብሰው ስል ቢላቸውን አዘጋጁ።
እስከ አስራ ሁለት ሰአት የዘለቀው መስተንግዶ ምሽቱን ሲጠናቀቅ መኮንን የሰሩበትን ተቀብሎ ከነጓዛቸው ከግቢው ራቁ። ጥቂት አለፍ ብለውም ከአካባቢው ግሮሰሪ ጎራ ብለው አንድ ሁለት ለማለት ተስማሙ። በዚህ መሀል ደምስ ከክፍያው የድርሻው እንዲሰጠው መወትወት ጀመረ። ሁኔታውን ያስተዋለው መኮንንም ገንዘቡን እንዳያጠፋው በሚል መቶ ብር ብቻ ሰጥቶ አሰናበተው።
ሶስቱ ባልንጀሮች ባረፉበት ግሮሰሪ ቢራ እየተጎነጩ ነው። ደምሰው ግን በተሰጠው ብር ተበሳጭቶ ከደጅ ሆኖ መነጫነጭ ጀምሯል። ይህን ያስተዋሉት ሌሎቹ ሊያሳምኑት ቢሞክሩም አልተሳካም። በዚህ መሀል ወደውጭ የወጣው መኮንንም ከደምስ ጋር ፊት ለፊት ሊጋፈጥ ተገዷል።
ወደ ሰፈር ለመመለስ ታክሲ ሲጠብቅ የነበረው ደምስ መኮንን ባየው ጊዜ ንዴቱ አገርሽቶ ጥያቄውን ደግም አነሳ። ከሻንጣው መሀል የራሱን ቢላዋ አውጥቶና በሽርጡ ጠቅልሎም ምላሹን ጠበቀ። መኮንን ሁኔታውን ባየ ጊዜ ንዴቱ ከእሱ ብሶ ገንዘቡን እንደማይሰጠው እየነገረ ቀረበው። ይህኔ ደምስ ብስጭቱ አየለ። ያለፈውን ከአሁኑ እያስታወሰም ቂም በቀሉን አመላለሰ።
በድንገት ከደምስ የተጠቀለለ ነጭ ሽርጥ ውስጥ በጨለማው ብቅ ሲል የታየው ስል ቢላዋ ማረፊያው ከመኮንን አንገት ላይ ሆነ። ደምስ እጁን ከቢለዋው ሳያነሳ ደጋግሞ ባልንጀራው አካል ላይ አሳረፈና ከመሬት ላይ ጣለው። ከወደቀበት ደርሶም ያለማቋረጥ እየወጋ መላ አካሉን ጨቀጨቀው።
ድርጊቱን ከዳር ሆነው ሲመለከቱ የነበሩ መንገደኞችና ባልንጀሮቻቸው ደምስ በቢላዋው ስላስፈራራቸው ሊቀርቡት አልቻሉም። ያሰበውን ፈጽሞ ለማምለጥ ሲሮጥ ያየው አንድ ወጣት ግን እንደሌሎቹ ጭካኔውን በድርጊት አልታዘበም። ከኋላው ተከትሎ ደረሰበትና እግሩን ዘርጥጦ ጣለው። በእጁ ያለውን ደም የነካ ቢለዋ ተቀብሎም ለህግ አሳልፎ ሰጠው።
የፖሊስ ምርመራ
ተጠርጣሪውን በህግ ቁጥጥር ስር ያዋለው ፖሊስ በምስክሮች ቃል ምርመራውን አጣራ። የደምስን ሀሳብ ተቀብሎም ቃሉን መዘገበ። በመርማሪ ኢንስፔክተር ግርማ በቀለ የተመራው ቡድንም በፋይል ቁጥር 263/06 በየዕለቱ በቂ መረጃና ከማስረጃ የሚሰፍርበትን ዶሴ አጠናከረ። ተገቢው ከስ ይመሰረትበት ዘንድም ጉዳዩን ለዓቃቤ ህግ አሳልፎ ሰጠ።
ውሳኔ
ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓ.ም የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ደምስ በለጠ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ በችሎቱ ተሰይሟል። ተከሳሹ በፈጸመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ በመሆኑም አስቀድሞ ክሱን እንዲከላከል ዕድል ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ተከሳሹ ወንጀሉን በማመኑና ይህም በበቂ የሰውና የህክምና ማስረጃዎች በመረጋገጡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ በሚታሰብ የ 16 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ አስራት እንዲቀጣ በሚል ተወስኖበታል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
መልካምስራ አፈወርቅ