
በቻይና የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ የወቅቱ መነጋገሪያ ሆኗል።በሽታው በርካታ ወገኖችን ለሞት መዳረጉና ወደተለያዩ ሀገራት በፍጥነት እየተዛመተ መምጣቱ ደግሞ በመላው የአለማችን ህዝቦች ዘንድ ከባድ ስጋት ፈጥሯል።ቫይረሱ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በግብፅ በአንድ የውጭ ሃገር ዜጋ ላይ መታየቱም በተለይ በአፍሪካ አህጉር ላይ ተጨማሪ ስጋት ደቅኗል።
ቫይረሱ በተከሰተባት በሀገረ ቻይናም ይበልጥ እንዳይስፋፋ በተለይ ቫይረሱ ይኖርባቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ዜጎች በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ እንዲቆዩ እየተደረገ ነው።ይህም ለብዙሃኑ ቻይናውያን ከባድ ውጣውረድ ቢሆንም ለአማተር የማራቶን ሯጩ ቻይናዊ ግን ባለበት ቦታ ላይ ሆኖ ልምምዱን ከመስራት አላገደውም ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ በድረገፁ አስነብቧል።
እንደ ብዙዎቹ የሀገሩ ሰዎች ሁሉ ፓን ሻንኩ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በምስራቃዊ ቻይና ዜጂያንግ ግዛት በአንድ አፓርትመንት ላይ እንዲቆዩ ከተደረጉ ቻይናውያን ውስጥ አንዱ ቢሆንም፣ በሽታው ግን በቀጣይ ሊወዳደርበት ካሰበው የአማተር የማራቶን ሩጫ ከወዲሁ አስቀድሞ የሚያደርገውን ልምምድ ከማድረግ አልገደበውም።
ሻንኩ በአፓርትመንቱ የሚኖርባትን አንዲት ጠባብ ክፍል የመሮጫ ትራክ በማድረግና ከወዲህ ወዲያ ሶምሶማ በመሮጥ 50 ኪሎ ሜትር ወይም 31 ማይል እንደሸፈነ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ለቋል። ‹‹ ለብዙ ቀናት ከክፍሌ ወጥቼ አላውቅም፤ ስለዚህ ዝም ብዬ መቀመጥ የለብኝም›› በሚል በክፍሉ ውስጥ ሶምሶማ ሩጫ እንዴት እንደጀመረ ሻንኩ ተናግሯል፡፡በሁለት ጠረጴዛዎች ዙሪያ የክፍሉን ስምንት ሜትር ርቀት ተመላልሶ ሶምሶማ በማድረግ 50 ኪሎሜትሩን በ4 ሰአት 48 ደቂቃ ከ 44 ሰከንድ መሮጥ እንደቻለ ጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም በአማተር የማራቶን ሩጫ 2 ሰአት ከ59 የራሱ ጥሩ ሰአት ያለው መሆኑን የጠቆመው ሻንኩ፤ በትንሿ ክፍል ውስጥ ሶምሶማ ሲያደርግ በተቻለው አቅም ጎረቤቶቹን ላለመረበሽ በዝግታ ሲሮጥ እንደነበረም በትስስር ገፅ ፅፏል።በዚህ ድርጊቱም በማህበራዊ ትስስር ገፅ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየ ሲሆን ያሳየው የልምምድ ስነ ምግባሩ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎለታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
አስናቀ ፀጋዬ