ኢትዮጵያ የብዙ ብሄርና ብሄረሰቦች ፣ የባህላዊ እሴቶች ፣ የቋንቋና የታሪክ ባለቤት መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤትም ነች።
ኢትዮጵያ በየማህበረሰቡ የሚከወኑ ቀደምት ባህላዊ እሴቶችና ትውፊቶች ፣ የስነ ፅሁፍ ፣ የኪነ ህንፃ፣ የሙዚቃና ሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች መገኛ ጭምር ነች ። ለዚህም ነው አገሪቱ በአንዳንድ የታሪክና የባህል ተመራማሪዎች ዘንድ «የባህል ሙዚየም» የምትባለው ።
የአገው ህዝብ በቀደምት ስልጣኔው በተለይም በስነ ህንፃ ጥበብ የሚታወቅ፣ የእርሻ ስራንና የከብት እርባታ ተግባራትን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበረከተ፣ ህግ አክባሪና ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር ተከባብሮ የመኖር እሴትን ያዳበረ፣ ሀገርንና ህዝብን መቀየር የሚቻለው በእውቀት እንደሆነ የሚያምንና ጠንካራ የስራ ባህል ያለው እንደሆነ በተለያየ አጋጣሚ ይነገራል።
የአዊ ህዝብ የብዙ ፈጠራ ውጤቶች ባለቤትና ተፈጥሮ የሰጠችውን ሀብት የሚያስተዳድርበትና ማህበራዊ ህይወቱን የሚመራበት ሀገር በቀል እውቀቶች ባለቤት መሆኑም የታሪክ ድርሳናትና ነባራዊው ሁኔታዎች ያስረዱናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ የሚኖር መሆኑም ይጠቀሳል። የአዊ ህዝብ በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ውስጥ እሱ እንዳለ ሁሉ በእሱም ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዳለ ለአፍታም የማይዘነጋ ፍጹም ኢትዮጵዊ መሆኑንም ያስመሰከረ ነው። የቀደመ አያቶቹ የሰጡትን ባህላዊ እሴቶች ያስቀጠለ ለመሆኑ ወቅታዊ አኗኗሩና ሰላሙ ገላጭ ነው። ይህ ህዝብ በርካታ ለሀገር የሚተርፉ ቅርሶች፣ ባህላዊ እሴቶች፣ ተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶችና ባህሎች ባለቤት ነው። አዊ ከባህላዊ ሥርዓቶቹ ውስጥ በዋነኝነት የሚታወቅበት የሰባት ቤት የአገው ፈረሰኞች ማህበር ትእይንት አንዱ ነው።
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች በዓል ከ1932 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በብሔረሰብ አስተዳደር በተለያዩ ወረዳዎች እየተዘዋወረ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ የሚገኝ የፈረሰኞች ባህላዊ በዓል ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዚህ በዓል አጀማመር ፈረስ በአድዋ ጦርነት ወቅት ያደረገውን አስተዋጽኦና ይህም ታሪክ እንደገና የጣሊያን ፋሽስት ወራሪ ጦር አገራችንን በወረረበት ጊዜ ባደረገው የአምስት ዓመታት የቅኝ ግዛት ሙከራ ጀግኖች አባቶች ጠላትን ድል ለማድረግ ፈረስና ፈረሰኞች ያደረጉትን የአርበኝነት ተጋድሎ ለማስታወስ ነው።
ይህ በዓል በየዓመቱ ጥር 23 የሚከበርበት ምክንያት አርበኞች በዚሁ እለት በአድዋ ጠላትን ድል ያደረጉበት በመሆኑ የጊዮርጊስን ገድል ለማሰብ ጭምር ነው። ይህ በዓል ከቀበሌ እስከ ዞን አባቶች ባቆዩለት ባህላዊ አደረጃጀት መሰረት ማህበሩ ከስድስት ሺ በላይ በሚደርሱ አመራሮች ራሱን በራሱ እየመራ ያለማንም ተጨማሪ አጋዥ በየዓመቱ ለአንድም ጊዜ ሳይቋረጥ እየተከበረ የመጣ በዓል ነው።
ይህ ባህላዊ አደረጃጀት ከዛሬ 80 ዓመት ጀምሮ ያልተማከለ አስተዳደርን እውን ማድረግ የጀመረ፣ በየአራት ዓመቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ የሚታወቅ፣ ከሃላፊነት ለሚወርዱ ሰዎች የአለቅነት ክብር በመስጠት የሚታወቅ፣ በሴቶች እኩልነት የሚያምን አንጋፋ ማህበር ነው።
ይህ ማህበር ደስታን በማድመቅ፣ ኀዘንን በመጋራት፣ በባህላዊ መንገድ ፍትህን በመስጠት፣ ኃይማኖታዊ በዓላትን በማድመቅ፣ በህዝቡ ዘንድ ወንድማማችነትን በማጠናከር፣ የእርስ በእርስ መረዳዳትና መተሳሰብን በማጎልበት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የአካባቢውና የብሄረሰብ አስተዳደሩን ብሎም የአገርን መልካም ገጽታ ለመገንባት እና ቅድመ አያቶች ያቆዩትን ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፊያነት የሚያገለግል ታሪክን፣ ባህልንና ኃይማኖትን አቀናጅቶ የያዘ በዓልና ቅርስ ነው።
“ባህላዊ ሥነ ሥርዓቱ የጥንቱን ከዛሬው ጋር የሚያስተሳስር ነው” የሚሉት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። 80ኛው ዓመት የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች በዓል ያለፈውን የኢትዮጵያን ታሪክ ከአሁኑ ጋር የሚያስተሳስር መሆኑን በፅኑ እንደሚያምኑም ያነሳሉ። ባሳለፍነው የጥር ወር ውስጥ በአዊ ዞን እንጅባራ ከተማ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት በእንግድነት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ፤ በአዊ ማህበረሰብ ታሪክ ፈረስና ፈረሰኞች ልዩ ቦታ አላቸው። በዚህ ልዩ ሥነሥርዓት ላይ መገኘት ልዩ ደስታን ይሰጣል።
“ከትናንት በጎ ታሪክ ተነስተን የነገን የበለጸገች አገር መመስረት ያስፈልጋል “ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ታላቅ ሃይል ለብልጽግናና ለአገር አንድነት ልንጠቀምበት ይገባል የሚል መልክታቸውን አስተላልፈዋል። አሁን አገሪቱ በተስፋና ስጋት ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው ፤ ጉዟችን አንድ እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ሊሆን አይገባም ሲሉም ተናግረዋል። ዛሬ የገጠመንን ፈተና በጥንቃቄ ማስተዋል እና ማየት ያስፈልጋል ብለዋል።
በክብረ በአሉ ላይ የተገኙት የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው ባስተላለፉት መልክት ፤ የምንወዳትና የምናከብራት አገራችን እስከነ ሙሉ ክብሯ የቆየችው በአባቶቻችን ተጋድሎና ትግል መሆኑን የተናገሩት አጽንኦት ሰጥተው ነው። አዲሱ ትውልድ ታሪክን አልምቶና አበልጽጎ ማቆየት ይገባዋል ፤ ለዚህ ደግሞ የአዊ ማህበረሰብ ጥሩ ተምሳሌት ነው። በተለይ የፈረስን ውለታ ሳይዘነጋ የመሰረተው ማህበር የሚያስደንቅ ነው። ፈረስ ለአዊ ማህበረሰብ የሃዘን፣ የደስታና የጀግንነት መገለጫ ነው። ማህበሩ ይበልጥ አድጎና ጎልብቶ ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍ አለበት።
ድጋግ (ጥላ)
የአዊ ህዝቦች ለኢትዮጵያ ያበረከቱት ብዙ እውቀቶች እንዳሉት በመነሻችን ላይ አንስተናል። ከዚህ ውስጥ የብሄረሰቡ ልዩ መገለጫ የሆነው የአዊ ጥላ (ድጋግ) ደግሞ ልዩ መገለጫውና ክብር ያለው ጌጥ ነው። በመሆኑም በዛሬው የባህል አምዳችን ላይ ሰፊ ዳሰሳ ልናደርግበትና ስለ ድጋግ ያልተነገሩ መረጃዎችን ልናቀብላችሁ ወደናል። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱን ጥላና የአዊ ብሄረሰብ ከባህላዊ እውቀቱና ክንዋኔው ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያለው ነው። ይህ የማህበረሰቡ ማጌጫ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍለ አገር ልዩ መገለጫ መሆኑ የሚታወቅና ለተለያዩ ሥነሥርዓቶች አገልግሎት ላይ የሚውል ነው።
ይህን አገር በቀል እውቀት በስፋት ለመተንተን ጥልቅ ጥናት እና ምርምር የሚጠይቅ ነው። ሆኖም ግን በወፍ በረር መረጃዎችን ለመስጠት እንሞክራለን። ጥላ በአዊ ብሄረሰብ የእለት ተለት ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር ጥብቅ ትስስር አለው።
ይህ ጥላ የሚሰራበት ጥሬ እቃ ቀርከሃ ሲሆን ብሄረሰቡ ተክሉን ለቤት ቁሳቁስ መስሪያ ብቻ አይገለገልበትም። ቀርከሃ ለመስቀል ችቦ፣ለህፃናት በትርፍ ጊዜ የሚጫወቱበትን እና በዝናብና በፀሃይ ጊዜ የሚከላከል ተጨማሪ ውበት የሚሆን ጥላ ይሰራበታል። አሁን ላይ ይህ ባህላዊ ጥላ በሰሌን ሳር፣ ቅጠል(ዝንጣፊ)፣ አክርማ፣ ቀርከሃ እንዲሁም ሌሎች በቀላሉ ሊሰነጠቁ የሚችሉ ቀጫጭን እንጨቶች በግብአትነት ይውላሉ።
አሰራር
የአዊ ጥላ ወይም ድጋግ የራሱ የአሰራር ጥበብ አለው። በመጀመሪያ መያዣ ዘንግ የሚሆነው ቀጭን እና ወጥ እንጨት በወፍራሙ በኩል እኩል ሆኖ ሰባት ቦታ እንዲሰነጠቅ ይደረጋል። በመቀጠል ድጋግ የሚሰሩት ባለሙያዎች ከተሰነጠቀው ዘንግ ላይ በቀጭኑ ተፍቀው ከቀርከሃ ዛፍ የተዘጋጁ ሰባት እንጨቶች መጀመሪያ በተሰነጠቀው የዘንግ ጫፍ እኩል እንዲሆኑ ይደረጋል። በጥንቃቄ እንዳይዛነፉ ጠብቀው ይታሰራሉ። የዘንጎቹ ጫፍም በተመሳሳይ ወጥ በሆነ ቀጭን የቀርከሃ ስንጣቂ በዘንጎቹ ቁጥር እኩል በአክርማ ይታሰራል።
በዚህ ሁኔታ የድጋጉ መሰረትና ቅርፅ ይዋቀራል። ከጫፍ ወደ መሀል ተሰንጥቆ በውሃ የተነከረ አክርማን እንደ ማገር በመጠቀም ከጫፍ ወደ አናቱ ወይም የጥላው የመሀልኛው ክፍል ከሰባቱ ዘንጎች በጥንቃቄ አግድም እየታሰረ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የሰሌን ቅጠል ከተደረደረው አክርማ ጋር በማዋሃድ የመለጠፍ ስራ ይሰራል። ይህን ውህድ ለመፍጠር ወስፌ እንደ መሳሪያነት የሚውል ሲሆን ይሄም የሚዘጋጀው ከቀርከሃ ነው።
የአዊ ጥላ ከውጭኛው በኩል መሃል ላይ ቆብ የሚመስል ጌጥ አለው። ይሄ የሚሰራበት የራሱ መንገድም አለ። ቆቡ የሚሰራው ከአክርማ ቅጠል የመሶብ ክዳን (ወስከንቢያ) እንዲመስል ተደርጎ ለብቻው ነው። ከዚያም የአክርማ ቀለም አልፎ አልፎ ይነከርና ውበቱን ለማጉላት እንደ መገልገያነት ይውላል።
የአዊ ጥላ ለመስራት የማህበረሰቡን ጥበብ በቅድሚያ መላበስ ያስፈልጋል። ጥላው የይድረስ ይድረስ የሚሰራና በቀላሉ የሚበላሽ አይደለም። ይሄ እንዳይሆን ደግሞ ጥንቃቄና ጥበብ ይጠይቃል። ጥላ ለመስራት ከአንድ ቀን ተኩል እስከ ሁለት ቀን ሊወስድ ይችላል።
ጥላውን ለመስራት ምንም አይነት የእድሜ የፆታ እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ገደብ የለውም። እንዲያውም ይህን የእጅ ሙያ ተክኖ የሚሰራ ባለሙያ በአዊ ባህል መሰረት የሚከበር እና የጥበብ ባለቤት ተደርጎ ይቆጠራል። ይህ ጥላ ፀሃይን ለመከላከል፣ ከዝናብ ለማምለጥ አሊያም ለውበት ጌጥ መገልገያ ብቻ ሳይሆን ከክፉ መንፈስ እንደመጠበቂያና መጠለያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በዚህ የተነሳ ድጋግ አገው ማህበረሰብ ውስጥ ልዩ ክብርና ቦታ የሚሰጠው ነው።
በሰርግ ጊዜ
በተለይ አዲስ ያገባች ሴት ከጫጉላ በወጣች ጊዜ ከቤት ወደ አማቶቿ ቤተሰቦችም ሆነ ወደ ሌሎች ዘመድ አዝማድ ዘንድ በምትሄድበት ወቅት ድጋግ ወይም የአዊ ጥላ ትይዛለች። ይሄ ድርጊት ሙሽሪትን ከተለያዩ ጎጂ መንፈሶችና ክፉ አይን ይጠብቃታል። ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም ሰው የፊት ገፅታዋን በቀላሉ እንዳያይ በማድረግ ሰዎች እርሷ ላይ ጉጉት እንዳያድርባቸው ለመከላከል ይረዳታል። በሌላ በኩል ደግሞ ሙሽሪት ይህን ጥላ ስታደርግ ከሰዎች ዘንድ ከበሬታን የምታገኝ ይሆናል።
ይህን ባህላዊ ሥርዓት የማትከውን ጥላ በሰርጓ እለት የማታደርግ እንዲሁም ፈረስ ላይ ሆና ፊቷን የማትሸፍን የአዊ ሴት በማህበረሰቡ ከበሬታን የምታጣ ይሆናል። ቤተሰቦቿም በባህሉ ሥነ ምግባር መሰረት አንፀው ስላላሳደጓት በተመሳሳይ ተወቃሽ ይሆናሉ።
የአዊ ማህበረሰብ በዛሬው ርእሳችን ላይ በስፋት ለመዳሰስ እንደሞከርነው ቀደምት ባህላዊ እሴቶችና ትውፊቶች ፣ የስነ ፅሁፍ ፣ የኪነ ህንፃ ፣ የሙዚቃና ሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች መገኛ ጭምር ነው። በተለይም የብሄረሰቡና የክልሉ ምሁራን የዚህን በዓልና ሌሎች ድንቅ የብሄረሰቡን ሀገር በቀል እውቀቶች በማጥናትና ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ አዲሱ ትውልድም ለገጽታ ግንባታ፣ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቹን መፍቻ፣ እንዲሁም የተለመደው ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ስሜቱ ሳይሸረሸር ለሀገር አንድነት እንዲጠቀምበት፣ የማድረግ ሃላፊነቱ ይኖርባቸዋል እያልን በዚሁ የዛሬውን ዳሰሳችንን እናጠናቅቃለን። ሰላም!!
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2012
ዳግም ከበደ