የአፍሪካ ህብረት ራሳቸውን “ንጉሠ ነገሥት” ብለው በሚጠሩት የቀድሞው የሊቢያ ገዥ ኮሎኔል ሙአመር አል ጋዳፊ ሃሳብ አመንጭነት እ.አ.አ መስከረም 9 ቀን 1999 በትውልድ ቀያቸው ሲርጥ ከተማ በተደረሰ ስምምነት መሰረት 55 አባል ሀገራትን በማካተት እ.አ.አ. ግንቦት 26 ቀን 2001 አዲስ አበባ ላይ የተቋቋመ አህጉር አቀፍ ህብረት ነው። ህብረቱ እ.አ.አ. በግንቦት 25 ቀን 1963 በ32 መስራች ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን /አ.አ.ድ/ ተክቷል። ድርጅቱ ከተቋቋመለት ዓላማ ቀዳሚ የሆነውን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ የአህጉሪቱን ዜጎች መብትና ነፃነት እንዲከበር ከመሥራት ይልቅ የአምባገነን መሪዎች ጠበቃና መከታ በመሆኑ ተቺዎቹ “የፈላጭ ቆራጮች ክበብ”/Dictators’ Club/ ሲሉ ይሳለቁበታል።
መቀመጫውን በጋምቢያ መዲና ባንጁ ያደረገው የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ኮሚሽን እ.አ.አ. በ1986 ሥራውን ቢጀምርም በሀገራችን በህብረቱ ዋና መቀመጫ በቀዳማዊ ትህነግ/ኢህአዴግ ለ27 ዓመታት ስለዘለቀው ዘግናኝ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያው መብት ጥሰት ጨምሮ በበርካታ ሀገራት በፅዋው ሞልተው ለፈሰሱ ግፎች ትንፍሽ አለማለቱን ስናስታውስ “የአምባገነኖች ክበብ” መባሉ አይበዛበትም።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንርሳውና የኮሎኔል ጋዳፊ አስተዋፅኦ የጎላ ነበር የሚባልለት የአፍሪካ ህብረት ሌላው ይቅርና አባት ሀገር ሊቢያ አፍንጫው ስር በቁሙ እንደ የአሽዋ ላይ ሰቀላ ሲፈራርስ አይቶ እንዳላየ አለፈ እንዳይባል ፤ አምባገነኑንና ለእረጅም ዓመታት አገዛዝ ላይ ያረጀውን የማአከላዊ አፍሪካ ፕሬዚዳንትን እና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የነበረውን ቴዎድሮስ ኦቢያን ንጉየማ ቀውሱን እንዲፈታና በሊቢያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲያመጣ መላኩ ለአፍሪካ ፣ ለምዕራባውያንና ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ስላቅ ነበር።
ህብረቱ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ አግባብ አንድም ግጭት ፈቶ አያውቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሌለን ሰላም ለማስከበር ወደ ዳርፉር ፣ ብሩንዲ ፣ ሶማሊያና ማሊ ሰላም አስከባሪ ኃይል ቢላክም ዛሬ ድረስ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን አልቻለም። በየመን፣ በሊቢያ፣ ደቡብ ሱዳንና በካሜሩን የእርስ በእርስ ግጭቶች ማስቆም ስለተሳነው የውክልና ግጭት መናኸሪያ እንደሆኑ ቀጥለዋል። ከአልጀርሱ ስምምነት በኋላ ህብረቱ ላለፉት 20 ዓመታት ዞር ብሎ ዓይቶት የማያውቀውን የኢትዮ – ኤርትራ ፍጥጫ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የሚቀሩ አንድ አንድ ነገሮች ቢኖሩም ሰላምና እርቅ ማውረድ ችለዋል፤ ውጥረቱንም አርግበዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ሳይታበዩ የሱዳን ተፎካካሪ ኃይሎችን እና ወታደራዊ ጁንታውን አቀራርቦ በማደራደር የሽግግር ስልጣን እንዲጋሩ እና ሰላም በማስፈን የማይተካ ሚና ከመጫወታቸው ባሻገር በሱማሊያና ኬንያ ፣ በኤርትራና በጅቡቲ እና በሌሎች ሀገራት መካከልም ሰላም እንዲወርድ ጥረት አድርገዋል። ምዕራባውያንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኖቤል የሰላም አሸናፊና ተሸላሚ በማድረግ ለጥረታቸው እውቅና ከመስጠት ባሻገር የበለጠ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግል ተነሳሽነትም ሆነ እንደ ኢጋድ ግጭቶችን በውይይት ፣ በድርድር መፍታት እንደሚቻል በአጭር ጊዜ የሄዱበትን እርቀት ስንመለከት ህብረቱ የሚጠበቅበትን ያህል አለመሥራቱን ያሳያል። ስድስት አስርት ዓመታትን ሊደፍን በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት የቀረው አ.አ.ድ / የአፍሪካ ህብረትን / 14 ዓላማዎች ቢኖሩትም የጋዜጣው አምድ ስለማይበቃ ዋና ዋናዎቹን ከእነ አፈፃፀማቸው እንመልከት፦
1ኛ. በሀገራትና በሕዝቦች መካከል የበለጠ መቀራረብ፣ወንድማማችነትና አንድነት መፍጠር፤ ይህን ዓላማ ከአውሮፓ ሕብረት እንዳለ የተገለበጠና ከወረቀት አልፎ እውን ሊሆን ሊተገበር የማይችል ሲሉ ልሒቃን ያጣጥሉታል። 55 ሀገራትንና ከ2 ሺህ በላይ ጎሳዎችን ይዞ ወደ ወንድማማችነት በመጨረሻም የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ አንድነት ፈጥሮ የተባበሩት የአፍሪካ ህብረት / United States of Africa ፡ USA / እውን የማድረግ ጉዳይ ፍጹም የሚታሰብ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።
ጋናዊው ጆርጅ አይቴ የውጭ ግንኙነትና ዓለምአቀፍ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስቶ በመሞገትና በመተንተን በሚታወቀው ፎሪን ፖሊሲ መፅሔት ” Disband the African Union ” በሚል ርዕስ ሞጋች ሳይሆን ቀጭን ትዕዛዝ ባስተላለፈ ጽሑፉ ፤ “ህብረቱ ጠንካራ የሆነውን ማዕከላዊነት ማላላት በአንጻሩ ደካማ አደረጃጀቱን ማጠናከር አለበት። አባል ለመሆን ግልጽና ጠንካራ መስፈርት ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ሀገራቱ ቢያንስ ዴሞክራሲያዊ፣ በነፃ ገበያና ንግድ፣ በነፃ ተቋማት የሚያምኑ ሊሆኑ ይገባል።
የሀገራቱ ቁጥርም ከ15 ሊበልጡ አይገባም። ሪፎርሙ ፣ማሻሻያው መሳካቱና ውጤታማ መሆኑ ሲረጋገጥ ህብረቱ በሒደት ተጨማሪ ሀገራትን በአባልነት እያቀፈ ይሄዳል። በሀገራቱ መካከል የሚኖረው ግንኙነትም በግልፅ የጋራ ራዕይ ላይ የተመሰረተና በኮንፌደሬሽን የሚመራ መሆን አለበት። ሀገራቱ ደግሞ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ወደ ታች በሚወርድ ቀጭን ትዕዛዝ ሳይሆን የሚመሩት በግልፅ በተሳተፉበት እና ባፀደቁት ዕቅድ መሆን ይጠበቅበታል።
አሁን ያለው ህብረት ግን ወደ መሬት ሊወርድና ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል እየተመለከትነው እንገኛለን። “የህብረቱ ሪፎርም ፣ እ.አ.አ. በ2020 ተኩስ የማይሰማባት አፍሪካ ፣ አዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት / ኔፓድ /እ. አ. አ 2001 ላይ ይፋ ቢሆንም የበላው ጅብ ዛሬ ድረስ አልጮኸም። ጆርጅ ህብረቱ የራሱን ቢሮ መገንባት አለመቻሉ የውድቀቱ ማሳያ ነው ሲል ይሞግታል። አይደለም የህብረቱ አባል ሀገራት 9 ቢሊዮን ዶላር በሙስና አካብተዋል የሚባሉት የቀድሞው የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ወይም የአንጎላው ፕሬዚዳንት ሴት ልጅና 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር እንደመዘበረች የሚነገርላት ኢዛቤል ዶስ ሳንቶስ በግላቸው ሊገነቡት ይችል ነበር ሲል ይሳለቃል።
ይህን መጣጥፍ እየጫርሁ እያለ ኢዛቤል ላይ የሙስና ክስ መከፈቱን ከእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ቢቢሲ ሰምቻለሁ። አንድ ቀን የእኛዎቹ የቀን ጅቦች ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥማቸዋል ብዬ አምናለሁ።
2ኛ. ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ፣ መርህንና መልካም አስተዳደር ማበረታታት፤ ቀዳማዊ ትህነግ/ኢህአዴግ ብቸኛ ተመራጭም መራጭም ሆኖ አሸነፍሁ ላላቸው አምስቱም ምርጫዎች፤ ህብረቱ ነፃ ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማለት እውቅና፣ ቡራኬ ሲሰጥ የቀደመው አልነበረም። የእኛን ሀገር አስቀደምሁ እንጂ ህብረቱ በአሁጉሩ “ነፃ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ” ያላለው ምርጫ የለም ማለት ይቻላል። ለዚህ ነው ተቺዎቹ የቀረቡለትን የምርጫ ውጤት ሁሉ ወዲያውኑ ሳይመረምር ስለሚያረጋግጥ “ራበር ስታምፕ” ሲሉ ቅፅል የሰጡት።
ጆርጅ ከፍ ብዬ በጠቀስሁት መጣጥፉ ፤ ” … ህብረቱ ሌላው ይቅርና ዛሬ ድረስ በዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ትርጉም ላይ እንኳ መግባባት አልቻለም። …” ይላል።
3ኛ. በአህጉሩ ሰላምን፣ ደህንነትንና መረጋጋትን ማስፈን፤ ይህ የህብረቱ ዓላማ አይደለም ሊሳካ ተባብሷል።
“በ2020 የተኩስ ድምፅ የማይሰማበት አህጉር ” እውን ለማድረግ ከ10 ዓመት በፊት የጣለው ግብ ከሽፏል። ግቡ ሲጣል ግጭት የነበረበቸው ሀገራት ቁጥር ከ10 ያልበለጡ ነበሩ። ዛሬ ላይ ግጭት ውስጥ ያሉ ሀገራት ቁጥር 20 ደርሷል። እነ ሊቢያን፣ የመንን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ማሊ፣ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
4ኛ. የሰብዓዊና የሕዝቦችን መብቶች በቻርተሩ መሰረት ማስከበር፤ ህብረቱ የዜጎች፣ የሕዝቦች ሰብዓዊ መብት በአምባገነኖች ሲጨፈለቅ፣ ሲጣስ ጥብቅና ይቆም የነበረው ለአምባገነኖች ነው። ኦማር አልበሽር በተለይ በዳርፉር በጦራቸውና ጃንጃ ዊይድ በተባለ ሚሊሽያ ዘግናኝ ግፍ ሲፈፀም ትንፍሽ አለማለቱ ሲያሳዝነን ዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ሲመሰርትባቸው ተላልፈው እንዳይሰጡ ሽንጡን ገትሮ ከመከራከር አልፎ ፤ ሀገራት ከዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲወጡ ግፊት ሲያደርግ ነበር። ይህን መጣጥፍ እያጠናቀርሁ እያለ ኦማር አልበሽር ለፍርድ ቤቱ ተላልፈው ሊሰጡ እንደሆነ ከቢቢሲ ስሰማ የተሰማኝን ደስታ አልደብቃችሁም።
እንደ መውጫ በዓለማችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ እንጉዳይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው ሕዝበኝነት /populism/፣ ቀኝ ዘመምነትና አክራሪነት አህጉር አቀፍ እና ድንበር ዘለል ትብብሮችን እያዳከመ ነው። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከ70 ዓመታት በላይ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና የነበራቸው እነ አውሮፓ ህብረትና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን /ኔቶ /ችላ እየተባሉ ነው። በተለይ “አሜሪካ ትቅደም!” የሚል ሕዝበኛ መፈክር አንግበው ወደስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት፣ በአውሮፓ ሕብረት፣ በኔቶ እና በሌሎች መሰል ስብስቦች ላይ የሚከተሉት የተንሸዋረረ አመለካከት ከፍተኛ ስጋት በመፍጠር ላይ ነው።
የኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂው ዓለምን ወደ ትንሽ መንደርነት እየቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት አክራሪ ብሔርተኞችና ሕዝበኞች ደግሞ መለየትን ፣ መነጠልን እየለፈፉ ዓለምን ግራ እያጋቡ ይገኛል። እንግሊዝ በእነ ትራምፕ አይዞሽ ባይነት ከሕብረቱ መነጠሏ እና በፈረንሳይ፣ በጣሊያንና በምሥራቅ አውሮፓ አክራሪ ብሔርተኝነት እየተጠናከረ መምጣቱ ሌላ ስጋት ሆኖ ብቅ ብሏል። ሩሲያም ሕብረቱም ሆነ ኔቶ እንዲዳከሙ ሌት ተቀን እያሻጠረች ነው። ይህ በአህጉር አቀፍ ስብስቦችና ተቋማት ላይ ጀንበር እያዘቀዘቀች መሆኑን ያሳያል። የአፍሪካ ሕብረት ፣ የእስያን ፣ የብሪክስ ፣ የላቲን አሜሪካ ስብስቦች ዕጣ ፈንታም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ፍንጭ የሚሰጥ ነው።
ወደ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ እሱን ወደ ተካው የአፍሪካ ሕብረት ስንመጣ ከውጫዊ ፈተናዎቹ ይልቅ ውስጣዊ ችግሮቹ የከፉ ሆነው እናገኛቸዋለን። አራምደዋለሁ የሚለው በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት አቋም ለችግሩ አንዱ መግፍኤ ነው። ተግዳሮቱ የዴሞክራሲ ተስፋ የሚታይባቸውን ሀገራት እና አምባገነናዊ አገዛዞችን ያለ አንዳች ልዩነት አግበስብሶ የሚጓዝ መሆኑ ነው። የሕብረቱ አባል ለመሆን ምንም ዓይነት መስፈርት አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል።
ዘመኑንም ሆነ ትውልዱን ታሳቢ ያደረገ አሠራርና አደረጃጀት የለውም። ከአህጉሩ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ከሚበልጠው ሕዝብ ውስጥ አብላጫው ወጣት ቢሆንም እሱን ተጠቃሚ ያደረጉ የትምህርትና ስልጠና ፣ የብድር አገልግሎትና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ግንባታ አለማመቻቸቱ ፤ ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች ላይ አለመንቀሳቀሱ ፤ ወጣቱን ወደ አመራርነት የሚያመጡ ሥራዎችን አለማከናወኑ ፤ የወጣቱ መሰረታዊ ጥያቄ እየሆኑ የመጡት የዴሞክራሲና የነፃነት ጥያቄዎች ላይ እግሩን የሚጎትት መሆኑ በነቃፊዎቹ ዘንድ ዘመኑንም ሆነ ትውልዱን የማይዋጅ ስብስብ በሚል ይወቀሳል። አፍሪካንና አፍሪካውያንን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ! አሜን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳይን )
fenot1971@gmail.com