ርዕሱ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ መቀመጡን ልብ ይሏል። የጥያቄው ምልክትም ሆነ በግራና በቀኝ ርዕሱን ያቀፉት ትምህርተ ጥቅሶች አገልግሎት ላይ የዋሉበት ዋና ምክንያት የርዕሱ ይዘት አወዛጋቢና አጠያያቂ ባህርይ ስለሚስተዋልበት ነው። ሌሎች እህትና ወንድም የአህጉራችን ሀገራት አፍሪካዊ ኬንያ፣ አፍሪካዊ ጋና፣ አፍሪካዊ ዛምቢያ፣ አፍሪካዊ ሞሮኮ ወዘተ. እየተባሉ ስለማይጠሩ በእኛይቱም ኢትዮጵያ ላይ «የአፍሪካዊነት» ቅጽል አክሎ መጥራቱ አግባብነት የሌለው ስለመሆኑ ከአንባቢያን የተሰወረ አይደለም። አሁንም «ለምን?» ብለን ብንጠይቅ ሌላ መሰል አውሮፓዊት ኢትዮጵያ፣ አሜሪካዊ ኬንያ፣ ላቲን አሜሪካዊ ጋና፣ ኖርዲካዊ ደቡብ አፍሪካ የሚባሉ ሌሎች ሀገራት ስለሌሉ ሀገራትን በአፍሪካዊነት ቅጽል ማጎላመሱ እጅግም አስፈላጊነቱ ረብ ስለሌለው ነው።
የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት አፍሪካዊነት በፍጹም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም፣ በተለምዶም ይሁን በአሉ ተባባሉ አፋዊ ቅብብሎሽ በብዙ ባዕዳን ዜጎች አንደበት «ኢትዮጵያውያን በአፍሪካዊነታቸው አያምኑም። ራሳቸውንም አፍሪካዊ ነኝ ብለው ለማስተዋወቅ አይደፍሩም» እየተባለ አዘውትሮ ሲነገርና ሲደመጥ ይስተዋላል።
በውጭ ሀገራት በሥልጠናና በትምህርት ላይ በነበርኩባቸው ዓመታት ያሰለቹኝ ከነበሩ ክርክሮችና የእሰጥ አገባ ሙግቶች መካከል አንዱ ጉዳይ «እናንተ ኢትዮጵያውያን የጥቁር አፍሪካዊነት ኩራት የላችሁም። ከአፍሪካዊነት ይልቅ ራሳችሁን የተሻለ አድርጋችሁ ለመቁጠርና ጥቁር አፍሪካውያን አይደለንም ለማለትም ራሳችሁን ከእስራኤል ጋር ማቆራኘቱን ትመርጣላችሁ» የሚሉ ዓይነት ሃሜቶች ይሰነዘሩልኝ ነበር።
ምናችን ከእስራኤል ጋር እንደተቆራኘ እንዲያስረዱኝ ሞጋቾቼን በምርም ሆነ በቀልድ የእኔን ደማቅ ጠይምነትና ተክለ ሰውነት ለምስክርነት እያቀረብኩ አበክሬ ብሟገታቸውም የሚሰጡኝ ማሳመኛ በአብዛኛው ከታሪካችንና ከሃይማኖታዊ ጉዳዮቻችን ጋር የተያያዙ እንደነበሩ ለመረዳት ችያለሁ። የመጀመሪያው መከራከሪያቸው በክርስቲያናዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለ እስራኤልና ስለ ኢትዮጵያ የተጠቀሱ በርካታ ታሪኮችን በመምዘዝ ሲሆን ሁለተኛው መከራከሪያቸው ደግሞ የነገሥታቶቻችንን «የሞአ አንበሳ ዘእምነ ነገደ ይሁዳ» ሥርዎ መንግሥት በማጣቀስ ነበር።
እንዲያውም ኢትዮጵያን በሚገባ የሚያውቅ አንድ አፍሪካዊ የኮሌጅ ጓደኛዬና አሜሪካዊ ወዳጄ በክርክር ሰቅዘው ይይዙኝ የነበረው ማስረጃችን የሚሏቸውን ጉዳዮች እንደሚከተለው እየጠቃቀሱ ነበር። «የሀገራችሁ በርካታ ከተሞች ሳይቀሩ የወረሱት የእስራኤልን ከተሞች ስሞችና አካባቢዎችን ነው። ለምሳሌ፤ ደብረ ዘይት፣ ናዝሬት፣ ገሊላ ቀራኒዮ ወዘተ. የሚሉት እንዴትና ለምን ሊሰየሙ ቻሉ?» የሙግታቸው መንደርደሪያ ነበር። «ብዙውን ጊዜ ለልጆቻችሁ የምትሰጡት ስምም ናትናኤል፣ ኢዮኤል፣ ሐና፣ ማርቆስ፣ ዮሐንስ ወዘተ. የሚሉ እስራኤላዊ ስሞችን ነው።» «ለምን?» እያሉ የሚወረውሯቸው ጥያቄዎች ማቆሚያ አልነበራቸውም።
«እናንተም ሀገር እኮ ጀምስ፣ ጆን፣ ሐና፣ ማርክ የሚባሉ ስሞች ሞልተዋል፤ ለምን የእኛን ብቻ ታዳምቃላችሁ። በአሜሪካ ግዛቶች ውስጥም በርካታ አካባቢዎች የእስራኤላውያንን የአካባቢ ስያሜዎች ወርሰው ይጠሩባቸዋል፤ የእኛን ብቻ ለምን ትነቅፋላችሁ?» ብዬ ስሞግታቸው «እኛን ከእናንተ የረዢም ዘመናት ታሪክ ጋር አታነጻጽሩ። እኛ አኮ በቅኝ ግዛት ስንደበደብና ገዢዎቻችን እንደፈለጉ ሲያደርጉን የኖርን ሀገራት ነን። እናንተ ግን የነፃነትን ክብርና ዋጋ በሚገባ እያጣጣማችሁ የኖራችሁ ሕዝቦች ናችሁ። ቋንቋችሁም ሆነ ባህላችሁ የራሳችሁና በራሳችሁ ጥበቃ ሥር ስለኖሩ ልትኮሩባቸው ይገባል።» የሚል ዓይነት መልስ ይሰጡኝ ነበር።
ከአንድ አሥርት ዓመት በፊትም ይህ ጸሐፊ በተገኘበትና በሊቢያ ሲርት ከተማ በተካሄደ አንድ የአፍሪካ ምሁራን ጉባዔ ላይ በርካታ የጥናት ወረቀቶች መቅረባቸው ትዝ ይለኛል። የጉባዔው ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ቀድሞው የሊቢያ መሪ ወደ ኮሎኔል ሞሐመድ ጋዳፊ ሀገር እንዲዘዋወር ለማግባባትና ተሰብሳቢውን ለማሳመን ነበር። አዲስ አበባ ለኅብረቱ መቀመጫነት ልትመጥን እንደማትችል ከዘረዘሯቸው የመሠረተ ልማት ጉድለቶችና የማሕበራዊ ህፀፆች በተጨማሪነትም ምሁራን ነን ባዮቹ ጉባዔተኞች በአብዛኛው እንደ ሁለተኛ ቅሬታ የጠቀሱት «የኢትዮጵያውያንን አፍሪካዊነት እንጠራጠራለን» የሚል ክብረ ነክና እርባና ቢስ ምክንያት ነው።
ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የ«ይሉናል» ሃሜቶችና መከራከሪያዎች ትርጉም አልባ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ጥርጣሬው እውነትም ሆነ ሀሰት «ለምን የአፍሪካዊነት ስሜት የላቸውም ልንባል ቻልን?» ብሎ ራስን መመርመሩ ግን አግባብነት እንዳለው ማስገንዘቡ አይከፋም። እርግጥ ነው የአፍሪካዊነታችን ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ባይሆንም፣ በማወቅም ሆነ ባለማስተዋል ብዙዎቻችን «እኔ አፍሪካዊ ነኝ» ብለን በአደባባይ በኩራት ለመናገር አንዳንዴ ሲተናነቀን ይስተዋላል። እንዲያውም ብዙ ጊዜያት ስለ አፍሪካውያንና ስለ «እማማ አፍሪካችን» ስንናገር ራሳችንን ሩቅ ቦታ አቁመን «እነሱ» እያልን ነው። እውነቱን ብንገልጥ ወደ ቀልባችን ለመመለስ ሊያግዘን ስለሚችል ጠንከር ብሎ ራሳችንን መኄሱ ጉዳት የለውም።
እውነታው!
ኢትዮጵያም ሆነች እኛ ልጆቿ እውነተኛ አፍካውያን መሆናችን በወዳጆችም ሆነ በጠላቶች ዘንድ የተረጋገጠ ነው። ለዚህ እውነታ ምስክር መጠራት ያለብን አይመስለኝም። እርግጥ ነው በረጂሙ የታሪካችን ምዕራፎች ውስጥ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በንግድና በባህል መስኮች ከአፍሪካ ውጪ ካሉ ሀገራትና ሕዝቦች ጋር ግንኙነት ፈጥረን ስለነበር ታሪካችን ከእነዚያ ሕዝቦችና ሀገራት ጋር በብዙ መልኩ ተጋምዶ ሊሆን ይችላል። ይሄ ማለት ግን የአፍሪካዊነታችን ማንነትና ክብር ተሸርሽሯል ወይንም ይሸረሸራል ማለት አይደለም። በፍጹም።
እንደየትኞቹም ወንድም የአፍሪካ ሀገራት ቅኝ ገዢ ወራሪዎች ሀገራችንን በተደጋጋሚ ትንኮሳና ጦርነቶች ለማንበርከክ ሙከራ ማድረጋቸው አልቀረም። ክብር ለጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን ይሁንና ጦርነቶቹን በሙሉ የተወጣናቸው በድል አድራጊነት፤ አንድም ጊዜ እጅ ለመስጠት አልዳዳንም። ብዙ አፍሪካዊ ሀገራት በቅኝ ግዛት ሥር ወድቀው መማቀቃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በዜጎቻቸው ላይ የደረሰው የሞራል፣ የሥነ ልቦና ቀውስና የታሪክ መዛባት ግን በቀላሉ ታጥቦ ሊወገድ አልቻለም። ይህንን እንደ ጓል የጠጠረ እውነታ በቀላሉ ፈረካክሶ ለመተንተን የጋዜጣው የአርብ ጥበትና አንዳንድ አይደፈሬ ምክንያቶች ባይገድቡን ኖሮ ብዙ ማለት ይቻል ነበር።
በረጅምና በአጫጭር ልቦለዶች፣ በቴያትርና በወግ ሥነ ጽሑፎቻቸውና በማሕበራዊ ኃያሲነታቸው ትልቅ የዝናና የተቀባይነት ማማ ላይ ደርሰው ከነበሩት ከአንጋፋው ኬንያዊ ደራሲ ጀምስ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ጋር እዚህ አዲስ አበባ በኢጣሊያ የባህል ማዕከል ውስጥ በተዘጋጀ አንድ ፕሮግራም ላይ ለመታደም መጥተው በነበረበት ወቅት የተወሰንን የሀገራችን ደራስያን በግላጭ አግኝተናቸው በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለመጨዋወት ዕድል አግኝተን ነበር።
ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ንግግራቸውን የጀመሩት፤ «እናንተ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ውስጥ ያላችሁን የከበረ ሥፍራ በሚገባ ተገንዝባችኋል? የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት መሆናችሁንስ ታውቁት ይሆን ወይ? ነባር ቋንቋዎቻችሁና ባህሎቻችሁ እናንተን ብቻ ሳይሆን እኛንም ያኮሩናል። እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ደራስያን በአብዛኛው የምትጽፉት ድንበር ተሻግሮ በሚያግባባን የጋራ ቋንቋ ሳይሆን በራሳችሁ ቋንቋ ገድባችሁ ነው። ስለዚህም እኛ አፍሪካውያን ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ የፈጠራ ጽሑፎቻችሁን ውበትና ድምቀቱን ልናጣጥም አልቻልንም። በራሳችሁ ቋንቋ መጻፋችሁ ለእናንተ የክብራችሁ መገለጫ ቢሆንም እኛን አፍሪካውያን ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን እንደበደላችሁን ግን ልታውቁት ይገባል። እኔና ሌሎች በርካታ አፍሪካውያን ደራስያን በአብዛኛው የምንጽፈው በቅኝ ገዢዎቻችን ቋንቋዎች ነው። አይደለም ሥነ ጽሑፋችን ባህሎቻችንና ስሞቻችንም ሳይቀሩ ዛሬም ድረስ ከቅኝ ግዛት ተጽእኖ ሊላቀቁ አልቻሉም። ለምሳሌ፤ የእኔ ስም የሚጀምረው ‹ጀምስ› የሚል የቅኝ ገዢዎቻችን ስም ታክሎበት ነው። ስጽፍ የኖርኩትም በእነርሱ ቋንቋ ነው። ከዚህ በኋላ ግን ስሜንም ሆነ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቼን ነፃ አውጥቼ አፍሪካዊነቴን አረጋግጣለሁ።» ዝርዝሩን ያቀረብኩት መጥኜ ቢሆንም በንግግራቸው ውስጥ የታጨቁትን እውነታዎች አንባቢያን እየመዘዙ እንዲተነትኗቸው አሳስቤ ማለፍ እወዳለሁ።
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን የመሰሉ ቀደምት የአፍሪካ ባለ ርዕይ መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በ1955 ዓ.ም ያቋቋሙት በእውነተኛ የአፍሪካዊ ልጅነት ስሜትና ቁጭት ነበር። «ነብይ በሀገሩ አይከበርም» እንዲሉ በሚያኮራው ታሪካችን አፍረን፣ በክብር ከፍ ማድረግ የሚገባንን የንጉሡን ስብዕና አርክሰን እንደምን እያዋረድናቸው ዓመታትን እንዳስቆጠርን ልባችንም ታሪካችንም በተሰበረ መንፈስ ይመሰክሩብናል።
የአፍሪካ ሀገራትን ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ለማውጣት በተደረገው የሞት የሽረት ትንቅንቅ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የታገሉት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ብቻ ነበሩ ማለት እንዳልሆነ ግን ሊሰመርበት ይገባል። የጋናው ክዋሚ ንክሩሁማ፣ የታንዛኒያው ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የጊኒው ሴኩ ቱሬ፣ የዛምቢያው ኬኔዝ ካውንዳ፣ የኬንያው ጆሞ ኬኒያታ (ጥቂቶቹን የአፍሪካ አባቶች ብቻ ነው ያስታወስኩት) ወዘተ. ያደረጉት የጋራ ተጋድሎ በፍፁም በትውልዶችና በታሪክ ፊት የሚዘነጋ አይደለም።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ብልህነትና ማስተዋል በተሞላበት ጥበብ ከፈጸሟቸው ተግባራት መካከል አንዱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በአዲስ አበባ ከተማ እንዲቋቋም ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አይዲዮሎጂ ይከተሉ የነበሩ ሀገራትንና ቂም የቋጠሩ ደመኞችን ማቀራረብና ማሸማገል መቻላቸው በራሱ ታሪክ ጮክ ብሎ ሊዘምርለት የሚገባው ዐብይ ጉዳይ ነበር።
በወቅቱ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በዋናነት ተከፋፍለው የተቧደኑባቸው ጎራዎች (Ideological blocs) ሦስት ያህል ነበሩ። የካዛብላንካ ጎራ ይባሉ የነበሩት ሀገራት ጋና፣ ጊኒ፣ ማሊ፣ ሊቢያ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮና አልጄሪያ ሲሆኑ እነዚህ ሀገራት በወቅቱ ሲያቀነቅኑ የነበረው ፍልስፍና ሥር ነቀል በሆነ ውህደትና ትሥሥር በፍጥነት የአፍሪካ ሀገራት ወደ አንድነት መምጣት አለባቸው የሚል ነበር።
በአንጻሩ የሞንሮቪያ ጎራ በሚል ስያሜ የተቧደኑት የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ ናይጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ቶጎና ሶማሊያ ሲሆኑ ያራምዱት የነበረው አቋም «የአፍሪካ ሀገራት ወደ ውህደት ሊመጡ የሚችሉት ቀስ በቀስና በጊዜ ሂደት እንጂ ‹ዛሬ፤ አሁን› ብለን መወሰን አይገባንም» የሚል ነበር።
በሦስተኛው ጎራ የተሰለፉት የብራዛቪል ጎራ ይባሉ የነበሩት ሀገራት አብዛኛዎቹ የፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራት ሲሆኑ፣ አስተባባሪያቸውም ሴኔጋልና አይቮሪኮስት ነበሩ። በዚህ ጎራ ስር የተሰለፉት ሀገራት ያራምዱት የነበረው የፈረንሳይን አቋም ነበር።
ውስብስቡንና ድብልቅልቁን የጎራዎች አቋም ይበልጥ አወሳስቦትና ለጥርጣሬ ጥሎት የነበረው ክዋሚ ንክሩሁማ «የተባበሩት የአፍሪካ ሀገራት» (United States of Africa) በአስቸኳይ መመስረት አለበት የሚለው ምክረ ሃሳብ ነበር። ይህንን የንክሩሁማ ሃሳብ በተመለከተ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ሉዓላዊነታችንን ይጋፋል እያሉ በጥብቅ ይቃወሙ ስለነበር ፈተናው ቀላል አልነበረም።
የሀገራችን መሪ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እኒህን መሰል አንዱ ከአንደኛው የሚቃረኑባቸውን ፍልስፍናዎች አስክነውና አርግበው የየሀገራቱን መሪዎች በማቀራረብና በመሸምገል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ያደረጉት ጥረት በእጅጉ ለአፍሪካዊነት ያላቸውን ጽኑ እምነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
«አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ» የሚለው አገላለጽ በግሌ አይስማማኝም። ለምን ቢሉ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት አሜሪካዊት ወይንም ላቲናዊት ኢትዮጵያ ተብላ የምትጠራ ሌላ ኢትዮጵያ ስለሌለች ነው። አንዳንዴ የቋንቋ አጠቃቀማችንና ግላዊ አመለካከታችን ሌሎች ሰዎችን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜና አቋም ሊመራ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም። ከአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ውጪ ምንም የውጭ ዜጋ በሌለበት ጉባዔ ውስጥ እንኳ ሆነን ራሳችንን ነጥለን «እርሱ ወይንም እርሷ አፍሪካዊ/ት» ናቸው ብለን ስንናገር ሌሎችን ሊያስከፋ መቻሉ ብቻ ሳይሆን ለእኛም አይጠቅመንም።
ስለ ኢትዮጵያ የሚነገሩና የሚታመኑ አንዳንድ አመለካከቶች ሙሉ ለሙሉ ይጠፋሉ ለማለት ባይቻልም፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሀገራችንን የሚመለከቱት በተለየ ፍቅርና አክብሮት ነው። ብዙዎቹ ሀገራት እኛ ለመጠቀም በማንደፍረው ገለጻ «ኢትዮጵያ የወደፊቷ አፍሪካ ተስፋ ነች!» እያሉ ሲናገሩ በኩራት እንጂ ተሸማቀው አይደለም። በተለይም በአሁኑ ጊዜ «ኢትዮጵያ ለብዙ መልካም ተሞክሮዎች በጉጉት እየተጠበቀች ነው!» የሚሉ ድምፆች እየተበራከቱ ነው።
«በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል» እንዳይሆንብን ምትክ የሌላትን ሀገራችንን ቆም ብለን በግል፣ በቡድንና እንደ ሀገር ራሳችንን ልንፈትሽ ይገባል። ነገሮቻችን ሁሉ በጨለምተኝነት ከታዩ ለሽንፈት ይዳርጉን ካልሆነ በስተቀር አይጠቅሙንም። ኢትዮጵያ ኩሩ አፍሪካዊት ሀገር ነች። እኛም ዜጎቿ የእማማ አፍሪካ ዜጎች ነን። ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com