ሰሞነ ሕማማት የትህትናው ሳምንት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰባት አይነት አጽዋማት አሉ:: ከሰባቱ አጽዋማት መካከል ዐብይ ወይም ሁዳዴ ጾም አንጋፋና በታላቅነቱ የሚታወቅ ትልቅ ጾም ነው:: ዐብይ ማለት ትልቅ ወይም ዋና ማለት ሲሆን፤ ሁዳዴ ደግሞ ሁዳድ ከሚለው ግስ የመጣ ነው:: ሁዳድ ማለት ሰፊ እርሻ ማለት እንደሆነ የቤተክህነት መምህራን ያስተምራሉ:: ሕዝበ ክርስትያኑም እራሱን ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከክፉ ነገሮች ሁሉ ቆጥቦ ከሁዳዱ ወይም ከሰፊው እርሻ የበዛ በረከትን ለማግኘት በየዓመቱ ዐብይ ጾምን ይጾማል::

ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዓመቱ በጉጉትና በስስት የሚጠብቀው ይህ የዐብይ ወይም ሁዳዴ ጾም ለ40 ቀናት የሚጾም ነው:: ጾሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው:: ዘንድሮም በተመሳሳይ ሕዝበ ክርስትያኑ የዐብይ ወይም ሁዳዴ ጾምን በመጾም ከሰፊው እርሻ ዘላቂ ሰላምን ለኢትጵያ ሀገራችን፤ አንድነትና ፍቅርን ለመላው ሕዝባችን ሲለማመን ሰነባብቷል:: ጾሙ ሰባት ሳምንታትን አሳልፎ እነሆ ከስምንተኛው ሳምንት ደርሷል:: ስምንተኛው ሳምንት ደግሞ ሰሞነ ህማማት የትህትናው ሳምንት በመባል ይታወቃል::

ሕማማት የሚለው ቃል ሐመመ ወይም ሐመ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን፤ ሲበዛ በብዙ ቁጥር ሲነገር ሕማማት ይሆናል:: ይህም መከራ ስቃይ ማለት ሲሆን፤ ሰሙነ ሕማማት ማለት የሕማማት ሳምንት ማለት ነው:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለበትን እና እንግልት የተፈራረቀበትን ሳምንት ሰሞነ ሕማማት በማለት በየዓመቱ ታስባለች:: ቤተክርስቲያን ሰሞነ ህማማትን በጾምና በጸሎት ማሰብ እንደሚገባ ታስተምራለች:: ጾምን ጾመው ሕዝበ ክርስትያኑ እንዲጾም አርአያ ሆነው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው::

ሕዝበ ክርስቲያኑም ይህንኑ አርአያ በመከተል ሳምንቱን ማለትም ሰሞነ ሕማማት በሚታሰብባቸው ስድስት ቀናት ከምግብና ውሃ ርቀው፤ ከደስታና ከጨዋታ ተለይተው በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ሕማሙንና ሞቱን ያስባሉ:: ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ሁሉ ከዳቢሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት በፈቃዱ የተቀበላቸውን ፅዋተ መከራዎች የሚታሰቡበት በሰሞነ ሕማማት በትህትናው ሳምንት ነው::

እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች የጌታን መከራና ስቃይ የሚያስቡት በዓመት አንድ ጊዜ በሰሞነ ሕማማት ብቻ አይደለም:: በተለያዩ አጽዋማት፣ ስርዓቶችና አስተምህሮዎች እንጂ፤ ለአብነትም ከሳምንቱ ቀናት ረቡዕ እና ዓርብን መጾማቸው አንድ ማሳያ ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ብሎ የተቀበለውን መከራ ማለትም ረቡዕ ሊሰቅሉት የመከሩበትን ዓርብ የሰቀሉበትን በማሰብ ነው::

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መዝሙር ሲዘመር ከበሮ መምታትን ጨምሮ ማሸብሸብና ማጨብጨብ የጌታን መንገላታትና በጥፊ መመታቱን በማሰብ እንደሆነ ቤተክርስቲያን ታስተምራለች:: ወረቡም እንዲሁ አምላክ ከተቀበለው መከራ ጋር የተያያዥነት አለው::

ንዋየ ቅድሳቱ ከበሮ ራሱ በአሠራሩ እላዩ ላይ ያለው ጨርቅ ያለበሱትን ቀይ ከለሜዳ ጨርቅ፣ በላዩ ላይ ያለው ጠፈር ደግሞ ሲገርፉት በሰውነቱ ላይ የወጣው ሰንበር ምሳሌ ነው የአንገታችን ማዕተብ ክርም ጌታ የታሰረበትን ገመድ ለማሰብ ነው:: ካህናት ለአገልግሎት ሲሰየሙ የሚለብሱት ልብስ ከፊትና ከኋላ ያለው መርገፍ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደታሠረ እንዴት እንደተጎተተ የሚያሳይ ነው:: ሌላው ቀርቶ አንድ ክርስቲያን በቀን እንዲጸልይባቸው የታዘዙት ሰባቱ ጊዜያት ማለትም 12 ሰዓት፣ 3 ሰዓት፣ 6 ሰዓት፣ 9 ሰዓት፣ 11 ሰዓት፣ ምሽት 3 ሰዓትና ምሽት 6 ሰዓት ሁሉም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ ዓርብ ከተፈጸመበት ግፍና መከራ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው::

ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ይህን በጎ ተግባር ዕለት ዕለት እንዲፈጽም እንጂ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲፈጽም እንዳይደለ ቤተክርስቲያን ታስተምራለች:: በዓመት አንድ ጊዜ ዐብይ ወይም ሁዳዴ ጾምን መሠረት በማድረግ በየአካባቢው የተራበን ሲያበሉ የታረዘን ሲያለብሱ የሚታዩ በርካቶች ናቸው:: በተለይም በሰሞነ ሕማማት በትህትናው ሳምንት በርካቶች ግንኙነታቸውን ከፈጣሪያቸው ጋር በማድረግ ለሀገራቸው ሰላምን ለመላው ሕዝባቸው አንድነትና ፍቅርን ይለምናሉ:: ይህ እጅግ ሊበረታታ የሚገባው በጎ ተግባር እንደመሆኑ ዕለት ተዕለት ሊተገበር ይገባል:: በዚህ ጊዜ ሰዎች ከክፉ ሃሳብና ተግባር በብዙ ይጠበቃሉና::

አሁን አሁን ደግሞ ስጋን የሚደክመው ጾም ከነፍስ ባለፈ ለሥጋም ጭምር ጠቃሚ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል:: የተለያዩ ጥናቶችም ይህንኑ እያረጋገጡ ነው:: ስለዚህ በጾምና ጸሎት ክፉን አሸንፈን ለምድራችን ሰላምን ለመላው ሕዝባችንም እንዲሁ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ብንለምን በብዙ እናተርፋለን:: ይህም ሲባል በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚመጣውን ዐብይ ወይም ሁዳዴ ጾምን በመጾምና በዓመት አንድ ጊዜ በሚገኝ ሳምንት በሰሞነ ሕማማት በትህትናው ሳምንት በጎ ተግባራትን በመፈጸም ብቻ አይደለም:: በማንኛውም ጊዜ በጾምና ጸሎት፣ በጎ በጎውን በመሥራት፣ በመረዳዳት፣ በፍጹም ትህትና በመከባባር ነፍስና ስጋችንን ልናሳርፍ ይገባናል::

ሰሞነ ሕማማት የትህትናው ሳምንት የሰው ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገረበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዘበት የመሸጋገሪያ ወራት ምሳሌም ጭምር ነው:: ስለዚህ እኛ ሰዎች የተከፈለልንን ትልቅ ዋጋ በልባችን በማሰብ ሁልጊዜም ቢሆን መልካሙን ሁሉ እናድርግ:: በርካሽና በማይረቡ ተግባራት ሳንጠመድ ሁልጊዜም ቢሆን ስለ ሰው ልጆች እኩልነት በማመን የተከፈለልንን ዋጋ እናስብ:: በታላቁ ዐብይ ወይም ሁዳዴ ጾም የምንከውናቸው በጎ ተግባራትን በሙሉ በየዕለቱ ብንተገብረው ታድያ በብዙ እናተርፍ ይሆናል እንጂ ፈጽሞ አንከስርም::

እርግጥ ነው ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ዕምነት እንጂ፣ አማኝ የለም›› እንተርት ይሆናል:: ያም ቢሆን ታድያ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው አማኝ ሕዝብ ነው:: ሁሉም በየዕምነቱ አስተምህሮ የፈጣሪውን መንገድ ሊከተል ይወዳልም ይጥራልም:: በተለይም በአጽዋማት ወቅት ብዙዎች የበረከት ሥራዎችን በብዛት ሲሠሩ ይስተዋላሉ:: ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን ጭምር ለበጎ ዓላማ በማዋል የፈጣሪን ትዕዛዝ ሲፈጽሙ መመልከት የተለመደ ነው:: ይህም በፈጣሪ ዘንድ ዋጋው ውድ ነው:: እኛ ኢትዮጵያውያንም የሚያምርብን መረዳዳት፣ መከባበርና አንድነት ነው::

ስለዚህ የተቀደሰው የጾም ወቅት ሲያበቃ ወደ ቸበርቻቻችን አንመለስ:: ታጥቦ ጭቃም አንሁን:: በዓለማችን እንዲሁም በዙሪያችን የከበቡንንና ዕለት ከዕለት አዲስ ሆነው የሚጋፈጡንን ችግሮች ሁሉ ለመሻገር በጎ ሥራችን ዋስትና ነው:: ለችግሮቻችን ሁሉ አፋጣኝ ምላሽ እንድናገኝ ታድያ የፈጣሪን ትዕዛዝ እንጠብቅ:: ስለ ሰው ልጆች ሁሉ የከፈለውን ዋጋም እናስብ:: ሃሳብና ተግባራችንም አንድ ይሁን:: በሰሞነ ሕማማት በትህትናው ሳምንት የምናሳየውን በጎና መልካም ነገሮች ሁሉ በዕለት ተዕለት ሕይወታችንም መርህ ይሁን ያኔ ሀገር ሰላም እኛም ደህና እንሆናለን:: መልካም ሰሞነ ሕማማት የትህትናው ሳምንት::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You