“ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል …! ?”

ሕይወትና ተፈጥሮ ሙዚቃዊ ስልት አላቸው የሚል መረዳት አለኝ። አዎ ሕይወትም ተፈጥሮም ዜማ፣ ምት፣ ቅንብር፣ ድርሰት ወይም ሌሪክ እና የሙዚቃ አዝማች አላቸው። እያንዳንዱን ሕይወት እና ተፈጥሮ በአንክሮ ብናስተውለው ለእዝነ ሕሊናም ሆነ ለልቦና የሚሰማ ዜማ፣ እንደ ልብ ትርታ በተመሳሳይ ሰዓት የሚደገም ምት፣ ዜማንና ምትን የሚያንሰላስል የሚያቀናብር አንድ ኃይል አለ። ለእኔ ይህ ኃይል ልዑል እግዚአብሔር ነው። ቀንና ሌሊትን የሚያፈራርቀው፣ ክረምትና በጋን የሚያመላልሰው፣ በዘረ አዳም እና በተፈጥሮ መካከል መስተጋብር የፈጠረው እግዚአብሔር ነው።

ዶሮ በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት አኩኩሉ የሚለው፤ አዕዋፍ ያለማንም ቀስቃሽ ሁልጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት ንጋትን የሚያበስሩን በአጋጣሚ ሳይሆን በእግዜሩ አቀናባሪነት ነው ብዬ አምናለሁ። እንድናስተውለው፣ እንድንረዳውና ትኩረት እንድንሰጠው የሚፈልገውን ነገር ደግሞ እንደ ሙዚቃ አዝማች ይደጋግምልናል። እኔም የስቅለቱንና የትንሣዔውን አንድምታ እንድንረዳው ቢያንስ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት እንደ ሙዚቃ አዝማች ደጋግሜዋለሁ። ምን አለፋችሁ በዚህ ዓምድ ለማስነብባቸው መጣጥፎቼ አዝማች አድርጌዋለሁ።

ይሄን የስቅለቱንና የትንሣዔውን ነገር ግን እንደ ሙዚቃ አዝማች ልብ ያልነው የተረዳነው አይመስለኝም። በስቅለትና በትንሣዔው መካከልም ተመሳሳይ ሙዚቃዊ ስልት አለ። ይሄን መለኮታዊ ዑደት በጥልቅ ከተረዳነው ሌሪክ፣ ምት፣ ዜማ፣ ቅንብርና አዝማች አለው። እንዲሁም ታዳሚ አለው። ታዳሚው ዘረ አዳም ነው። እግዜሩ ዘረ አዳም እንዲረዳው የሚፈልገውን ነገር እንደ አዝማች በሕይወቱ ይደጋግምለታል። ዓርብ ስቅለትን፣ እሁድ ትንሣዔን እንደ ሙዚቃ አዝማች በየዓመቱ ይደጋግምለታል። አዎ እስኪረዳው ለ2017ኛ ጊዜ ደጋግሞለታል። ልብ የሚሰብረውና የሚያሳዝነው የትላንቶቹ ሆኑ የዛሬው ትውልድ በቅጡ ልብ አላሉትም። አላልንም። እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብ በሕይወታችን ዓርብና እሁድ ቢፈራረቁም አድሮ ጥሬ ነን። ነገር ግን በዚህ ተስፋ አልቆርጥም። ዛሬ ዓርብ ቢሆን እሁድ ይመጣል። አዎ ዛሬ ስቅለት ቢሆንም ትንሣዔው ይመጣል። ከወጪ ቀሪ ሒሳብ ስናወራርድ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ዓርብ ላይ ነን። ግን እሁድ ይመጣል። ይህ ለእኔ እንደ ሙዚቃ አዝማች ነው።

ዛሬ ዓርብ ቢሆንም፣

እሁድ ይመጣል፤ (×2017)

/እግዜሩ ይሄን አዝማች 2017 ጊዜ ደጋግሞልናል ለማለት ነው። ግን ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው አልተረዳነውም። አልኖርነውም። በሕይወታችን አልገለጥነውም።/

ወደእዚህ መጣጥፌ ዘፍጥረት ጄነሲስ ስመለስ፤ መጋቢ ኤልደር ዊርዝሊንስ ሰሞነኛውን ስቅለትና ትንሣዔን ታሳቢ በማድረግ “ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል።” የሚል ዘመን ተሻጋሪና ወርቅ ይትበሀል ትተውልን አልፈዋል። ጨለማ፣ የምድር መናወጥ፣ ክረምት፣ ሰደድ እሳት፣ በረዶ፣ ጎርፍ፣ መገፋት፣ መዋረድ፣ መገረፍ፣ መቸንከር፣ መካድ፣ መሸጥ፣ መሰቀል፣ ወዘተረፈ ዓርብ ቢሆንም፤ መንጋቱ፣ ብርሃን በጨለማ ላይ መንገሡ፣ የምድር መናወጡ መቆሙ፣ ብራ ፀደይ መምጣቱ፣ መከበሩ፣ መፈወሱ፣ ትንሣዔ፣ ቀን መውጣቱ፣ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ፣ ወዘተረፈ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ እንደተነሳበት እሁድ ሁሉ ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ከችግር፣ ከድህነት፣ ከተመፅዋችነት፣ ከኋላ ቀርነት፣ ከፈተና፣ ከወረርሽኝ፣ ከጭቆና፣ ከአፈና፣ ከጥላቻ፣ ወዘተረፈ ነፃ የምንወጣበት አንገታችን በክብር ቀና የምናደርግበት፤ ትንሣዔያችንን፣ ሕዳሴያችንን የምናይበት ቀን ይመጣል። እሁድ ይመጣል። “ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል።” እያልን በእምነት በተስፋ እንጠባበቃለን። ደግሞም ይሆናል።

ከስምንት ዓመት በፊት ባጋጠመኝ አደጋና የጤና እክል ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኜ ቤት ለመዋል፣ ተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር)፣ አጓጓዥ /ወከር/ና ከዘራ ለመጠቀም ተገድጄ ነበር። ለመልበስ፣ ለማውለቅ፣ ውሃ ለመጠጣት፣ ለመመገብ፣ ለመታጠብ፣ ለመተኛት፣ ለመነሳት የሰው ርዳታ ያስፈልገኝ ነበር። ስልክ ለማነጋገር፣ የቲቪ ቻናል ለመቀየር ርዳታ ያስፈልገኝ ነበር። ሁሉ ነገሬ በሰው ርዳታ ላይ የተመሠረተ ነበር። መላ ሕይወቴ ተመሰቃቅሎ ነበር። ሥራዬን አጣሁ። በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ከአአዩ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመያዝ ጥቂት ሲቀረኝ ተቋረጠ። ሕልሜ ተስፋዬ ተጨናገፈ። በመጨረሻ ለጭንቀትና ለድባቴ ተዳርጌ ነበር ።

ዓርብ ነበርና!

እንዲህ አይነት ብዙ የሕማማት “ዓርቦችን” በሕይወቴ እንዳሳለፍሁት ሁሉ እናንተም ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ በሕይወታችሁ መውደቅ መነሳቶችን፣ ሕማማትን፣ ዓርቦችን ማሳለፋችሁ አይቀርም። በግል ሕይወታችሁ፣ በትምህርታችሁ፣ በፍቅራችሁ፣ በትዳራችሁ፣ በንግዳችሁ፣ በሕልማችሁ፣ በራዕያችሁ፣ በድርጅታችሁ፣ በሃይማኖታችሁ፣ በጤናችሁ፣ በቤተሰባችሁ፣ በማኅበረሰባችሁ፣ በሕዝባችሁ፣ በሀገራችሁ፣ ወዘተረፈ ላይ ዓርብ ሆኖባችሁ /ጨልሞባችሁ/ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ተዛብቶባችሁ፣ ተገምድሎባችሁ፣ ታስራችሁ፣ ተገርፋችሁ፣ ተሰቅላችሁ፣ ተቸንክራችሁ፣ ተዋርዳችሁ፣ ተፈትናችሁ፣ ባመናችሁት ተክድታችሁ፣ በባልንጀራችሁ በ’33’ ብር ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ፣ ሰማይ ተደፍቶባችሁ ፣ ቀን ጨልሞባችሁ፣ ወዘተረፈ ይሆናል። ዛሬም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያለፋችሁም ይሆናል።

ዓርብ ነውና!

ካለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ወዲህ ያሉትን ጊዜያት እንኳ ብንወስድ እንደ ሕዝብ እንደ ሀገር ሺህ ዓርቦችን፣ በድርቅ፣ በረሃብ፣ በቸነፈር፣ እናት ልጇን እስከ መብላት የተገደደችበት እንደ ክፉ ቀን ያለ እንደ 67ቱ በረሃብ የሞተች እናቱን ጡት የሚጠባበት፣ እንደ …77…87… ወዘተርፈ ያሉ ጠኔዎችን፣ ችጋሮችን አሳልፈናል። ዛሬም ከዚህ አዙሪት ሰብረን መውጣት አልቻልንም። እንደ ኅዳር በሽታ፣ ፈንጣጣ፣ ከ1976 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ጥላውን እንዳጠላብን አለን። በግብፅ፣ በደርቡሽ፣ በቱርክ፣ በእንግሊዝ፣ በጣሊያን፣ በሶማሊያ፣ በኤርትራ ተወረናል። ዛሬም የክተት ነጋሪት የሚያስጎሹምብን አልጠፉም።

በመቶዎች ሊቆጠሩ በሚችሉ የርስ በእርስ ግጭቶች አልፈናል። ከዘመነ መሳፍንት እንኳ ብንጀምር በመሳፍንቱ፣ በመኳንንቱ፣ በነገሥታቱ መካከል ለሥልጣን፣ ለዘውድ ሲባል በተካሄደ የርስ በእርስ ግጭት ጦርነት ወገናችን ተጨራርሷል። ዓፄ ቴዎድሮስ፣ ዓፄ ዮሐንስ፣ ዓፄ ምኒልክ፣ ልጅ እያሱ፣ ንግሥት ዘውዲቱ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንና መንግሥቱ ጉዳቱ፣ ጥፋቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም በርስ በእርስ ግጭት፣ ጦርነት ተፈትነዋል።

የሀገር የሕዝብ ዓርብ ነበርና !

ባለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በተቀነቀነ የማንነት ፖለቲካ የተነሳ በሀገራችን ጥላቻ፣ ቂም፣ በቀል፣ ልዩነት ተጎንቁሏል። ጎሣን ፣ ሃይማኖትን ፣ አይዶሎጂን መሠረት አድርገን ተጋጭተናል። ተጋለናል። አብያተ ክርስቲያናትን፣ መስጊዶችን አቃጥለናል። ቀይ፣ ነጭ ሽብር ተባብለን ተጨራርሰናል። እናት አባት በቀይ ሽብር የተገደሉ ልጆቻቸውን እሬሳ ሲለምኑ የጥይት ዋጋ ጠይቀናቸዋል። የዚችን ሀገር ታሪክ እስከወዲያኛው ሊቀይር የሚችል ፍም እሳት የሆነ አንድ ትውልድ ጨርሰናል። በርስ በእርስ ጦርነት በብዙ አስር ሺህዎች የሚቆጠር ዜጋ አጥተናል። የሀገር ሀብት ወድሟል። ሀገር አጥተናል። ዛሬ ድረስ ከዚህ ሀንጎቨር አልወጣንም ።

የሀገር የሕዝብ ዓርብ ነበርና !

በፖለቲካ አመለካከታችን፣ በጎሣችን በጅምላ ተገርፈናል። ተገልብጠናል። ተሰቃይተናል። ተግዘናል። ተሰደናል። ሰው በመሆን ብቻ ከፈጣሪ የተቸርናቸውን የማሰብ፣ የመናገር፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ መብቶች ተረግጠዋል። በደምሳሳው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል። በገዛ ወንድሞቻችን እንደ ባሪያ ተገዝተናል። ተረግጠናል። ተገፍተናል። ሀብታችንን ሀገራችን በቀን በአደባባይ

ተዘርፈናል። ሀገር በቁሟ በአውሬዎች ተግጣለች። የድሀ ጉሮሮ ታንቆ ፣ በእኛ ድህነት ጥቂቶች በተድላ ፣ በቅንጦት ፣ በደስታ ፣ በፍሰሐ ተንደላቀዋል።

ዓርብ ነውና !

ዜጎችን በማንነታቸው አፈናቅለናል፣ ገለናል፣ ከእነ ሕይወታቸው በእሳት አቃጥለናል። ወደ ገደል ጥለናል። ሩጦ ተጫውቶ ያልጠገበን ሕጻን ብላቴና ብልት ሰልበናል። እህቶቻችንን ደፍረናል። ዛሬ ድረስ አግተናል። በሕዝብ ፣ በክልልና በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ የማንነት ግጭት እንዲቀሰቀስና ሀገር ወደ ለየለት ቀውስ እንድትገባ በአደባባይ ቀስቅሰናል። ለፍፈናል።

ዓርብ ነበርና!

ወደ እኔ ሕይወት ስመልሳችሁ ታምሜ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዤ ሳለ “ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል። ” እያልሁ እጽናና ተስፋ አደርግ ነበር ። ዛሬ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆን ፣ የማይነጋ ፣ ዙሪያው ገደል፣ ተራራ፣ ተስፋ ቢስ ቢመስልም፤ ነገ ቀን ይወጣል ፣ ይነጋል፣ ደልዳላ ይሆናል እሁድ ይመጣል እያልሁ እጽናና ነበር። እምነቴም አምላኬም አላሳፈረኝም። ዛሬ ጤናዬ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል። በቅርብ ሙሉ በሙሉ ይሻለኛል ብዬ አምናለሁ። የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያዬን በደጋግ ሰዎች እገዛና ማበረታት ጀምሬያለሁ። ተስፋዬ ለምልሟል። በዋሻው መውጫ ብርሃን እየታየኝ ነው። በዚች ሀገር የሚዲያ ኢንዱስትሪ የዜግነት ድርሻዬን እወጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ዛሬ ላይ እንዲህ ሕልመኛ የሆንሁት ዓርብ አልፎ እሁድ እንደሚመጣ በማመኔና ተስፋን በመሰነቄ ነው። ከስቅለቱ በኋላ ትንሳኤው እንደሚመጣ በማመኔ ነው።

እሁድ ይመጣል !

ኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋረደባት፣ ከተተፋባት፣ ከተገረፈባት፣ ከተቸነከረባት፣ እንደ ወንበዴ፣ ወንጀለኛ አንዳች መተላለፍ፣ ነቀፋ ሳይገኝበት፣ ሞት የተፈረደበት፣ በመስቀል ተቸንክሮ ከተሰቀለባት፣ ጎኑ ከተወጋባት በኋላ” ዓርብ” እንደ ተቀሩት የሳምንቱ ቀናት የጊዜ መለያ ብቻ አልሆነም። የጨለማ፣ የስቃይ፣ የመከራ፣ የፈተና፣ የውርደት፣ የግፍ፣ የበደል፣ የመገፋፋት፣ የራቁትነት የመስቀል ወዘተርፈ ተምሳሌት ጭምር እንጂ። ኤልደር ” ዛሬ ዓርብ ነው ” ያሉት ይሄን መሰሉን ቀን ፣ ዓመት፣

ዘመን ነው ፡፡

ዛሬ አርብ ነውና ፤

ሆኖም መግነዙን ፈቶ፣ የመቃብሩን ቋጥኝ አንከባሎ፣ ሞትን ድል አድርጎ፣ በብኩርና በሶስተኛው ቀን በድል ተነስቷል። አርጓል። በደሙ ዘላለማዊ ድህነትን፣ በግርፋቱ ሕያው የፈውሱን አክሊል አቀዳጅቶናል። ሀጢያትን ደምስሶ ከልዑል እግዚአብሔር አስታርቆናል። ከኦሪታዊ ሕግ ፣ ከባርነት፣ ከሀጢያት አሽክላ ነጻ አውጥቶናል።

እሁድ መጥቷልና !

ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ ፣ ሕዝብና ሀገርም እንዲህ ባለ ተመሳሳይ ጨለማ፣ ፈተና፣ መከራ፣ ቸነፈር፣ ውርደት፣ ግርፋት፣ መቸንከር፣ ደም መፍሰስ፣ ስጋ መቆረስ፣ ጀርባ መተልተል፣ ግማደ መስቀሉን ተሸክሞ ተራራ መውጣት፣ ጎን መወጋት፣ የሾህ አክሊል መድፋት፣ ወዘተረፈ አልፈዋል ። እልፍ አእላፍ ዓርቦችን አሳልፈዋል። ዳሩ ግን የትንሳኤው እሁድ ይመጣል።

እሁድ ይመጣልና !

ከእዚህ ክፉ ወረርሽኝ፣ ከፖለቲካ ስብራት፣ ከጥላቻ፣ ከስግብግብነት ፣ ከደባ ፖለቲካ፣ ከድህነት፣ ከእርዛት፣ ከርሃብ፣ ከኋላ ቀርነት፣ ከልዩነት ፣ ወዘተረፈ ወይም ከዓርብ ወጥተን ፤ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረን፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ገንብተን ዓርብን አልፈን ለእሁድ እንበቃለን። ሌት ተቀን በመትጋት ፣ ሙስናን ፣ ብልሹ አሰራርን፣ ስንፍናን ፣ ዳተኝነት በማስወገድ ዓርብን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገራለን። እሁድን በተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን። ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ ጎሰኝነትን፣ የታሪክ እስረኝነትን፣ የታሪክ ምርኮኝነትን የሴራ ፖለቲካን ወይም ብዙ ዓርቦችን በጽናት በብርታት አልፈን ለትንሳኤና ለሕዳሴ / ለእሁድ እንበቃለን። ደግሞም እናምናለን ይሆናል።

ስለ ስቅለቱና ትንሳኤው ካነሳሁ አይቀር ትንሽ ላክል። በጲላጦስ ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት፤ ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ መከራን ተቀበለ፤ ጲላጦስ በሶስት ሰዓት ይሰቀል ዘንድ ሲፈርድበትም፤ ‹‹መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ›› (ዮሐ.19፥17) የራስ ቅል ስፍራ ቀራንዮ-ጎልጎታ አዳም ዐጽም የተቀበረበት ቦታ ነበር። በዚያም የአዳም መቃብር የሆነች ዋሻ አለች፤ የመስቀሉንም እንጨት በዚያ በምድር መካከል አይሁዶች ተከሉት፡፡

የአዳም አጽም ቀድሞ ከአዳም ትውልዶች ሲተላለፍ ከኖኅ ደርሷል፤ ኖኅም ወደ መርከብ እንደታቦት አስገብቶት በኋላ መልከጼዴቅ ቀብሮታል። ጌታችንም ከአዳም የራስ ቅል በላይ ሊያድነው መስቀል ተሸከሞ ተንገላታ፤ አይሁዶችም የቀራንዮን ዳገት እየገረፉ ከወደ ጫፍ አደረሱት፤ ሁለቱንም እንጨት አመሳቅለው ዐይኖቹ እያዩ እጆቹንና እግሮቹን ቸነከሩት፤ በዕለተ ዓርብ ቀትር 6 ሰዓት ላይም ተሰቀለ፡፡

ጌታችን የተሰቀለበት ሰዓት ፀሐይ በሰማይ መካከል በሆነ ጊዜ የጥላ መታየት በሚጠፋበት፤ ወደ ሰው ተረከዝም በሚገባበት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ምድር ጨለመች፤ ፀሐይ፤ ጨረቃ፤ ከዋክብት ብርሃናቸውን ከለከሉ፤ ምክንያቱም የፈጣሪያቸውን ዕርቃኑን ይሸፍኑ ዘንድ ነበር፤ ‹‹ቀትርም በሆነ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፤ ምድርም ሁሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ጨለማ ሆነ›› ማር.15፥33፡፡

በዘጠኝ ሰዓት በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ስለ ጌታችን በሰማይ ሶስት በምድር አራት ተአምራትን ሲያደርጉ አይቶ በእውነት አምላክ እንደሆነ አመነ፤ ‹‹አቤቱ በመንግሥት በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ባለ ጊዜ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ግን ‹‹እስቲ አምላክ ከሆነ እራሱን ያድን›› ብሎ ተዘባበተ። ፍያታዊ ዘየማን ግን ‹‹እኛስ በበደላችን ነው የተሰቀልን፤ እርሱ ግን ምንም ሳይበድል ነው፤ እንዴት በአምላክ ላይ ክፉ ነገርን ትናገራለህ›› ብሎ ገሰጸው ፤ ፍያታዊ ዘየማንም ጌታችን በጌትነት መንበረ ጸባዖት (መንግሥት) ሆኖ ታየው፤ እርሱንም አይቶ ‹‹ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ›› ቢለው ጌታችን ‹‹ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት›› ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶታል፤ በኋላ ገነት ሲገባም መልአኩ አንተ ማነህ፤ አዳም ነህ፤ አብርሃም ወይንስ ይስሐቅ? እያለ ጠይቆታል።

መልአኩ ሳያውቅ የጠየቀ ሆኖ አይደለም፤ እንኳን በመጨረሻ የጸደቀ ፍያታዊ ቀርቶ በዘመናቸው የኖሩ ጻድቃንን ያውቃል፤ አዳምን ፤ አብርሃምን፤ ይስሐቅን ሳያውቅ ቀርቶም አይደለም። ነገር ግን ሊቃውንት ሲተረጉሙት ‹‹አዳም ነህ›› ማለቱ የአዳምን ያህል ሥራ አለህን? አብርሃም ነህ ሲለው ደግሞ የአብርሃምን ያህል ሥራ አለህን? ለማለት ነው። ‹‹በጌታችን ኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፤ የእናቱም እኅት፤ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፤ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር›› (ዮሐ.19፥55) ‹‹እነርሱም ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜም ነበሩ›› (ማር.15፥40)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተናገራቸው የአደራ ቃላት አንዱ እመቤታችን ለቅዱስ ዮሐንስ መሰጠቷ ነው፤ ለወዳጁ ዮሐንስ ከስጦታ ሁሉ ስጦታ የሆነች እናቱን እናት ትሁንህ ብሎ ሰጠው፤ ‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› (ዮሐ.19፥26)። በኋላ ወደ ቤቱ ወስዷት 15 ዓመት ኖራለች፤ በዚህም የዮሐንስ ቤት በአቢዳራ ቤት ተመስላለች፤ እመቤታችንም የሚያጽናናትን ወዳጁ ዮሐንስን ሰጥቷታል። የእመቤታችን ለዮሐንስ መሰጠት ቀድሞ በሙሴ አንጻር ጽላቷ ለሕዝቡ ሁሉ እንደተሰጠች፤ በዮሐንስ አንጻርም እመቤታችን ለሁላችን ለምእመናን ተሰጥታናለች፡፡

ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› ብሎ በታላቅ ቃል ተናገረ፤ (ማር.15፥34)። በዚያም ቆመው የነበሩት ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ፤›› የሚለውን ድምጽ የሰሙ ኤልያስን ይጣራል እያሉ አሙት፤ ክህደትንም ተናገሩ፤ ያንጊዜ አንዱ ወታደር ሮጦ ሆምጣጤ የመላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና በሰፍነግ መልቶ በሂሶጽም አድርጎ በአፉ ውስጥ ጨመረለት፡፡

በመስቀል ላይ ሳለ ጌታችን ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ሁሉ ተፈጸመ አለ፤ (ማር. 15፥37)፤ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ። አይሁድም እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ፤ ምክንያቱም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። የሁለቱ ወንበዴዎች፤ ፈያታይ ዘየማንንና ፈያታይ ዘጸጋምን አብረው አወረዷቸው፤ ከጌታችን ዘንድ ቢቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ። ሌላው ግን የተመሰለው ምሳሌ ፍጻሜ ሲያገኝ ነው፤ የፋሲካውን በግ ‹‹አጥንቱን ከእርሱ አትስበሩ›› የተባለው አሁን ተፈጸመ፤ (በዘፀ.12፥10)፡፡

ከጭፍሮቹም አንዱ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው እንዲል ከወታደሮቹ አንዱ የሆነው ለንጊኖስ የጌታችንን ጎን ቢወጋው ትኩስ ደምና ቀዝቃዛ ውኃ ፈሷል። ለንጊኖስ ጥንተ ታሪኩ አንድ ዐይኑ የጠፋ ሲሆን ጌታችን በተሰቀለበት ጊዜ ወደ ጫካ ሸሽቶ ርቆ ነበር፤ ምክንያቱም ከዚህ ሰው ሞት አልተባበርም በማለት ነው። አመሻሹ ላይ የአይሁድ አለቆች ሲመለሱ ከመንገድ አገኙቱ፤ ስለምን ከመሢሑ ሞት አልተባበርክም አሉት? እርሱም ምንም ስላላገኘሁበት አላቸው፡፡

ከዚያም በኋላ እንደሕጋቸው እንደሚቀጡት ቢነግሩት እየሮጠ ሔዶ የጌታችንን ጎን ሲወጋው ደሙ በዐይኑ ላይ ፈሰሰ፤ ያን ጊዜ ዐይኑ በራለት፤ ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደም እንደ ለ ቅርጽ ሆኖ በሁለት ወገን ደምና ውኃ ሆነ። ከጌታችንም የፈሰሰውን ትኩስ ደም መላእክት በጽዋ ቀድተው በዓለም ላይ ረጩት፤ ይህ መሠረት ሆኖ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታነጸው የጌታችን ደም የነጠበበት ነው። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› ያለው (ሐዋ.20፥28)። ከጌታ ጎን የፈሰሰው ውኃ ደግሞ ምእመናን የልጅነት ጥምቀትን ስንጠመቅ ውኃውን ካህኑ ሲባርከው ማየ ገቦ ይሆናል።

ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፤ ይህ ቅዳሜ ጌታችን ሥጋው በመቃብር የዋለበት በመሆኑ እኛም እንደ ሐዋርያት የትንሣኤውን ብርሃን ሳናይ እህል አንቀምስም በማለት በጾም ስለምናሳልፈው ነው። ቄጠማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤው ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሰሩታል፤ የቄጠማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፤ ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጠማ ይዛ በመግባት ነው። ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ኃጢአት ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፃነት ተሰበከና ታወጀ በማለት ካህናቱ ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበስሩበታል፡፡

በዚህች ቅድስት ቅዳሜ፤ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ፤ በዚህች ዕለት ከሥራው ሁሉ ያረፈባት ዕለት ናት። ጌታችን የተቀበረበትም ስፍራ ለተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ነበር፤ ዮሴፍ ከኒቆዲሞስ ጋር ሆኖ ጌታችንን እንደፍጡር በሐዘንና በልቅሶ ሲገንዙት የጌታችን ዐይኖች ተገለጡ ‹‹እንደፍጡር ትገንዙኛላችሁን? በሉ እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ሕያው›› አላቸው፡፡

ትንሣኤ፡- ትንሣኤ ተንሥአ ተነሣ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙ መነሣት ማለት ነው። ይኸውም የሰው ልጅ ሞቶ ሥጋው ፈርሶ በስብሶ እንደማይቀር እና በዳግም ምጽአት ጊዜ እንደሚነሣ የሚያመለክት ነው። የሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠውን ትእዛዝ ባለመጠበቁ ምክንያት የሞት ሞት ተፈርዶበት ነበረ። “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም” ተብሎ ነበርና። (ዘፍ.3፣3) በዚህም ምክንያት ከአቤል ጀምሮ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ የሰው ልጅ በሥጋ የሚሞት ሆኗል። ነገር ግን እንደሞትን አንቀርም። ሁላችንም ትንሳኤ አለን። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት የትንሣኤያችን በኩር ሆኖናልና። (1ኛ ቆሮ.15፣21)፡፡

“ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሳኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗል›› እንዲል። ዘለዓለማዊ ሞታችን እና ፈርሶ በስብሶ መቅረት የቀረልን አካላዊ ቃል ሥጋችን ተዋሕዶ ሰው ሆኖ ሞትን በሞቱ ድል ከነሣልን በኋላ ነው። ሊቁ ሱኑትዩ በሃይማኖተ አበው “ሞተ ክርስቶስ በሞተ ዚኣነ ከመ ይቅትሎ ለሞት በሞቱ፤ ሞትን በሞቱ ያጠፋልን ዘንድ ክርስቶስ በተዋሐደው ሥጋ የእኛን ሞት ሞተ ብሎ እንደገለጠው። (ዮሐ.11፣25)

“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ያለ ጌታ በጥንተ ትንሣኤ መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሑድ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። መልአኩም ማር.(16፣6) “አትደንግጡ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስ ትሻላችሁን? ተነሥቷል” ብሎ ለቅዱሳት እንስት ነግሯቸዋል። (ሉቃ.24፣6)፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ ከአልዓዛር ትንሣኤ የተለየ ነው። አልዓዛርን ያስነሣው ራሱ ክርስቶስ ሲሆን ትንሣኤውም መልሶ ሞት ነበረበት። ክርስቶስ ግን የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው። ዳግመኛ ሞትም የለበትም። (ዮሐ.2፥19፤ 10፥ 18)”ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሧዋለሁ” ካለ በኋላ እርሱ ግን ይህንን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለተባለ ሰውነቱ ነበር ይለዋል። በሌላም የወንጌል ክፍል “እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥም… ይላል። (ሐዋ.4፣10) በሃይማኖተ አበው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ አስነሳው የሚል ይገኛል። ይህን ቢል ሦስቱ አካላት አንዲት ግብረ ባሕርይ ስላላቸው ያችን ለእያንዳንዱ አካላት አድሎ መናገሩ ነው። አብ አምላክ፣ ወልድ አምላክ፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ቢል ሦስት አምላክ አንልም። አንድ አምላክ እንላለን እንጂ። (ዮሐ.10፥30) “እኔና አብ አንድ ነን”(ዮሐ.10፥9) እንዲል። ማስነሣት ሦስቱ አካላት አንድ የሚሆኑበት ግብር ስለሆነ አብ አስነሣው፣ በራሴ ሥልጣን ተነሣሁ፣ መንፈስቅዱስ አስነሣው ቢል አንድ ነው፡፡

” ዛሬ አርብ ቢሆንም

እሁድ ይመጣል !”

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

Recommended For You