ጥምረታቸው ከትዳር አጋርነትም በላይ ነው። በሥራ ቦታም አብረው ሲውሉ ያየ የሁለቱ አብሮነት ከቤት ውስጥም ያለፈ ትርፍ ያስገኘ መሆኑን ይረዳል። ጥንካሬን በተግባር ያሳዩ ባለትዳሮች መሆናቸውን ደግሞ በርካቶች የሚመሰከሩት ሐቅ ነው።
የተትረፈረፈ ሀብት ባይኖራቸውም አብረው የመሥራታቸው ልምድ ግን ለሌላውም የሚተርፍ ስሜት ኮርኳሪ፣ ሃሳብ አመንጪ አቅም አለውና ወደሚገኙበት አዲስ አበባ ጀሞ ኮነዶሚኒየም አካባቢ አምርተናል። ስለሥራቸው ተጨዋውተን ለእናንተ በሚሆን መልኩ አቅርበነዋል፡፡ ስለሥራቸው ከማውጋታችን በፊት ግን ነገርን ከስሩ ውሃን ከምንጩ እንዲሉ ነውና ጥቂት ስለታሪካቸው ጀባ እንበል።
አቶ ወንደሰን ተካ የተወለደው በአፋር ክልል ዱብቲ በተሰኘችው ከተማ ነው። በሥራ ምክንያት አፋር ክልል የኖሩት ቤተሰቦቹ በተለያዩ መስኮች ላይ ተሰማርተው ነበር። በአንድ ወቅት የከብት ንግድ ውስጥ በሌላ ጊዜ ደግሞ እርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተው ሲያሻቸው ደግሞ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን እየከወኑ ልጆቻቸውን አሳድገዋል።
ለቤተሰቡ ዘጠነኛ እና የመጨረሻ ልጅ የሆነው ወንደሰን ከልጅነቱ ጀምሮ የእናትና አባቱን ሥራ እያየ እና ስለታታሪነት እየተማረ ማደጉን ይናገራል። ዱብቲ በሚገኘው አዋሽ ሸለቆ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማረ በትርፍ ሰዓቱ ቤተሰቦቹን በንግድ ሥራቸው ላይ ያግዝ ነበር። ከዚያም ዱብቲ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአስኳላ ትምህርቱን ተከታትሏል።
12 ክፍል ሲጠናቀቅ ግን አዲስ አበባ መጥቶ በቀደሞው ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ጤናና ሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ክፍል ገባ። በኮተቤ ለሁለት ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በዲፕሎማ ተመርቆ ወደአፋር ተመለሰ።
ከምረቃ በኋላ በአፋር ክልል ሚሌ ከተማ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በስፖርትና ማጎልመሻ መምህርነትን ተቀጠረ። የመጀመሪያ ደመወዙ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከ600 ብር ያነሰ መሆኑን ያስታውሳል። በወቅቱም ከጓደኞቹ ጋር ቤት ተከራይቶ ለአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ አስ ተምሯል።
ወንደወሰን ቀጥሎ የተሸጋገረው ወደክልሉ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ነው። በቢሮው ስር ተቀጥሮ የወጣቶች ማህበራዊ ልማት አስተባባሪ ሆኖ መሥራት ጀመረ። በክረምት ወቅት ግን የትምህርት ዕድል አገኘ። በየዓመቱ የክረምት ወቅት ሻሸመኔ አቅራቢያ በምትገኘው ኩየራ ከተማ የኢትዮጵያን አድቬነቲስት ኮሌጅ ውስጥ በማህበረሰብ ልማት እና አመራርነት ክፍል ትምህርቱን ተከታትሏል።
በአፋር ክልል የስፖርት ቢሮ ሥራውን እንደቀጠለ ትምህርቱንም አገባደደ። በቢሮውም በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ተዘዋውሮ ለ10 ዓመታት ሠርቷል። በወቅቱ ግን አቶ ወንደሰን ለሥራ ጉዳይ ወደ መቀሌ ሲያመራ ከአንዲት ልጅ ጋር ይተዋወቃል። ልጅት ደግሞ የአሁኑ ባለቤቱ ወይዘሮ ፍረሰናይ ዓለም ነች።
ፍረሰናይ በጊዜው ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደመቀሌ አምርታ በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራ ነበር። እናም ወንደወሰን እና ፍረሰናይ በአጋጣሚ ተዋውቀው ቅርርባቸው በመጠንከሩ ወደትዳር አመሩ። በትዳርም ለአንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ ፍረሰናይ ሁለቱም ተቀጥረው መሥራታቸው እንደማያዋጣ በማሰብ የግል ሥራቸውን መጀመር እንዳለባቸው በመንገር ባለቤቷን ለአዲስ ሥራ አነሳሳችው።
ባለትዳሮቹ በጉዳዩ በደንብ ካሰቡበት በኋላ አዲስ አበባ መጥተው ለመሥራት ይወስናሉ። ጀሞ አካባቢ የሚገኝ እና የቤተሰብ ንብረት የሆነ የኮንዶሚኒየም ቤት የታችኛው ወለል ተከራይተው የተለያዩ ምግቦች እና ቡና እያፈ ሉ ማቅረብ ይጀምራሉ።
አቶ ወንደሰንም የመንግሥት ሥራውን ከመልቀቁ በፊት ባለቤቱ ሥራውን እየተቆጣጠረች እርሱ ደግሞ አለፎአልፎ እየተመላለሰ ሥራውን በጋራ ማስኬድ ጀመሩ። ጀሞ ላይ ከስድስት ዓመታት በፊት የተጀመረው ሥራ እየተሻሻለ እና ደንበኞች እየበዙ ሲመጡ ግን አቶ ወንድወሰን ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ለቆ ከባለቤቱ ጋር አዲስ አበባ ላይ በጋራ መሥራቱን ተያያዘው።
ፍረሰናይ እራሷ አብስላ የምታቀርበውን ምግብ ባለቤቷ ለደንበኞቹ ያቀርባል። ቡናም እያፈላች ለባለቤቷ ትሰጠዋለች ፤እርሱ ሂሳብ ለደንበኞች እያቀረበና እየተቆጣጠረ በጋራ ማስተናገዱን ተካኑበት። በአጭር ጊዜ ውስጥም ከቅጥር ሥራ ይልቅ የግል ሥራቸው የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝላቸው የተረዱት ባልና ሚስት ንግዳቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አላቅማሙም።
አንድ ተጨማሪ ሠራተኛ ቀጥረው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማስተናገዱን ተያያዙት። ከምግቡ ይልቅ ግን የቡና ገበያው እየደራ በመምጣቱ ባለትዳሮቹ ይበልጥ ትኩረታቸው ወደቡና ገበያው ሆኗል። እናም የምግብ ሥራውን ጋብ አድርገው የቡና ገበያው ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ወሰኑ።
የቡናውን ትክክለኛ ጣዕም በያዘ መልኩ እራሱ ቆልቶ የሚያቀርብ ሁለት ሜትር ቁመት ያለው ዘመናዊ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ማሽን አሠርተው መጠቀም ጀመሩ። ማሽኑ ከ40 ሺ ብር በላይ የሚያወጣ እና ከውጭ የሚመጡ የቡና ማዘጋጃ ማሽኖችን የሚተካ ነው።
ባል ቡናውን በማሽን ቆልቶ በማሽን ፈጭቶ ለሚስት ሲያቀርብ ሚስት ደግሞ ፍሬ ቡና በሚል ስም በሰየመችው ንግድ ቤታቸው ውስጥ በሚገባ አፍልታ ታቀርባለች። በዚህ ወቅት በአንድ ጊዜ ከ50 ሰው በላይ ሊያስተናግድ የሚችለው የኮንዶሚኒየም ንግድ ቤት በደንበኞች መጥለቅለቅ ጀመረ፤ በረንዳቸውም ጭምር ጠጠር መጣያ አይገኝበትም።
በርካታ ደንበኞችም በፍሬ ቡና አቅራቢያ ያለው የቡና መዓዛ ጭምር ስቧቸው ቡናውን እንደቀመሱት እና በጣዕሙ እና አፈላሉ ልዩነት የተነሳ የሁልጊዜ ደንበኛ ሆነው መቅረታቸውን ይመሰክራሉ።
ደንበኞች የቡናውን ጣዕም መውደዳቸውና የገበያው መድራት ይበልጥ እንዳበረታታቸው ባለትዳሮቹ ይናገራሉ። አቶ ወንደሰን እንደሚናገረው ቤቱ በበርካታ ሰዎች ተሞልቱ ፋታ የሌለው ሥራ የሚሠራባቸው ጊዜያት አሉ። በመተለይ ምሳ ሰዓት እና የመንግሥት ተቋማት የዛይ ሰዓት ዕረፍት ላይ በርካታ ደንበኞች ይስተናገዳሉ።
አብዛኛው ሰው ደግሞ በአገልግሎቱ ተደስቶ እና ነገም እምጣለሁ በሚል ስሜት ተሞልቶ ከፍሎ ሲወጣ ማየት ደግሞ ለወንደሰን የሚያረካው ጉዳይ ነው። አሁን ላይ ሁለት ሠራተኞችን ቀጥረው ሰፋ ያለውን የቡና ንግዳቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ሥራው በሚያይልበት ወቅት ደግሞ እንደየአስፈላጊነቱ አንድ ተጨማሪ ሰው ጨምረው ይሠራሉ። የወይዘሮ ፍረሰናይ እህትም ሥራውን እያገዘች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ አምስት ሰዎች ሥራ ላይ ናቸው። አቶ ወንድወሰን እና ወይዘሮ ፍረወይኒ ከቡናው ንግድ ጎን ደግሞ ከፀብና ክርክር ውጨ የሆነ እና ለመዝናኛ አገግሎት የሚውል የፑል መጫወቻ አላቸው።
ከቡናው ጎን አቶ ወንድወሰን ወጣቶች በእርጋታ እንዲጫወቱ እየተቆጣጠረ በጨዋታ መሃል ደግሞ ቡና ለሚፈልጉ ወጣቶች እያቀረበ ገንዘቡን ይሰበስባል። ይህን የባልና የሚስትን ታታሪነት የሚመለከቱ የጀሞ አንዳንድ ነዋሪዎች ታዲያ ይህን ይበል የሚያሰኝ መተጋገዝ ሳያደንቁ አያልፉም። በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡና ደንበኞች ያላቸው ባለትዳሮቹ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ያገኛሉ። ባለትዳሮቹ በእያንዳንዱ ቀን ሰውን አስተናግደው ሲጨርሱ ደግሞ የዕለት ሂሳባቸውን አስተካክለው ወደቤታቸው ይገባሉ።
ቤት ውስጥም መተጋገዙ እንዳለ መሆኑን አቶ ወንድወሰን ይናገራል። ወደሦስት ጉልቻ ካመሩ በኋላ የተገኙ ሁለት ልጆቻቸውንም ማታ ቤት ውስጥ ሲያገኟቸው ደግሞ እንክብካቤ ከመስጠቱ ባለፈ ስለትምህርት ጉዳይ መወያየቱ እና የጥናት ጉዳይን መከታተሉ የሁለቱም ወላጆች ኃላፊነት ነው። በመደጋገፍ ውስጥ ተሳስበው የሚሠሩት ባለትዳሮቹ በቡናው ንግድ አማካኝነትም ልጆቻቸውን እያስተማሩ ይገኛል። ይህ ጥምረት እና መተሳሰብ ደግሞ ለተሻለ ስኬትም እንደሚያበቃቸው ተስፋ ሰንቀዋል።
ጥንዶቹ አሁን ላይ ለተሻለ ህይወት የሚረዳቸውን ቡና ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ የሚረዳውን የንግድ ሃሳባቸውን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ አዘጋጅተዋል። በዚህም መሰፈረት ቡንና አፍልቶ ከመሸጥ ባለፈ ቆልተውና ፈጭተው በእራሳቸው ስም አሽገው ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጁ ይገኛል። ለሥራው የሚረዳቸውን የገበያ ጥናት እና ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። ቡናን እራሱ ቆልቶ እና ፈጭቶ በዘመናዊ መንገድ የሚያሽጉ ማሽኖችን በመጠቀም ለመሥራት አስበዋል። ማሽኖቹ እያንዳንዳቸው ከሦስት መቶ ሺህ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ድረስ እንደሚያወጡ ጥናት አድርገዋል።
ለሥራው የእራሳቸው የፋይናንስ አቅም እንዳለ ሆኖ መንግሥት ደግሞ በብድር መልክ ገንዘብ እንዲያቀርብላቸው ፍላጎት አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ ቡናን የማሸጉ ሥራ ሰፋ ያለ ቦታ የሚያስፈልገው በመሆኑ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ቢሮዎች ጥያቄ አቅርበው ከተፈቀደላቸው ሙሉ በሙሉ ቡናን ዕሴት ጨምረው ወደ ውጭ ለ መላክ ዕቅድ ይ ዘዋል።
አቶ ወንድ ወሰን እና ፍረሰናይ በሥራ ዓለም ውስጥ ባልና ሚስት በጋራ የመሥራታቸው ጉዳይ ላይ እነርሱ የመጀመሪያዎቹ ባይሆኑም በቡና ማፍላቱ ሥራ ግን ምን ያህል አብሮ መሥራት ለተሻለ ውጤት እንደሚያበቃ ማሳያ እና ምስክር መሆን የሚችሉ ሰዎች ናቸው። ብዙዎች በመጋጨት እና በአሉባልታ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ፤ ትዳራቸውንም አደጋ ላይ ይጥላሉ። ይህ ግን አብሮ ለማደግ ፈጽሞ ጠላት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። እናም ባለትዳሮች ምን ጊዜም ህይወታቸውን ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት በመተባበር እና በመደጋገፍ የአንዱን ሥራ አንዱ ሳይንቅ በጋራ መሥራት ቢችሉ ሀገርም ይለወጣል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በርካታ ወጣቶች ወደትዳር ይገባሉ። ይህን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመፍጠር ሚስት አንድ ንግድ ከጀመረች ባልም ሳይጠየፍ ማገዝ እና ሚስትም በባሏ ሥራ ላይ ተጨማሪ ጉልበት በመሆን በፍቅርና በመተሳሰብ ቢሠሩ የተሻለ ገቢን ማግኘት ይችላሉ የሚለው ደግሞ የጥንዶቹ በመጨረሻ ያስተላለፉት ምክር ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
ጌትነት ተስፋማርያም