አኗኗራችን ሙሉ በሙሉ የሚመስለው እኛን ነው። ሌላው ቀርቶ ቤታችን ፣ የቤት እቃችን ፣ ብዕራችን፣ ልብሳችን፣ የኑሯችን ነጸብራቅ ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን፣ እኛ ራሳችን ራሳችንን የማንመስልበት ብዙ ጊዜ አለ። ያኔ ነው ታዲያ ኧረ ተው አንተ ሰው፣ ስንቱን ትሆናለህ የምንለው።
አሁን እንኳን ማንሳት የፈለግሁት ስለራስ ስህተትና ክህደት ሳይሆን አንዱ በሌላው ላይ ስላለው ተጽእኖ ነው። ቀላል ተጽእኖ ይፈጥራል መሰላችሁ እንዴ? ሰው፣ አንድ ሰው ሆኖ በሰው ላይ፣ ሰው በማህበረሰብ አስተሳሰብ ላይ ፣ ሰው በቤቱ፣ ሰው በሐገሩ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላል ፤ ያውም አንድ ሆኖ በመቶ ሺህ ሰዎች አስተሳሰብና ፈቃድ በሚሊዮኖች እምነት ላይ ፣ ጫና መፍጠር ይችልበታል።
ይህንን በሐገራችን በክፉም ሆነ በደግ በመልካምም ሆነ በመጥፎ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን አይተናል። ሰው ለሰው ደግና መድኃኒት፣ የመሆኑን ያህል ሰው ለሰው የማያምርና የሚመር የሚሆንበት በርካታ ሁኔታዎችአሉ።
ከጥንት አፈ ታሪካችን አንድ ምሳሌ ልወርውርልዎት። በአንድ ሐገር ውስጥ እንደ እኛው አለቃ ገብረሐና ጨወታ አዋቂ የሆነና በብዙዎች እንደፌዘኛ የሚቆጠር ሰው ነበረ። ይሁንናም ከንጉስ አደባባይ ጠፍቶ አያውቅም። አንድ ቀን ንጉሱ ከአማካሪዎቹ ጋር ለአንድ ጉዳይ ዘወር ብሎ እስኪመለስ አጅሬ ፣ በንጉሱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ እንቅልፍ እንደወሰደው ሰው ያንጎላጃል።
ንጉሱ ከምክር ቤቱ አዳራሽ ሲወጣ፣ በርቀት መንበሩ ላይ ሰው ተቀምጦ ያያል፤ እየቀረቡ ሲመጡ የተቆጡት ሌሎች ባለስልጣናት ከንጉሱ አንደበት ትእዛዝ ከመውጣቱ በፊት ተንደርድረው በመሄድ ያንን ሰው ከዙፋኑ ላይ አውርደው በእርግጫና በቦቅስ ያጣድፉት ገቡ። ሰውየውም ንጉስ ሆይ! እየሆነ ያለውን አየህ አይደል? ብሎ ሲጮህ እጃችሁን ከእርሱ ላይ አንሱና ወዲህ አምጡት አላቸው።
ከመጣ በኋላም “ለምን እንዲህ አደረግክ?” ሲል ሰውየውን ጠየቀው።
ቦታው ምንያህል እንደሚመች ላየው ስለፈለግሁ ነው፤ የተቀመጥኩበት ሲል መለሰለት።
እናስ እንዴት አገኘኸው?
አየሁት እኮ፣ ምን ያህል ጥፊና እርግጫ ፣ ጉንተላና ስድብ እንዳለበት … ንጉስ ሆይ ይህን ሁሉ ችለህ በመቀመጥህ አደንቅሃለሁ፤ ሲል መለሰለት።
እንዴት?
እንዴትማ አንተ እድሜህን ሙሉ በምትቀመጥበት ዙፋን ላይ ፣ እኔ ለጥቂት ደቂቃ በመቀመጤ እንኳን፣ ለመጠየቅ ከመፈለግ ይልቅ ለመፍረድ ስንቶች እንደተጣደፉብኝ አየሁ። ለአንድ ቀን ብቆይ ይገድሉኝ እንደነበረም አሰብኩ። አንተን ያልገደሉህ ፣ ስለማይችሉ እንጂ ቢችሉ ዘርጥጠው ጥለው መሳቂያ ያደርጉህ ነበረ። ስልጣንና እውቅና እሾህና ጦር አለበት። እንዴት እንደ ቻልከው ባላውቅም መጥኔውን ይስጥህ፤ አለው።
ንጉሱም ሣቅ ብሎ አንተን የመቱህ የበታቾቼ ናቸው እኔን የሚመቱኝ ደግሞ በቤቴ የምመግባቸው ሥጋዎቼ ናቸው አለው ይባላል።
ለ”ነገስታት” ብርታቱን ይስጣቸው። እንዲህ እንደኛ ሀገር ሁሉ ፖለቲካን ተንታኝ፤ ሁሉ ስልጣንን ተመኝ፣ ሁሉ ጨወታውን ተዋኝ፤ በመሰለበት ሀገር ለመሪዎች መጥኔውን ይስጣቸው ማለት ተገቢ ነው።
እኔ ብሆን እንዲህና እንዲያ አደርግ ነበረ ፣ ብሎ የሚልን ሰው፣ ለሚያደርገው ሰው አስተዋጽኦእስቲ አድርግ ሲባል ቁና ቁና እየተነፈሰ እፍን ሲያደርገው ይታያል።
የሰዎች ተጽእኖ ቀላል የማይሆንባቸው በርካታ የህይወት ምዕራፎች አሉ። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በጎ ተጽኖን ጭምር በመሟገትና በመሞገት ክፋታቸው በልዕልና እንዲንሰራፋ ይፈልጋሉ። የፈለጉትም ሃሳብ ይሁን ክፉ ራእይ የሚቀርበው ደግሞ በመብት፣ በእኩልነትና በነጻነት ስም ነው። ሃሳባቸው በተበድልንና በተገፋን አዝማች ካልታጀበ ውሃ አያነሳላቸውም፤ ስለዚህ ስለመጨቆን ፣ ስለመበደልና ስቃይ አውርተው አይጠግቡም። በከንፈር መጠጣ እና በጥላቻ ሐረግ የተጠመዘዘውን ሃሳባቸውን በለቅሶ አጅበው ያቀርቡታል።
ስለዚህ ከልባቸው የሚወጣው የሀውልት ቅርጽ እንኳን የድል አድራጊነት ወኔና መጪ ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ሳይሆን፣ መከራን የተላበሱ፣ ሰቀቀን የሚነበብባቸው ፊቶች፤ የተቆራረጡ አካላት ፣ አንገት የሌለው ምስልና ወንዝ የሚሞላ እንባ ነው።
ስለጠሉት አካል አውሩ ከተባሉ አውርተው ውለው ፣ መሽቶ ሊነጋ ይችላል፤ እንቅልፉ ካልጣላቸው። እና ዓላማችሁ ምንድነው ብትሏቸው “ በደሉን ማውራት ነው” አይሏችሁም፤ ታሪክን እየተረክን ነው የሚሏችሁ። ታሪክን ለባለታሪክ እንተውና ነገን ዛሬ ላይ እንስራ ስትሏቸው ትናንት የማይተረክበት ዛሬ አያስፈልገንም ከማለት ወደኋላ አይመለሱም። የአጥቂና ተጠቂ፣ የአጥፊና ጠፊ ወግ የሌለበት ነገር አይጥማቸውም።
እኒህን መሰል ሰዎች ፣ አንድ ነገር እንዴት እንደማይቻል እንጂ የመቻል እድል ስላለበት መንገድና ስልት አይነግሯችሁም። “ፍቅራቸው” ያለው አሳዛኙ መደምደሚያ ላይ እንጂ በድል ስለሚደመደመው ደስታ አእምሯቸው አያስብም። ሲነጋም ሲመሽም እምጵፅፅ….. የሚያስብል ከንፈር መጠጣ ያለበት ተረክ ነው፤ ነገራቸው ሁሉ።
በነገር የገነነ ስም ያለው ከእነርሱ ሃሳብ የተለየ ሃሳብ ያለው ሰው ከገጠማቸው፣ እንደምንም ዘርጥጠው ከማውረድና የራሳቸውን ትልቅነት በሰውየው ውርደት ውስጥ የሚፈልጉ ጠምዛዦች ናቸው።ሊጥሉት የፈለጉትንም ሰው፣ የበደሉን መዓት ከቡና ሰፈር እስከ አደባባይ አለፍም ሲል በሚዲያ በመውጣ ቅጣንባሩ በጠፋ ተረክ ያብጠለጥሉታል። አንዳንዴ በደላቸውን ከግንኙነታቸው መነሻ ይጀምሩና ለምን ወዲያው አላቆማችሁም ታዲያ ሲባሉ መሐል ላይ ሲደርስ ጠባዩ ተቀየረ ብለው ውንጀላቸውን ለማሳመር ይሞክራሉ። ወረድ ብለው ከላይኛው ሃሳብ ጋር የሚጣላ ትረካም ያመጣሉ።
የጥላቻቸው ምንጭ መልካም ዝናው የሚያስከትለው ጥላ የሚፈጥርባቸውን ግርዶሽ ለመቋቋም ያለመፈለግ ጭፍን ጥላቻ ነው። አንድ ምሳሌ እነሆ፤ አስረኛ ክፍል እያለን ከረብሻና ጸብ በስተቀር ክፍል መግባት የማይወድ ከሌላ ሀገር የመጣ አንድ የክፍላችን ተማሪ ነበረ። እና አጅሬ፣ የሚድ ሴሚስተር ፈተና ውጤት ሲሰጥ ከ20 ታርሞ የመጣው ውጤቱ ዝቅተኛ ነበርና ወረቀቱን የተቀበልን የክፍሉ ልጆች ሰብስበን ስንሰጠው፣ የፈተና ወረቀቱን እያየ እንግሊዝኛ 4/20 ፣ ማትስ 2/20፣ ባዮሎጂ 1/20፣ ፊዚክስ 2/20….. አማርኛ 4/20 የሚለው ውጤት ጋር ሲደርስ አማርኛ እንኳን ይኼን ላምጣ ሲል የሰማው ልጅ፤ እሱንም አስተማሪው ለተማሪው ሁሉ የሰጠውቦነስ ማርክ መሰለኝ፤ ዜሮ ከሃያ ነው፤ ያመጣኸው ፤ ማለት ነው፤ ሲለው ቆይ አስተማሪው ማነው? ብሎ ጠየቀ ፤ የእኛ ክፍሉ ተንኮለኛ ልጅ ታዲያ ግድንግዱ የስፖርት መምህር ሲገባ ጠብቆ እሱ ነው፤ አለው።ፀጥ ብሎ ተቀመጠ። የአማርኛ አስተማሪዋ ግን ሴት ነበረች። እንደዚህ ያሉ የማይችሉትን በጭፍን የሚፈርዱና የሚመዝኑ ምስኪን ሰዎች በቢሯችን ፣ በቀያችን ፣ በሰፈራችን፣ በሀገራችን ሞልተዋል።
እናም ሳይማሩና፣ የአስተማሪውን ማንነት፣ ጾታ እንኳን ለይተው የማያውቁ “ገልቱ” ተማሪዎች ሳይማሩ በወደቁበት ትምህርት አስተማሪውን ጣለኝ ለማለት አያፍሩም። የዘንድሮ የተቃውሞ መንፈስ አራማጆችና መልካም ሰራተኛ ሰዎችን የሚጠሉ ሰዎች ችግርም ይሄው ነው። የሚቃወሙት መቃወም ስለፈለጉ እንጂ የሚቃወሙበት ውሃ የሚያነሳ ሃሳብ ስላላቸው አይደለም። ቢያነሱም የትም የማያራምድ ሃሳብ ነው።
የሃላፊነቱ ደረጃ ምንም ይሁን ምን ወደ ሃላፊነት የሚመጣ ሰው፣ ከዘለፋ ፣ ከወቀሳና አለፍም ሲል በጉልበት ከሚቃጣ ጉሸማ ላያመልጥ ስለሚችል ይህንን ከሃሳቡ ተገዳዳሪዎች መጠበቅ አለበት። በኒውተን ሶስተኛ ህግ መሰረት ፣ “ለእያንዳንዱ እርምጃ እኩል አፀፋ እርምጃ አለው” (For every action there is an equal and opposite reaction) እንዳለው፣ ሃሳቡን መገዳደር ሲያቅታቸው የተናገረውን አንሻፍፈው የሚተረጉሙ፣ በመንገዱ ላይ እሾህ የሚነሰንሱ፣ ሣር ለበስየማይታይ ጉድጓድ የሚቆፍሩ እንዳሉ መጠበቅ አርቆ አስተዋይነት ነው። ስትቀድማቸው ላለመቀደም ብቻ አይደለም፤ አንተን ለመጎተት መነሳታቸውን ለአፍታም መዘናጋት የዋህነት ነው።
ምንም እንኳን ከላይ የታዘዘው ነገር፣ ከላይ የተፈቀደው ስጦታ የማይቀር ቢሆንም ንጋት መምጣቱ ላይቀር ክፉዎች ነገርን ሁሉ የጨለማ ጉዞ ለማድረግ መዳከራቸው አይቀርም። ይሁንናም “ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም”፤ ይባላልና። ከመንገድህ ተዘናግተህ አትፎርሽላቸው፤ ቀጥል እንጂ።
የሚገርመው ፣ የሰው ልጅ የሥነ ፍጥረት አባቱን እግዚአብሔርን ይከሰዋል እኮ፣ ያውም “ወይ ውረድ ወይ ፍረድ” ብሎ ነዋ። ስለዚህ ሰው፣ ሰውን ያህል እኩያ ፍጥረቱን ቢናገር ቢያንኳስስና ቢያንጓጥጥ ምንም አይገርምም። እንዲያውም ትከሻ ለትከሻ የመለካኪያ መንገድ አድርጎ ነው፤ የሚቆጥረው። ስለዚህ መነካካትና ቢቻል ማነኳኳት ይሞክራሉ።
የአንዳንዱ ሰው የተቃውሞ መነሻ፣ መቃወም ነው፤ ተቃውሞውም ለመቃወም ያህል ነው። እዚህ ላይ አንድ የተስፋዬ ካሣ ቀልድ ትዝ አለችኝ። እድሜያቸው ገፋ ያለ ሰውን ጋዜጠኛው፣ አብዮት አደባባይ ሰልፍ ላይ ያገኛቸውና አባቴ ወደዚህ ሰልፍ ለምን መጡ ሲላቸው፣ መልሳቸውን የጀመሩት ፣ ሰልፍ በጣም ጥሩ ነገር ነው። ሰልፍ ከሰው ይቀላቅልሃል፤ በዚያ ላይ ያጠነክርሃል ካሉ በኋላ ፣ ከንጉሱ የዘውድ በዓል ጀምሮ ሰልፍ እወጣለሁ፤ በደርግ ጊዜ ከዚህ አደባባይ ተለይቼ አላውቅም፤ ኢህአዴግም ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ሰልፍ ሲጠራ ከፊት ነው የምገኘው፤ ሲሉ ነው መልስ የሰጡት። እና ዛሬም የወጡት ….ሲል ሰልፍ ጥሩ ነገር ነው፤ ሰው ካደባባይ እንዴት ይጠፋል ሲሉ ነው፤ ያረጋገጡለት። ሰልፉን የሚሰለፉት ለሰልፍነቱ ነው። ተቃውሞን ለተቃውሞ እንደሚያቀርቡት ሰዎች ማለት ነው።
ወደ ሐገራችን ጉዳይ ስንመጣም በተመሳሳይ ውንጀላና ክስ የሚያበዙ ሰዎች፤ ለበጎነቱና ለመረጋጋቱ ከሚያዋጡት ነገር ይልቅ የሚያባብሱበትና የሚካሰሱበት ሰበባ ሰበብ ይበልጣል። ሲጀመርም ቋንቋቸው፣ በዛቻና ማስፈራራት ጀምሮ በአንለቃችሁም የሚደመደም ቀረርቶ ነው፤ እንጂ ቦታውን የሚመጥን፣ የረባ የመቃወሚያ ሃሳብ የላቸውም።
እነዚህን መሰል ሰዎች ፣ በር ሲዘጋባቸው የተዘጋውን በር ለማስከፈት ውንጀላን መሳሪያቸው የሚያደርጉ፣ አለፍምሲል እንደ ደፈጣ ተዋጊ ሃይል ወደመጠቀም የሚያዘነብሉ፣ የአስተሳሰብ ድሆች ስለሆኑ በየደረሱበት ሃሳባቸውን በተገለልን፣ በተገፋን፣ ተደፈጠጥን፣ ተናቅንና ተጨቆንን ስልት ከማቅረብ ወደኋላ የማይሉ ናቸው። በአስተሳሰባቸው ዘውግ ውስጥ ግን “ሁሉንም ወይም ምንም” ብለው ስለሚያስቡ የጠቅላይነት ስሜቱ፣ የአዛዥ ናዛዥነት ፍላጎቱ ነው፤ አስክሮ የሚያንገዳግዳቸው።
ስለሰው ጥፋትና ክሳት ሳስብ ማንንም ሰው ንጹህ ማድረግ እንደማይቻል አስባለሁ፤ የሚሰራ ሰው ደግሞ ከስህተት አይነጻም። እየሰራ ይነጻል ፤ እየነጻ ያበራል እንጂ። የሚያስቸግሩት የሚሰሩቱ ሳይሆኑ የሚያወሩቱ ናቸው።ስለዚህ ለእነርሱ ምላሽ ለመስጠት እሰጥ አገባ ውስጥ ከመግባት በመስራት መብለጥ ነው። ለራሱ ለአምላክ በማይመለስ አዳማዊ ተክለሰውነት የተሰራው የሰው ልጅ የተቃውሞ ልብ፣ ለእኩያው ሰው ይተኛል ተብሎ መታሰብ የለበትም። ሁሉንም ግን በተቃውሞ ሚዛን ማየት አያስፈልግም። ምክንያቱም ሁሉንም መቃወም ሁሉንም ማጣት ያስከትላልና። ለነገሩ ተቃውሞ ገጠመኝ በሚል ልብ መንሸራተት እንዳይገጥም ለማሳሰብ እንጂ የተቃውሞ ሃሳብ ማለቂያ የለውም። ቁም ነገሩ ለአለሙለት ዓላማና ራዕይ መኖር ነው።
ሰሞኑን ስራዬ ላይ እያለሁ የተኳረፉ ባልና ሚስት ቢሮዬ መጡና ወደአማካሪዎች ክፍል ሄዳችሁ አናግሯቸው፤ አልኳቸው። አንተ ካላነገርከን አይሆንም አሉኝ። ለዚሁ አገልግሎት የተቀመጡ ሰዎች ስላሉ ከእኔ ይልቅ፣ እነርሱ ያግዟችኋል ፤ ብላቸውም አጥብቀው ስለተሟገቱኝ ይሁን እስኪ ንገሩኝ አልኳቸውና ቀጠሉ።
ባልየው፣ ይቺ ሴትዮ ምንም አትሰማኝም ፤ ምክር ያስፈልጋታል ብሎ ጀመረ። ሌላስ አልኩት ፤ ጆሮ የላትም ፤ የምትረባ አይደለችም አለና ቁና ተነፈሰ። አንቺስ አልኳት ፤ አለመስማትማ በእርሱ ይብሳል፤ ልጆቻችን ፊት አትናገረኝ፤ እያልኩት ስለሚሰድበኝ፣ እነርሱም የምላቸውን እንደርሱ አልሰማ እያሉኝ ነው፤ ቦታ ምረጥ ስለው አይሰማኝም አለችኝ። አሁንስ ታክቶኛል ብላ እንባዋን ዘረገፈችው። አየህ በእንባዋ ስታታልልህ አለ፤ ቀጥሎ።
በመጨረሻም እኔ እንድናገር ፍቀዱልኝ አልኳቸው። ያነሷቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ልተወውና፣ ሰማችሁ አልኳቸው። አሁን ከነገራችሁኝ እንደተረዳሁት፣ ሁለታችሁም ተስፋ የተቆረጠበት፣ የተበላሸና የማይጠገን ስህተት ያለባችሁ መስሏችኋል እንጂ፣ ጥሩ ሰዎች ናችሁ። አንተም ማድመጥ ትችለበታለህ፤ አንቺም እንደዚሁ። ጸባችሁንለብቻችሁ አድርጉት፤ ፍቅራችሁን ግን ልጆቻችሁ ባሉበት ስፍራ ይሁን። ፍቅር እንጂ የምታካፍለው ጸብ እንዴት ለልጆች እይታ ይቀርባል? ስትጣሉ መኝታ ቤት ስትሞጋገሱ ልጆቻችሁ ፊት ይሁን፤ እሱን ከተዋችሁት የገጠማችሁ ነገር በጣም ቀላል ነው፤ ብዬ በምስጋና ተሰነባበትን።
አሁን እኛ ሀገር ላይ፣ ያለው ነገር ትናንሹን ፀብ ሁሉ ወደ አደባባይ እያወጡት፣ በየፌስቡኩ፣ በየትዊተሩ፣ በየዩቲዩቡ፣ አንዳንዴም በተለያዩ ቲቪ ቻነሎች ላይ እያወጡት እርቅ ሲደርጉ እና ሲስማሙ ግን ሁሉ ነገር በጓዳ ይቀራል። አንዳንዴ ግን ከአንዳንዱ እርቅ ፀቡ መስመር ያስለያልና ይመረጣል። የጸቡ ማሳረጊያ ደምና መለያየት ፤ ፍጭትና ትርምስ አይኑርበት እንጂ በመልካም የቅራኔ አያያዝ ከተያዘ ጥሩ ነው። አንዳንድ ምግብ ቤት ውስጥ የምታዩት ማስታወቂያ ጥሩ የሞራል መጠበቂያ ስልት ነው። “ችግራችንን ለእኛ፣ ጥሩ ነገራችንን ለወዳጆቻችሁ ንገሩልን”ይላሉና።
እና ስለተቃውሞ ቅሬታና ምሬታ፣ ኡኡታና እሪታ ሳስብ እግዚአብሔር በማይገሰስ ዙፋኑ ላይ መሆኑ በጀ እንጂ ሰውማ ገና ድሮ ከየልቡ ወንበር ላይ አንስቶ መጣሉ አጠያያቂ አይደለም። ምን ሲደረግ እንዲህ ሆነ፤ ምን አስከፋው ይህን ያህል የሚያስብል ብዙ ነገር ነው፤ የሰው ልጅ ያለው።
አውስትራሊያ ላይ የደረሰውን የደን ቃጠሎና ቃጠሎው ያስከተለውን ጥፋት ለሚያስብ ሰው፤ የሰውልጅ በገዛ እጁ ጦስ ለመጣበት መዘዝ እንኳን ተጠያቂነቱን ወደሰማይ ከመውሰድ የማይመለስ መሆኑን ያሳያል። በዚያ ክፉ የእሳት ሰደድ፣ 24 የሰው ልጅ፣ 500 ሚሊዮን የዱር እንስሳት፣ 8 ሺህ ኳዋላዎች፣ 5.5 ሚሊዮን ሔክታር የደን መሬት እንደጧፍ የነደደ ሲሆን 1400 ቤቶችም ወድመዋል። እግዚኦ አስበን ፤ ይባል ይሆናል እንጂ ምን ስላጠፋን አይባልም። ማጥፋትማ አጥፍተናል፤ የምድሪቱን የአየር ሙቀት መጠን በክለነዋል፤ መርዘነዋል። በተለይ ያደጉት ሀገሮች የኢንዱስትሪ ጋዝ ልቀት ፣ ኢንዱስትሪ አልባ የሆኑትን ያላደጉ ሀገሮችንም ዋጋ እያስከፈለ ነው። አምላክ ግን መወቀሱ አልቀረም። አባት ሆይ! ስንቱን ችለኸዋልማ!!!?
እየሰራህ ካለህ የማትወቀስና የማትከሰስ የለህምና መስራትህን አታቁም፤ መቀጠልህን ከቶውንም አታዘግይ።የሚፈልጉት መጎተትና ቢቻል ማስቀረት ነውና ለጠላፊዎችህ አትመቻ ቸው። ጨክኖ የመጓዝ ጊዜ ይሁንላችሁ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ